>
9:31 am - Saturday November 26, 2022

እንዲህ ናት እምዬ ኢትዮጵያ!… (ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው)

እንዲህ ናት እምዬ ኢትዮጵያ!…
ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው
በዘር የተደራጀ ፓርቲ፤ ከራሱ ዘር በስተቀር ሌላውን ከማዳከም ውጪ በፍትሕና በርትህ መሥራትን  አያቅበትም። ዘረኞች ዘወትር የወንበዴ ሥራ በመከወን ሌሎችን ማንበርከክ ውጥናቸው ነው። “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ” ብለው ሳይጨርሱ የዘረኝነት ካርድ ባለዕድል ሆነው ሲገኙ ከመገረም ውጪ ምን ይባላል? በሁለት በዘር በተደራጁ ፓርቲዎች ግፍ ስለተፍፀመበትና እየተፈፀመበት ስላለው የዘመን ባንክና የአክሰስ ሪል እስቴት መሥራች ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ጥቂት ልንል ወደድን!!!
.
ከዚያ ሁሉ በኋላ…
“ቤት ልስራ ብለህ ከህዝቡ የሰበሰብከውን 1.4 ቢሊዮን ብር በመዝረፍ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመሃል” ተብሎ ለዘመናት ብዙዎች ደምና እንባቸውን ወዳፈሰሱበት የሰቆቃ ግቢ ወደ ማዕከላዊ ከተወረወረ…
የዋስትና መብቱን ተነፍጎ በታጎረበት የማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ጧት ማታ ምርመራ ሲደረግበት ከሰነበተ…
በወንጀል ሊያስከስሰው የሚችል ተጨባጭ ማስረጃ ለማግኘት ያቃተው ፖሊስ ለ8 ጊዚያት ያህል የተጨማሪ ምርመራ ቀነ ቀጠሮ እየጠየቀበት፣ ለወራት ፍርድ ቤት ሲመላለስ ከከረመ…
ህይወቱን ለከፋ አደጋ ባጋለጠ አስደንጋጭ ህመም መላ ሰውነቱ ከቆሳሰለና በማዕከላዊ ቅጽር ግቢ አሳር መከራውን ሲቆጥር ከኖረ…
እጁን ይዞ ወደዚያ የሰቆቃ ግቢ የከተተው ፖሊስ፣ ከ128 ቀናት በኋላ ድንገት ካቴናውን ከፈታለት…
“በል ውጣ…” ብሎ እንደዋዛ የማዕከላዊን በር ከከፈተለት…
ከዚያ ሁሉ ስቃይ፣ ከዚያ ሁሉ በደል፣ ከዚያ ሁሉ የመብት ጥሰት፣ ከዚያ ሁሉ እንግልት በኋላ…
ኤርሚያስ ኤርሚያስ ሆኖ ይቀጥላል ብዬ በፍጹም አላሰብኩም ነበር፡፡
ከእስር ከተፈታ ከቀናት በኋላ፣ ወደ ቤቱ ስሄድ…
የእስር ቤት ኑሮ ያጎሳቆለውን፣ በፍትህ እጦት ሞራሉ የተነካውን፣ ተስፋ የቆረጠውን፣ አገሩን ያኮረፈውን፣ ቅስሙ የተሰበረውን፣ ጭብጥ ኩርምት ብሎ የሚቆዝመውን፣ እንዲህ ያለውን ልብ የሚበላ ኤርሚያስ እያሰብኩ ነበር፡፡
በሩን ከፍቼ ስገባ ግን፣ ይሄን ኤርሚያስ አጣሁት፡፡
በዚያች ገራሚ ሳቁ የተቀበለኝ ኤርሚያስ እንደሰጋሁት ቅስሙ አልተሰበረም፣ እንደፈራሁት ለደልና ስቃይ አልተበገረም!…
ይልቁንም ባልጠበቅኩት መልኩ የበለጠ ጠንክሮ፣ የባሰ ገንግኖ ነበር ከእስር ቤት ወጥቶ የጠበቀኝ – ገረመኝ!…
ይህ ብቻም አልነበረም የገረመኝ…
ይህ ሁሉ በደልና ግፍ ተፈጸመብኝ ብሎ፣ በአገሩም በአገሩ መንግስትም ቂም አልያዘም፡፡
ኤርሚ ልክ እንደተፈታ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው፣ ብታሰቃየውም ቂም ለማይይዝባት አገሩ የሚበጁ ሙያዊ የጥናት ጽሁፎችን በማዘጋጀት ላይ ነበር፡፡ ሙሉ ጊዜውን የሰጠው የጥናት ጽሁፎችን ለማዘጋጀትና ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን አዳዲስ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለመቅረጽ ነበር፡፡
ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ከእስር ከተፈታበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ የጥናት ጽሁፎችንና የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን በማዘጋጀት ለመንግስት አቅርቧል፤ በጋዜጦች ላይም ለንባብ አብቅቷል፡፡
