>
5:18 pm - Tuesday June 15, 4438

የአልጀሪያው ቡተፍሊካ የሚያስታውሰን ነገር… (ምሕረት ዘገዬ)

የአልጀሪያው ቡተፍሊካ የሚያስታውሰን ነገር…

ምሕረት ዘገዬ

የአንድ ሀገር ጠ/ሚ ወይም ፕሬዝደንት “ውኃ ለሰው ልጅ ጠቃሚ ነው” ስላለ ብቻ ስለውኃ ጠቀሜታ በተናገሩ ቁጥር ያን የባለሥልጣኑን ንግግር እንደምንጭ መጠቀም ከቀልድ የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡ በጣም ግልጽ ጉዳይ ስለሆነ፡፡ እናም ኦሾም ይናገረው ሎብሳንግ ራምባ በቅጡ ካልያዛቸውና ካልተቆጣጠራቸው በስተቀር የሰው ልጅ የሚሰነካከልባቸው ዋና ፍላጎቶቹ ሥልጣን፣ ገንዘብና ወሲብ መሆናቸው እማኝ መጥቀስ በማያስፈልግበት ሁኔታ ግልጽ ነው፡፡ ዝርዝሩን “Power, Money and Sex” በሚለው መረጃ ማፈላለጊያ ወደኢንተርኔት በመግባት ማግኘት ይቻላል፡፡

የአልጀሪያው መሪ ማንትስ ቡተፍሊካ ከ20 ዓመት በላይ አልጀሪያን ገዝቶ አሁንም ቅም አላለውም፡፡ ፈጣሪ ከላይ በስትሮክ አደባይቶት አንደበቱን ጨምሮ ሁለመናው በእግዜር እጅ ተይዞ በዊልቼር እየተገፋ በሚንቀሳቀስበት በአሁኑ ሰዓት እንኳን ለአምስተኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫ ለመወዳደር ያለውን ቁርጠኝነት ከመግለጽ ቅንጣት አላፈረም – ሰው እንዲህ ነው፡፡ እኔ ግን ስለርሱም፣ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮም፣ ስለሀገራችን አንዳንድ እምቢ አላረጅም ፖለቲከኞችም ክፉኛ አፈርኩ፡፡ ይህ የቡተፍሊካ ጉዳይ በራሱ ሰው መሆንን እንድንጠየፈው ያደርጋል – በበኩሌ ተጠየፍኩት፡፡ ደግነቱ ግን የጦር መሪው በሰጠው መግለጫ ሰውዬው አርፎ መጦርና በሽታውን ማስታመም እንደሚገባው ስለተናገረ አልጀርያውያን ጥያቄያቸው መልስ እያገኘ ይመስላል፡፡ የኛ አለ እንጂ እንደሽሮ እየተንተከተከ ወዴትኛው አቅጣጫ እንኳን እንሚገነፍል ያልታወቀ፡፡ ወደ ሩዋንዳ ወይንስ ወደ ሦርያ? ዝም ብለሽ ጠብቂ አዳሜ፡፡ ዱሮውንም ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው፡፡

“አፍሪካውያን ስለሆን ይሆን ይሄ የሥልጣን ሱስ እንዲህ የሚያናውዘን?” ብዬ አሰብኩ፡፡ ግን በጠንካራ ህጎች ስለተሸመቀቁ እንጂ የየትም ሀገር መሪዎች ይህን የሥልጣን ፍቅርና ሱስ በቀላሉ እንደማይተውት ደግሞ አስታወስኩ፡፡ ሥልጣን በጣም መጥፎ ነው፡፡ ያጓጓል፡፡ ያቃዣል፡፡ ኅሊናን ያስታል፡፡ ምክንያታዊነትን ያጠፋል፡፡ ይሄውና የት ይደርሳል የተባለው የኛው ዶ/ር አቢይስ ምላሱን አድጦት ይሁን ከልቡ አምኖበት ከብዕርና አንደበት ውጪ ምንም ዓይነት የጦርም ሆነ የዐመፅ መሣሪያ ከሌለው እስክንድር ነጋ ጋር በአዲስ አበባ ጉዳይ “ግልጽ ጦርነት እንገባለን!” በማለት ቀደም ሲል “መግደል መሸነፍ ነው” ብሎ የተናገረውን አንድ ዓመት ሳይሞላው ሻረው አይደል? አቢያችን አይመስለኝም እንጂ ሁኔታዎች ተመቻችተውለት እንደ ቡተፍሊካ 20 ዓመታትን ሥልጣን ላይ ቢቆይ ደግሞ – ያኔም ለሥልጣን ገና ወጣት እንደሚሆን በታሳቢነት ይያዝልኝ – በምን መልክ ሥልጣኑን ሊያስቀጥል እንደሚችል እስከዚያን ጊዜ የምትቆዩ የምታዩት ይሆናል፡፡ እኔ ወደምገኝበት ስትመጡ ታዲያ እንድትነግሩኝ አደራ – የትም ልሁን ወደዚያ የሚመጣ መቼም አይጠፋም፡፡ ለማንኛውም የሀገራችን የተቃዋሚዎች ቁጥር ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ካልተስተካከልኩ ብሎ በየቀኑ እያሻቀበ ያለበት ሁኔታ የሚጠቁመን ብቸኛ ነገር የፖለቲካ ደናቁርትና የሥልጣን ስግብግብ መሆናችንን ነው፡፡ እናሳዝናለን፤ እናሳፍራለንም፡፡ ይህን በሽታችንን ማየትም ሆነ ማከም የሚሻ ደግሞ የለም፡፡

