>
12:01 pm - Thursday December 8, 2022

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ…ተስፋ የማልጥልባቸው ሰው ናቸው”  (ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ)

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ…ተስፋ የማልጥልባቸው ሰው ናቸው” 
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ
“በኢሳት ውስጥ የሚገኘው አፋኝ ቡድን…አፈና እንዲፈጽም ያደረገው በአብይ አህመድ መንግስት አካሄድና ውሳኔዎች ላይ የሰላ አመክንዮአዊ ትችት መሰንዘሬ ነው”
በረራ:- በአሁኑ ሰዐት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታን እንዴት ትገመግመዋለህ፤ ከግምገማህ በመነሳትስ ሃገሪቱ ወደየት እየሄደች ነው? 
ቴዎድሮስ:- ኢትዮጵያችን ያለፈውን ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የሆነ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም የሰው ልጅ የማይመጥን ኋላቀር የነገድና የጎሳ ስርዐት ተዋቅሮባት ከብሄር ወይም ዘር በቀር ሌላ ማንነትን የማያውቅ“ህገ መንግስት”ተጭኗት ነው ያሳለፈችው:: ማንም እንደሚያውቀው አሁንም ይኸው ህገ መንግስታዊና መዋቅራዊ ቀንበር እንደተጫናት አለች:: ይህንን መሰል ከዘር በቀር ሌላ የሰብእ ማንነትን የማይገነዘብ ስርዐትና ህገ መንግስት ያዋቀሩ ሀገራት ከዚህ ቀደም በገቡበት የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥም ትገኛለች:: ስለሆነም አሁን ኢትዮጵያችን ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳት ወይም ተራ አስተዳደራዊ መጓደል አልያም የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመግባባት ተብሎ ሊገለጽ ከቶ የሚችል አይደለም:: የተዘፈቅነው በስርዓታዊና ህገ መንግስታዊ መከራ ውስጥ ነው:: አሁንም ሆነ ባለፉት ህወሀት በገዛ በነዳባቸው 27 አመታት እየተፈጠሩና እያደር ስር እየሰደዱ የሄዱት ግጭቶች መዋቅርና ህገ መንግስቱ የወለዳቸው ናቸው:: በሀገራችን ሊዘንብ ያዳመነው መከራ ምንጭ ይኸው ህገመንግስትና መዋቅር ነው:: ይህ ስርዐት ደግሞ አንደኛ በኢትዮጵያውያን መሀል የሚፈጠርን መለያየት የህላዌው ምክንያት ያደረገ፣ ሁለተኛ የሰውን ልጅ ጥልቅና ውስብስብ ፍጡርነት ረስቶ አንድ ቁንጽል መገለጫውን ብቻ የወሰደ፣ ሶስተኛ በወደፊት የዜጎች ተስፋ ላይ ሳይሆን አርቃቂዎቹ ትላንት ተፈጽሟል በሚሉት ምንም የሀቀኛ ታሪክ ምርኩዝ በሌለው የብሄር ጭቆና ትርክት ላይ የተመሰረተ፣ አራተኛ ለዚህም እንደ መፍትሄ ብሎ የዜግነት እርከን የሰራና ለየብሄሩ የሀገሪቱን ግዛት የሸነሸነ፣ የልዩ ባለቤትነትን አደገኛ ጽንሰ ሀሳብ ያስተዋወቀ፣ አምስተኛ ህገ መንግስታዊ ሂደት ያላለፈና በህዝብ ፈቃድና ስምምነት ያልመጣ የአፈና እንዲሁም የህወሀትና የኦነግ የፖለቲካ ርዕዮት ውጤት የሆነ ሰነድ ነው::
