>

አዲስ አበባ የእግር ኳስ ሜዳዎቿ በ "ባለ ጊዜ ነን" ባዮች ወደ እርሻ ማሳነት እየተቀየሩ ነው!!! (አበበ ለማ)

አዲስ አበባ የእግር ኳስ ሜዳዎቿ በ “ባለ ጊዜ ነን” ባዮች ወደ እርሻ ማሳነት እየተቀየሩ ነው!!!
አበበ ለማ
ከአሁን በኋላ የአዲስ አበባ ጓዳና ላይ የምታየው እንደድሮው በጀርባው ጆንያ ተሸከሞ “ቁሪያለው” የሚል የመርኬ ስራ ፈጣሪ ሳይሆን…በምትኩ ሞፈር፣  ቀንበር እና በሬዋቹን አቀናጅቶ የሚታረስ የእግርኳስ ሜዳ የሚያስስ ገበሬ ነው የምታየው።
ለምን? ብለህ ከጠየከኝ መልሴ ሂድና ታኬ ከንቲባውን ጠይቀው መልስ ካለው ያስረዳሃል…
ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የግንቦት 20 ዕለት ከኳስ ሜዳነት ወደ እርሻ ማሳ የተቀየረውን የቦሌ ክፍለከተማ የወረዳ 10 የእግርኳስ ሜዳን ማየት ከበቂ በላይ ነው።
በእዚህ ምስል ላይ የምታዩት የታረሰ ቦታ እንዲህ የተስተካከለ ያማረ የእግርኳስ መጫወቻ ስፍራ ከመሆኑ በፊት የጤና ጠንቅ የሆነ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ ነበር።
ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት ያአካባቢው ነዋሪዋቹ በመተባበር እና ፊርማቸውን በማሰባሰብ ወደ ወረዳ 10 ጽሕፈት ቤት በመሄድ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር ተነጋግረው ለአካባቢው ህጋዊ (Green Area) የመጫወቻ መስክ አድርገው አዘጋጅተውታል።
ለዚህም ተግባር የአካባቢው ነዋሪ ገንዘብ በማዋጣት እና ከዛም በላይ ፍቃደኛ የሆኑ ሁለት ነዋሪዋች የኮንስትራክሽን ማሽነሪዋች በማቅረብ ቆሻሻ መጣያ የነበረው ቦታ ለሕብረተሰቡ ጥሩ አገልግሎት እንዲሠጥ አስችለውታል።
ነገር ግን ትናንት ግንቦት 20 ቀን 2011 ዓ. ም.  ግን ይህ ሁሉ ነገር ታሪክ የሚያደርግ ድርጊት ተፈፀመ። ያ የእግርኳስ ሜዳ በአንዴ #በማን_አለብኝነት ወደ እርሻ ማሳነት ተቀየረ።
ከየት መጡ የማይባሉ ወጠምሻ ጎረምሶች አራት ጥማድ በሬዋቻቸውን (8 በሬዋች ማለት ነው) ጠምደው ወፍ ጭጭ ሳይል ግንቦት 20ን (ሥራ የሌለበትን ቀን) ሽፋን አድርገው በማለዳው ያርሱት ጀመር።
መንደርተኛው ለማነጋገር ቢሞክሩም ጆሮ የሚሰጡ ሰዎች አልነበሩም። የአራሽ “ገበሬዋቹን” አዛዥ ነኝ የምትል አንዲት ወይዘሮ ደግሞ “መሬቱ የኔ ነው ግብር እየገበርኩበት ነው” ብላ ሽንጦን ገትራ ቆማ አሁንም #በማን_አለብኝነት ስታሳርስ ዋለች።
በጉዳዩ የተደናገሩ የሠፈሩ ነዋሪዋች የህግ ከለላ ለማግኘት ወደ ክፍለ ከተማ እና ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት እርዳታ ቢጠይቁም… ባልገመቱተ መልኩ ወፍ የለም።
በዚሁ አካባቢ ከሳምንት በፊት የወረዳው ደንብ አስከባሪዋች መጥተው ጨለማን ተገን አድርገው የተቆረቆሩ አዳዲስ የጨረቃ ቤቶችን አፈራርሰው ነበር። ምናልባት የእርሻም ጉዳይ ያገባቸዋል በሚል ግምት የወረዳው ደንብ አስከባሪዋችንም ለማናገር ቢሞከር ከግንቦት 20 ጋር በተያያዘ ቢሮም ዝግ ስለነበር በወቅቱ እርዳታ “ሀይ” ባይ ባለስልጣን ማግኘት የሰማይ ያህል እሩቅ ሆነ።
አራሾቹም (ደሞ ጭብስ ብለው ጠትተው ነበር) በቀመቀሙት ካቲካላ ግፊት የቻሉትን ያህል ግማሽ የኳስሜዳውን አርሰው “ደሞ ሌላ ቀን እንመጣለን ብለው” ጀንበር ሳታዘቀዝቅ  በሬዋቻቸውን እየመሩ ወደ መጡበት ሄዱ።
ስለዚህ ዛሬ እዚህ ሰፈር የተጀመረው “የጨረቃ እርሻ” ነገ አብዮት አደባባይ ይገባኛል ባዮ በዝቶ “የአደባባይ ቅርሻ” የማይሆንበት ምክንያት የለም። በጊዜው “ሃይ” ሊባል ይገባል።
ነፍሴ ከእንግዲህ በሬ በጎዳና ላይ ስታይ ለፋሲካ ፆም መፍቻ ወደ ቄራ የሚጋዝ ሰንጋ እንዳይመስልህ… ምንአልባት በረንዳህን ሊዘራበት ያቀደ ታታሪ ነኝ ባይ የከተማ ገበሬ ሊሆን ይችላል።
Filed in: Amharic