አፍሪካም ሆነች በጥቅሉ ዓለማችን ዕድለቢሶች ናቸው፡፡ ሥልጣንን በተመለከተ እነአብዱላዚዝ ቡተፍሊካን፣ ካሙዙ ባንዳን፣ ሮበርት ሙጋቤን፣ ሙኣማር ጋዳፊን፣ አፄ ኃ/ሥላሤን፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን፣ መለስ ዜናዊን፣ አፄ ቦካሣን፣ ኢዲያሚንን…. የመሰሉ የዕድሜ ልክ አምባገነኖችን አስተናግደዋል – አንዳንዶቹን ሞት ቢቀድማቸውም ቢያንስ በፍላጎትና በዕቅድ ደረጃ፡፡ ሥልጣን ደግሞ የሁሉም መሠረት ነው – ገንዘብ ታገኝበታለህ፣ ዕውቅናንና ዝናን ታተርፍበታለህ – ባል ኖራት አልኖራት ያሻህን ሴት በአጃቢዎችህ ወደመኖሪያህ እያስመጣህ ታማግጥበታለህ፡፡ እናም ዓለማችን ቢል ጌትስንና ዋረን ባፌን የመሳሰሉ ደጋግና ለሰው ልጅ ቅን አሳቢ ከበርቴዎችን የማፍራቷን ያህል ስም መጥራት ሳያስፈልግ በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም የታዩና የሚታዩ ዕድሜም ሆነ ተሞክሮ የማያስተምራቸው ሴሰኛ ሀብታሞችን ታዝበናል – ምንም እንኳን ከነዚህ አንዳንዶቹ ቸርና ለጋስ ቢሆኑም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሦስትም አንድም የሆኑ ሰውን አዋራጅ ነገሮች በአግባብ ካልተያዙ ሀገርን እሰክማፍረስ ይደርሳሉ፡፡ አላህ ካልታደገን፣ እግዜር ካልገሰጸልን የኛዋን ፈረሳ እያጠናቀቁ ይመስላል፡፡

ሥልጣንን በተመለከተ ወደ ሀገራችን ስንመጣ ነገሩ የተለዬ መልክ የለውም፡፡ የተማረ የምትለውም ያልተማረ የምትለውም በነዚህ ሦስት ወጥመዶች የመጠለፍ ዕድሉ እጅግ ሰፊ ነው፡፡

ነፍሱን ይማር አፈሩንም ገለባ ያድርግለትና አቶ አሰፋ ጫቦ አንድ ወቅት ስለአንድ ፕሮፌሰር የጻፈው የሥልጣን ወዳድነት ምን ጊዜም ከአእምሮየ አይጠፋም፡፡ ፕሮፌሰሩ በሥልጣን ፍቅር ከመጠበሱ የተነሣ አሰፋን ምሣ ጋብዞ በማግባባት ሥልጣኑን ለርሱ አጽንቶለት ወደ ውጭ እንዲሄድ (ሊሄድ ስለነበር) ተማጥኖታል፡፡ ያ ሰው አሁንም ድረስ በሥልጣን ፍቅር እንደተለከፈ አለ – ከ30 ዓመታት ላልተናነሰ ጊዜ ሲገኝ የጥምረትና የኅብረት፣ ያ ዕድል ሳይገኝ የዜግነትና መሰል ድርጅቶች አመራር እንደሆነ አሁን ድረስ አለ – 7 ቁጥር አከፋፋይ፡፡ ያሳዝናል፡፡ ይህ የሥልጣን ጉጉት ደግሞ አያድርስ እንጂ በጠበልም ሆነ በሥነ አእምሮ ህክምና የሚለቅ አይመስልም፡፡ ልክፍት ነዋ!

