>
12:32 pm - Sunday December 4, 2022

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት - ክፍል አራት (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤...)

ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት
ደራሲ፡ ጌቱ ሙጨ
የታተመበት ዓመት፡ 2011
የገፅ ብዛት፡ 200

በሰሎሞን ዳውድ አራጌ
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ እንግሊዝኛ ቋንቋና
ስነፅሁፍ ትም/ት ክፍል መምህር

ክፍል አራት

በእድሜ ትናንሾቹ ጀግኖች አርበኞች አጭር ታሪክ

ከእነዚህ ሁለት ስመ ገናና ጀግኖች (አባ ጃዊና አባ ድፈን) ጎን ሕይወታቸውን ሰጥተው፣ መስዋዕት ሆነው ትግሉን የመሩና የተሳተፉ ዕልፍ ቢሆኑም ከዚህ በታች ታሪካቸው በአጭሩ የቀረበው ጀግኖች ግን ታሪክ ሊረሳቸው የማይገቡ ጀግኖች ከጀግናም በላይ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው፡፡

• አርበኛ ሙሐቤ በለጠ (1973 – 2009 ዓ.ም) በቅፅል ስሙ ጀርመኑ በመባል ይታወቃል፡፡
ከአቶ በለጠ ዘውዱና እናቱ ወ/ሮ ደብሬ እንየው በሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በዳባት አውራጃ በጠገዴ ወረዳ ሸኒ ሊቋስ መንደር የግንቦት ባዕታ ማርያም በ1973 ዓ.ም ተወለደ፡፡ በንግዱም በግብርናውም የሚሳካለት ሙሃቤ በጉርምስና ዕድሜው ትዳር መስርቶ ሁለት ሴትና ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርቷል፡፡ ታታሪ ሰራተኝነቱ፣ ድርድር አዋቂነቱ፣ ሰው አክባሪነቱ፣ ታጋሽነቱ የሚታወቅ ሲሆን ትእግስቱን ተላልፎ ለመጣበት ግን የብስጭቱና ወንድነቱ ግዝፈት ወሰን የለሽ ነበር፡፡ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የነፃነት ታጋይ የነበረ፤ በማንነቱ የማይደራደር ደፋርና ንቁ ወጣት ነበር፡፡ ከወንድሙ አባይ በለጠ ዘንድ ልዩ ፍቅር ያለው ሙሃቤ የበርሃ እርሻ ስራ ሲለምድ ጊዜ በርሃ ሲኖር ቆይቶ በቃህ ጎንደር ግባ በሎ ዘምድ ወንድም በመከረው መሰረት ጎንደር ከተማ ገብቶ መኖር ጀመረ፡፡
አልሞ ተኳሹ ሙሃቤ ወንድም ና ተከተለኝ ብሎት ያልወጣበት ትግል አልነበረምና በሃምሌ 05/ 2008 ተዋግቶ ለጠላት ምስ ሆኖ የዋ ሲሆን ከአባ ጃዊ ዘንድ ዘምቶ ፍርሃትን ገድሎ ሕዳር 16/ 2009 ዓ.ም ተሰዋ፡፡

• አርበኛ ሰጠኝ ባብል ( – 2008 ዓ.ም)