እንግዲህ እዚህ ህገ መንግስታዊና መዋቅራዊ ችግር ውስጥ ያለ አገር የሚያስፈልገው ሊድን የሚችለው እንደ ችግሩ ሁሉ ህገ መንግስቱንም ሆነ መዋቅሩን መለወጥ ሲችል ነው:: አሁን የተበራከቱትን ግጭቶችና የስርዓት መፈራረስ ማንም ባለ ጉልበትና ጠብመንጃ ሊያስቆመው የሚችል አይመስለኝም:: መፍትሄው እርሱ አይደለም:: የገጠመን ስርዓታዊ እክል ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ወቅት እየተካሄደ ያለውን ማናቸውንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የምመዝነው ከዚህ መሰረታዊ ጭብጥ አንጻር ነው:: በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው የሚባልለት ለውጥ እነኚህን መሰረታዊ የአገር ህልውና ጥያቄዎች ጉዳይ ያደረገ ነውን? ብለን ከጠየቅን ለእኔ መልሱ ቀላልና በግልጽ የሚታይ ነው ባይ ነኝ:: ይህ በሂደት ላይ ነው የሚባል ለውጥ እነኚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ትኩረቱም ግቡም አይደሉም:: በእስካሁኑ የአንድ አመት ጉዞ እነኚህን ስር ነቀል ለውጦች የማካሄድ ፍንጭ ከቶ አላሳየም:: ስለሆነም ዘወትር እንደምለው ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተካሄደ ያለው ሽግሽግ እንጂ ሽግግር አይደለም:: የመቀሌውን ወይም የአድዋውን ዘውጌ ፓርቲ የበላይነት በአዳማ ወይም ጂማ ወይም ወለጋ ዘውጌ ፓርቲ የበላይነት የመተካት ሽግሽግ ነው:: በተጨማሪም፣ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ፣ ከ“ኤርትራ”ወደ አዲስ አበባ፣ ከ“ኤርትራ”ወደ“ኦሮሚያ፣ ከ“ኤርትራ”ወደ“ትግራይ”የተሸጋሸጉ ሀይሎችም አሉ:: ታሪክና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ የሚያስረዱን አንድ ሀቅ ቢኖር በዚህ ህገ መንግስትና መዋቅር ስር አንድ ቀን ባሳለፍን ቁጥር እንደ ሀገር መቀጠላችን ወደ አደጋ እየተጠጋ መሆኑን ነው:: በዚህ አንድ አመት ውስጥ በህዝብ የህይወትና የደም ክፍያ የመጣ ውስን የፖለቲካ መከፈት ቢኖርም ይህ ግን የህግና የተቋም ዋስትና የለውም:: ስለሆነም፣ በኢትዮጵያ ያለውን የ1 አመትሂደት ባጭሩ ብገልጸው ገደሉን ፊት ለፊት ከማየት ይልቅ ለገደሉ ጀርባ ሰጥቶ ግን እዚያው የማንቀላፋት አይነት ነው:: አሁን ለውጥ ተብዬውን እመራለሁ የሚለውም ቡድን ንግግሩ እንጂ ተግባሩ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ አይደለም:: ስሙን ቀይሮ ኦዴፓ የተሰኘው ይህ የዘውግ ፓርቲ እንደ ፈጣሪው እንደ ህወሀት ሁሉ ከእዚያው ከዘውጉ አጥር መውጣት ያልቻለ፣ ከዚህ የዘውግ ርዕዮትና መዋቅር ብወጣ ከባህሩ እንደተለየ አሳ እሞታለሁ ብሎ የሚያምን፣ ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድር የሚሊዮኖች ያልተቆጠበ ድጋፍ ቢቸረውም በለመደው የዘውግ አጥር ካልተወሰንኩ የሚል አገራችንንም፣ ዘመኑንም መዋጀት የማይችል አገራዊ ራዕይ የሌለው ምናበ ትንሽ ፓርቲ ነው፡
በረራ:- አዲስ አበባ ከተማ ላይ የተፈጠረው ህገ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ችግር ሊፈታ የሚችለው እንዴት ነው? አዲስ አበባ የማን ናት? የኦሮሞ ነገድ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ልዩ መብት ሊያሰጠው የሚችል ታሪካዊ ጭብጥ አለው? 
