>

የጭምብል አስወላቂው እስክንድር ነጋ ጉዳይ!!! (አስቻለው አበራ)

የጭምብል አስወላቂው እስክንድር ነጋ ጉዳይ!!!
 
አስቻለው አበራ
የዓለም ባንክ ፈንድ የሚያደርጋቸውን  ፕሮጀክቶች ውጤታማ መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን የሚገመግምበት ሁለት መሰረታዊ መስፈርቶች አሉት።
እነሱም አንደኛው መስፈርት ፕሮጀክቱ ቢኖር ወይም ባይኖር (with or without)  የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ ከፕሮጀክቱ በፊት እና ከፕሮጀክቱ በሗላ (before  and after) በሚል ማነፃፀር ነው።
የእስክንድርንም ጉዳይ በእነዚህ በሁለቱ መስፈርቶች ለመመዘን እሞክራለሁ።
እስክንድር ታስሮ ፣ ተፈትቶ ፣ ተሸልሞ ብዬ ስለእሱ የጀርባ ታሪክ ሳላንዛዛ በቀጥታ ወደ ገደለው እገባለሁ ።
ከወራት በፊት እስክንድር የአዲስአበባ ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር የለም፣ “ከንቲባው” አዲስአበባ ህዝብ ላይ የቆሙ እንጂ ለአዲስአበባ ህዝብ አልቆሙም፣ በሚቀጥለው ምርጫ ልዩ ጥቅም እናስከብራለን የሚሉትን በምርጫ እንቀጣለን የሚሉ እና የመሳሰሉ  አስተያየቶችን መስጠቱን ተከትሎ የተወሰኑ ወዳጆቼ እና ሌሎችም ሰዎች እስክንድር የሰጠው አስተያየት አላስፈላጊ ነው፣ እንዲያውም ጠብ ያለሽ በዳቦ ነው፣ አክራሪ ኦሮሞዎችን የበለጠ ያነሳሳል (provocative) በሚል ሲተቹት፣ እኔን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ በምርጫ እንቀጣለን ማለት ሰላማዊ አገላለፅ ስለሆነ ማንንም ሊያነሳሳ አይገባም። ምክንያቱም ሌላውም ቡድን በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም በምርጫ እንቀጣለን ለእዛ ያድርሰን በሚል ፋይሉን መዝጋት ይቻላል የሚል አስተያየት ነበረን ።
ሆኖም ከሌላው ወገን የተሰጠው ምላሽ ማስፈራሪያ የታከለበት እና በምርጫ ብቻ ሳይሆን በጡጫም ቢሆን ስልጣን አንለቅም የሚል ሆኖ አረፈው።
ከዚያም ለአንድ ሰሞን ይሄ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ሰነበተ እና ለአጭር ጊዜ ፋታ ከአገኘ በሗላ በኩየጨፌ የተሰሩት ኮንደሚኒየም ቤቶች እጣ በተመለከተ ከአክራሪው የኦሮሞ ቡድን ሌላ የማስፈራሪያ መግለጫ መሰጠቱን ተከትሎ በብዙ የኦሮሚያ ከተሞች ዱላዊ ወይም ገጀራዊ (ሰላማዊ ላለማለት ነው) ሰልፎች ተካሄዱ።
ሰልፉን ያቀነባበረው ኦዲፓ መሆኑን በሚያሳብቅ መልኩ፣ ድርጅቱ በሰልፈኞቹ እና ሰልፉን የማስጀመር ፊሽካ የነፋው ግለሰብ ከጠየቁት ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መግለጫ ሰጠ።
ከዚያም አልፈው በአዲስአበባ ልዩ ጥቅም ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባለቤትነትን ለማረጋገጥ እንሰራለን አሉ።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ድምፁ ያልተሰማው የድርጅቱ ሊቀመንበር አብይ አህመድ ከእሱ ይሁንታ ውጪ መግለጫዎቹ እንደተሰጡ እና እንዲያውም አብይ ብቻውን ነው እንርዳው የሚሉ ድምፆች ከብዙሃኑ ይደመጡ ነበር።
