>

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት - ክፍል ሶስት (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤...)

ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት
ደራሲ፡ ጌቱ ሙጨ
የታተመበት ዓመት፡ 2011
የገፅ ብዛት፡ 200

ክፍል ሶስት

በሰሎሞን ዳውድ አራጌ

ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ እንግሊዝኛ ቋንቋና
ስነፅሁፍ ትም/ት ክፍል መምህር

 

የአርበኛ አባ ጃዊ መጨረሻ ምሽትና የሞት ፅዋ!

በየካቲት 20/ 2009 ዓ.ም አባ ጃዊ ከቤተሰብ ተደውሎ ስንቅ እንደተላከለት ይነገረዋል፤ ስንቁን ይቀበሉ ዘንድ ያን ሁሉ መከራ ከጎኑ ሆነው ያሳለፉትን እኒያ ሁለት አርበኞች ላካቸው፤ ከጎኑ ግን ይህ እንግዳ ሰው ብቻ ቀረ፡፡ እኒ የቁርጥ ቀን ሰዎቹ ከጎኑ መራቃቸውን የተመለከተው ይህ ተላላኪና አዲስ ሰው ብሎም ዘመድ አባ ጃዊ የዋለለትን ረስቶ፤ ለሕዋሓት ጭብጥ ጉርሻ ሲል ያለ ምንም ርህራሄ፤ ራሱ ባስታጠቀው ጠብመንጃ አባ ጃዊን ተኩሶ መታው፡፡ እኒያ ሳተናዎች ጥይት ሰማን ምንድን ነው ብለው ለዚሁ አዲስ ሰው ቢደውሉለት አይ ራቅ ያለ ነው ዘምብላችሁ ሂዱ አላቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም ተኩስ ተደጋግሞ ሰሙ፤ አሁንስ ምንድን ነው ሲሉት ወታደሮች መጥተውብን ተታኩሰን አምልጠናል እንዳትመጡ አላቸው ያልፈጠረለትን ወንድነት ለራሱ ሰጥቶ ሸወዳቸው፤ አባ ጃዊ ያ ክንደ ብርቱ ውጊያ ክንዱን አዝሎት፤ ሕመም ፀንቶበት ለአፍታ ዕረፍት ጋደም ካለበት መሬት ላይ ዳግም ላይነሳ፤ ባመነው ሰው በጥይት ተደብድቦ አሸለበ፡፡ የተፈጠረውን ማመን ያቃተው የመከላከያ ሰራዊት አዲሱን ሰው በወታደራዊ አጀባ ከነቤተሰቡ የካቲት 21/ 2009 ወደ ጎንደር ወሰደ፤ አስከሬኑ የአባ ጃዊ መሆኑን አረጋግጠው ቤተሰቡም አስከሬን እንዲያነሳ አስደረገ፡፡

አርበኛ (አባ ጃዊ) ጎቤ መልኬና (አባ ድፈን) መሳፍንት ተስፋ ምንና ምን ናቸው;

ለህዝብ ነፃነትና ለሃገር ክብር ሲሉ ቤትና ቤተሰባቸውን ጥለው በርሃ (ዱር) ቤቴ ያሉ እኒህ ሁለት የትግል መሪዎች አባ ጃዊና አባ ድፈን ምንም የስጋ ዝምድና ሳይኖራቸው ይልቁንም የቤተሰብ መቃቃር በመሃከላቸው መኖሩን እያወቁ የጋራ ጠላታችንን እንጣል ብለው መሳሪያ ዘልለው፤ ትከሻ ለትከሻ ተሳስመው፤ የጋር ምክር አደረጉ፡፡ የአባ መሳፍንትን መንደርና የአርበኞች አባላት ከነትውልድ ስፍራው ከተዋወቀ በኋላ በየትኛውም አጋጣሚ አንደሚተጋገዙ ተማምለው፤ በመሳፍን ሰዎች ተሸኝቶ፤ አባ ጃዊ ከአርበኞቹ ጋር በመረባና ጃኒ ፈንቀራ በኩል ወደ ቆላ ወገራ አቀና፡፡ በእግረ መንገዱም ከአባ ድፈን መሳፍንትና እነቃሽ ነብር ጠማጅ አርበኞች ጋር የጥምረት ተጋድሎ ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን በየውጊያውና ምርኮው ሁሉ እየተመካከሩ፤ ጥቃትና መታፈን ሲደርስባቸው አብረው እየመከቱና መረጃ እየተለዋወጡ የነፃነት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ አባ ጃዊ ከአባ ድፈን ሲመለስ የሚሸኙ ሰዎች ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ፍቅሬና ገብሬ የተሰኙ ዘመዶቹን በመንገድ አግኝቶ ሰው ባልደረሰበት በማያውቅ ቦታ ለሳምንት ያህል መሽገው የትግል ዕቅድ አውጥተው ጨረሱ፡፡

