>

ይድረስ ባለቀ የውክልና ዘመን "ተወካይ" ነን ለምትሉ!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ይድረስ ባለቀ የውክልና ዘመን “ተወካይ” ነን ለምትሉ!!!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
ለክቡር/ክብርት…………………………………
የአዲስ አበባ ም/ቤት አባል
በአዲስ አበባ ከተማ……………ክ/ከተማ ምክር ቤት አባል
በአዲስ አበባ ከተማ……ክ/ከተማ……ቀበሌ ም/ቤት አባል
ጉዳዩ: የህዝብ ውክልና ማለቁን ስለማሳወቅ
ከላይ በርዕሱ እንደተገለፀው ክቡርነትዎ የዛሬ ስድስት አመት በተካሄደው የከተማ፣ የክፍለ ከተማ እና ቀበሌ ምርጫ ኢህአዴግን በመወከል ብቻዎትን ተወዳድረው በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ክቡርነትዎ እርሶም እንደሚያውቁት የመዲናይቷን እጣ ፈንታ ሲወስኑ የነበረው የከተማውን ነዋሪ የአምስት አመት ውክልና ተሰጥቶኛል በማለት ነበር። ይህም ሆኖ በእያንዳንዱ አዲስአበቤ ውክልና ተሰጥቶኛል ብለው የቆዩበት ምክር ቤት ዘመኑን ከጨረሰ እነሆ አንድ አመት አልፎታል።
ስለሆነም ክቡርነትዎ ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ በየደረጃው ምክር ቤት ቆይታ እያደረጉ ያለው የነዋሪውን ውክልና ሳይዙ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። በሌላ በኩል ያለ አዲስአበቤ ውክልና የሚያሳልፉት ውሳኔም ከተጠያቂነት እንደማያድኖት ከወዲሁ ሊያውቁት ይገባል። በመሆኑም ነዋሪው ሰጥቶኝ ነበር የሚሉትን ውክልና ማለቁን ተገንዝበው ምክርቤቱን በክብር እንዲሰናበቱ በማክበር እጠይቆታለው።
 በቀጣይ በመዲናይቱ በሚካሄደው ምርጫ መሪ ድርጅቶት የሆነው ኢህአዴግን በመወከል ለመወዳደር ከመጡ በደስታ የማስተናግዶት እና የእጩ ሆኖ የመቅረቢያ መተማመኛ ወረቀት ላይ ፊርማዬን እንደማኖርሎት ከወዲሁ ቃል እገባለው። አዲስአበቤ ከመረጦት በዳግም ክብርና ግርማ ሞገስ የሚወዱትን ምክር ቤት ይቀላቀላሉ። ይወስናሉ። ያስወስናሉ። እስከዛው ድረስ ግን ከላይ እንደገለጽኩት የነዋሪውን ውክልና የጨረሰውን ምክር ቤት ለቀው እንዲወጡ በድጋሚ አሳስቦታለሁ።
                                           ከሰላምታ ጋር
                                           ስምና ፊርማ
ማሳሰቢያ:- እያንዳንዱ አዲስአበቤ በአካባቢው ለሚገኙ የከተማ/ የክፍለ ከተማ/ የቀበሌ(ወረዳ) የምክር ቤት አባላት በማህበራዊ ድረ ገፅ ፣ ኢሜይል፣ በፅሁፍ፣ በቃል መልዕክቱን ያስተላልፍ። የምክር ቤት አባላቶቹን በመዝናኛ፣ በለቅሶ፣ በእድር፣ በሀይማኖት ተቋማት፣ በማህበር፣ በእቁብ፣ በትራንስፓርት ወዘተ ሲያገኛቸው እያስቆመ ይንገራቸው። ይሄን በማድረግ ኦዴፓ በቀጣይ በምክር ቤቱ ሊያሳልፍ የፈለገውን አደገኛ ውሳኔ ያስቁም። ኦዴፓ የከተማውን ምክር ቤት ተሻግሮ በፓርላማ አስወስናለው የሚል ትምክህት ውስጥ ከገባ በፓርላማ አዲስአበቤ ወክሎናል በማለት ለተቀመጡት 26 የሸንጐው አባላት ተመሳሳይ መልዕክት ማስተላለፍ ይገባል። እንደ ለመዱት አዲስአበቤ አንዳችም ውክልና በሌለው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ይወስኑ። የዛኔ አዴፓ/ ብአዴን በአዲስአባ ላይ የያዘው አቋም ከአንገት ይሁን ከአንጀት ይታወቃል።
ሰላማዊ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል
Filed in: Amharic