>

"ተወደደም ተጠላም ይህ የአሁኑ ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት!!!" (የአዴፓው አመራር አቶ መላኩ አላምረው፣ )

“ተወደደም ተጠላም ይህ የአሁኑ ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት!!!”
የአዴፓው አመራር አቶ መላኩ አላምረው፣
* “ሕገ-መንግሥቱ ሳይሻሻል የተሻለች ኢትዮጵያን አናስቀጥልም፤ በዚሁ እንቀጥል ማለት አሁንም በአማራ ሀገር አልባነት ላይ ሀገር እንገንባ እንደማለት ነው።”
—>
(፩) “በአንድ ክልል ጠያቂነት ተነስተን ሕገ-መንግሥቱን ልናሻሻል አንችልም” ማለት ይቻላል። ይህንን “አንድ” የተባለን ክልል ያገለለን ብቻ ሳይሆን ከመሠረቱም ያላካተተን ሕገ መንግሥት ይዞ እየመሩ መቀጠል ግን አይቻልም።
(፪) የአማራ ሕዝብ ጉዳይ “የአንድ ክልል” ጉዳይ አይደለም፤ ፈጽሞ ሊሆንም አይችልም።
መሠረታዊ ስህተቱ በመላው ሀገሪቱ ያለን ሕዝብ በውስን ቦታ ከልሎ ለመሳል ሲሞከር ነው። ሲጀመር አማራን ርስት/ሀገር አልባ የሚያደርግ ውስን ክልል መስጠቱ መታረም የሚገባው ሆኖ ሳለ ጭራሽ የሰፊውን የአማራ ሕዝብን ጉዳይ የአንድ ክልል ጉዳይ እያደረጉ ማየት ድርብ ስህተት ነው። አሁን “የአማራ ክልል” ተብሎ ከሚታወቀው ምድር ውጭ የሚኖረው ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርስ አማራ የት ተጥሎ ነው የአማራ ጉዳይ የአንድ ክልል ብቻ ጉዳይ ሊሆን የሚችለው?
(፫) የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት መሠረት አድርገው የተቀረጹት የአንዳንድ ክልል ሕግጋታ መምግሥትታ በግልጽና በማያሻማ መልኩ የየክልላቸውን “ነባር” ሕዝቦች ብቻ የመሬት ባለቤት አድርገው “መጤ” ያሏቸውን ደግሞ መሬት አልባ አድርገዋል። በመሠረቱ “ነባርነት” እና “መጤነት” በራሱ ሌላ ትርጓሜ ይሻል። በታሪክም በነባራዊ ሁኔታም በሌላም ስሌት ተመርምሮ በየትኞቹ ክልሎች የትኞቹ ሕዝቦች “ነባር” የትኞቹ ደግሞ “መጤ” እንደሆኑ ራሱ ግልጽ አይደለም። “በፈራጆቹ” ልክ ወርደን እንፈርጅ ከተባለም… መልስ የሚሹ ቁልፍ ጥያቄዎች አሉ፦ ከመቼ ጀምሮ የኖረ ነው ነባር? መጤስ? በታሪክ አጋጣሚ የትኛው ሕዝብ በየትኛው መሬት ላይ ቀድሞ ኖረ? የትኛው በሌላኛው ቀደምት ርስት ላይ ሰፈረ ሰው ተወልዶ ዕትብቱ በተቀበረበት ቦታ መጤ የሚባለው በምን መስፈታርት ነው? መጤነትና ነባርነት በዘር ይተላለፋል? …እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ያላስገቡ ወይም የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ/ሰብዓዊ መብት የጣሱ የየክልል ሕጎችን እንኳን በአስገዳጅነት የማያስተካክል ሕገ-መንግሥት ነው ያለን።
.