ከአባቱ አቶ ባብል ከበደና ከእናቱ ወ/ሮ የሽመቤት ሲሳይ አርማጭሆ ላይዮ አካባቢ፤ እድገቱ ዋልያ አካባቢ የነበረ ለቤተሰቡ ብቸኛ ወንድ ልጅ ነበርና በአያቱ ሰጠኝ የሚል ስም ተቸረው፡፡ በግብርናና ከብት ርባታ ስራ የሚተዳደር፤ ስድስት (5 ወንድ) ልጆችን ያፈራ ጎልማሳ ነበር፡፡
አቶ ሰጠኝ ዋልያ፣ ሳንጃ፣ ድፍን አርማጭሆ፣ አብራጅራ፣ አጅሬ ጃኖራ ድፍን ሃገረ ጎንደርን ያስታርቅ የነበረ የልጅ ሽማግሌ ነበር፡፡ 120 በላይ ከመንግስት ጋር ተጣልተው በሽምቅ ከሚዋጉ ሃይሎች ጋር ተደራድሮ ስምምነትን የፈጠረ የጠባይ ጌታ፣ መልካምና ታማኝ ሰው ነበር፡፡
አቶ ሰጠኝ ባብል በሃገር ጉዳይ ድርድር የለውምና በኤርትራ መገንጠል ማኩረፉን የተመለከተ የወያኔ ቡድን አፈና አድርጎ በእስር አንገቶታል፤ የግል መሳሪያውንም ነጥቆታል፡፡ በጉርምስና ጊዜው ሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ አውጢር በተባለ ቦታ 500 ሄክታር የእርሻ ቦታ ነበረው፤ አከባቢው ሰላም ሲያጣ ወደ ቤተሰብ ደርሶ በተመለሰ ግዜ እርሻውን ለአንድ የትግራይ ተወላጅ ተሰጥቶ ቦታው በሕዋሃት ወታደሮች ሲጠበቅ ቆየው፤ በነበረ የክስ ሂደት 25 ሄክታር ማስተዛዘኛ ብአዴን ሰጠው፤ ቆይቶም 30 ሄክታ መሬት ታክሎት ግብርና ስራውን ይሰራ ነበር፡፡
በሐምሌ 05 / 2008 ኤም ፎርቲን ይዞ ጠላትን ሲያርድ የዋለው ጀግናው ሰጠኝ ባብል ሕንፃ ላይ በተጠመደ የብሬል ጥይት ተመትቶ ወደቀ፡፡ ለብዙዎች ትግል ጧፍ ሆኖ ነደደ፤ ብዙሃኑም በስሙ እየተማማለ፤ በጀግንነቱ እየተበረታታ ለወሬ ነጋሪ እንዳይተርፉ አድርጎ ድል መታ፡፡

• አርበኛ ደሳለኝ አዱኛ (ጦር ቀማሽ) ( – 2009 ዓ.ም)

ትውልዱ በደባርቅ ወረዳ ቀበሻ ቀበሌ ሲሆን እድገቱ ግን አጅሬ ነበር፡፡ እድገቱ አጅሬ ጃኖራ ነውና፤ ከልጅነት ዕድሜው ጀም ተኩስና ኢላማ ያደገበት ነው፡፡ በኢላማ ተኳሽነቱ ወንድ የማይደርስበት ደሳለኝ ታታሪ ገበሬም ነበር በሳንጃ፣ በዳንሻና ሁመራ ሞፈር ዘመትና ካምፕ አስተባባሪ ሆኖ ሕይወቱን ያሸነፈ ትዳር መስርቶ ሁለት ልጆችን (1 ወንድ) ያፈራ ጀግና ነበር፡፡
በሰላም ከሚኖርበት ቀዮው መሳሪያ አውርድ ሲል ከመጣው የወያኔ ቅልብ ሰራዊት ጋር አፈሙዝ ተዟዙሮ አካባቢውን ለቆ ምቹ ቦታ ጎድቦ መኖር ጀመረ፡፡ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮም መንግስት ጋር ቅራኔ በመፈጠሩ በጦርነት ልምድ ያላቸውን ወጣቶችና የተገፉ አርበኞች በማስተባበር ይሰራ ነበርና የጃኖራው መሳፍንት ተስፉን ለመቀላቀል ጠይቆ፤ በስንቅ አለመሟላት ስዘገይበት ወደ አባ ጃዊ ጎቤ ዘንድ ሄዶ አርበኞችን ተቀላቀለ፡፡ በሁሉም የአባ ጃዊ ፍልሚዎች የማይጠፋውና ወሳኝ ርምጃ ይወስድ የነበረው አርበኛ ደሳለኝ በመጨረሻ የአመራ ቁስቋም ዳገት ወጥቶ የአባ ጃዊን ጥሩምባ ሰምቶ ከግራ ከቀኝ የተኮለኮሉትን የትሕነግ ቅልብ ወታደሮች በክላሽ ጥይት አለንጋ ገርፎ፤ እርሱ ግን ቤቱን ቤተሰቡን ጥሎ እዚያው ፍልሚያ ላይ ተሰዋ፡፡

