>

አፋኝነት ከብሔረተኛ መንግስት ወደ ብሔረተኛ ቡድኖች የተሸጋገረ ይመስላል (ያሬድ ሃይለማሪያም)

ትላንት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ሃሳባቸውን በመግለጻቸው የተነሳ ይቆጣና ጥቃት ይሰነዝር የነበረው በወያኔ የሚመራው የጎሳ ብሔረተኛው ቡድን እና አጃቢዎቹ ነበሩ። ሰዎች ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ ሽብርተኛ እየተባሉ በየማጎሪያው ይታሰሩ እና ይሰቃዩ እንደነበር የቅርብ ትውስታችን ነው።

ብሔረተኛ ገዢዎቹ ዛሬም በስልጣን ላይ ያሉ ቢሆንም የአፈናው ነገር ለጊዜው ጋብ ብሏል። እንደገቡት ቃልም ከተፈጸመ ከነወዲያኛው ሰዎች በሃሳባቸው የማይታሰሩባት፣ የማይዋከቡባት እና የማይሰደዱባት ኢትዮጵያ እውን ትሆን ይሆናል። በእዚህ ተስፋ ውስጥ እያለን አፋኝ የሆኑ እና የአፋኝነት ዝንባሌን ከወዲሁ እያሳዩ ያሉ ብሔረተኛ ቡድኖች፣ ግለሰቦች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን መፍላታቸው አፈናን የማስወገዱ ትግል ገና ብዙ መንገድ እንደሚቀረው ነው የሚያሳየው። ለዚህም አንዳንድ የቅርብ ትውሳቶቻችንን እንደማሳይስ ላስቀምጥ፤

  • ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ከአመት በፊት በኢሳት ከወንድማገኝ ጋሹ ጋር ባደረጉት ታሪክ ተኮር ውይይት ከኦሮሞ ልሂቃን እና አክቲቪስቶች የደረሰባቸው ወከባ፣ ስድብ እና ውርጅብኝ፣
  • ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም አማራ የሚባል ሕዝብ አለ የለም በሚል ቀደም ሲል ባቀረቡት ሃሳብ ጋር ተያይዞ በተከታታይ ከአማራ ልሂቃን እና አክቲቪስቶች የደረሰባቸው ስድብ እና ክብራቸውን የማይመጥን የማንቋሸሽ ዘመቻ፤
  • ኢሳት በተደጋጋሚ ከትግራይ፣ ከኦሮሞ እና ከአማራ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች ይደረሰበት የነበረው ዛቻ እና ማስፈራሪያ (በኢሳት በኩት የተፈጸሙ የጎሉ ስህተቶች እንደተጠበቁ ሆነው)፣
  • የግንቦት ፯ አመራሮች በባህርዳር የገጠማቸው በነፍጥ የተደገፈ ወከባ፤ እንዲሁም በርካታ የተቃዋሚ ድርጅቶች በኦሮሚያ ክልል ተንቀሳቅሰው ሕዝብ ማደራጀት አለመቻላቸው እና የደረሰባቸው ወከባ፤
  • የአረና ፖርቲ አመራር የሆነው አምዶም ገብረስላሴ በመቀሌ በተካሄደ የምሁራን ስብሰባ ላይ ሃሳቡን በመግለጽ ላይ እንዳለ የደረሰበት ወከባ እና እንዳይናገር በአዳራሹ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ብሔረተኛ ምሁራን እና አክቲቪስቶች የፈጸሙበት አፈና፤
  • የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣን የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በአንቦ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ ላይ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብን ታሪካዊና የረዥም ጊዜ ግንኙነት በተመለከተ ባቀረቡት የመወያያ ሃሳብ ላይ የቡርቃ ዝምታ፤ የተሳፋዮ ገብርአብ ቅዠት እንጂ እውነተኛ ታሪክ አይደለም በማለታቸው የተቃውሞ ሰልፍ እና ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚያሳስብ ሰፊ ዘመቻ በኦሮሞ አክቲቪስቶች የተከፈተባቸው መሆኑ፤
  • ትላንት ምሽት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በኢሳት ቴሌቪዥን ዶ/ር አንማው አንተነን አቅርቦ ባወያየበት መድረክ መምህሩ በእሳቸው ምልከታ አማራ የሚባል ብሔር እንደሌለ እና እራሳቸውንም በዛ መልክ እንደማይገልጹ አስረግጠው መግለጻቸውን እና በዛ ደረጃ መደራጀት ለሳቸው ያለውን ትርጓሜ መግለጻቸውን ተከትሎ የአማራ ብሔረተኛ የሆነው እና የኢትዮጵያን የፖለቲክ ትግል ከተቀላቀለ የጨቅላ እድሜ ያለው አብን መምህሩን፣ ኢሳትን እና የመብት ተሟጋች እና አንጋፋውን ምሁር ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን እከሳለሁ የሚል መግለጫ ማውጣቱን፤

እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላ።

ከላይ ለምሳሌነት የጠቀስኳቸው ክስተቶች ሁለት ነገር ያመላክታሉ፤

የመጀመሪያው ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ ለማሸማቀቀ የሚደረገው ጫና እና አፈና ከመንግስት እጅ ወጥቶ በብሔረተኛ ቡድኖች መቀጠሉን ሲሆን፤ እነዚህ ቡድኖች ማሰር ባይችሉም ያሸማቅቃሉ፣ ያዋክባሉ፣ ያጠለሻሉ፣ አንዳንዴም እንደ አቶ አዲሱ አረጋ አይነት በራሱ የማይተማመን ፈሪም ሲያገኙ በአደባባይ የተናገረውን ነገር መልሶ እንዲውጠው እና አምኖ የተናገረውን እውነት ተሸማቆ ይቅርታ እንዲጠይቅበት ያደርጉታል።

ሁለተኛው አስገራሚ ነገር እራሳቸውን የሕዝብ ተወካይ አድርገው በማቅረብ ሕዝብ ተሰደበ በሚል ሙግት እና ክስ ማቅረባቸው ነው። እርግጥ የብሔረተኞች አንዱ መገለጫ የሄው ነው። የአንድን ብሔረሰብ ወይም ኃይማኖት ወይም ቡድን ስሙን ይዘው ስለተደራጁ ብቻ እራሳቸውን የሕዝቡ ብቸኛ ተወካይ አድርጎ ማቅረብ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ውክልና ያለው ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የፖለቲካም ሆነ ሌላ አይነት ድርጅት ወይም ቡድን ገና አልተፈጠረም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገር ደረጃም ሆነ በብሄር ደረጃ እራሱን ወክሎ አያውቅም። እድሉን መች አግኝቶት፣ ማንስ ሰምቶት።

ለማንኛውም ግለሰቦች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ በሕዝብ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር ተቆርቋሪነት ስም የሚደረጉ ጫናዎች እና ማስፈራሪያዎች የዲሞክራሲ ባህል እንዳይኖር ከማድረግም ባሻገር አፈናን ያጸናል። ይህ አይነቱ በሽታ የህዝብ አይንና ጆሮ ነን በሚሉ የኢሳት አይነት ሚዲያዎችም ሲፈጸም እያየን ነው። በቅርቡ በጋዜጠኛ ርዕዮት እና በቴውድሮስ ጸጋዮ ቃለ ምልልስ ላይ የተደረገውም አፈና የዚህ አንዱ መገለጫ ነው።

ሃሳቦች በሃሳብ ይሞገቱ። ሕዝብ ሃሳቦችን የማወዳደር እድል ይሰጠው። የሃሳብ ገበያን እያነጠፉ ዲሞክራሲ ሊገነባ አይችልም። የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚገነባው በሃሳቦች ገበያ ነው። በአደባባይ የሚደረጉ የሃሳብ ሙግቶች ሦስት ነገሮችን ይጠይቃሉ። በሚናገሩበት ጉዳይ ጥልቅ እውቀት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የሚመጣውን ተጠያቂነት ለመቀበል የሚያስችል ድፍረት እና ሥልጡን የሆነ የሃሳብ አገላለጽ ክህሎት። እነዚህን እሴቶች ካላዳበርን ነገራችን ሁሉ ከርሞ ጥጃ ነው የሚሆነው።

የቡርቃ ዝምታ ውሸት ነው ያለን ሰው በሰልፍ እና ዛቻ ጸጥ ማሰኘት፣ አማራ የለም ያለውን ሰው በክስ አፉን ለመለጎም መዳዳት፣ የታሪክ ምርምር ውጤቱን የሚናገር እንደ ፕ/ር ሃይሌ ላሬቦን አይነት ምሁርን በዛቻ እና በስድብ እንካ ሰላምታ መግጠም የሃሳብ ነጻነት ላይ የተነጣጠረ የፈሪዎች ዘመቻ ነው። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ በጊዜ ካልተገራ እያደር የፖለቲካ ባህል ይሆናል። ያኔ በተበላሸው እና መደማመጥ ቀድሞውንም በጠፋበት የፖለቲካ ባህላችን ላይ ይህ ሲታከልበት ያው እንኳንም ዘንቦብሽ ነው የሚሆነው።

   መልካም የፋሲካ ባዕል ለሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች

Filed in: Amharic