አሰፋ ሀይሉ
የኤርትራን ምድር መረገጫቸው፣ የቀይ ባህርን መንሳፈፊያቸው ያደረጉ የኢጣልያን ቅኝ ገዢዎች — በመላው ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ታላቅ ተጋድሎ — በአድዋ ላይ በ1888 የማይቀለበስ ሽንፈት ደረሰባቸው፡፡
ያ የኢትዮጵያውያን የአድዋ ድል — በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር በባርነት ለሚማቅቁ ለመላው ዓለም ሕዝቦች — በተለይም ለአፍሪካ ሕዝቦች — ትልቅ የድል ብሥራትና የለኮሰ — በተሰበረ ቅስማቸውን የጠገነ — በሃፍረት የተደፉ አንገቶቻቸውን የቀለሰ — ታላቅ የኢትዮጵያውያን አንበሦች አንፀባራቂ ድል ነበር፡፡
ይህ ለእኛ አንፀባራቂ የሆነው የአድዋ ድል ግን — ለኢጣልያኖች ድቅድቅ ጨለማን ነበር በላያቸው የደፋባቸው፡፡ ኢጣልያኖችን — በመላ አውሮፓ መሣለቂያ እንዲሆኑ የዳረጋቸው — ከእነ ኔሮ እና አውጉስተስ ጀምረው በሚቆጥሩት የረዥም ዘመናት የገናናነት ታሪካቸው — ፈጽሞውኑ ይደርስብናል ብለው ያልጠበቁት፣ ያላለሙት ታላቅ የታሪክ ውርደት ውስጥ ነበር የከተታቸው፡፡
እናም 40 ዓመት ሙሉ ያረገዙትን ቂም በቀል — በኢትዮጵያ ምድር ላይ እና — በኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ላይ — እንደ ጥፋት ውሃ፣ እንደገሞራ እሳት፣ እንደመቅሰፍት — ከሰማይ፣ ከምድር፣ ከየብስ ከባህር፣ ሊያወርዱብን — ምለው ተገዝተው ተነሱ።
የጥፋትን መዝሙር በአንድ በኩል — የሥልጣኔ ፋናወጊነትን መዝሙር በሌላ በኩል — የዲያብሎስን የሰቆቃ ጩኸት በአንድ በኩል — የሮማ ክርስቲያን ካቶሊኮችን መንፈሳዊ የመላዕክታትና የቅድስት ድንግል ማርያም ዜማ በሌላ በኩል — እያዛነቁ — እየዘፈኑ — እየሸለሉ — እየደነፉ — ተነሱ።
በኦጋዴንም ጥግ ከሶማሊያ — በአምባላጌም ጥግ በትግራይ በኩል አሳብረው — ለዘመናት አናስነካም ብለን ደማችንን ያፈሰስንባቸውን፣ አጥንታችንን የገደገድንባቸውን፣ እንባና ደም ያዘራንባቸውን — እነዚያን የተቀደሱ የኢትዮጵያውያንን የጀግኖች ድንበር — በቃልኪዳን ጀግኖች የተዋደቁላቸውን እነዚያን ቅዱሳን ድንበሮቻችንን — እየበረቃቀሱ — በከፍተኛ ቂም በቀል በተጠነሰሰ — እና — በከፍተኛ ፋሺስታዊ የዘረኝነት ልክፍት በናወዘ — አቅል በሌለው የጥፋት በትር — ሊያጣድፉን — 40 ዓመታት ሙሉ ለጥፋት ካደፈጡበት ምሽጋቸው — ወደምድራችን እየገሰገሱ፣ ወደሰማያችን እየከነፉ — አይገቡ የለ — ገ ቡ !!!