ቴዎድሮስ:- ከታሪክ እንጀምር:: አዲስ አበባ ከአንድ ሺህ አመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በተለያየ ደረጃና ስያሜ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ልብ እና የስበት ማእከል ሆና ያገለገለች ጥንታዊት ከተማ ስለመሆኗ ሞልቶ የተረፈ የታሪክ ማስረጃ አለ:: ሆኖም በቀደመው ጥያቄ ላይ እንዳነሳሁት ይህ ስርአት ከ“ብሄር”ማንነት በቀር ሌላ አያውቅምና አገሪቱን በቋንቋና በነገድ ሲሸነሽን ለዚህ ስሌት ጨርሶ ካልተመቹ በርካታ ከተሞች አንዷና ምናልባትም ዋንኛዋ አዲስ አበባ ናት:: ስለሆነም ህወሀት፣ አንድም የዘረጋውን ስርአት የሚገዳደርና የሚቀይር አዲስ የፖለቲካ ሀይል እንዳይፈጠር ከወዲሁ ለመቅጨት፣ በራሷ ጉዳይ የማትወስን የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ቅርጫ እንድትሆን በማድረግ፣ አንድም ደግሞ ስልጣኑ በሚፈተንበት ወቅት በዜግነት ፖለቲካ ናፋቂዎችና በኦሮሞ የነገድ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች መሀል ግጭት መለኮሻ የመጫወቻ ካርድ አድርጓት ቆይቷል:: አዲስ አበባ ከዚህ ህገ መንግስት ስራ ላይ መዋል በፊት እራሷን የቻለች ክልል ማለትም ክልል 14 የነበረች መሆኗን ልብ ይሏል:: ህወሃትም ቀደም ሲል ለጠቀስኳቸው እኩይ አላማዎች መሳካት ሲል በዜጎች መሀል እርከን የሚፈጥርና የዜግነት ተዋረድ የሚሰራ የልዩ ጥቅም ጽንሰ ሃሳብ አካተተ:: ይህም አስቀድሞም ኦሮሚያ ተብሎ የተከለለውን የኢትዮጵያን ግዛት ነጥሎ ኩርማን አገር የመመስረት ቅዠት ለነበራቸው ኦነጋውያን ቀላል የማይባል ድል ነበር:: አዲስ አበቤም በዚህ ፖለቲካዊ አሻጥር ሳቢያ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፤ አሁንም እየከፈለ ነው:: ይህ የህገ መንግስት አንቀጽ የማይጠረቃ ፍላጎት ላላቸው የኦሮሞ ዘውገኛ ልሂቃን የውስጥ ድክመት መሸፈኛ፣ የውስጥ ትብብር መፍጠርያና እነርሱ ሌሎች በሚሏቸው የተቀሩ ኢትዮጵያውያን ላይ መዝመቻ አጀንዳ አድርገውት ይገኛል:: ችግሩ የሚፈታው ፖለቲካችን የዚህን መዋቅርና ህገ መንግስት የሀሳብም ሆነ የመሬት ላይ አጥር መጣስ የቻለ እንደሆነ ነው:: አዲስ አበባ የማን ናት? ለሚለው ጥያቄ የማያወላውል መልሴ፤ የአዲስ አበባ ባለ ቤቶች፣ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ሁሉ ኢትዮጵያውያን በጠቅላላ ናቸው:: የአዲስ አበባ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤቶች ግን ነዋሪዎቿና ነዋሪዎቿ ብቻ ናቸው:: በአሁን ወቅት ግን አዲስ አበባ፣ ነዋሪዎቿ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መብቶቻቸው ባለቤት ያልሆኑባት፣ ነዋሪዎቿ በእራሳቸው ህይወት፣ እጣ ፈንታና የአስተዳደር ዘዬ ላይ መወሰን የማይችሉባት፣ በከተማዋና ህዝቧ ላይ ባቄሙ አምባገነን የዘውግ ብሄረተኞች የምትተዳደር የባርነት ከተማ ናት::
ወደሌላው ጥያቄህ ስሻገር፣ የኦሮሞ ነገድ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለየ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ መብት እንዲያገኝ የሚያስችለው አንዳችም የታሪክ፣ የህዝብ አሰፋፈርና የቦታ አቀማመጥ መነሻ የለም ብዬ በጽኑ አምናለሁ:: እነኚህን ነጥቦች በየተራ ላብራራቸው::
