>
5:13 pm - Sunday April 18, 5999

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የረጅም ጊዜ ሰላማዊ ትግልና የሰሞኑ ድል (አበጋዝ ወንድሙ)

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የረጅም ጊዜ ሰላማዊ ትግልና የሰሞኑ ድል

 

አበጋዝ ወንድሙ

መንግስት በሃይማኖት ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም ፣ላለፈው ሰባት ዓመት ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል፣በዚህ ሳምንት በተካሄደው የኢትዮጵያ ሙስሊም ዑላማዎች ጉባኤ ፍጻሜ፣ ስኬት ደጃፍ ላይ ደርሷል። እዚህ የድል ደጃፍ ለመድረስ በርካታ ዜጎች ታስረዋል፣ ኑሮዋቸው ተስተጓጉሏል፣ ቤተሰባቸው ተበትኗል ፣ተሰደዋል እንዲሁም ተገድለዋል።

አህባሽ የተባለውን አስተምህሮ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ በግድ ለመጫን የህወሀት /ኢህአዴግ መንግስት ያደረገው ጥረት ተቃውሞ የገጠመው የነበረ ቢሆንም፣ ህዳር 2004 ዓም ፣ ጽንፈኝነት ያስፋፋሉ በሚል ሰንካላ ሰበብ ፣ የአወልያ ትምህርት ቤት መምህራንና አስተዳዳሪዎችን በጅምላ ሲያባርር የተለኮሰው አሳት፣ ውሎ አድሮ ለሀውሃት ከኢህአዴግ አድራጊ ፈጣሪነት ተነስቶ በአብይ አስተዳደር መተካት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ በቅቷል።

በየካቲት ’66 አብዮት ወቅት ወሳኝ ኩነቶች ከነበሩት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለመብታቸው መከበር ያካሄዱት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ (ክርስቲያን ወገኖቻቸውም ይሀን የመብት ትግል በመደገፍ አብረው ተሰልፈዋል) እንደነበር በወቅቱ የነበሩና፣ ታሪክም የሚያስታውሰው ነው። በዚያ ወቅት የተካሄደውም ትግል ፍሬ አፍርቶ፣ህጋዊ የሃይማኖት እኩልነትን ፣ታላላቅ የሙስሊም ባዕላትን በብሄራዊ ደረጃ እንዲከበሩ ያደረገ የመሰሉን የተወሰኑ ድሎችም ተጎናጽፎ እንደነበርም ይታወሳል።

ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ፣ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ ደጋግሞ መለፈፉና፣ በህገመንግስቱ ውስጥም የተካተተ መሆኑ ቢታወቅም ፣ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ተቋማት ውስጥ ግን ጣልቃ መግባቱ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የተከተለው መንገድ ነበር ።

ህወሃት /ኢህአዴግ የሁሉንም ሃይማኖቶች ተቋማት አመራር ለሱ ተገዥ በሆኑ ግለሰቦች ለመሙላት ጥረት በማድረግ፣ በአንድ ወቅት የሁሉም ሃይማኖቶች በሚባል መልኩ ተሳክቶለት ስለነበር ፣ በብዙሃን አማኞችና የቤተ እምነት መሪዎች መሃል ክፍተት ሊፈጥር ችሎ ነበር።

በተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያደረገው ጣልቃ ገብነት ሁለት ሲኖዶሶች ተፈጥረዋል እስከማለት ያስደረሰ እንደነበርና ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋም የሆነውን መጅሊስ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ስለተቆጣጠረው ፣ ህዝበ ሙስሊሙን ትልቅ ቅሬታ ውስጥ ከቶ ከተቋሙ ጋር የላላ ግንኙነት እንዲኖረው አድርጎ ነበር።

