>
5:16 pm - Tuesday May 23, 5505

ኑ የመቃብር ጠባቂነታችንን ትተን  የኢትዮጵያን ትንሣኤ እናብሥር!! (የጠ/ ሚ ዶ/ር  አብይ የትንሳዔ በዓል መልዕክት)

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  አብይ የትንሳዔ በዓል መልዕክት
 
ኑ የመቃብር ጠባቂነታችንን ትተን 
የኢትዮጵያን ትንሣኤ እናብሥር!!!
የክርስትና እምነት ተከታይ የሆናችሁ መላ የሀገሬ ህዝቦች፤ ለሁለት ወራት ያህል በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና ከአምላክ ጋርም በተመስጦ ልቦና በመገናኘት ያሳለፍነውን ዐቢይ ጾም እንኳን በሰላም እና በፍቅር አጠናቀቃችሁ፤
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
ከመነሣት የበለጠ ታላቅ ነገር የለምና ትንሣኤ ታላቅ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ፣
መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል መነሣቱን የምናበሥርበትና የምናስብበት በዓል ነው፡፡
ከአእምሮ በላይ የሆነውን ሥራ ዕጹብ ድንቅ ብለን፣ በደስታና በፍቅር የምናከብርበት ታላቅ በዓል ነው፤ ከመሞት በላይ ውርደት ከመነሣትም በላይ ክብር የለምና፡፡ ከሞት አጠገብ ሕይወት፣ ከመቃብር አጠገብ ትንሣኤ መኖሩን የምናስብበት፣ በአእምሯችንም ሰሌዳ የምናትምበት በዓል ነው፤ ትንሣኤ፡፡
በትንሣኤ ጉዞ ውስጥ ዓርብ፣ ቅዳሜና እሑድ አሉ፡፡ ዓርብ እውነትና ሐሰት፣ ወዳጅና ጠላት፣ ተሥፋና ሥጋት፣ እምነትና ፍርሐት፣ አምባ እና ሳቅ፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ጽናትና ድካም የተቀላቀሉበት ጊዜ ነው፡፡ እየነጋ ባለ ፀሐይና በድቅድቅ ጨለማ መካከል ያለውን ቀጭን መሥመር ለመለየት የሚያስቸግርበት ቀን ነው – ዓርብ፡፡
በአንድ በኩል በጦር ጉልበታቸው የሚተማመኑ ሮማውያን፣ በሌላ በኩል እናውቃለን የሚሉ የአይሁድ ሊቃውንት አንድ ሆነው ፀሐይ እንዳትወጣ የሚታገሉበት ቀን ነው -ዓርብ፡፡ የተስፋ ፀሐይ እንጂ አማናዊት ፀሐይ ገና አልወጣችም፡፡ ውስጥ ዐዋቂ ነኝ የሚለውን ይሁዳን ያገኙ ግብዞች፣ ፀሐይን የቀበሩ መስሏቸው፣ ሐውልት ሊያቆሙባት የሚሮጡባት ቀን ነች – ዓርብ፡፡
በዕለተ ሆሳዕና ምንጣፍ ሲያነጥፍና፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ ሲደግፍ የነበረው ሕዝብ፣ በዕለተ ዓርብ ‹ስቀለው ስቀለው› ይላል፡፡
ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ይለብሳል፤ ከዋክብትም ይረግፋሉ፡፡ በዚያ ሰዓት ነገን አሻግሮ ማየት፣ ከእውነትም ጋር አብሮ መቆም ከባድ ነው፡፡ ሀገር ‹ሆ› ብሎ ከሚነጉድበት ስሜት መውጣት፣ የግራ ቀኙን ጩኸት ታግሦ – ዓርብ በሐሳብ፣ እሑድ ግን በተግባር ከሚታየው ትንሣኤ ጋር ለመቆም፣ እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያለ ጽኑዕ ሰብእና ይጠይቃል፡፡
ስቀለው ከሚለው የዓርቡ ጩኸት ሣልስት የትንሣኤ ድል እንደሚኖር ማሰብ፤ ደም ከለበሰችው ጨረቃ ወዲያ አማናዊ ብርሃን እንደሚኖር ለማየት፣ ከሚረግፉት እልፍ አእላፍ ከዋክብት ባንሻገር ሞትን በሞት በሚገድል አምላክ ክንድ የሚረግፉ ችግሮች መኖራቸውን ለማመንብር ሰው መሆን ይፈልጋል፡፡ ዓርብ ዕለት ከበዛው ጩኸት ይልቅ ከተሰቀለው እውነት ጎን ለመቆም ልብ ያለው ሰው መሆን ይጠይቃል፡፡
ቅዳሜ ድንግዝግዝ ነው፡፡ እውነት ድል የተነሣች፣ ፀሐይም ጨልማ የቀረች፣ መቃብርም ታትማ የምትኖር፣ ሞትም አንቆ የሚያስቀር፣ ሲዖልም አሽጋ የምትቀብር የሚመስልበት ወቅት ነው፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ አይለይም፡፡ እንዲህ ባለው ወቅት እምነት፣ ጽናትና ቆራጥነት እንጂ ማስረጃና መረጃ ለማቅረብ ከባድ ይሆናል፡፡
በመቃብሩ ዙሪያ ጠባቂዎች፣ በመቃብሩም ላይ ማኅተም አለ፡፡ ከሁሉ ይሻላሉ የተባሉት ሐዋርያት ተበትነዋል፡፡ ሕዝቡም የምሥራች ወሬውን ጨርሶ – ዐቋሙም በወሬ ብዛት ተፈረካክ የክፋት መልእከተኞች የክፋት ወሬ በሕዝቡ ውስጥ ተናፍሶ፣ ወሬውም ከብዙዎች ዘንድ ደርሶ… ሥጋትና ተስፋ መቁረጥ አይሏል፡፡
 ሕዝቡ የሽንፈትና የድካም ነገር ያወራል፡፡ ዓርብ ዕለት ያየው ስቅለት – ደም – ግርፋት – ጩኸት እና እንግልት የመጨረሻው መጨረሻ መስሎት አለቀ፣ ደቀቀ – ይላል፡፡
የትናንቱን የዓርብን ነገር የሚያወሩ ብዙ ናቸው፡፡ የነገውን የእሑድን ምሥጢር ለመተንበይ የቻሉ ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
ገብቶናል፣ ተረድተናል፣ ተምረናል፣ ዐውቀናል የሚሉት እንኳን በወሬው ተሸንፈዋል፤ በስሜቱ ተውጠዋል፡፡ ነፋሱንና ጎርፉን መቋቋም አቅቷቸው፣ በነፋሱና በጎርፉ ተወስደዋል፡፡
አንድ የማይቀር እውነት ግን አለ፡፡ ትንሣኤ ይመጣል፡፡ ጩኸት ቢበረታም፣ ሽብር ቢነዛም፣ ኃያላን ቢነሡም፣ እውነት የተሸነፈች ብትመስልም – ትንሣኤ ግን በግድ ይመጣል፡፡ ወሬውና ሽብሩ አስደናቂውን ትንሣኤና ትንሣኤውን ተከትሎ የሚመጣውን እልልታ ፈጽሞ ሊያስቀረው አይችልም፡፡ ጠባቂዎቹና ማኅተሙ፣ የሞት ፉከራ እና የጉልበተኞች ጉርምርምታ በጭራሽ ትንሣኤን አያግዱትም፡፡
