>

"ኢህአዴግ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን  ለመሸጥ የሚያስችል የህዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ የለውም!!!"   (አብን)

ኢህአዴግ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን  ለመሸጥ የሚያስችል የህዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ የለውም!!!”
አብን
ስለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች  መግለጫ የሰጠው አብን  ውሳኔው ከኢኮኖሚያዊ አዋጭነት አንጻርም ተቀባይነት የሌለው ነው ያለ ሲሆን የኢትዮ ቴሌኮምን ሽያጭ በተመለከተ ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ እና ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ ውሳኔውም ብሏል።
ሙሉ መግለጫው ከዚህ በታች ቀርቧል።
 
 ሀገር የማዳን ጥሪ!
**
ሀገራችን ኢትዮጵያ 4ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ከጥቂት ወራት በኋላ ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል።
ላለፉት 28 አመታት በስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ በስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን ሲመራበት የነበረውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በድንገት በመቀየር ለበርካታ አስርት ዓመታት በመንግስት ባለቤትነት እና ይዞታ ስር የቆዩ ስትራቴጅክ ሀገራዊ ሀብቶቻችንን ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ ውሳኔ አሳልፏል።
ኢህአዴግ ስልጣን የያዘው እና በስልጣን ላይ የቆየው በህዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ እንዳልሆነ ቢታወቅም ከእነጉድለቱም ቢሆን የራሴ የሚለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርጾ ስራ ላይ በማዋል፣ ተለይቶ በሚታወቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሀገር ሲያስተዳድር መቆየቱ የሚታመን ነው። ኢህአዴግ ሲመራበት የቆየበት ዋነኛው የኢኮኖሚ ፖሊሲ “ልማታዊ መንግስት” በሚል ፍልስፍና የሚታወቀው እና ስልታዊ እና ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ዋና ዋና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በመንግስት ይዞታ ስር ማቆየት የሚል የነበር ሲሆን በቅርቡ ወደ ስልጣን በመጡት ሊቀመንበሩ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር አማካኝነት ስር ነቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ በማድረግ በመንግስት ባለቤትነት እና ይዞታ ስር የሚገኙ ግዙፍ የኢኮኖሚ ዘዋሪ ድርጅቶችን ለውጭ ባለሀብቶች ለመሸጥ እና ድርጅቶችን ወደ ውጭ የግል ባለሃብቶች ለማዛወር መወሰኑን ለህዝብ በማሳወቅ ድርጅቶቹን ለመሸጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል።
በመሰረቱ አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ ፓርቲ በድንገት ለዚያውም በምርጫ ዋዜማ ላይ ሀገር የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመሰረቱ ለመለወጥ የሚያስችል ህጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ የስልጣን መሰረት የለውም። ኢህአዴግ የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ ስልጣን እንዳልያዘ ቢታወቅም፣ ስልጣን የያዘው በህዝብ ይሁንታ እና በምርጫ አሸንፎ ነው ቢባል እንኳ ገዥው ፓርቲ ሀገር የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመቀየር የሚችለው አዲስ ምርጫ ሲደረግ እና አዲሱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምርጫ ውድድር አቅርቦ የህዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ ሲያገኝ ብቻ ነው። ኢህአዴግ ምንም አይነት የህዝብ ይሁንታ እና ፈቃድ ሳያገኝ፣ ይልቁንም በህግ አግባብ የስልጣን ዘመኑ በሚጠናቀቅበት ዋዜማ ላይ ሆኖ ስር ነቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ላለፉት 100 እና 75 አመታት በመንግስት ይዞታ ስር የቆዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ መወሰኑ የህግ፣ የሞራል እና የፖለቲካ ቅቡልነት (Legitimacy) የሌለው ውሳኔ ነው።