ህወሃት/ኢህአዴግ ለስልጣንና ቁጥጥር ስግብግብ ነበርና፣የህዝበ ሙስሊሙን ተቋም መቆጣጠሩ ሳያንሰው ፣ ከላይ እንዳልኩት አህባሽ የተባለውን አስተምህሮ በግድ ለመጫን ያደረገው ጥረት፣አብዛኛውን የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት ከማሳዘኑም በላይ ሃይለኛ የሆነ ቁጣ በመቀሰቅስ፣፣ አመታት የፈጀ አልህ አስጨራሽ ትግል እንዲቀጣጠል ምክንያት ለመሆን በቅቷል።

በ 1997 ተደርጎ የነበረውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ፣ በህወሃት/ኢህአዴግ የምርጫ ዘረፋ ምክንያት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽ ለመደፍጠጥ መንግስት በወሰደው መጠነ ሰፊ እስርና ግድያ ተቀዛቅዞ የነበረው ህዝባዊ ትግል እስትንፋሱ የተመለሰውም፣በዚህ በህዝበ ሙስሊሙ በተቀጣጠለው ሰላማዊ ትግል አነሳሽነት ነበር ለማለት ይቻላል።

እንደ አብነትም የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ትግልን ተከትሎ ጥያቄያቸውንም ደግፎ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ በሚል በበርካታ የሀገራችን ክፍል ያደረገው ሊጠቀስ ይችላል።

የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ትግል ፍጹም ሰላማዊ ከመሆኑ ባሽገር፣ህብረብሄራዊና ሃገራዊ መሆን ልዩ መለያው ስለነበር፣ ህዝብን በብሄር ከፋፍሎ በመምታት ልምድ ያካበተው ህወሃት/ኢህአዴግን ይይዘው ይጨብጠውም አሳጥቶታል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የትግል አርአያነት ተከትሎ የመጣው ፣በኦሮሚያ፣ አማራ ክልል፣ ኮንሶና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱት ትግሎች፣ ከህዘበ ሙስሊሙ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምረው ነው ህወሃት/ኢህአዴግ ላይ ጫና ማሳረፍ የቻሉትና፣ አገዛዙንም ከስሩ ያናጉት። ይሄ መሰረታዊ መናጋትም ነው የለውጥ ሃይል ነን የሚል ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ ተፈጥሮ አሁን ያለንበት ስፍራ ልንደርስ ያስቻለው ።

ለህዝብ መብት የሚደረግ ትግል ለፉክክር፣ ለግል እውቅና ወይንም ለዝና ባለመሆኑ፣ ዛሬ አገራችን የሚታየውን የለውጥ ተስፋ፣ እኔ ነኝ ያመጣሁት የሚል አጉል ሽሚያ ቢኖርም፣ ያለፉት ሰባት አመታት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያልተቋረጠ ትግል ፈር ቀዳጅና አነሳሽ እንድነበር እውቅና መስጠት የግድ ነው።

ለህዝበ ሙስሊሙ የትግል ስኬትና ለሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ትግል አርአያና የመታገያ ስልት የሆኑ በርካታ የሰላማዊ ትግል ዘዴዎችም በዚህ የትግል ወቅት የተፈጠሩ ነበሩ። ለአመታት፣ ዘወትር አርብ አርብ የጁማ ሶላትን አስታኮ፣ መጀመሪያ አዲስ አበባ ባሉ መስጊዶች ፣ በቀጣይም በርካታ ክልሎችን ያቀፈ ፍጹም ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞ መካሄዱ መንግስትን እረፍት በመንሳቱና በማደናገጡ ፣ በተለያዩ መስጊዶች ውስጥ የሃይል እርምጃ በመውሰድ በወገኖቻችንን ላይ ግድያ እስከ መፈጸም ቢያደርሰውም፣ ህዝበ ሙስሊሙን ግን፣ ከጀመረው ሰላማዊ ተቃውሞ ሊገታው ወይንም ወደ አልተገባ መንገድ ተገፋፍቶ እንዲሄድ ሊያደርገው አልቻለም።