አንደኛ፣ በአዲስ አበባ ላይ የሚቀርብ የልዩ ባለቤትነት ጥያቄ የተመሰረተበት ትርክት ሀሰተኛና የፈጠራ ትርክት ነው:: በታሪካችን ፊንፊኔ የተባለ ምንጭ እንጂ ፊንፊኔ የተባለ ከተማ ኖሮ አያውቅም:: ፊንፊኔ ያሉት ስያሜም ምንጩ አማርኛ ነው:: ይህ የእኔ አተያይ ሳይሆን ሀቅ (Fact) ነው:: በዝያ ላይ እዚያ ስፍራ ላይ የኦሮሞ ብሄረተኞች የሚያነሱት ታሪክን የተመረኮዘ የይገባኛል ጥያቄ እውነት አይደለም እንጂ እውነት ቢሆን እንኳ ታሪክን መርጦ የሚያስታውስ ግራ አቋም ነው:: ታሪክ ከዳግማዊ ምኒሊክ አይጀመርም:: የኋላም ኋላ አለው:: አዲስ አበባ እንደገና በትንሳኤ መልሳ ከመቆርቆርዋ ከ350 አመታት ገደማ በፊት በዝያው አሁን ከተማዋ ባለችበት ስፍራ ላይ ኢትዮጵያውያን በነገድ ሳይለያዩ፣ በሀይማኖት ሳይከፋፈሉ በአንድነት ይኖሩባት የነበረች፣ የውጪ ዜጎችን ሳይቀር ያስጠለለች እጅግ ዘመናዊ ከተማ ነበረች:: ስሟም በራራ ነው:: ከዚያም ወደኋላ መሄድና ታሪክ ማጣቀስ እንችላለን:: ለጊዜው ግን ይኸው ይብቃን:: ይህንን ታሪካዊ ሀቅ እነኚህ የነገድ ብሄረተኞች ሊሰሙት አይሹም:: ቢያጣጥሉትም፣ ለዚህ ታሪካዊ እውነት ጆሮአቸውን ቢደፍኑም፣ ሀቁን ግን መቀየር አይቻላቸውም:: ስለሆነም ታሪክን ተመስርቶ በአዲስ አበባ ላይም ሆነ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ላይ የብቸኛና ልዩ ባለቤትነት ጥያቄ የማቅረብ መብት ያለው ነገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም::
ሁለተኛ፣ የእነርሱን ቀመር እየጎረበጠኝም ቢሆን ተውሼ የከተማዋን የብሄር ተዋጽኦ ብመለከት፣ ከ80 በመቶ በላይ ነዋሪው የኦሮሞ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች እንደራሳቸው ወገን የማይቆጥሩት ሌላው ኢትዮጵያዊ ነው:: ይህም በህዝብ አሰፋፈር ምርኩዝነት የሚጠይቁት ምንም የልዩ ባለቤትነት ጥያቄ እንዳይኖር ያደርጋል::
ሶስተኛውና በእነኚህ የነገድ ብሄርተኞች በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ምክንያት ደግሞ አዲስ አበባ በኦሮሚያ የተከበበች በመሆኗ የሚል ክርክር ነው:: ይህ ክርክር አሁን ያለው ህገ መንግስት አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ እንዲወሰድ በመፈለግ ሆን ተብሎ ከሚፈጸም ፖለቲካዊ ማደናገር የሚመነጭ ነው:: እውነቱ ግን ኦሮሚያ የምትባል ክልል 30 አመት ያልሞላት የዚህ የዘር ህገ መንግስት ልብወለድ የሆነች አካል ስትሆን አዲስ አበባ ግን እንደገና እንኳን ከተቆረቆረች 130 አመት ያለፋት እድሜያማ ከተማ ናት:: ታድያ በምን አመክንዮ ነው 30 አመት የማይሞላት ልብወለድ እንደገና ከተቆረቆረች 130 አመት የሞላት እውነት ብቸኛ ባለቤት ልትሆን የምትችለው? ትርጉምም ስሜትም አይሰጥም:: የዚህ ችግር አንዱና ምናልባትም ቁልፉ መፍትሄ ግን የአዲስ አበቤው መደራጀትና መደራጀት ብቻ ነው:: መደራጀት ለአዲስ አበቤ ለነገ የሚባል ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው::
በረራ:- አንዳንዶች ቴዎድሮስ ፀጋዬ ከለውጥ እንቅፋቶች ወገን ነው ሲሉ ይደመጣሉ:: የቴዎድሮስ ፖለቲካዊ አቋም አለ ከሚባለው ለውጥ ጋር እንዴት ይታያል? 