ገቡ፡፡ እና የጥፋት በትራቸውን በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ አበራዩ፡፡ የዱቼ ሙሶሊኒ ዘረኛ የፋሺስት ጄነራሎች — መረብ ወንዝን ተሻግረው የኢትዮጵያን መሬት ወረሩት፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከላይ ከታች እንደ ጥሬ ቆሉት፡፡ እንደክምር ጭድ በላዩ ላይ ሰደድ እሳትን አነደዱበት፡፡
መረብን ተሻግረው እንጥሾን፣ ሃውዜንን፣ አዲግራትን፣ አጋሜን፣ ገራልታን፣ ተምቤንን፣ መቀሌን፣ ቅድስቲቱን ከተማ አክሱምን ሣይቀር — ከላይ በአውሮፕላን፣ ከታች በብረት ለበስ ጦር፣ ከጎን በመትረየስና ታንክ፣ እጭድ አርገው ሃገሩን ባዶ ኦና ሜዳ አደረጉት።
በዚያ እልቂት አውራ የነበሩት የፋሺስት ኢጣልያ አረመኔ የጦር ጄነራሎች እነ ጄነራል ኤሚሊዮ ደ ቦኖ፣ የመካናይዝድ ብርጌድ መሪዎቹ እነ ጄነራል ፊደንዚዮ ዳሎራ — የኬሚካል መርዝ ጋዝ ከሠማይ እያርከፈከፉ ሕዝቡን የፈጁት እነ ጄነራል ፒዬትሮ ባዶግሊዮ — የደብረ ሊባኖሱን ገዳም እልቂትና ጭፍጨፋ የመሩት እነ ጄነራል ባሌቲ — የአዲስ አበባውንና የአንኮበሩን የግፍ እልቂቶች እና በኦጋዴንም በኩል የቦርዶዲን የትንኮሳ እልቂት የመሩት እነ ጄነራል ሮዶልፎ ግራዚያኒ — ሌሎችም፣ ሌሎችም።
ሌሎችም ደም የጠማቸው — ዓይናቸው ለደም የፈጠነ፣ ክንዶቻቸው ለጭካኔ የበረታ ብዙ፣ ብዙ፣ በጣም ብዙ የፋሺስት የጦር አለቆች — ከነጥፋት መሣሪያቸው — ከነጋሻ ጃግሬአቸው – በምስኪኑ እና አትንኩኝ ባዩ ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ — ያለከልካይ ሠለጠኑ፣ ፋነኑ፣ ህፃና ካሮጊት ሳይሉ — ያገኙትን ሕዝብ ሁሉ በግፍ ጨረሱ!!!
ያን ሁሉ ግፍ የፈፀሙት የኢጣልያ ፋሺስት አረመኔዎች — የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር — ከሞት የተረፉ — በፅናት በርትተው ለዚህች ለቆምንባት ምድር ደማቸውን ያፈሰሱ — እልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን አርበኞችን አስከትለው — በ1933 ወደ መዲናችን ወደ አዲስ አበባ በተመለሱ ሰዓት ግን — እና እነዚያ አረመኔ አራጅ ፋሺስቶች — እንዲያ ያለከልካይ ባፋነኑበት ምድር ላይ — ጭልፊት እንደመጣባት ጫጩት ይገቡ ይደበቁበት ጠፍቷቸው — በፍርሃት በሚርበደበዱበት ሠዓት — የኢትዮጵያውያን ምላሽ ምንድን ነበረ???
የማያውቅ ካለ የነበሩት የሰጡትን እማኝነት ያገላብጥ፡፡ ለማወቅ የፈለገ ቢኖር ድርሳናትን ይፈትሽ፡፡ እንዲያ እንደ በግና እንደ አንበጣ መንጋ ከልካይ በሌላቸው መርዘኛ ፋሺስቶች እጅ — በግፍ ሲጨፈጨፍና ሲረፈረፍ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ — እና ታላቁ ንጉሠ ነገሥታችን — እና ኢትዮጵያ እናታችንም — ያደረገችው ነገር — የሰጠችው ምላሽ — አንድ እና አንድ ብቻ ነበር፡፡ ምህረት፡፡ ምህረትንና ምህረትን ብቻ፡፡
አንድም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው — አንድንም ኢጣልያዊ ምርኮኛ ወይም ፈርጣጭ ቢያገኝ — ከፀጉሩ አንዲት እንዳያጎልበት ብያለሁ — ይህን የተላለፍክ ሰው — ትንሽ ከትልቅ ሳትለይ — የኢትዮጵያ ጠላት ነህ!!! የሚል አዋጅ ነበር ያስነገረችው ኢትዮጵያ!!!
ሌላ ሌላውን የመጣብንን ሁሉ ነገር ትተን — አንዳንዴ ይህን ስናስብ እኮ ነው — በዚህች ድንቅ፣ መሐሪ፣ ፈሪሃ እግዜር ባደረባት — የሥልጡኖችና አትንኩኝ ባዮች ሃገር — በዚህች በተባረከች የኢትዮጵያ ድንቅ መድር መወለድ ብቻ እኮ በራሱ — እንዴት ያለ ኩራት ኖሯል??!!! — የምንለው በሙሉ አፍ! በሙሉ ልብ! በሙሉ ቀልብ!!!!
