>
5:16 pm - Wednesday May 23, 4057

እኛና ፖለቲከኞቻችን!!! (ኤፍሬም እንዳለ)

እኛና ፖለቲከኞቻችን!!!

ኤፍሬም እንዳለ
      

“‘ወተቱን በነጻ የምታገኝ ከሆነ ላም መግዛት ለምን ያስፈልግሀል!’ የሚሉት ነገር አለ፡፡ በባዶ ‘የአእምሮ ትጥቅ’ ፖለቲከኛ መሆን ከተቻለ፣ የምን ‘የትምህርት ፖሊሲ፣’ ‘የጤና ስትራቴጂ’ ብሎ ጭቅጭቅ ነው!–”


 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የፖለቲከኞቻችን፣ ወይም “ፖለቲከኞቻችሁ ነን…” የሚሉትን አብዛኞቹን ጠጋ ብላችሁ ስታዩዋቸው የሆነ ግርም የሚል ነገር አለላችሁ:: (የእኛ አገር ፖለቲካ በአብዛኛው የመስመር፣ የአማራጮችና የፖሊሲ ጉዳይ እንዳልሆን ልብ በሉልኝማ!)  ለምሳሌ…አሁንም ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት ከገባበት ‘የፖለቲካ ኮማ’ ውስጥ ያልወጣ ፖለቲከኛ አለላችሁ፡፡ አለ አይደል… “በሽልንግ ሦስት ፊልም የሚታይበት ሲኒማ አድዋ መፍረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው…” አይነት ‘አገር የሚነቀንቅ’ አጄንዳ የያዘ:: “የፓስታል ፉርኖ ዋጋ ከብር ከስሙኒ ከፍ እንዳይል እንሠራለን አይነት ‘ራዕይ’ ያለው ‘ሪቮሊዩሺነሪ!’
ኮሚክ እኮ ነው… ‘ሆረር ፊልም’ በሚመስል መልኩ ስለተወደደው ኑሮ ማውራቱ፣ የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረቡ ከፖለቲከኞቻችን አጣዳፊ አጄንዳዎች አንዱ ነው፡፡ ግን ደግሞ አሁንም በግ በአምስት ብር ተገዝቶ ቆዳው በአራት ብር ይሸጥበት ስለነበረው ዘመን ማውራት፣ ከ‘ኮማ’ ያለመውጣት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ነቅቶ እንኳን ያልተቻለው ፖለቲካችን፣ ያውም በዘመን ኮማ ውስጥ ሆኖ!
ደግሞላችሁ…‘አንጋች ፖለቲከኛ’ አለላችሁ፡፡ በቃ በዚህም ሆነ በዛ ‘ጊዜ የሰጠው ነው’ ያለው የፖለቲካ ቡድን መሪዎች ስር፣ ስር የማይጠፋ…በተለይ ከዘር ጋር የተያያዘ ሲሆን!  በተለይ አሁን፣ አሁን ‘አንጋች ፖለቲከኛ’ እየበዛ ነው የሚመስለው፡፡
እኔ የምለው …በተለይ ስልጣን አላቸው የሚባሉ ፖለቲከኞች ዙሪያ አለሁ፣ አለሁ ላይለቀን ነው! የተማረው በሉት፣ ‘አርቲስት’ የሚባለውን በሉት፣ ከሆነ እምነት ጋር የተያያዘውን በሉት፣ በ‘ሰፈር ልጅነት’ በሉት…ብቻ እንደምንም ብሎ ‘ከባድ ሚዛኖቹ’ ፖለቲከኞች አካባቢ ሆኖ፣ በቴሌቪዥን ካሜራዎች ውስጥ ለመግባት የሚደረገው እሽቅድድም ቀሺም ነው፡፡
ፖለቲከኛ ለመሆን ፖለቲካ ማወቅ ከማያስፈልግባቸው ሀገራት ስንተኞች ነን?
ደግሞላችሁ… የበቀቀን ተፈጥሯዊ መብትን የቀማ ፖለቲከኛ አለላችሁ፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… የበቀቀን ፖለቲከኛ መቼም ቢሆን  “የእኔ” የሚለው ሀሳብ የለውም፡፡  “በጉዳዩ ላይ እኔ በግሌ ያለኝ አስተያየት…” ብሎ ነገር አይሞክረውም፡፡ “እኔ ክቡር ሊቀመንበሩ ባሉት ላይ የምጨምረው የለኝም…” “ክቡር ሰብሳቢው ነገሩን በጥሩ ሁኔታ አስቀምጠውታል…” ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ‘የበቀቀኖች ተፈጥሯዊ መብቶች አስጠባቂ ድርጅት’ ምናምን የሚሉት ነገር የተቋቋመ ጊዜ፣ የፖለቲካ መንደራችን ጭር ይላል ብለን የማንፈራሳ!