ቴዎድሮስ:- ከዚህ ቀደም ባገኘኋቸው አጋጣሚዎች ሁሉ እንደገለጥኩትና አሁንም እንደምገልጸው፣ እኔ በዜግነት ፖለቲካ የማምን፣ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንደ ብቸኛ አገሪቱን ከማጥ የሚያወጣ የብርሃን መንገድ የምቀበል፣ በሀገሬ ለ ሺህ አመታት የተዘረጋ ሰፊ ታሪክ የምኮራ ኢትዮጵያዊ ነኝ:: ይህ አሁን መጣ የሚባለው ለውጥ ከመምጣቱም በፊት በርዕዮት ሚድያ የኢንተርኔት አገልግሎት አማካይነት ለአመታት የህወሀትን ጨቋኝ አገዛዝ ስቃወምና የዚህን ህገ መንግስትና መዋቅር አገር አፍራሽነት በአደባባይ ሳስተጋባ የነበርኩና አሁንም ያለሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ:: ይህንን እውነታ ማንም የኢንተርኔት Access ተደራሽነት ያለው ሰው ሊያረጋግጠው የሚችል ነው:: ስለዚህም አስቀድሜ እንዳመለከትኩት በኢትዮጵያ የሚካሄድን ማናቸውንም ለውጥ የምመዝነው እንቅስቃሴው ለኢትዮጵያዬ እንደ ሀገር መቀጠል ዋስትና ይሆናል ወይ? ስርአታዊ ለውጥ ያመጣል ወይ? ዜግነትን መሰረት ወደ ሚያደርግ ፖለቲካ ይወስዳል ወይ? የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍትህ ያሰፍናል ወይ? በሚሉና ከዚሁ ጋር ተያያዥ በሆኑ መለኪያዎች ነው:: አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳል የሚባለው ለውጥ ደግሞ እነኚህ ነጥቦች ሰፈር የመድረስ ሀሳብ እንደሌለው በተለይ አሁን ላይ በግልጽ አውቀናል:: እነኚህን መሰረታዊ ቁምነገሮች ጉዳዩ ያላደረገ ለውጥ ደግሞ ለውጥ የሚያመጣ ለውጥ አይደለም:: ለውጥ ከሌለ ደግሞ አይደናቀፍም:: የእኔ ተስፋ ሊለወጥም ሆነ ሊለውጥ በማይችለው በኢህአዴግና በፍንካቾቹ ሳይሆን በዜጎች ነው:: ኢትዮጵያዊነትን መሰረት ከሚያደርግ ማናቸውም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ንቅናቄ ጎን ለመሰለፍ ከዝግጁ በላይ ነኝ:: ለምሳሌ ለአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ያለኝ ከፍተኛ ድጋፍም ከዚህ መርሄ የሚመነጭ ነው:: ለሌሎች በኢትዮጵያዊነትና በዜግነት ፖለቲካ ላይ የማያወላውል አቋም ለያዙና ለአጀንዳቸው ለታመኑ ማናቸውም እንቅስቃሴዎችም እንዲሁ::
በረራ:- ለመሆኑ ዶር አብይን ታምናቸዋለህ? ዕውነት እርሳቸው እንደሚሉት “እምዬ ኢትዮጵያን” ለመታደግ የመጡ መሲህ ይመስሉሀል? 
ቴዎድሮስ:- ጉዳዩ አንድን ግለሰብ ከማመን ካለማመን ጋር ብቻ ተያይዞ ባይገለጥ እወዳለሁ:: ከጠቅላላው ሀሳብ ልነሳ:: እንኳን ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ ሀገር፣ እንኳን ኢትዮጵያን ያህል በረዥም ዘመናት ታሪኳ ተነግሮ የማያልቁ ጸጋዎች ያካበተችና በዚያውም ልክ ውስብስብ ችግሮች የተጋረጡባት ሀገር፣ ማንኛውም ሌላ አገርም ቢሆን በአንድ ግለሰብ በጎነት ላይ ተንጠልጥሎ ወደ ብርሃን ይሻገራል ብዬ አላምንም:: እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ግለሰብ፣ ኢህአዲግ እንደ ፓርቲ እንኳን ሀገሪቱን ማሻገር አይችልም:: እንኳን አሁን በሀገሪቱ ካሉት ችግሮች ቀላል የማይባሉትን እራሱ የፈጠረው ኢህአዲግ ቀርቶ፣ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች በጠቅላላ ተሰብስበውም የሀገራችንን ችግር መፍታት አይሆንላቸውም:: ይህ ችግር ሁለንተናዊ የህዝቡን ተሳትፎ የሚሻ፣ ኢትዮጵያ ያበቀለቻቸውን እውቀት፣ አስተሳሰብና ምሁራን በሂደቱ በማሳተፍ ብቻ ልንሻገረው የምንችል ከባድ ፈተና ነው:: እንደ ግለሰብ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየቴን እንድሰጥ ከጠየቅኸኝ አይቀር ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእኔ እምነት የሚናገሩትን ያልሆኑ፣ ሂስ ለመቀበል ጫንቃቸው የማይችል፣ ገና ወደ ስልጣን ሲመጡ ባለፉት 45 አመታት ማንም መሪ ባላገኘው መጠን ህዝብ አለስስት የቸራቸውን ፍቅርና ድጋፍ ወደ ፍሬ ሳይለውጡ እንዲሁ ያባከኑ፣ ተስፋ የማልጥልባቸው ሰው ናቸው ብዬ ብቻ ልለፈው::
በረራ:- ሰሞኑን አንድ አስገራሚ ሁኔታ ተፈጥሯል:: ይሄውም ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ካንተ ጋር ያደረገችውን ቃለመጠይቅ ኢሳት በቅድመ ምርመራ ሰበብ አፍኖታል። ሊያሳፍን የሚችል ሁኔታ የተፈጠረው ቃለምልልሱ ላይ ምን ብትናገር ነው? 