ከዚያም የእነ እስክንድር ቡድን አዲስአበባ ላይ በግልፅ እየመጣ ያለውን አደጋ ለመከላከል ህዝቡን የማደራጀት ስራ ጀመሩ።
የአዲስአበባ ህዝብ መደራጀት ኦዲፓ/ኦነግ ላቀደው የአዲስአበባ የባለቤትነት ጥያቄ አስጊ መሆኑን ስለተረዱ የመጨረሻውን ወሳኝ ጥይት መተኮስ እንዳለባቸው ስለተገነዘቡ ፣ አብይ ጭምብሉን አውልቆ የእነ እስክንድርን ቡድን ላይ ግልፅ ማስፈራሪያ እንዲያደርግ እና የማደራጀቱ ሂደት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲታቀቡ አደረገ።
ምንም እንኳን የአብይ ማስፈራሪያ ባልደራስ ላይ የተወሰነ ጊዜያዊ እቀባ ቢያደርግም ለአብይ እና ለድርጅቱ ኦዲፓ ሊጠገን እና ወደኋላ ሊመልሱት የማይችሉት ዋጋ ሊያስከፍሏቸው ችሏል።
ከላይ በዝርዝር የፃፍኩት ብዙ ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ስለሆነ ለመግቢያ ያህል ይሄን ካልኩኝ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ማለትም የእስክንድርን ተሳትፎ በሁለቱ መስፈርቶች ልመዝንናቸው፣
አንደኛ : የእስክንድር ተሳትፎ ጨርሶ ባይኖር ኖሮ እና ተሳትፎው መኖሩ  ያመጣቸው ለውጦች ምንነት።
ጉዳት ማስከተልን በተመለከተ የእነ እስክንድር ተሳትፎ መኖሩ ለአንድ ሰሞን የሚዲያ ውዝግብ እና ያንን ተከትሎ ከተፈጠረው ጊዜያዊ ውጥረት ውጪ የአዲስአበባ ነዋሪ ላይ ያስከተለው ይሄ ነው የሚባል ጉዳት ለእኔ አልታየኝም። የአጭር ጊዜው ውጥረት ከእረዥም ጊዜ ጠቀሜታው አንፃር ሲታይ ሚዛን አይደፋም።
በእስክንድር ተሳትፎ ምክንያት የተፈጠሩ ሌሎች የታዯችሁ ችግሮች ከአሉ አስተያየታችሁን አስቀምጡ።
የእስክንድር ተሳትፎ መኖር ያመጣውን ጠቀሜታ በጥቂቱ  ለመዘርዘር ያህል፣
1.1: አክራሪው ቡድን በአዲስአበባ ጉዳይ የምርጫ ውጤት ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆነ እና በጉልበትም ቢሆን የመቆጣጠር ህልም አይሉት ቅዠት እንዳለው ይፋ ማስደረግ መቻሉ።
1.2:  ኦዲፓዎች  በአዲስአበባ ላይ የልዩ ጥቅም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም የባለቤትነት ጥያቄ እንዳላቸው የተደበቀው አላማቸውን ይፋ ማድረጋቸው።
1.3: አዲፓ እና ደህዲን በአዲስአበባ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም ይፋ ማውጣታቸውና ኦዲፓን ውጥረት ውስጥ መክተታቸው።
1.4: አብይ አህመድ ከጭንብሉ ወጥቶ በአዲስአበባ ጉዳይ ላይ ከአክራሪው ቡድን የተለየ አቋም እንደሌለው እንዲጋለጥ ማድረጉ እና የአብይን የተደበቀ የአምባገነንነት ባህሪ የሚያጋልጥ ሁኔታ መፍጠሩ ።