ታዲያላችሁ…ማንም ነገሬ ብሎ አላየልንም እንጂ በፖለቲከኞች ድልደላ፣ ለዓለም የምናበረክተው መአት ነገር አለን እኮ! የምር.. ለምሳሌ ‘ድንኳን ሰባሪ’ ፖለቲከኛ፣ ከእኛ ሌላ ስንት አገር ይገኛል? ልክ ነዋ…የሰርግ ቤት ድንኳን ሰባሪ፣ የተጋቡት ማንና ማን ይሁኑ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሰርግ ቤት ማለት ምግብና መጠጥ አለ ማለት ነው፡፡ አለቀ፣ ደቀቀ፡፡ ሙሉ ልብሱን ግጥም አድርጎ ሰተት ነው፡፡ በፖለቲካ ደግሞ ነገሩ ሞቅ፣ ደመቅ ሲል፣ ወሬው በርከት ሲል፣ ስብሰባ በሽበሽ ሲሆን፣ ካሜራዎች ብልጭታ ሲያበዙ በቴሌቪዥን መታየት ማለት ነው፡፡
በቴሌቪዥን መታየት ማለት ደግሞ… አለ አይደል… የፖለቲካ ምግብና መጠጥ በሉት:: ታዲያ ይሄ ድንኳን ሰበራ ካልሆነ ምን ይሆናል! ለምሳሌ የሆነ ፖለቲካ ስብሰባ ላይ “ስለ ስብሰባው አካሄድ የበኩልዎትን አስተያየት ሊሰጡኝ ይችላሉ?” ብሎ የሚጠይቅና “የሆነን ሰው ብቻ ቀርጬ ወደ ቂማዬ ቶሎ በሄድኩ” የሚል ጋዜጠኛ ስለማይጠፋ እንደ ምንም ድንኳን መስበር ነው፡፡ ደግነቱ የሚያስጨንቅ ነገር የለም… “እርስዎ አባል የሆኑበት ድርጅት፣ የትምህርት ፖሊሲው ምን ይመስላል?” ምናምን ብሎ የሚያፋጥጥ ጋዜጠኛ የለማ!
“ወተቱን በነጻ የምታገኝ ከሆነ ላም መግዛት ለምን ያስፈልግሀል!” የሚሉት ነገር አለ፡፡ በባዶ ‘የአእምሮ ትጥቅ’ ፖለቲከኛ መሆን ከተቻለ፣ የምን ‘የትምህርት ፖሊሲ፣’ ‘የጤና ስትራቴጂ’ ብሎ ጭቅጭቅ ነው!
ፖለቲከኛ ለመሆን ፖለቲካ ማወቅ ከማያስፈልግባቸው ሀገራት ስንተኞች ነን?
እናላችሁ… ‘ኮቴ ቢስ’ ፖለቲከኛ ደግሞ አለላችሁ፡፡ የዛሬ ምናምን ወር እንትን በሚባል ‘ፓርቲ’ ስብሰባ ላይ ፊት ረድፍ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፡፡ ከዛላችሁ… ጥፍት ይላል፡፡ ይቆይና በየት አሳብሮ ይምጣ፣ በየት አየሁት የሚል ሳይኖር፣ ከሌላኛው የፖለቲካ ቡድን ጋር አሁንም ፊት ረድፍ ታገኙታላችሁ፡፡ የዓይናቸው ቀለም ደስ ስላለው ይሁን፣ ‘አካሄዳቸው’ ጭብጦ አያስቀማም ብሎ ስላሰበ ይሁን… መሄጃውን ሳታውቁት ‘ደርሶ’ ታገኙታላችሁ፡፡
የደፈጣ ፖለቲከኛም አለላችሁ፡፡ .ብቻ የሆነ ስፍራ ያደፍጥና፣ ወከባ ከሆነ ጎመና በጤና ብሎ ይሸሸጋል፤ ነገሩ ደግሞ የማያሰጋ ከሆነ፣ ቼ ጉቬራን የሚያስንቅ ታጋይ ይሆናል፡፡ ከዛ ነገሮች ሲጠይሙ ወደ ዋሻው ይመለሳል፡፡
እናላችሁ… ፖለቲካችን “ስማ ደብሮኛል፣ ለምን ፖለቲካ ፓርቲ ምናምን ገብተን ጊዜያችንን አናሳልፍም!” አይነት ስለሆነ ሰተት ብሎ መግባት፣ ሰተት ብሎ መውጣት ችግር የለውም፡፡
ደግሞላችሁ የችርቻሮ ፖለቲከኛ አለላችሁ:: ፖለቲካው ለእሱ የትርፍና ኪሳራ ጉዳይ ነው፡፡  የበዓል ሰሞንን መምጣት እየጠበቁ ዋጋ እንደሚጨምሩ ነጋዴዎች፣ አጠቃላይ የፖለቲካውን ነፋስ አቅጣጫ አይተው የፖለቲካ ቡድን የሚለዋውጡ አሉ፡፡