ቴዎድሮስ:- በጥያቄህ ላይ በትክክል እንዳመለከትከው የተፈጸመው አፈና የመብት ጥሰት ነው:: ይህም ጨርሶ ተቀባይነት የለውም:: ስለ ሀሳብ ነጻነት እንታገላለን ይሉ በነበሩ ግለሰቦች ይህ መፈጸሙ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳፋሪ ይበልጥም አጸያፊ ያደርገዋል:: ይህም ኢሳት በህወሀት አገዛዝ ዘመን ለህዝብ ከሰጠው እጅግ በጎ አገልግሎትና የሀሳብ ነጻነትን በማረጋገጥ ረገድ ሊኖረው ከሚችለው ሚና ጋር ይጻረራል:: ክልከላውና አፈናው በኋላ ጀግናዋ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ርዕዮት አለሙ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቃለምልልስ ፈቅዳልኝ ጥያቄዎች አቅርቤላት ነበር:: የጠየቅኋት አንዱ ጥያቄ፣ በውይይታችን ውስጥ የግለሰቦች ስምና ሰብእና ተነስቷል ወይ? ከስነምግባር መመዘኛ ጋር የሚቃረን ይዘት ነበረው ወይ? በህዝብ መሀል ግጭት የሚፈጥር ሀሳብ ተነስቶ ነበር ወይ? የሚል ነበር:: ርዕዮት አለሙም በፍጹም እርግጠኝነትና ልበ ሙሉነት“በፍጹም፣ እንዲያ ያለ ይዘት በቃለምልልሱ ውስጥ የለም”በማለት ነው የመለሰችው:: ስለዚህ በ51 ደቂቃው ቃለምልልስ ውስጥ በኋላ ለተከተለው በኢሳት ውስጥ በሚገኘው አፋኝ ቡድን አባላት ለተወሰነው የአፈና ውሳኔ የሚዳርግ አንድም አረፍተ ነገር የለም:: የዚህ አፋኝ ቡድን ችግር ሌላ ነው:: ቡድኑ በዚያ ቃለምልልስ ላይ አፈና እንዲፈጽም ያደረገው በአብይ አህመድ መንግስት አካሄድና ውሳኔዎች ላይ የሰላ አመክንዮአዊ ትችት መሰንዘሬ ነው ብዬ አምናለሁ:: ለአገዛዝ ወግኖ ዜጎችን ማፈን ግን ስለነጻነት እንታገላለን ሲሉ ከኖሩና በመናገራቸው በህወሃት ከተሳደዱ ሰዎች ፈጽሞ የማይጠበቅና ሊኮነን የሚገባው ነው:: ዛሬም ጥሪዬ የኢሳት Management ይህንን በጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ርዕዮት አለሙ ጠያቂነትና በእኔ መልስ ሰጪነት የተካሄደውን የ51 ደቂቃ ቃለምልልስ ሳይቆራርጡና ሳይሸራርፉ እንዲያቀርቡት ነው::
በረራ:- ለመሆኑ ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት አጣብቂኝ እና መስቀለኛ መንገድ ተጠያቂው ማን ነው? መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ብለህ የምታምነው አደረጃጀታዊና ፖለቲካዊ ጎዳናስ የትኛው ነው? እዚህ ላይ አያይዘህ “የአማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ መታገል ለኢትዮጵያ ስጋት ነው” የሚሉ ወገኖችን ሃሳብ እንዴት ነው የምታየው?