አርበኛ አባ ድፈን መሳፍንት ማነው;

ከገበሬ አባቱ አቶ ተስፋ ይልማና እናቱ እማሆይ ዝናየ መልካሙ ታከተ የተገኘው አርበኛ መሳፍንት ተስፋ ጨዋ፣ ሰው አክባሪ፣ ሐይማኖቱን ጠባቂና ጨዋታ አዋቂም ሰው ነው፡፡ በኪዳነ ምህረት ዋሻ ሎሚዮና ቅርን አምባ ኪዳነ ምህረት የተወለደውና ያደገው አባ ድፈን ዛሬም ድረስ ተፈርቶና ተከብሮ የሚኖር ጀግና ሰው ነው፡፡
አባ ድፈን አጅሬ ያሰኘው በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነቱና ዛፍ ቅጠሉም ለእርሱ ጆሮ ሆኖ መረጃን በማነፍነፍና በማድረስ የሚሰራለት በመሆኑና አልፎም እርሱ ዘንድ ተልኮ የደረሰ ሰራዊት እግሩ ከካምፑ ሳይወጣ የሞት ደብዳቤው የተፃፈለት መሆኑን የታመነበት ጀግና መሆኑ ነው፡፡

በርካታ የትግል ጓዶች ያሉት አባ ድፈን በሁሉም አቅጣጫ በጅንገር፣ በመረባ፣ በእንቃሽ፣ በድልድይና በቀንጣ፣ በጃኖራ ያሉ ግብረ አበሮቹ ሁሌም ዝግጁ ናቸው፡፡ አባ ድፈን ዘንድ ለጠብ የመጣ ሁሉ አይመለስም፤ አስከሬኑም ለውሬ ቀለብ መሆኑ ቁርጥ ነው፤ የአካባቢውም አቀማመጥ ለእርሱ ምቹ፤ ለደራሽ ጠላት ግን መቀበሪያ ጉድጓድ ነበር፡፡
አባ ድፈን ሁሌ የሚያወሳቸውና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የእንቃሽ ነብር ጠማጅ አርበኞችን ሲሆን ከሌሎችም ጋር በአጋነት ይሰራል፤ እንደ አባ ጃዊና ፋኖ ጋር ይተባበራል፤ ለአብነትም በጥር 24/ 2008 ዓ.ም በእንቃሽ አርበኞች አይቀጡ ቅጣት የቀመሰው የአግአዚ ጦር፣ በህዳር 18/ 2009 ዓ.ም የገባውና በእንቃሽ ሜዳ የቀረው የመከላከያ ሰራዊት፣ በጥር 30/ 2009 ዓ.ም አምባ ጊዮርጊስ ላይ የቡጅሌና ሚኒሻ አባላት እና ሌሎች ተጋድሎዎችን የፈፀሙት በሕብረት ነበር፡፡

የአርበኛ አባ ድፈን መሳፍንት የትግል ሕይወት

በትግል ሕይወት ዘመኑ ከፍተኛ መሪር ሃዘን ውስጥ የጨመሩት ሁለት አጋጣሚዎች እርሱ በርሃ ለበርሃ ለብዙሃን ነፃነት ሲንከራተት ወላጅ አባቱ ታምሞ አይዞህ ከጎንህ ነኝ ሳይለው፤ ሳያሳክመው መሞቱና የባለቤቱ አባት እርሱን ሊወጋ ከመጣ ጦር ጋር ተዋግተው ፍልሚያ ላይ መሰዋታቸው ናቸው፡፡

የአባ ድፈን አርበኝነት የሚቀዳው አባቶቹ በፋሽስት ወራሪ ሃይሎች፣ የጣሊያን ሹምባሽ ተላላኪዎች ጋር ባደረጉት ታላቅ ፍልሚያና ተጋድሎ በተከናወነበት ቀዮ ማደጉና አካባቢው ያን የወንድነት መንፈስ የረበበበት ስለነበር፤ ከዚያ ተችሮት በማደጉ ነበር፡፡ እርሱም ነፍስ ካወቀበትና ቤተሰብ ከመሰረተበት ግዜ አንስቶ በህዝቡና በአካባቢው ላይ በሰፈነ ኢሰብዓዊ አስተዳደር የሚከነክነው አባ ድፈን በማረፊያና የእርግና ዘመኑ ሳቀር ነፍጥ አንስቶ ደሩ ቤቴ ብሎ እምብኝ እንዲል ያደረገው በትውልዱ ላይ የሰፈነው አፈናና በደል ነበር፡፡