በተቃራኒው ይሄ ህዝበ ሙስሊሙ ያሳየው ጽናት ህወሃት/ኢህአዴግ በተፈበረከ ክስ፣ ወኪሎቼ ብሎ የመረጣቸውን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ለእስር ከመዳረጉ በፊት፣ ለይስሙላም ቢሆን ከወኪሎቹ ጋር በፌደራል ምኒስቴር ደረጃ ድርድር እንዲቀርብ አስገድዶት ነበር።

በነዚህ በየሳምንቱ በሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችም፣አንድ ጊዜ እጆችን በማውለብለብ፣ አንድ ጊዜ አፍን በጨርቅ ወይንም በወረቀት በመሸፈን ፣አንድ ጊዜ ሁለት እጆችን አጣምሮ ከፍ አድርጎ በድምጽ የታጀበ ተቃውሞ ማሰማት፣ ( ፈይሳ ለሊሳ ሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በመጠቀም ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ አድርጎታል)፣ አንድ ጊዜ ጽሁፍ ያዘለ ነጭ ወረቀት በማውለብለብ፣ ሌላ ጊዜ ቢጫ ጨርቅ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ የተነፋና ልዩ ልዩ ቀለማት ያሉት ፊኛ በማውለብለብና፣ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ድምቀት ያላቸውን አነቃቂ ሰላማዊ ሰልፎች በማድረግ፣ ከጊዜ በዃላ ሚሊዮኖችን እስከ ማንቀሳቀስ የቻለ የ’ድምጻችን ይሰማ’ እንቅስቃሴ ሊሆን በቅቷል።

በድርድሩ መሪዎቹን ማስፈራረትም ሆነ መደለል ባለመቻሉ፣ አመራሩን በማሰር ትግሉን ማኮላሸት ይቻላል በሚል እምነት በተፈበረከ ክስ በሽብርተኝነት ለእስር ቢዳርጋቸውም ፣ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ በብዙ መቶዎች በመሆን፣ እስረኛ ለመጠየቅ በተፈቀዱት ቀናት ሁሉ በእስር የሚገኙ መሪዎቻቸውን በመጠየቅ፣ ቤተሰቦች ችግር ላይ እንዳይወድቁ በመደጎም የራሳቸውንና የመሪዎቻቸውን የትግል ወኔ ከማነሳሳታቸውም በላይ ፣ትግሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ችለዋል። ይሄም ሰላማዊ ትግልን አስመልክቶ የተፈጠረ አዲስ የትግል ዘዴ ነበር።

ዛሬ በሀገራችን የሚታየውን የለውጥ ተስፋ ያመጣሁት እኔ ነኝ ወይንም እኔና እከሌ በማለት ከሞፈከር ታልፎ፣ በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል ትልቅ ሚና የነበራቸውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ጥያቄያቸውን አንግቦ ዘወትር አርብ አርብ ለአመታት የታገለውን የአዲስ አበባ ህዝብ ፣ የት ነበርክ እስከመባል ሲደርስ ፣ አግራሞት የሚጭረውም ለዚህ ነው።

ሆኖም ጽናት ያለው ትግል ብርቱ የአመራር አካል ካለውና ህዝቡን በአንድነት ከጎኑ ማሰለፍ ከቻለ፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ስኬቱ አጠራጣሪ አንደማይሆን በድጋሚ ላሳሰበን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግልና፣ ድል ደጃፍ ላደረሰው ስኬቱ የእንኳን ደስ አለን መልዕክት ተገቢ ነውና እንኳን ደስ አለን።

ቀጣዩም ትግል የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን አንድነትን አጠናክሮ አመራርን አጎልብቶ ከመጓዝ ሌላ አማራጭ ስለሌለ፣ ስኬታማውን የሰላም ትግል ማስቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዞ ይሆናል ፣ ድሉም አጠራጣሪ አይሆንም።

Filed in: Amharic