>
8:56 am - Tuesday January 25, 2022

የኦሮሞና የአማራ፣ የሶማሌ ሆነ የሲዳማ ብሔርተኞች የህወሓት ቦት_ጫማ ከመሆን የዘለለ ሚና የላቸውም!!!  (ስዩም ተሾመ)

የኦሮሞና የአማራ፣ የሶማሌ ሆነ የሲዳማ ብሔርተኞች የህወሓት ቦት_ጫማ ከመሆን የዘለለ ሚና የላቸውም!!! 
ስዩም ተሾመ
እውነት እንነጋገር ከተባለ፤ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያና አማራ ክልል የታየው ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ  የታሰሩ እና የሞቱ ሰዎችን ከመቁጠር አልፎ ለውጥ ማምጣት የጀመረው #የኦሮማራ_ጥምረት አማካኝነት ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ፉከራ በብሶት የተሞላ ለቅሶ ነበር፡፡  የአማራ ብሔርተኞች ቀረርቶ ያለመቻል ስቅታ ነበር፡፡ በጥቅሉ ብሔርተኞች እያለቀሱ ከመገደል፣ እያቅራሩ ከመሞት ባለፈ ነገሮችን አርቆ ማየትና ማስተዋል አይችሉም፣ በተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሠረተ የመፍትሄ ሃሳብ በማፍለቅ በህልውናቸው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ የሚያስችል ዕውቀትና ብቃት የላቸውም፡፡ የኦሮሞና አማራ ብሔርተኞች ህወሓት/ኢህአዴግ እንደ ሁኔታው እየቀያየረ የሚያጠልቃቸው የቦት ጫማ ናቸው፡፡ የአማራ ብሔርተኞች ጠንከር ሲሉበት የኦሮሞ ብሔርተኞችን ተጫምቶ ይመጣና ይጨፈልቃቸዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ጫን ሲሉት የአማራ ብሔርተኞችን ተጫምቶ ይደፈጥጣቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን የኦሮሞና አማራ ብሔርተኛ አንዱ ሌላውን እየሰደበና እየረገመ ከማልቀስና ከመውቀስ ባሻገር የጋራ ጠላታቸውን በመለየት እርስ-በእርስ መተባበርና በጋራ መታገል  አይችሉም፡፡ ብሔርተኛ ከለቅሶና ብሶት የዘለለ ዕውቀትና ግንዛቤ የለውም፡፡ በመሆኑም የኦሮሞና አማራ ብሔርተኞች በህወሓት የበላይነት ላይ የተመሰረተውን ጨቋኝና ጨካኝ ስርዓት ከጫንቃቸው ላይ ለማስወገድ በተደረገው ትግል ሬሳና እስረኛ በመቁጠር ብሶትና ለቅሶ ከማሰማት በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል አስተዋፅዖ አላበረከቱም፡፡ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የሚለያቸው ነገር ቢኖር ሌሎች ተደብቀው ሲያለቅሱ ብሔርተኞቹ ስምና አድራሻቸውን ደብቀው፣ አሊያም ውጪ ሀገር ተወሽቀው ማልቀሳቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጠዋት-ማታ እየዬ ማለት አያመጣም፡፡ ከዚያ ይልቅ የጨቋኙ ስርዓት ምን ላይ እንደቆመ ለይቶ ማወቅና የቆመበትን መሠረት ለመናድ የሚያስችል ተግባራዊ ዕቅድ ማውጣትና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ዕውን ማድረግ የተቻለው የህወሓት ባህሪና ዓላማ የገባቸው ጥቂት ሀገር ወዳዶች በፈጠሩት የኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት ነው፡፡ ኦሮሞና አማራን ጨምሮ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው በአብሮነትና የትብብር ሃይል እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ አማራና ኦሮሞ በተናጠል የሚያደርጉት ትግል እርስ-በእርስ ለመጠላለፍ እና ለመጨፈላለቅ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የለውም፡፡ ይህ ባለፉት 27 አመታት ህወሓት በተግባር ያደረገውና ደግሞ-ደጋግሞ ያረጋገጠው ሃቅ ነው፡፡ የህወሓት የጭቆና ቀንበር ተገርስሶ የወደቀው በኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተዘረጋውን ያለመተማመን እና ጥላቻ ግንብ በከፊልም ቢሆን ማፍረስ በመቻሉ ነው፡፡
ነገር ግን ብሔርተኞች ትላንት፣ ዛሬ ሆነ ነገ ከብሶትና ለቅሶ በዘለለ የተለየ ነገር ለማድረግ የሚያስችል ዕውቀት ሆነ ቀናነት የላቸውም፡፡ ቂምና ጥላቻን ከመስበክ ባለፈ ለአብሮነትና እኩልነት የሚበጅ ሃሳብና አስተያየት ሲሰነዝሩ አይስተዋልም፡፡ ከእነሱ የተለየ ሃሳብና አስተያየት በሰጡ ሰዎች ላይ የስድብ ውርጅብኝ በማውረድ የተጠናወታቸውን የዕውቀት ድርቀትና ድንቁርና ከማጋለጥ ባለፈ የራሳቸውን ሆነ የሌሎችን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ  አይችሉም፡፡ የተሻለ የመፍትሄ ሃሳብ በራሳቸው መናገር አይችሉም፤ የመፍትሄ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች እንዲናገሩ አይፈቅዱም፣ ቢናገሩ እንኳን በሰከነ መንፈስ ማዳመጥ አይችሉም፡፡ ብሔርተኞች የሚችሉት ነገር ሌሎችን መንቆርና መደናቆር ነው፤ ከማሰብ ይልቅ መሳደብ ነው! በእኩልነትና ፍትህ ላይ የተመሠረተ ስርዓት ከመገንባት ይልቅ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ መዝጋት ነው፤ ወደዚያ ለመሄድ የሚጥሩትን ማንጏጠጥና ማደናቀፍ ነው፤ ህወሓትን ይጠላሉ እንጂ በራሳቸው ከህወሓት የተለየ ነገር የላቸውም፤ ዶ/ር አብይን ቢጠሉትም-ቢወዱትም የእሱን የፖለቲካ ፍልስፍና ጨርሶ አያውቁትም፣ ቢያውቁትም አይደግፉትም!!! የኦሮሞና አማራ፣ የሶማሌ ሆነ ሲዳማ ብሔርተኞች የህወሓት ቦት ጫማ ከመሆን የዘለለ ሚና የላቸውም!!!
Filed in: Amharic