ሙስና እና ብልሹ አሰራር ዋነኛ መገለጫው የሆነው ኢህአዴግ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው በማታውቅ ከፍተኛ የውጭ መንግስታት እዳ /Sovereign Debt/ ውስጥ እንድትዘፈቅ አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ በብድር የተገኝውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያለምንም ተጠያቂነት ከአባከነ እና የግንባሩ አባል ድርጅቶች በህገወጥ መንገድ ለሚነግዱባቸው የፓርቲ የንግድ ድርጅቶች ገንዘቡን ካሸሸ በኋላ ተከታታይ ትውልዶች ተቸግረው ያቆዩንን ሀገራዊ ሀብቶቻችንን እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ የሆነውን አየር መንገዳችንን ለውጭ ባለሀብቶች ለመሸጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ ፓርቲው ለሌላ ዙር ዝርፊያ ራሱን እያዘጋጀ  እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ ውሳኔ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ከሀገር የተዘረፈ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር መኖሩን፣ የተዘረፈው ገንዘብ ተደብቆ የሚገኝባቸው ሀገራት ተለይተው እንደሚታወቁ እና ሀገራቱ ገንዘቡን ተመላሽ ለማድረግ ለትብብር ፈቃደኛ እንደሆኑ ገልጸው መንግስታቸው የተዘረፈውን ገንዘብ እንደሚያስመልስ ቃል ቢገቡም አንድ ሽራፊ ሳንቲም ወደ መንግስት ካዝና ሳይመለስ የኢትዮጵያውን አንጡራ ሀብት የሆኑትን የንግድ ድርጅቶችን እና ብቸኛው ወደባችን እና የሉዓላዊነታችን መገለጫ የሆነውን አየር መንገዳችንን በመሸጥ ፓርቲያቸው እና መንግስታቸው ለሌላ ዙር መንግስታዊ ዝርፊያ እየተዘጋጀ ይገኛል። ለግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እና ለመሰረታዊ ማህበራዊ ልማቶች በከፍተኛ ወለድ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ከውጭ መንግስታት ተበድሮ (ዕዳችን ካጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 60% ይሸፍናል)፣ ገንዘቡን በማባከን ሀገራችንን ለብድር አዙሪት የዳረገ ፓርቲ እና መንግስት፣ የሀገር አንጡራ ሀብት የሆኑ ድርጅቶቻችንን ከሙስና እና ብልሹ አሰራር በጸዳ ሁኔታ ለውጭ የግል ባልሀብት ለማስተላለፍም ሆነ ከሽያጩ የሚገኝውን በቢሊየን የሚቆጥር ዶላር በኃላፊነት ይገለገልበታል ተብሎ አይታመንም።
                           ክፍል ፪
ፓርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ኢህአዴግ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለመሸጥ ያሳለፈውን ውሳኔ በዋነኛነት የሚቃወመው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ድርጅቶችን ለመሸጥ የሚያስችል የህዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ /political legitimacy/ ስሌለው ቢሆንም አብን የመንግስት ውሳኔን ከኢኮኖሚ አዋጭነት አንጻር በመተንተን፦
የኢትዮ ቴሌኮምን ሽያጭ በተመለከተ ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ እና ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ ውሳኔ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽያጭን በተመለከተ ግን ውሳኔው ከስግብግብነት ውጭ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ አመክንዮ የሌለው መሆኑን አረጋግጧል።
በመንግስት ባለቤትነት እና ይዞታ ስር ያሉ በተለይም በሕግ በብቸኝነት የመነገድ እና አገልግሎት የመስጠት መብት /Monopoly Rights/ የተሰጣቸው ግዙፍ የንግድ ተቋማት ከመሸጣቸው እና ወደ ግል ባሀብቱ ይዞታ ከመዞራቸው በፊት በቅድሚያ ድርጅቶቹ የተሰማሩበትን ዘርፍ ለውድድር ክፍት የማድረግ /Liberalization/ ስራ ሊሰራ ጠንካራ ተፎካካሪ አገልግሎት ሰጭ የንግድ ተቋማት ሊገነቡ እና ዘርፉን የማተስተዳር እና የመምራት ጠንካራ አቅም /Regulatory Framework and Capacity/ ሊገነባ እንደሚገነባ ፓርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ያምናል፡፡ No Privatization before Liberalization!
፩.  ኢትዮ ቴሌኮም በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ100 መቶ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠ ብሐራዊ ሀብት ሲሆን ተቋሙ አሁን ዓለም ከደረሰበት የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት እና ደረጃ አንጻር ብዙ እጥረቶች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ ዘርፉ ሊዘምን እና ለግል ባለሀብቱ ውድድር ክፍት ሊሆን እንደሚገባው ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ነገር ግን ዘርፉን የማስተዳደር እና የመምራት ጠንካራ አቅም (Regulatory Framework and Capacity) ሳይፈጠር እና ዘርፉ ለውድድር ክፍት (Liberalization) ሳይደረግ፣ በብቸኝነት ለመነገድ እና አገልግሎት ለመስጠት በህግ ከለላ የተሰጠውን ተቋም በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደግል ሀብት ይዞታ ለማዞር መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ፣ ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ እና ህዝባችንን ለከፍተኛ ብዝበዛ የሚያጋላጥ ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ በመሆኑ ውሳኔው ሊቀለበስ የሚገባው ነው፡፡