ይህ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎችም ሞልተዋል፡፡ ያቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅት የነርሱ ፒኤልሲ እስኪመስላቸውና እኛ ታዛቢዎችና አባሎቻቸውም እስኪመስለን ድረስ እንደግል ንብረት የሚቆጣጠሩ ብዙ ናቸው፡፡ አሁንም ስማቸውን አናነሳም፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በሥነ ልቦናው ዘርፍ የ megalomania ሥነ ልቦናዊ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑ መረዳት ቀላል ነው – ብዙ ነገሮች ከአእምሮ ጤንነት ጋር ይያያዛሉ፡፡ እነሱ ከሌሉ ድርጅቱም ከዚያም በተያያዘ ሀገሪቱም ኅልውናቸው እንደሚያከትም ያምናሉ፤ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የሚገነዘቡት ሞት ሲያልፍ እንደማይነካቸው ዘላለማውያን እንጂ አሁን ታይቶ ከደቂቃዎች በኋላ እንደሚጠፋ ጉም ወይም ጤዛ አይደለም፡፡ በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ልዩ ፍጡራን ናቸው – ምንም ዓይነት ምክር አይጥማቸውም፡፡ ምክንያቱም ለራሳቸው የሰጡት ግምት ከማንምና ከምንም በላይ ነውና፡፡ እናም የዛሬ 10 እና 20 ዓመት በአርአያቸውና በአምሣላቸው ቀርጸው ባቋቋሙት ንቅናቄ ወይም ግምባር ውስጥ የመሪነቱን ቦታ ለይምሰል እንኳን ለተወሰነ ጊዜ ለማንም ሳይሰጡ እነሱ በፈለጉት መንገድና ባሰኛቸው የሹፍርና ሥልት ከየምናምኑ እያላጉ ድርጅቱን ይነዱታል፡፡ “ዐመድ በዱቄት ይስቃል” እንዲሉ በነሱ ብሶ ደግሞ ሌሎችን በኢ-ዴሞክራሲያዊነት ሲያብጠለጥሉና ሲወቅሱ የሚስተካከላቸው የለም፡፡ ይህንንም እስኪሰለቸን የታዘብነው የሰዎች ከንቱነት ነው፡፡ የሚገርመው ሌላው ከዚህ ጋር የተያያዘ ነገር ደግሞ እነዚህ ሥልጣን ወዳድ ግለሰቦች በሥራቸው የሚኮለኩሏቸው ሰዎች ሲጠሯቸው “አቤት” ሲልኳቸው “ወዴት?” የሚሉ ደናቁርትና የኢኮኖሚ ወይም የአስተሳሰብ ጥገኞች መሆናቸው ነው፡፡ “ግም ልግም ተያይይህ አዝግም”፡፡ በቃ – ተያይዞ መጥፋት፡፡ በዚህ ዓይነት የኤሊ ጉዞ ደግሞ ሀገር አትለወጥም፡፡ ቁልቁል መንጎድ እንጂ ሽቅብ መጓዝ አይታሰብም፡፡ ዕውር ለውር ቢማራ መጨረሻው ገደል ነው፡፡

ዘመኑ ከፍ ያለ ነው፡፡ ዛሬ እንድትናንት አይደለም፡፡ የዛሬን ትውልድ በትናንቱ ቅኝት ልግዛው ብትል “አልሰማህም!” ነው የሚልህ፡፡ ቋንቋው ሳይቀር ተለውጧል – ዱሮ በኛ ዘመን “አልሰማህም!” የሚባል ፈሊጥ እንዳልነበረ ያስቧል ለምሣሌ፡፡ የዘመነ ኢሕአፓና መኢሶን አስተሳሰብና የአመራር ቅኝት ትውልዶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ለወጣቱ ዕድል መስጠት ይገባል፡፡ ከኋላው ሆኖ መምከርና ልምድን ማካፈል ሲገባ በዱሮው በሬ እንረስ ማለት ፍትጊያን ማጠናከርና ገመድ ጉተታውን ማደስ ነው፡፡ ከዚያም “ኬኛ፣ ኬኛ” እያሉ ወደ ጥልቁ የእሳት ባህር ተያይዞ መውደቅ፡፡
ቡተፍሊካን እግዜር ይይለት፡፡ አርፌ የተቀመጥኩትን ሰውዬ አስለፈለፈኝ – ሊያውም ሰሚ ላይገኝ፡፡