1.5 : የአዲስአበባ ህዝብ እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በአዲስአበባ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ኦዲፓ/ኦነግ እየሸረቡ ያሉትን ሴራ ከምርጫው በፊት ተረድቶ ተደራጅቶ እና ተነቃቅቶ እንዲጠብቅ ማዘጋጀቱ የሚሉት ናቸው።
በሁለተኛው መስፈርት ወይም ከእስክንድር ወይም ከባልደራስ በፊት እና ከባልደራስ በኋላ በሚለው መመዘኛ ሲታይ ደግሞ ፣ ከባልደራስ በፊት የኢትዮጵያ እና የአዲስአበባ ህዝብ ሊያውቅ የማይችላቸውን እና በባልደራስ ምክንያት ሊያውቅ የቻላቸውን መሰረታዊ ነገሮች በጥቂቱ ለመዘርዘር እሞክራለሁ።
2.1 አክራሪው የኦሮሞ ቡድን የምርጫውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆነ እና በጉልበትም ቢሆን አዲስአበባን ኦሮሞ ላልሆነ የፓለቲካ ቡድን አሳልፎ ላለመስጠት ሃይል ጭምር ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑን እንዲታወቅ አድርጓል። የእስክንድር ተሳትፎ ባይኖር አክራሪው ወገን ይሄ አላማ እንዳለው ከወዲሁ ማወቅ አይቻልም ነበር።
2.2: ኦዲፓ በአዲስአበባ ባለቤትነት ያለውን አቋም እንዲያውቅና የከተማው ነዋሪ ምርጫውን እንዲያስተካክል ረድቶታል።
3.3. ምናልባት አዲፓ እና ደህዲን በተናጠል አዲስአበባ ላይ ወይም በሌሎች ክልሎች የሚወዳደሩ ከሆነ በአዲስአበባ ጉዳይ ከኦዲፓ የተለየ  አቋማቸውን ከወዲሁ ህዝብ እንዲያውቅ ረድቷል ።
2.4 : ከሁሉም በላይ የአዲስአበባ እና የኢትዮጵያ ህዝብ አብይ አህመድን የሚያውቀው ለኢትዮጵያ አንድነት እንደሚቆም እና በአክራሪው ቡድን ተፅዕኖ ስር ወድቋል የሚለውን መላምት ፉርሽ  አድርጎ አብይ  በተለይ በአዲስአበባ ጉዳይ ያለው አቋም ከአክራሪው ቡድን  የተለየ እንዳልሆነ ለማሳወቅ ረድቷል።
ይሄ እውነት እንዲጋለጥ የእስክንድር ቡድን አስተዋጽኦ ባያደርግ ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ የአብይን እውነተኛ ማንነት እና የአምባገነንነት ባህሪ ሳይረዳ በሚቀጥለው ምርጫ አብይን ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ ሲል ከእነግሳንግሱ እንዲመርጠው እና ህገመንግስት የማሻሻልም ሆነ የአዲስአበባ ባለቤትነት ጉዳይ የሚያበቃለት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር ። አሁን ግን የኦዲፓንም ሆነ የአብይን ትክክለኛ ማንነት ከአወቀ በኋላ መምረጥ ወይም ያለመምረጥ የህዝቡ ሃላፊነት ይሆናል። ቢያንስ ቀድሜ ባውቅ ኖሮ ከሚል ቁጭት ይድናል።
ስለዚህ ተቀበልነውም አልተቀበልነውም አሁን ግልፅ ሆነልንም ወይም እያደር ቢገለፅልንም ፣ እስክንድር አውቆም ሆነ ሳያውቅ የኢትዮጵያን የፓለቲካ ዳይናሚክስ ወደኋላ እንዳይመለስ አድርጎ ቀይሮታል።
የአዲስአበባን ጉዳይ በአማራ እና በኦሮሞ ፓለቲከኞች ወይም አክቲቪስቶች መካከል ብቻ ያለ ውዝግብ አስመስሎ አሳንሶ ማየቱ የተለመደ ስህተት ነው።
በአጭሩ የአዲስአበባ ጉዳይ የኢትዮጵያ  የህልውና (make or brake)ጉዳይ ነው።
Filed in: Amharic