• አርበኛ ሞላጃው ሙላው ( – 2009 ዓ.ም)

ከአባቱ አቶ ሙላው አለሙና ከእናቱ ወ/ሮ እናና ከበደ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ የተወለደው ወንድ ብላቴና ለቤተሰቡ በተለይም ለእናቱ ደስታን የፈጠረ ሲሆን ከእርግዝናው ጀምሮ ፆታውን ሲያጠኑ የነበሩ የአባቱ ጠላቶች ለአፈና ሲዳርጉት ጥሎ ጠፋ፤ ያለአባትም አደገ፡፡ ሙላጃው በሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ወረዳ ማሰሮ ደምብ ቀበሌ ተወልዶ እድገቱና ሕይወቱን በፈተና ያሳለፈ ወጣት ነበር፡፡
የኋላ ኋላ አባቱ በዱር በገደል ኑሮውን አድርጎ ኖሮ በ26 ዓመቱ መጣሁልህ ቢለውም ገና መጣሁ ብሎ ደስታውን እንዳበሰረወ በጥንተ ጠላቶቹ በጥይት ተመትቶ ሞተበት፤ ድንገቴ ተስፋውን መንሶ የተነጠቀው ሞላጃው ወደ ሕይወት ፈተና ፊቱን አዙሮ የእናቱን በብቸኝነት ልጅ የማሳደግ መከራ፤ እያሰበ የሙዚቃና ድራማ ቡድኖች ዘንድ በመሳተፍ ይኖር ነበር፡፡ በዚህ መሃል ጉርምስና እድሜው ላይ አባቱን ገዳዮች ዜና ደጋግሞ መስማት ግድ ሆነበት፤ ደም ይመልስብናል ያሉ ጠላቶቹ ሕይወቱ ስኬታማ እንዳይሆን መሰናክል አበዙበት፡፡ መሳሪያም ያልነበረው ሞላጃው አርበኞች ግምባርን ተቀላቅሎ ኤርትራ በርሃ ወረደ፤ ሰልጠናውንም ጨርሶ በሌሊት መንደሩ የዘለቀው ሞላጃው፤ የአባቱን ደም ለመመለስ ማሰቡን የሰሙ ታላላቅ ሰዎች መክረውት በምህረት ሳለ፤ ሕይወቱ መደላደሉን ያዩ ጠላቶቹ መድረሻ አሳጡት፤ ዘበኝነት ተቀጥሮ ከሚሰራበትም በጥይት ሳቱት፤ ይሄኔ ወዳጅ ዘመድ መክረው ወደ አዲስ አበባ ላኩት፡፡ ወጣትነቱን የተቀማው ሞላጃው አዲስ አባባም ሳለ በሚሰራበት መስሪያ ቤት ሱር ኮንስትራክሽን መንገድ ስራ ንብረት ጠፋ ሲባል ጥሎ ጠፋ፤ ማደኛ ወጥቶ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጎ ድብደባ ተፈፅሞበት፤ ለእስር ተዳረገ፤ ጎንደር ማረሚያ ቤትም ሳለ ማረሚያ ቤቱ ተቃጥሎ 72 በላይ ሰዎች በሞቱበት አደጋ ሕይወቱ ለጥቂት ተረፈች፡፡ በአንገረብ እስር ቤትም ሳለ ሰነዱ ተቃጥሎ ስለነበር ከወታደሮች ጋር ውዥንብር ፈጥሮ ጥሎ ጠፋና በርሃ ገባ፡፡ በበርሃም የአባ ጃዊን የአርበኞች ጦር ተቀላቀለ፤ በዚያም ከወያኔ ጦር ጋር በተደረገው ፍልሚያ በጀግንነት ታግሎ፤ ስሙን በታሪክ ማህደር ላይ አስፍሮ ተሰዋ፡፡

• አርበኛ ቃቁ አወቀ (1980 – 2009 ዓ.ም)