እና ያ ጦርነት አበቃ፡፡ የሌሎቹ የፋሺስቶቹ ግብረአበሮች — የዘረኞቹ ናዚዎች ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም — የዓለም ሕዝብ አምርሮ ተዋጋቸው — መጨረሻቸውም አሳዛኝ መቅሰፍት ሆነ፡፡
ፋሺስት ዘረኞች ሁሉ — በየተነሱበት ሃገር — ራሳቸውንም — አምኖ የተከተላቸውን ሕዝብም ይዘው — እርቀቱ የማይታይ የእሳትና የጥፋት እንጦረጦስ ውስጥ ነው የተደረገሙት!! ያሳዝናል!!
ለሥራቸው እግዜሩ ይፍታቸው! እንጂ – በእንዲህ ያለ የዘረኝነት አባዜ የተወለደን ‹‹ሶሻል ማድነስ›› (ማህበራዊ እብደት!) ምን ስያሜ ልትሰጠው ትችላለህ???? ‹‹ይበለኝ ይበለኝ ይበለኝ በጣም፤ እንዲህ ካላረጉት እብድ አይቀጣም!›› አይደል ያለችው ያገራችን አዝማሪ??!! ወቸ ጉድ!!
ብቻ ያ ዘረኛ ቀውሶች ያቀጣጠሉት የናዚዎችና የፋሺስቶች ጦርነት ብዙዎችን ከማገደና ከፈጀ በኋላ — በስተመጨረሻ መቼም አምላክ የተመሰገነ ይሁን — እነዚያ ጥፋትን ያነገቡ ዘረኞች ወደ መቀመቅ ገብተው — ጦርነቱ በነፃነት ኃይሎች ድል ተጠናቀቀ፡፡
በጦርነት መቼም አሸናፊም ተሸናፊም የለውም ይባላልና — የጦርነትን እልቂት — አሸንፈንም እንኳ ስናስበው — እጅግ እጅግ እጅግ እጅግ ያሳዝናል፣ ያሰቅቃል፣ አንገትን ያስደፋል፣ ያስለቅሳል፣ ያሰቅቃል!!!
ፋሺስቶች ለምን ሁል ጊዜ እንደዚህ ያለ ጥፋትና በደም መጨማለቅ ደስ እንደሚያሰኛቸው ሁልጊዜ የዓለምን መሰል ታሪክ ባገላበጥን ቁጥር የሚፈጠርብን ጥያቄ ነው፡፡ ለምን? ለምን? ለምን? — መልሱ ግን — መልስ የለውም! የሚል ብቻ ነው — እንጂ መልስ የለውም ይሄ — በተጠየቅ አይመራም — በጤነኛም አይመራም — በቃ — መልሱ የለም፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በተጠራው የፓሪስ ዓለማቀፍ የሠላም ኮንፍረንስ ላይ ያቀረበው በማስረጃ የተደገፈ የኢትዮጵያውያን የሞት ሰለባዎች ሪፖርት — አሃዙ ሲታይ — ያውም ያን ጊዜ ጥቂት ሕዝብ በነበረን ሠዓት — ፋሺስቶች ሕዝባችንን ሆነ ብለው እንዴት እንዳጠፉት — እንዴት የሞትን መቅሰፍት እንደዘሩበት ማየት ይቻላል፡፡ ያኔ ኢጣልያኖች የቀጠፏቸው ኢትዮጵያውያን ስንት ናቸው???
በኢጣልያን ፋሺስቶች እጅ ደማቸው እንደጎርፍ የታጠበው፣ ቆዳቸው በመርዝ ጋዝ የተለበለበው፣ አጥንታቸው በታንክ የተጨፈላለቀው፣ በአውሮፕላን ቦንብ የተርከፈከፈባቸው፣ በተደበቁበት በጎራዴና በሳንጃ አካላቸው የተተለተለው — እነዚያ የዚህች ምድር ብቃዮች — እነዚያ ሰማዕታት ጀግኖች ወገኖቻችን ስንት ነበሩ ?? — ብሎ ለሚጠይቅ ይኸውና መልሱ ፦ 760,000 — ሰባት መቶ ስድሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን!!!
በቁጥር ሰባት መቶ ስድሳ ሺህ ሶስት መቶ ኢትዮጵያውያን — በዚያ ዘመን — በፋሺስቶች የበቀል እጅ — በግፍ ተጨፍጭፈዋል!!!! Italian Fascist Massacres: 760,000 murdered human beings!!!!