(በነገራችን ላይ ከመሠረቱ ሲሰየሙ ኃላነንትና ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ነው የተከወነው። ክልሎች ለተሰየሙበት መጠሪያ ስም ያዋሱ ሕዝቦች በምን መስፈርት ተመረጡ? በሕዝብ ቁጥር እንዳንል አናሳ(Minority) ሆነው የተሰየመላቸው አሉ። ከተሰየመላቸው በኋላ ለመጠሪያነት ስም ያዋሱት ክልሎችን የግል ንብረት አድርገው እንዲያዩ መደረጉ ሌላው ስህተት ነው። ለምሳሌ የአማራ ክልል መሬት መኖሪያነትም ባለቤትነትም ለአማራዎች ብቻ አይደለም። የኦሮሚያ ክልል መሬት መኖሪያነትም ባለቤትነትም ለኦሮሞዎች ብቻ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። የሌሎች ክልሎችም እንዲሁ። በአንዲት ሀገርነት እንቀጥል ከተባለ ክልሎች የአስተዳደር ወሰን ብቻ ሆነው መኖሪያነታቸውና ባለቤትነታቸው ግን የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆን አለባቸው፤ ይህም በአስገዳጅ ሕጎች ሊተገበር ይገባል። ይህ ካልሆነ ክልሉ በስሙ የተሰየመለት ሁሉ እየተነሳ ሌላውን በመጤነት እየፈረጀና እያፈናቀለ የምትቀጥል የጋራ ሀገር ግልጽ ሆና አትታየኝም።)
(፬) የአማራ መገለሉ፣ መፈናቀሉ፣ አጠቃላይ ፍዳና መከራው ተባብሶ የሚቀጥለው አሁን “ክልልህ” ተብሎ የተሰጠውን ምድር ብቻ ይዞ ለመቀጠል ከወሰነ ነው። ይህን ታሪኩንም ሆነ ነባራዊ አኗኗሩን የማይወክል “ክልል” ይዞ ስለቆየ ነው አማራው በገዛ ሀገሩ ተወልዶ ባደገበት ምድሩ ሁሉ “መጤና ሰፋሪ” እየተባለ የተፈናቀለውና የተገደለው። አማራ ለሺህ ዘመናት በኖረባቸው ቦታዎች ሁሉ ነው የመጤነት ታርጋ የተለጠፈለት። ይህ በሰው ልጅ ዘንድ መሠረታዊና ዋና የሆነን ተፈጥሯዊ መብት የካደ አከላለል የክልሎች ባለቤትነት ጉዳይ ሳይታረም ነው እየቀጠልን ያለነው። በዚሁ እንቀጥል???
(፭) ተወደደም ተጠላም ይህ የአሁኑ ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት። ምክንያቱስ?
አንደኛ፦ “አይወክለኝም/አልተወከልሁበትም” የሚል ሕዝብ እስካለ ድረስ በየትኛውም ሕዝብ ላይ በግድ የሚጫን ሕግ መኖር ስለሌለበት። አይወክለኝምም አልተወከልሁበትምም እያለ ሰሚ ያጣ ሕዝብ ደግሞ አለ። ለምሳሌ አማራ። (በነገራችን ላይ አማራ አለመካተቱን/አለመወከሉን የሚናገረው አማራ ብቻ ሳይሆን የሌሎች የተካተቱ ሕዝቦች መሪዎችም ናቸው። ለምሳሌ የኦነጉ መሥራችና የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ/አጽዳቂ አካል አባል ኦቦ ሌንጮ ለታ “ከኦነግ፣ ከሻዕቢያና ከሕወሓት ውጭ የተካተተ ማንም የለም” ብሏል።)
ሁለተኛ፦ ይህ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በሁሉም ዘንድ ቅቡል ካለመሆኑም በላይ ሊመልሳቸው የማይችል በርካታ ጥያቄዎች ስለሉ። (እነዚህ በሕግ ባለሙያዎች የበለጠ ተተንትነው መቅረብ ቢኖርባቸውም) ለምሳሌ የክልሎችን አከላለል ማንሳት ይቻላል። (ሀ) ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት የተካለለን ጉዳይ “በሕገ መንግሥት” መፍታት የሚቻለው በምን አግባብ ነው? የክልል አከላለልን ጉዳይ ያህል ወሳኝ ጥያቄ የማይመልስ ሕገ መንግሥት ምን ይሠራል? ልመልስ ካለስ ያልነበረበትንና ቀድሞ ያልወሰነውን ጉዳይ እንዴት አድርጎ ይመልሳል? (ለ) የፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት የየክልል ሕግጋተ መንግሥታትን ማስተካከል ይችላል? ከቻለ በተፈጥሮም ሆነ በሕግ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት የሆነን የመኖር መብት የሚገፉ እያሉ ለምን ዝም አለ? አንድ ሰው ተወልዶበት ዕትብቱ በተቀበረበትና ሀብት ንብረት አፍርቶ ባደገበት፣ ቤተሰብ መስርቶ በሚኖርበት ቦታ “መጤ እንጅ ነባር አይደለህም” ከማለትና የመኖር መብትን ከመንፈግ በላይ ምን መብት ሊጣስ ነው?
ባጭሩ…….ሕገ-መንግሥቱ የአንድ ክልል/ሕዝብ ፍላጎት ሆነም አልሆነም ሊሻሻል ካልቻለ የተሻለች ሀገር አትኖረንም የሚለው…. (የጸና አቋሜ)… ነው። “አብዛኛው የተስማማበት” ብሎ ነገርም ለሁልጊዜ አይሰራም። እና… አብዛኛው አሁንም አማራን ሀገር አልባ ለማድረግ ቢስማማ ይህ ጸድቆ ይቀጥላል ማለት ነው?
(የሕግ ባለሙያ አይደለሁምና የሕግ አግባብን ጥሼ ቢሆን በቅንነት የሚያርመኝን አስቀድሜ አመሰግናለሁ።)
Filed in: Amharic