በተለይ ከ1974 ዓ.ም ወዲህ በምድረ ኢትዮጵያ የነገሱ “ደመነፍሳዊ” ትውልዶች የሚመራው የሃገር ጠላቶችና መንግስት ተብየዎችን ለመዋጋ በጸረ ሽምቅነት ባሳየው ግልፅ ትግል ጥርስ ውስጥ ገባ፤ እኒሁ አካላት ስሙ መሳፍንት መባሉን ሳይቀር ይፈሩት ጀመር፡፡ የትሕነግ ሰዎች የግድያ ሴራ ወጥነውለት አልተሳካላቸውም፡፡ ሲፈጅ በማንኪያ … የተካኑበት ወያኔዎች በ1985 ዓ.ም ምህረት ጠይቆ እንዲገባ ፈቅደውለት የነበረ ቢሆንም አንደገና በወልቃይት ጉዳይ እምቢ አለ፡፡ በዚህ ወቅት አታለው ይዘው ሽራሮ ባዶ ስድስት የሚባል ማጎሪያ አስገቡት፡፡ በዚም እስር ቤት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ የጠባቂውን መሳሪያ ነጥቆ ተዋግቶ አመለጣቸው፤ ከሽራሮ የገሰገሰ ባደገባቸው የጎንደር በርሃዎች ደርሶ፤ ጫካው ቤቴ አለ፡፡ በእስርም ሳለ በታሳሪዎቹ ላይ በተለይም በወልቃይት ሰዎች ላይ ለተፈፀሙ ግፎች የዓይን ምስክርም ነው፡፡

አሁንም በድጋሜ ወደ ቤተሰቡ የተቀላቀለው አባ ድፈን በ1997 ዓ.ም የአካባቢውን ምርጫ አሸንፎ ስለነበር ለድጋሜ በቀል ይዘጋጁ ጀመር፡፡ በምርጫ መጨበርበር ሰበብ ወደ እስር ሊያስገቡት የፈለጉት የመንግስት አካላት ወይም ፀረሽምቅ ተላከበት፤ ከፍተኛ ዕልቂት ሆነ፤ በውጊያው ሞቶ ይሆናል ብሎ ሃሴትን የሰነቀው መንግስት ማንም ሱሪ ያለው እርሱን አይቻለሁ ወይም ገድያለሁ የሚል ጠፋ፤ ይልቁንም በርካቶች በመንግስት ወገን አለቁ፡፡ በ2001 ድጋሜ ምህረት ተደርጎልሃ ግባ ተባለ፤ በወቅቱም ለሁሉም በርሃ ገብ አርበኞች መንግስት ጥቅማጥቅሞችን ሲያሟላ ለአባ ድፈንም 60 ሄክታር የእርሻ መሬት ቋራ ወረዳ ተሰጠው፡፡

የ2002 ምርጫ ደረሰ አፉን መዝጊያ ታቦ የተሰጠው ብዙ ቃዳ መሬት ያላታለለው አርበኛ እንደፈለጉት ሳይሆንላቸው ቀረና በመሃላቸው ሌላ ውጥረት ነገሰ፡፡ ድሮም እኔ የተፈጠርሁት ለበርሃ ነው ብሎ ይቅር ለቤቴ ብሎ ወደ በርሃ ወረደ፡፡ እስከ 2008 ድረስም ቤተሰቡን በትኖ በብቸኝነት ለመኖር ተገደደ፤ በጠቅላላው ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በጎጆው መቀመጥ የቻለው ከሁለት ዓመታት አይበልጥም፡፡

በጠቅላላው አርበኛ አባ ድፈን መሳፍንት ማለት ለሕዋህት የእግር እሳትና ሲጠግቡ አቅማቸውን የሚያሳያቸው ሃግ ባይ አለቃቸው ነበር፡፡ በሽምግልና ጠይቀው፣ 7000 ያል ሰራዊት አዝምተው፣ በሄሊኮፕተር አስሰው ቢፈልጉትና ቢቋምጡ እጁን መጨበጥ ያቃታቸው ሲሆን በመጨረሻም በታህሳስ 02/ 2009 ዓ.ም መንግስት ነን ባዮቹ ጥቃት ከፍተው ብዙ ሰው ዕልቂት አስከተሉ፤ የሰራዊቱን አስከሬን ለምነው በኦራል ጭነው ወደ ጎንደር ወሰዱ፤ ሽንፈታቸውን ዋጡ፡፡ ከእንቃሽ ነብር ጠማጅ አርበኞች ወገን ትግሉ ቀኝ ዕጅ የነበረው አርበኛ በሬ አረጋ ተሰዋ፤ አባ ድፈንና እንቃሽ ግን በዚህ መንኩ ተቀናጅተው ለጠላታቸው ኮሶ ሀኑ፡፡

 

ጸሃፊውን ለማግኘት : solomon123@yahoo.com

ክፍል አራት ይቀጥላል

የቀድሞዎቹን ክፍሎች ካላነበባችሁ ቀጥሎ ያለውን ማጣቀሻ በቅደም ተከተሉ ይጫኑ።

 

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤    

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – ክፍል ሁለት 

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – ክፍል ሶስት 

Filed in: Amharic