>
11:23 am - Wednesday November 30, 2022

ደመቀ በእነዚያ ቀናት…. (ውብሸት ሙላት)

ደመቀ በእነዚያ ቀናት….
ውብሸት ሙላት
ሐምሌ 5 ዙራ ደረሰች፡፡ መቼም የኮሌኔል ደመቀ ዘዉዱን ነገር ሳስብ የሆሊዉድ የፊልም ባለሙያዎች ኢትዮጵያዉያን ቢሆኑ ኖሮ የዓመቱ ቁጥር አንድ ፊልም ይሠሩበት እንደነበር አልጠራጠርም፡፡ ደግሞ ብዙም ፈጠራ አያስፈልገዉም፤ ፈጠራ ከተጨመረበት በጭራሽ የማይሆን እና የማይታመን adventure ይሆናልና፡፡
የቹቹ አለባቸዉን “ዳገት የበረታዉ የአማራዉ ፍኖት” የሚለዉን መጽሐፍ ሳነብ በወቅቱ ጎንደር የነበሩ የነበሩ ወዳጆቼም፣ ኮሌኔል ደመቀም፣ መቶ አለቃ ደጀኔ ማሩም ካጫወቱኝ በላይ ነዉ ነገሩ፡፡ ትህትና ይዟቸዉ መሰለኝ ብዙዉን ጉዳይ የቀናነሱት፡፡
አስኪ በቹቹ መጽሐፍ ላይ ተመርኩዤ ከሐምሌ 4 ከሌሊቱ 10፡10 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 6 ቀን ከቀኑ 8፡30 ድረስ በነበሩት ወደ 35 ሰዓታት ገደመ ኮሌኔል ደመቀ የፈጸማቸዉን ጀብዱ በአጭሩ ልዘርዝራቸዉ፡፡
ከሁመራ ተነስቶ ጎንደር የገበዉ አፋኝ ቡድን  ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም.  ሌሊት ላይ እስከ 10፡00 ሰዓት የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት መካከል አታላይ ዛፌን፣ጌታቸዉ አደመን፣አለነ ሻማን እና መብራቱ ጌታሁንን በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡ የመጨረሻዉ ተልእኮ ወደ ኮሌኔል ደመቀ ነዉና ወደ እሱ ቤት ተጓዙ አፋኝ ቡድኑ!
ኮሌኔል ደመቀን መጨረሻ ላይ ለመያዝ የታቀደዉ፣ እጁን እንደማይሰጥ ስለሚያዉቁ ገድለዉም ቢሆን አስከሬኑን ሁመራ ይዘዉ ለመሄድ ትእዛዝ ስለተሰጣቸዉ ነዉ፡፡ በማናቸዉም ሁኔታ አስከሬኑን ሳይዙ መሄድ እንደሌለባቸዉ ቁርጥ ዉሳኔ ተላልፏል፡፡
አፋኝ ቡድኑ ከኮሌኔል ደመቀ ቤት ሌሊት 10፡10 ደረሰ፡፡ “ቤትህን ክፈት” ሲሉት “በሌሊት ምን አስመጣችሁ ጧት ኑ፡፡” አልበለዚያ አልከፍትም አለ፡፡ ከዚያ በሃይል ለመክፈት ተሞከረ፤ ቀጥሎም ጠኩስ ተከፈተ፡፡
ቤት ዉስጥ ሦስት ልጆቹና ባልተቤቱ አሉ፡፡
ልጆቹና ባልተቤቱ ሻወር ቤት ተቀመጡ፡፡ ወደ ኬሌኔል ደመቀ ጥይት ይተኮሳል፡፡ እሱም አልፎ አልፎ ነገር ግን አልሞ ይተኩሳል፡፡
ባልተቤቱ ከሻወር ቤት ብቅ እያለች ኮሌኔሉ በሕይወት መኖሩን አረጋግጣ ለልጆቿ ትናገራለች፡፡  (በባልተቤቱ ቦታ ሆናችሁ አስቡት፡፡ ልጆቿን ምን እንደምትል ጨምሩበት!)