የብዙዎች ተስፋ መቁረጥና የተሰናካዮች ወደ ኋላ መመለስ ከመምጣት አይገቱትም፡፡ ከሞት አጠገብ ሕይወት፤ ከመቃብርም አጠገብ ትንሣኤ አለ፡፡ እምባ እና ደም ያጠየሟት ዓርብ የሥርየትና የሐሴት መሠረት ነች፡፡ የጭንቋ ቀን ቅዳሜ የትንሣኤው የመዘጋጃ ቀን ናት፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ በዝማሬ የምትደምቅ እና በትንሣኤም የምትከብር እሑድ መኖሯን ያመነ ሰው – እርሱ እውነትም ወንዝ ተሻጋሪ ሰው ነው፡፡
ትንሣኤ የዘገየ ይመስላል እንጂ አይቀርም፡፡ አለቀ፣ ደቀቀ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ የሚሉትን ሁሉ አሳፍሮ ክርስቶስ በእኩለ ሌሊት ተነሥቷል፡፡ መቃብሩ ባዶ ነው፡፡ ‹ሞተ› የሚለው መርዶ ቀረ፡፡ ዜናው – ተነሣ – ሆነ፡፡ አለቀ የሚለው መርዶ ቀረ – ዜናው -እንደገና ተጀመረ – ሆነ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ታሪክ ሆኖ – ራሱ ተስፋ ከሞት ተነሣ፡፡ የተበተኑት ተሰበሰቡ፡፡ ፈርተው የሸሹት ተመለሱ፡፡ ወሬና ሽብር ያስቀራቸው እንደገና መጡ፡፡ የተቆረጠ ተቀጠለ፤ የደከመ በረታ፣ ታሪክ ተለወጠ፡፡ ትንሣኤ መኖሩ ብቻ ሳይሆን በምንም ሰበብ – በማንም ክልከላ- በየትኞቹም የመቃብር ጠባቂዎች ብርታት እንደማይቀር ተረጋገጠ – ይህንን ነው ከትንሣኤ በዓል የምንማረው፡፡
ኢትዮጵያን ሰቅሎ መቅበር፣ ቀብሮም ማስቀረት አይቻልም፡፡ የተሰቀለች፣ የተቀበረች የምትመስልበት ጊዜ ግን አለ፡፡ በጠላቶቿ የተሸነፈች የምትመስልበት ቀን ግን ነበረ፣ አለ፡፡ ራቁቷን በጨለማ ውስጥ የቆመች የምትመስልበት ጊዜ ግን ነበረ፣ አለ፡፡ ወዳጆቿ ሸሽተዋት፣ ልጆቿ ተስፋ ቆርጠውባት፣ ዐዋቂዎቿ ሟርት ነጋሪዎች ሆነውባት፣ ፀሐይ የጨለመባት፣ ጨረቃም ደም የለበሰችባት፣ ኮከቦቿም የረገፉባት የሚመስልበት ጊዜ ነበረ፣ አለ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ትንሣኤ ይመጣል፡፡ የዓርብም ሆነ የቅዳሜ ጉዞ ወደ ትንሣኤ ነው፡፡
በግርግር ውስጥ፣ በስሜትና በነውጥ ውስጥ ያለ ሰው፣ አርቆ ለማየት ተሥኖት እንጂ ትንሣኤ የሚጀምረው ከዓርብ ነው፡፡ ዓርብ ዕለት ብዙ ሰው የሚያየው የሕዝቡን ጬኸት ነው፤ የክርስቶስን መሰቀል ነው፤ የፀሐይን መጨለምና የጨረቃን ደም መልበስ ነው፤ የከዋክብትን መርገፍ ነው፡፡
የትንሣኤን ታሪክ ማየት የሚችሉ ጥቂቶች ግን የመጋረጃውን መቀደድ፣ የዐለቶችን መሰንጠቅ፣ የመቃብሮችን መከፈት፣ የሙታንንም መነሣት ዓርብ ዕለት ያያሉ፡፡ በዓርብ ጨለማ ውስጥ የትንሣኤን ብርሃን ከተሻረችው ሰንበት ጀርባ ይማትራሉ፡፡