ከአባቱ አቶ አወቀ ይርጋና እናቱ ጥሩየ ተረፈ በሰሜን ጎንደር ታች አርማጭሆ ሳንጃ ወረዳ ከንበው በ1980 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ዕድገቱ በግብርና ሙያ ላይ የሚያጠነጥነው ቃቁ ብዙ ግዜውን በእርሻ ማሳዎቹ ያሳልፍ የነበረ ስራ ወዳድ ወጣት ገበሬም የነበረ ሲሆን በትዳም ተወስኖ ሕይወቱን እየመራ ባለበት ቅፅበት የአካባቢው ሰላም አለመረጋጋት ያስጨነቀው ቃቁ ከነፃነት በኋላ ይደርሳል በማለት በርሃ ወርዶ፤ አባ ጃዊን ተቀላቀለ፡፡ በሕዳር 16/ 2009 ከጓዶቹ ዘንድ በመሆን ጠላትን አርዶ ሕይወቱን ለትግሉ ሰውቷል፡፡

• አርበኛ አወቀ አታክልት (ከ1979 – 2009 ዓ.ም)

ከአባቱ አቶ አትክልት እንየውና ከእናቱ ከወ/ሮ ውብነሽ ሙጨ በሰሜን ጎንደር ጠገዴ ወረዳ አዳቦ ቀበሌ ተወለደ፡፡ ይህ የሰላሳ ዓመት ጎረምሳ እንደማንኛውም የአርማጭሆና ጠገዴ ወጣት ጠልጅነት ህልሙ አልሞ ተኳሽነት ነበርና በልጅነቱ ልምዱን የሰነቀው ይህ ወጣት ሕይወትን በግብርና ስራ ጀምሮ የተለያዩ የንገድ ስራዎችን እንደ ሰሊጥ ግዥና ሽያጭ ተሰማርቶ የነበረ ቢሆንም የሕዋሃት ገዥ ሃይል በደልና ግፍ እንደ ማንኛውም የአማራ ወጣት ቢያደርስበት የአባቱን መሳሪያ አንስቶ በ2001 ጫካ ገባ፡፡ የወያኔ አመራሮችም ከሽፍቶች ዘንድ ግንኙነት አለው ሲሉ ይዘው ለዕስር ዳረጉት፤ በታሰረበትም ካምፕ ወታደሮቹን አሳምኖ ወደ ሽፍትነት ይዞ ወጣ፤ በመሃልም ወታደሩን ወደ ካምፑ አንዲመላስ በመሳሪያ አስፈራርቶ እሱ ጫካውን ገባ፤ የወታደሮቹ አመራሮችም በከፍተኛ ጦር አዝምተው ቢፈልጉትም አላገኙትም፡፡ ይህ በሆነ ከብዙ ወራ በኋላ በአባ ጃዊ አደራዳሪነት መሳሪያውን አስመልሶ አስታረቀው፤ ዕድሜ ለአባ ጃዊ በ2003 ወደ ከተማ እንዲገባ አድርጎ አዲስ መሳሪያ አስታጠቀው፡፡ አወቀ አታክልት አስከ ሐምሌ 05 /2008 ዓ.ም ግርግር ድረስ ጠንካራ ሰራተኛና ታጋይ ነበር፡፡ መስከረም 25/ 2009 ዓ.ም አርበኛ አወቀ የተጋድሎ ግብዓቶችን ጠቅልሎ በርሃ ገባ፡፡ የአርበኛ አባ ጃዊ ጎቤን ትግል ተቀላቀለ፤ ወያኔም አብዝቶ የአርበኞችን ትግል ለማኮላሸት በርካታ አሉባታዎችን ይልክ ስለነበር በአባትና በልጅ መካከል ሳይቀር አለመተማመንን አስፍኖ የበረው መንግስት በፈጠረው ችግር አንድ ዓላማ ይዘው የወጡት አባ ጃዊና አወቀ አታክልት በለት ጎራ ተከፍለው ትግሉን ጫፍ ለማድረስ ተለያዩ፡፡

ጸሃፊውን ለማግኘት : solomon123@yahoo.com

 

የቀድሞዎቹን ክፍሎች ካላነበባ ች ሁ ቀጥሎ ያለውን ማጣቀሻ በቅደም ተከተሉ ይጫኑ።

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤    

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – ክፍል ሁለት (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – ክፍል ሶስት (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤…)

Filed in: Amharic