መጠነኛ አሃዛዊ ግድፈት ያለው ቢመስልም በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውና በኢጣልያም መንግስት ታምኖ ለካሣ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የወገኖቻችን መስዋዕትነት ኦሪጂናሉ እንዲህ ይነበብ ነበረ፦
‹‹In 1946, the Ethiopian Government presented a memorandum to the Paris Peace Conference which reported the following disconcerting losses:
Killed in action: 275,000
Patriots killed in battle: 76,000
Women, children and the sick killed by bombs: 17,800
Massacre of 19 February 1937: 30,000
Patriots killed by martial courts: 24,000
Patriots dead in labor camps due to deprivation and ill-treatment: 35,000
people death due to deprivation due to the destruction of their villages: 300,000
TOTAL: 760, 300 murdered human beings.››
ይህች ሃገር በደማችን የተገኘች ሃገር ነች የምንለው በምክንያት ነው፡፡ ምድራችን ውድ ዋጋ ተከፍሎባታል፡፡ ይህች መቀመጫ ያጣንባትም — በነፃነት አንገታችንን ወደ ሰማይ ቀልሰን የምንንቀሳቀስባትም – ውድ ሀገራችን – ውድ ባንዲራችን — የማይተመን የሰው ልጅ ህይወት፣ የማይተካ የሰው ልጅ ክቡር ነፍስ ተሰውቶባታል፡፡ እያንዳንዷ የምንረግጣት መሬት — የብዙ ባለውለታ ጀግኖች አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ደም የፈሰሰባት — የጀግኖች ትውልድ በመሆናችን የተቸረችን ብርቅ ሥጦታ ነች!!
ዛሬ ላይ ያለን፣ ወደፊትም ፈጣሪ ዕድሜና ጤናውን ሰጥቶን በዚህች ውድ እናት ሀገራችን ምድር የተገኘን ኢትዮጵያውያን ሁሉ – በየእርምጃችን – ጀግኖች ሰማዕታት ኢትዮጵያውያኖቻችንን እናስብ፡፡ በየትንፋሻችን ለዚህች ሃገር አንድነትና ነጸነት የወደቁ አባቶቻችን ትኩስ የጀግና ትንፋሽ ያሙቀን፡፡
ይህን ለራሳችን አመላልሰን እናስበው፡፡ የመጣንበት መንገድ ቀላል አልነበረም፡፡ የምንሄድበት መንገድም፣ የምንደርስበት ርቀትም እንዲሁ ቀላል እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ አንድነት ኃይላችን ነው፡፡ ጀግንነት ደማችን ነው፡፡ ደግነትና ምህረት በፈጣሪ ለምድሪቱ ብቃዮች የተቸረ በረከታችን ነው፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን እና ጀግኖች ሰማዕቶቿን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡
ይህች ምስኪኒቱ እናት ሃገራችን — እና አንገታቸውን ደፍተው ያሉ ምስኪን ወገኖቻችን ሁሉ — አንድ ቀን አንገታቸውን በኩራት ቀና አድርገው — በፀጋና ብልፅግና የሚረማመዱበት ቀን — ያቺ አባቶቻችን የሞቱላት ፀሐይቱ ቀናችን — ሩቅ እንደማትሆን — እናምናለን — አምላክንም ደጋግመን እንለምነዋለን፡፡
የአምላክ የበጎነት ልቦናና መንፈስ . . . በእኛ በኢትዮጵያውያን ልቦች ውስጥ ሁሉ….. ስፍፍፍፍ…. ስርፅፅፅፅፅ…. ይበልልን!!!
ኢ ት ዮ ጵ ያ ዬ – በአይበገሬ ልጆቿ ተከብራ — በፍቅር፣ በብልፅግና፣ በአንድነት — ለ ዘ ለ ዓ ለ ም ት ኑ ር ፡፡
ድኅረ ማስታወሻ፦
እንደብዙ ግፈኞች ሁሉ የሙሶሊኒ መጨረሻ ይህ ነበረ ፦ ከፍቅረኛው ከክላሬታ ጋር በኢጣልያ የቁርጥ ቀን ፀረ ፋሺስት አርበኞች ተይዞ — በሮማ አደባባይ በተዘጋጀ መስቀያ — ከነፍቅረኛው – ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ – የተረሸነው — በበቀል የናወዘው የፋሺስት ኢጣልያኖች ጥጋበኛ አምባገነን መሪ – የቤኒቶ (ዱቼ) ሙሶሊኒ — የፕሮፓጋንዳ ፎቶ፡፡