ያዙ እንግዲህ ልመርቃችሁ – አሜን በሉ፡፡ ወገኖቼ ከሥልጣን ፍቅር ይሠውራችሁ፡፡ ከወሲብ ቅሌት ያድናችሁ፡፡ ከገንዘብ አራራ ይታደጋችሁ፡፡ ከጤናማ ኅሊናችሁ ጋር ያስማማችሁ፡፡ ከዝነኝነት አባዜ ይታደጋችሁ፡፡ አስመሳዩን ሳይሆን እውነተኛውን ክርስቶሳዊ ትኅትናን ያላብሳችሁ፡፡ ለተፈናቃይ ክልል አራት ሚሊዮን ብር መድቦ ለአፈናቃይና ተወልጄበታለሁ ለሚለው ክልል መቋቋሚያ 35 ሚሊዮን የ“ፌዴራል” መንግሥትን የጋራ ሀብት ከሚሰጥ ዘረኛ የባንክ ማኔጅመንት ይሠውራችሁ፡፡ በአፉ እያዋዛ በልቡ ጩቤ ከሆነ አነሁላይና አማላይ የሀገር መሪ ይጠብቃችሁ፡፡ እንደዱሮው የንጉሠ ነገሥቱ ጠ/ሚኒስትር ለሚሠራው ሸፍጥ ጊዜ እንዲያገኝ “ፋታ ስጡኝ” እያለ ላይ ላዩን ለሁሉም የሚሠራ በመምሰል በውስጥ ግን የአንድን ሀገር ቢሮክራሲ በራሱ ነገድ ከሚያጥለቀልቅ አስመሳይ ተረኛ የገዥ ቡድን ይጠብቃችሁ – አሜን በሉ እንጂ ምንድን ነው ዝምታው፡፡ ከትዕቢትና ትምክህት፣ ከዘረኝነትና ከጎጠኝነት ይጠብቃችሁ፡፡ ነገ ለምትጠፋ ብልጭልጭ ዓለም ከማጎብደድ ይታደጋችሁ፡፡ ከአባቱ ኦህዲድ/ኦነግ ጋር ወደ ሱቅ እንደገባ ቄሮ ሕጻን ከመሆን አምላክ ይሠውራችሁ፡፡ የለማ የለማውን ከተማ እየመረጣችሁ “ኩኒ መጋላ ኬኛ/ kuunnii magaalaa keygnaaa” ከሚል ዘመኑን ያልዋጀ ቧልታይና ድንቃይ አስተኔ የውርደትና ቅሌት ድራማ ይጠብቃችሁ፡፡ በሕይወት ከተረፍኩ ያኔ ያገናኘን ታዲያ፡፡ mz23602@gmail.com

ማሳሰቢያ፡-

ኦዴፓ ወይም አዴፓ አንድኛችሁ ስማችሁን ለውጡልን፡፡ ብዙ መምታታት እያስተዋልን ነው፡፡ ስማችሁ ተቀራራቢና የተኮራረጀ በመሆኑ ብዙ ጸሐፍያን ሳይቀሩ እየተምታታባቸው “ኦዴፓ” ለማለት “አዴፓ” ይላሉ፤ “አዴፓ” ለማለትም “ኦዴፓ” ይላሉ፡፡ ስለዚህ በትዕዛዝ ከላይ የወረደ(የተሰጠ) ስም እንደሆነ ቢገመትም እባካችሁን በዚህ እንኳን አታምታቱን፡፡ እውነቴን ነው፡፡ የታዘብኩትን ነው የምናገረው፡፡ እናንተው በዘር ስም እየተጠራችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የነፃነት ጮራ ይፈነጥቃል ማለት ደግሞ ህልም ነው፡፡ አንድ ፓርቲ በዘርና በሃይማኖት ወይም በፆታ ከተጠራ አግላይ ነው፤ ፓርቲ ሳይሆን ዕድር ወይም የጽዋ ማኅበር ነው እንጂ ሀገርን ለማስተዳደር የተዘጋጀ የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡ ወይ ኢትዮጵያ! ስንትና ስንት ጉድ ነው የኸለቀብሽ ከቶ፡፡ አየ የመከራሽ ጽናቱ!

Filed in: Amharic