የአፋኝ ቡድኑን መሪ ኮማንደር ሐለፎምን ጨምሮ ብዙዎቹ አፋኞች እያለቁ ስለሄዱ የመገናኛ ሬዲዮ የያዘዉ ወታደር ኮማንዶ ይላክልኝ እያለ ይናገራል፡፡ ኮሌኔል ደመቀ ይሰማል፡፡ ኮማንዶ ከየት ይመጣል አሁን ቤቱ በአዳፍኔ እንዲመታ በሬዲዮ ለሚያወራዉ ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ ወተዳ እንዴት አደርጌ፣ሕጻናት አሉ ይላል፡፡ ዝም ብለህ በለዉ ይባላል፡፡ ይህንን ሁሉ የሬዲዮ ንግግር ኮሌኔል ደመቀ በቤቱ ግድግዳ ተጠግቶ ይሰማል፡፡ ከዚያ የመከለላከያ ሠራዊት ተጨመረ፡፡
ኮሌኔል ደመቀ ለቁርጥ ቀን ጓዱ ለደጀኔ ማሩ ስልክ ደዉሎ ታፍኛለሁ ድረስልኝ ይለዋል፡፡ ይሄ ሰኞ ጧት ከ3 እስከ 4 ሰዓት ባለዉ መካከል ነዉ፡፡  ደጀኔ ማሩ ያለዉ አርማጨሆ፣ ሰሮቃ ነዉ፡፡ ከቀኑ 5 ሰዓት የራሱን ታጣቂዎች ይዞ ለአርማጨሆ ሰዉ እየነገረ ማታ 12 ሰዓት ጎንደር ገባ፡፡
እስከዚህ ሰዓት፣ አልፎ አልፎ በረድ እያለ፣አልፎ አልፎ ደግሞ ኮሌኔሉ ጋር እየተዋጉ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል የክልሉ ልዩ ሃይልና መደበኛ ፖሊስ በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊቱና የፌደራል ፖሊስ እንደተፈጠጡ የደጀኔ ማሩ ጦር በቀሃ ወንዝ በኩል ከተፍ ብሎ የሚገደለዉን ገድሎ የሚማረከዉን ማርኮ የኮሌኔሉን ቤት ከመከላከያ ሠራዊቱና ከፌደራል ፖሊስ ነጻ አወጣዉ፡፡  መንግሥት ባመነዉ መሠረት 19፣ በሌሎች መረጃዎች መሠረት ግን ወደ 40 ፖሊስና ወታደር ሞቷል፡፡
ከዚያም መንግሥትና እነ ደጀኔ ማሩ የምርኮኛ ልዉዉጥ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ እንደ ቹቹ መረጃ፣ ከአርመጨሆ የመጣዉ ሰዉ (አብዝሃኛዉ የታጠቀ)  ከ800 እስከ 1000 ይደርሳል፡፡ ይሄ ማክሰኞም ጭምር የገባዉ ነዉ፡፡  ከብዙ ድርድር በኋላ መከላከያ ሠራዊቱ ምርኮኛ ልዉውጥ ለማድረግ ተስማሙ፡፡ መንግሥት 11 ምርኮኛ መለሰ፡፡ ትጥቃቸዉን ግን አስፈትተዉ ስለነበረ ደጀኔ ማሩ ትጥቃቸዉን ካላመጣችሁ በእኔ ስር ያሉትን ምርኮኛ ብዛትም አልናገርም፣አልመልስምም ብሎ እምቢ አለ፡፡ ከዚያ ትጥቃቸዉን አመጡ፡፡ መጨረሻ በእነ ደጀኔ ሥር ያሉ ምርኮኞች ተመለሱ፡፡ የደጀኔ ምርኮኛ ግን አንድ የቆሰለ እና በሕክምና ላይ የነበረ ወታደር ብቻ ነበር፡፡
ደጀኔና ደመቀም ተገናኙ፡፡ ኋላም ወደ ከንቲባዉ አቶ ተቀባ ቢሮ ከሽማግሌዎች ጋር ሆነዉ ይዘዉት ሄዱ፡፡
አቶ ተቀባ ቢሮ ከሄዱ በኋላ እነ ደጀኔ ማሩና ጎቤ መልኬ፣ ኮሌኔል ደመቀን አርማጨሆ ይዘን እንሄዳለን አሉ፡፡ ከብዙ ልመናና ድርድር በኋላ  ኮሌኔል ደመቀ ጎንደር ቀረ፡፡
ለዚህ ዓመቷ ሐምሌ 5 ፊልሙ ሊደርስ አይችልም፡፡ ለአምስተኛ ዓመቱ ግን የኮሌኔል ደመቀ ጀብድ ከሐምሌ 4 ሌሊት ጀምሮ እስከ ሐምሌ 6 ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ ያለዉ ብቻዉን አስደማሚ ፊልም ይሆናል፡፡ መሠራትም አለበት፡፡ ማንም ሰዉ ሊያዉቀው የሚገባ በተለይ ደግሞ እያንዳንዱ አማራ ይቺን ሁነት በደንብ ሊገነዘባት ይገባል፡፡
ዝርዝር ታሪኩን ከቹቹ መጽሐፍ አንብቡት!
Filed in: Amharic