፪. መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመሸጥ ያሳለፈው ውሳኔ ፍጹም ሃላፊነት የጎደለው እና በየትኛውም የኢኮኖሚ ትንታኔ ስሜት የማይሰጥ ውሳኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስራ ላይ በቆየባቸው ላለፉት 75 አመታት አንድም ጊዜ የመክሰር እና የመፍረስ አደጋ ያላገጠመው ለኢትዮጵያውን ኩራት፣ ለአፍሪቃውያን ደግሞ በአለም መድረክ ላይ በሚደረግ የንግድ ውድድር አፍሪቃውን ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ ያነቃቃ እና የይቻላልን መንፈስ በአፍሪቃውያን ላይ ያሳደረ ብሄራዊ ሀብታችን ብቻ ሳይሆን ህያው ቅርሳችን ጭምር ነው፡፡ አየር መንገዱ አሁን ባለው ወቅታዊ አቋሙ ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ ብዙ ቅሬታዎች የሚነሱበት ቢሆንም ባለው ውጤታማነት እና ትራፋማነት ከአህጉራችን አፍሪቃ ቀዳሚው አየር መንገድ ሲሆን በዓለም ከሚገኙ ትርፋማ እና ምርጥ አየር መንገዶች አንዱ ነው፡፡ እውቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በጥናታቸው እንዳረጋገጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደግል ባሀብቱ ለማዞር የሚያበቃ ምንም አይነት ስሜት የሚሰጥ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ ከ2013/14 እስከ 2015/16 ባለው ጊዜ ውስጥ ባማካኝ ከ8% በላይ የትርፍ ህዳግ ያስመዘገበ ሲሆን አለም ላይ አሉ ከሚባሉ ሰባት የአሜሪካ አየር መንገዶች ካስመዘገቡት 4.9% የትርፍ ህዳግ በእጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ አየር መንገዱ በአንድ መንገደኛ የሚያስገኝው የዶላር መጠንም የአውሮፓ እና የአሜሪካ አየር መንገዶች ከሚያስገኙት የዶላር መጠን የሚበልጥ ነው፡፡ የአየር መንገዳችን ዕዳ ከአየር መንገዱ ጠቅላላ ሀብት በእጅጉ የሚያንስ በመሆኑ አየር መንገዱን ለመሸጥ የሚያስገድድ አይደለም፡፡ አየር መንገዳችን ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር በኢህአዲግ የተለመደ የሀገር ጥቅምን አሳልፎ የመስጠት ፖለቲካዊ ባህል ምክንያት ወደብ አልባ ለሆነችው ሀገራችን ብቸኛ ወደብ ሆኖ ከመላው ዓለም ጋር የምንገናኝነበት ነጻ በራችን በመሆኑ ለሉዓላዊነታችን እና ብሔራዊ ጥቅማችን  መከበር የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የኢህአዴግን ያለፉት አመታት የሙስና እና የሀብት ብክነት የገነገነ ልማድ ልብ ላለ፣ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ የሚገኝውን በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚባክን ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ሽያጩ ጊዚያዊ የዶላር እጥረታችንን ይቀርፋል ቢባል እንኳ ገዥዎቹ ከሚገዟቸው ድርጅቶች የሚያገኙትን ዓመታዊ ትርፍ በየዓመቱ በውጭ ምንዛሬ የሚወስዱ በመሆኑ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ውስጥ የዶላር እጥረቱን የበለጠ የሚያባብስ ውሳኔ ነው፡፡
ኢህአዴግ በምርጫ ዋዜማ ላይ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ውሳኔ ቢወስንም ውሳኔውን የሚተችም ሆነ ውሳኔውን ለማስቆም ጥረት የሚያደርግ አንድም የተደራጀ የፖለቲካ ሀይል ባለመኖሩ አደጋውን የመቀልበስ ኃላፊነት በፓርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ትከሻ ላይ ወድቋል።
                             ክፍል ፫
በመሆኑም፦ 
ሀ) የሚቀጥለው ምርጫ ተደርጎ በህዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ የቆመ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ኢህአዴግ የህዝብ ይሁንታን እና ፈቃድ ከሚጠይቁ ስር ነቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥና ውሳኔዎች እንዲታቀብ እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለውጭ የግል ባለሃብቶች ለመሸጥ እና ለማስተላለፍ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲሰርዝ ፓርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ለ) ኢህአዴግ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለውጭ ባለሀብቶች ለመሸጥ ያሳለፈው ውሳኔ፣ መላ ኢትዮጵያውንን በቋንቋ፣ በብሔር እና በሀይማኖት ሳይለይ የሚጎዳ፣ የሁላችንም ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ ለቅርጫ ያቀረበ እና በገዛ ሀገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንቆጠርበትን ሁኔታ የሚፈጥር ውሳኔ በመሆኑ መላው የሀገራችን ህዝብ ውሳኔውን እንዲያወግዝ እና እንዲቃወመው ፓርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ጥሪውን ያስተላለፋል፡፡
ሐ) መንግስት ውሳኔውን እስኪቀለብስ ድረስ ፓርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ እና ትግላችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እያስታወቅን፣ በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት በምናደርገው ትግል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግላችን አጋር እንዲሆን አብን ጥሪውን ያስተላለፋል፡፡
ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ
Filed in: Amharic