በተአምራት፣ በደም እና በጩኸት ከታረሰው የዓርብ ሰማይ አልፎ፣ ቀቢጸ ተሥፋ ከተጣባው የቅዳሜ ጀምበር ወዲያ፣ የተሥፈኛው ብርቱ ልብ እሑድ ሌሊት ላይ የሚገለጠውን ትንሣኤን ያያል፡፡
ኢትዮጵያችንም እንዲሁ ናት፡፡ የተሸነፈችና የደከመች፣ የተሰቀለችና የሞተች፣ ያለቀላትና ያከተመላት በሚመስልበት ጊዜ ውስጥ ትንሣኤዋ ከሩቁ ይታያል፡፡ በዛሬው ማዕበል የማይወሰዱና፣ በአይሁድ የሐሰት ወሬ የማይናዱ የማይቀር ትንሣኤዋን ያዩታል፡፡ አየሩን ክፉ ወሬ ቢሞላውም፤ ከሙታን የተነሡት ግን ወደ ከተሞች ገብተው መልካሙን ወሬ ያወራሉ፡፡ ልጆቿ የተከፋፈሉ ሆነው ዓርብን ያሳልፉታል፡፡ እንደ ዮሐንስ ያሉት ጸንተው፣ እንደ ጴጥሮስ ያሉት ተጠራጥረው፣ እንደ ይሁዳ ያሉት ክደው፣ሌሎቹ ደግሞ ፈርተውና ደንግጠው ዓርብን ያሳልፋሉ፡፡ ትንሣኤ ሲመጣ ግን የካዱት ይጠፋሉ፤ የተጠራጠሩት ያምናሉ፤ ያመኑት ይጸናሉ፤ የፈሩትም ይደፍራሉ፡፡ እንደገናም ተመልሰው ላይበተኑ አንድ ይሆናሉ፡፡ በዕለተ ትንሣኤ ሁሉም ይደመራሉ፡፡
ድንጋዩም ይነሣል፣ መቃብሩም ይከፈታል፤ ሙስናም ይቀራል፤ መግነዙም ይፈታል፡፡ ትንሣኤው እንዳይኖር ከብበው የሚጠብቁ ይበተናሉ፡፡ አለቀ ደቀቀ እያሉ ሲተነትኑ የነበሩ ያፍራሉ፡፡ በነፍሳችን ሲወራረዱ የነበሩ ሁሉ ይደነግጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ተስፋ የላትም ያሉ ሁሉ እነርሱ ራሳቸው የትንሣኤዋ ማስረጃዎች ይሆናሉ፡፡ ዓርብ የጀመረው ትንሣኤ እሑድ ይደመደማል፡፡ እንደ አይሁድ ለብቻቸው አድመው ዕጣ ፈንታችንን የወሰኑብን ሁሉ ከእውነቱ ጋር ይጋፈጣሉ፡፡ ‹በሞት ተፈጸመ፣ በመቃብርም ተደመደመ› ብለው ታሪካችንን ሊጽፉ የቋመጡ ሁሉ እንደገና ብዕራቸውን ለትንሣኤያችን ያነሣሉ፡፡
እኛ የሞት መልእክተኞች አይደለንም፤ የሕይወት አብሣሪዎች እንጂ፡፡ እኛ የመቃብር ጠባቂዎች አይደለንም፤ የትንሣኤ መለከቶች እንጂ፡፡ እኛ የጨለማ አበጋዞች አይደለንም፣ የብርሃን መልእክተኞች እንጂ፤ እኛ ከጨለመች ፀሐይና ደም ከለበሰች ጨረቃ ይልቅ የተተረተረውን መጋረጃ፣ የተከፈቱትን መቃብሮች፣ የተነሡትን ሙታን፣ የተናወጡትን ተራሮች እናያለን፡፡ እኛ ከሕማማት በኋላ ፋሲካ፣ ከመከራም በኋላ ደስታ መኖሩን እናምናለን፡፡ ለእርሱም እንጋደላለን፡፡ የትናንቱን ዛሬ ዘግተን፤ የነገውን ዛሬ እንጀምራለን፡፡ ይህቺ ኢትዮጵያ ናት – ዓርብን አሳልፋ፣ ቅዳሜን ድል ነሥታ – እንደ ገና የምትነሣ፣ እንደገናም የምታሸንፍ።
 ኑ ፣ የመቃብር ጠባቂነታችንን ትተን – የኢትዮጵያን ትንሣኤ እናብሥር
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መልካም በዓል
Filed in: Amharic