>

ዋጋ የሚያስከፍል እውነት !!! (ሳምሶን ሚሀይሎቪች)

ዋጋ የሚያስከፍል እውነት !!!
ሳምሶን ሚሀይሎቪች
* ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ለ የሰጡት ቃለ መጠይቅ በቅንጭብ ቀርቧል። ከቃለ መጠይቁ ውስጥ ” የባለ አደራ ም/ቤት አያስፈልግም ” ጩኸት ቀስቅሷል። 
 
* ዶ/ር ብርሀኑ በዚህ ቃለ መጠይቅ ታክቲካል ስህተት የሰራ ቢመስልም እውነት የመናገር ድፍረቱን ፣ ጭብጨባ ላለመከተልና ዘላቂውን የሀገር መረጋጋት ላይ ትኩረት ማድረጉ አሁንም የሚደነቅ ነው
” አዲስ አበባ የሚያሻት ባለ አደራ መንግስት ሳይሆን የከተማዋን ህዝብ የፍታሐዊነትና እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መንግስትን የሚተቹ ተጽዕኖ ፈጣሪ ንቅናቄዎች ፖለቲካና ሲቪክ ማህበራት ናቸው !! “
አዲስአበባ ባለአደራ ም/ቤት እንደማያስፈልጋት እሙን ነው። እነ እስክንድር ነጋም እያቋቋሙት ያለው ስብስብ አሁን ያለውን ም/ቤት የመገዳደር ፍላጎት ያለው አይነት ሳይሆን የከተማው ህዝብ ድምጹ እንዲሰማ የማድረግ ሀሳብ ያለው ነው። እስክንድርን ተከትሎ የተነቃነቀው የህዝብ ስሜት መንግስትን አለፍ ብሎ ጽንፈኛ ኦሮሞዎችን እንቅልፍ እንደነሳ ግልጽ ሆኗል። ለዚህም ነው የእስክንድር ንቅናቄ ሆነ ተብሎ በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት እንዲመስል ፕሮፓጋንዳ የተከፈተበት።
ብርሀኑ ባለአደራ ዉይም አሸጋጋሪ ም/ቤት አያስፈልግም ማለቱ እውነት ነው። ያም ቢሆን ሁለት ኪሳራ ይዞበት እንደሚመጣ ከወዲሁ ግልጽ ነው። አንደኛው ኪሳራ በአዲስአበባ ህዝብ ዘንድ በጥራጣሬ መታየት ነው። ህዝብ ጉዳዩ በግልጽ እስኪብራራለት ድረስ ግራ መጋባቱ አይቀርምና።
ሁለተኛውና ትልቁ ኪሳራ በቀጣይ ከጽንፈኛ ኦሮሞዎች አዲስአበባ ላይ የሚመጣው ዘመቻ ነው። እነ ጃዋር መሀመድ ይህንን አጋጣሚ እስክንድርን ለማጥቃት እና  የአዲስአበባ ብቸኛ ባለቤትነት ጥያቄያቸውን ለማጦዝ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የብርሀኑ ንግግር እውነት ቢሆንም ታክቲካል ጠቀሜታው ” ለፊንፊኔ ኬኛ ” ሊሆን ይችላል።
ዶ/ር ብርሀኑ በዚህ ቃለ መጠይቅ ታክቲካል ስህተት የሰራ ቢመስልም እውነት የመናገር ድፍረቱን ፣ ጭብጨባ ላለመከተልና ዘላቂውን የሀገር መረጋጋት ላይ ትኩረት ማድረጉ አሁንም የሚደነቅ ነው። ዶ/ሩ በተናገረ ቁጥር ሶሻል ሚዲያው ከፍ ዝቅ ማለቱ ደግሞ የሰውየውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያሳያል። እዚህ ሁሉ ውይይት ውስጥ አዲስአበባ የማን ናት የሚለው ጥያቄን ድርጅቶች የያዙት አቋም ተረስቶ ክርክሩ ሰለ ባለአደራ ም/ቤት መሆኑ የሚዲያ ሰዎች እንዴት በቀላሉ የጩኸት ፓለቲካ ውስጥ ሊከቱን እንደሚችሉ ያሳያል።
Filed in: Amharic