ኤርሚያስ ደጋግማ ብትበድለው ለማይሰለቻት ኢትዮጵያ ይበጇታል ብሎ ካዘጋጃቸው የተለያዩ የጥናት ጽሁፎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ…
THE ETHIOPIAN ECONOMY AT A CROSS ROAD – 2018
ETHIOPIAN STOCK EXCHANGE – A NOVEL APPROACH
ETHIOPIAN BANKING – THE CASE FOR ALLOWING FOREIGN OPERATORS
ETHIOPIA – A FRAGILE STATE
ETHIOPIA’S JOB CREATION IMPERATIVE
OMNI-CLOUD፡ ENABLING DIGITAL TRANSFORMATION IN ETHIOPIA
THE ETHIOPIAN INSURANCE INDUSTRY – THE CASE FOR ALLOWING FOREIGN OPERATORS
ETHIOPIAN DIASPORA ENGAGEMENT – ROAD-MAP
PRIVATIZATION IN ETHIOPIA – A ROAD-MAP
ከዚህም ሁሉ በኋላ…
ብዙ በጀትና የሰው ሃይል መድባ ያቋቋመቺው የፖሊሲ ጥናት ተቋም ሊወጣው ይገባው የነበረውን አገራዊ ተልዕኮ፣ በራስ ተነሳሽነት በሙሉ ነጻ ፈቃድ ለብቻው የተወጣላትን…
አለማቀፍ አማካሪ ድርጅት ቀጥራ ብታሰራው ሚሊዮኖችን ሊያስወጣት የሚችለውን ትልቅ ተግባር፣ ሽራፊ ሳንቲም ሳይጠይቅ በብላሽ ያከናወነላትን…
ኢኮኖሚዋን ከገባበት አዘቅት በምን መልኩ ማውጣት እንደምትችል፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን የለገሳትን…
(በነገራችን ላይ ኤርሚያስ ኢኮኖሚውን ከገባበት አዘቅት ለማውጣት ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ትልልቅ የመንግስት የልማት ድርጅቶች መሸጥ እንዳለባቸውና ሌሎች የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን የለገሰበትን THE ETHIOPIAN ECONOMY AT A CROSS ROAD – 2018 የተሰኘ ባለ 27 ገጽ የጥናት ጽሁፉን “ለለውጡ መንግስት” ከላከ ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ነበር፣ መንግስት እነ ኢትዮ ቴሌኮምን በመሸጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መወሰኑን ይፋ ያደረገው)
ሌሎች ባለሃብቶቿ ይቅርና ምሁራኗ እና ዩኒቨርሲቲዎቿ ያልሞከሩትን ለአገር ለወገን የሚበጅ ትልቅ ስራ፣ እውቀቱንና ከእስር የተረፈውን ጊዜ መስዋዕት አድርጎ ከፍሎ ሲሰራላት የከረመውን እንቁ ልጇን ከእስር ቤት አጥር ውጭ ልታየው አትፈልግም!!!
ሰውዬው ማን እንደሆነና ምን እየሰራ እንደሆነ በቅጡ ልታስብ አትፈልግም!…
ሳሙናና ክብሪት አስመጥቶ የሚቸረችር ዝም ብሎ ሃብታም እንዳልሆነ ልታምን አትፈቅድም!..
ምሬትና ጭንቀቱን እንጂ አእምሮና እውቀቱን አትፈልገውም!…
በእጁ ካቴና እንጂ በአንገቱ ሜዳይ ልታስገባለት አትፈልግም!…
የተቋም እንጂ የግለሰብ ዋጋ እንዳለው ያልተረዳችውን እንቁ ልጇን ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋን፣ ያለሃጢያቱ አስራ ስታማቅው ኖራ በፈታችው በፈታችው በወራት እድሜ ውስጥ፣ እንደልማዷ ድንገት እጁን ይዛ ወደ ወህኒ መልሳ ወረወረችው!
እንዲህ ናት እምዬ ኢትዮጵያ!…
.
ለኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጠው የሚጠይቀውን ይህንን የድጋፍ ፊርማ የምናሰባስበውም የታሰረው ትልቅ ጭንቅላት እንጂ ዝም ብሎ ነጋዴ እንዳልሆነ ስለምናውቅ ነው!
Filed in: Amharic