ቴዎድሮስ:- የዚህን ጥያቄ መልስ ለቀደሙ ጥያቄዎችህ በሰጠሁት መልስ በስፋት ስለሄድኩበት ዕጅግ ባጭሩ ሃሳቤን ላካፍል:: ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት አጣብቂኝ ብቸኛውም ባይሆን ዋናው ተጠያቂ ዘርን መሰረት ያደረገው ይህ የህወሀትና የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም የሆነው ህገ መንግስትና ከዚሁ የሚወለደው መዋቅር ነው:: ህገ መንግስቱም ሆነ መዋቅሩ በህዝብ ፈቃድ አልመጣምና ዲሞክራሲያዊ አይደለም:: ዜግነትን አያውቅምና የኢትዮጵያውያንን ህይወት አይመስልም:: በኢትዮጵያ ውስጥ የነገድ እንጂ አገራዊ ማንነት መኖሩን አይቀበልምና ዘረኛ ነው፡: እናም እነሆ በኢትዮጵያችን በየአመቱ በወጥነት ቁጥሩና የሚያካልለው ስፍራ እያደገ የሄደ የብሄር ግጭት በከፍተኛ መጠን ተንሰራፍቶ ይገኛል:: በአሁን ወቅት ከአጎራባች ክልሉ ጋር በመሬት ይገባኛል ጥያቄ የጎሪጥ የማይተያይ ክልል ካለ አንተ ንገረኝ:: በዚህ ላይ በየክልል ተብዬዎቹ ውስጥ ያለው ግጭትና ግድያ ሲጨመርበት ያለንበት ሁኔታ ምን ያህል የከፋ መሆኑን የሚያስገነዝብ ይመስለኛል:: ከዚህ ችግር የመውጫው መንገድም የነገድ ብሄረተኞች ወደው ሳይሆን በጥንካሬው ተገድደው የሚያነጋግሩትና የሚደራደሩት ኢትዮጵያዊ አደረጃጀት መፈጠሩ ነው:: ይህ መዋቅራዊና ህገ መንግስታዊ ለውጥ ዜጎችን በሚያስማማ ሂደትና ውጤት ከተከወነም እንደ ሌሎቹ ብሄሮች ሁሉ የአማራም በአማራነቱ መደራጀት አስፈላጊነት ይቀንሳል ወይም ይቀራል ብዬ አምናለሁ::
በረራ:- መጨረሻ ላይ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ? 
ቴዎድሮስ:-ኢትዮጵያዊነት የተስፋና የብርሃን ማንነት ነው:: ምንም እንኳ ሀገራችን አሁን የገጠማትን አይነት በዘር መከፋፈል በታሪኳ ገጥሟት ባያውቅም ሌሎች ከባባድ ችግሮቿን የተወጣችው ግን በአያት ቅድመ አያቶቻችን ጽናት፣ መስዋእትነትና ተስፋ ነው:: ዛሬም አዳኛችን ይኸው ጽናት፣ መስዋእትነትና ተስፋ ነው:: ተስፋዬ በዜጎች ነው:: ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ አገራችንን ማዳን ነገ አደርገዋለሁ የማንለው አሁንና ዛሬ መከወን ያለበት ተግባር ነውና፣ ሁላችሁም በየፊናችሁ የሚቻላችሁን ሁሉ በጎ አድርጋችሁ ውድ ሀገራችንን እንድትታደጉ ኢትዮጵያዊ ጥሪዬን አደርግላችኋለሁ:: የዛሬ መከፋፈላችንን ሳይሆን የቀደመ አንድነታችንን አስቡ:: የልጆችን ጠብ ሳይሆን የአያቶችን ፍቅርና ውህደት አስተውሉ:: ከጎጥና ከነገድ አጥር ወጥተን ታላቋን ኢትዮጵያን እንመለከት ዘንድ እማጠናችኋለሁ:: ኢትዮጵያ ብሄሮችን ፈጠረች እንጂ ብሄሮች ኢትዮጵያን አልሰሯትም:: ታድያ፣ ዜጋም ብሄርም ሆኖ ለመኖር ኢትዮጵያ ታስፈልጋለች:: ለማለምም ለመቃዠትም ኢትዮጵያ ታስፈልጋለች:: ኢትዮጵያ አማራጭ የሌላት ምርጫ ናት:: ስለተሰጠኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ::
አዲስ አበቤነት ይለምልም፤ 
ኢትዮጵያ ምን ጊዜም በክብር ትኑር::
Filed in: Amharic