የምር ግን እኮ ኮሚክ ነው፡፡ ‘እፍረት’ ‘ይሉኝታ’ ምናምን የሚባሉ ‘ኋላ ቀር’ ነገሮች የሉም፤ “ሰው ምን ይለኛል” ብሎ ነገር የለ…  ትናንት “አፈር አይንካህ” ያለውን ነገ ደግሞ “አፈር ብላ” ለማለት ምንም አይነት ‘የሀሳብ ልዩነት’፣ ‘የመስመር ልዩነት’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር የለም፡፡ ለነገሩ ልዩነት የሚኖረውም እኮ መጀመሪያ ላይ ‘ሀሳብ’ ሲኖር አይደል! ለፖለቲከኝነት ፖለቲካ ማወቅ አያስፈልግማ! ስሙኝማ…እግረ መንገድ ትዝ ብሎኝ ነው…መቼም እንደ ዘንድሮ ኮሚቴ በኮሚቴ የሆንበት ጊዜ የለም፡፡ (“ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ” ያልከው ወዳጃችን ማንን ለማነካካት ነው!) እናላችሁ… የሆነ ኮሚቴ አቋቁሞ ሊቀመንበር መሆን ነው፡፡ “አንድ ሰሞን ጭብጨባ ያማረው፣
ሰልፍ ያማረው… በቦሌ ኤርፖርት እቅፍ አበባ  ያማረው…ወጥቶ ይምጣ…” የምትል ፌዝ ቢጤ ነበረች፡፡ (እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አሁን፣ አሁን እሱ ነገር በቃ መሰለኝ:: ገብተው ጨረሱ እንዴ?! “መግባት ብቻ! ጭራሽ እነሱ ትተው የመጡትን ክፍት ቦታ እኛ ሄደን እንድንሞላው እየገፉን አይደል እንዴ!” ለማለት ጊዜው ሲደርስ ቀድሞ ‘ኢንፎርሜሽን’ የሚደርሳችሁ ሹክ በሉንማ!)
ደግሞላችሁ…“ጭር ሲል አልወድም…” ፖለቲከኛ አለላችሁ፡፡ ከአራቱ የሂሳብ መደቦች ካለማባዛት ሌሎቹን የተማረ አይመስልም:: የሆነች ስንጥቅ የመሰለች ነገር ከታየች…አለ አይደል…“ተመልከቱ፣ ጠቅላላ ደረመሱት እኮ!” የሚል፡፡
ደግሞላችሁ… መቼ ይሰጥ፣ መቼ አይሰጥ እንደማይታወቅ የመንግስት መስሪያ ቤት እርከን አይነት ፖለቲከኛ አለላችሁ፡፡ ለዓመታት የት ይግባ፣ የት ይውጣ ሳይታወቅ፣ ድንገት አየሩ ፖለቲካ፣ ፖለቲካ መሽተት ሲጀምር ስብሰባ አዳራሽ ፊት ረድፍ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ አሀ… እኛ እኮ ማንነቱ  ጠፍቶናል፡፡
እናላችሁ… ደሞዝ ስንቀበል፣ ከወር ሀያ ዘጠኝ ቀን “የት አለህ?” ብሎ የማይጠይቅ ሰው፣ የልደታ እለት ከየትም ፈልጎ እንደሚያገኝ ጓደኛ፣ እነሱም የሆነ አየሩ ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ሲሸት ብቅ ይላሉ…(ጎበዝ! በ‘ፖለቲካችን’ እኮ ‘ተንቀናል፣ ተደፍረናል፤ ብታምኑም ባታምኑም ኳስ አድረገውናል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
የራሳችንን ጠንካራ ጎን ከማሳየት ይልቅ ሌላውን ለማሳነስ፣ ሌላውን ለማሳጣት፣ ሌላውን ለማሸማቀቅ እንቅልፍ የምናጣ የበዛንበት ዘመን ነው፡፡ “ደግ ነገር ተናገርኩ…” ብላችሁ ሳታበቁ፣ የተናገራችሁትን ሠላሳ ሦስት ቦታ የሚበልት፣ በጸጉር ልክ የሆነበት አስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡
ፖለቲከኛ ለመሆን ፖለቲካ ማወቅ ከማያስፈልግባቸው ሀገራት ስንተኞች ነን?
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Filed in: Amharic