>
1:12 am - Thursday December 1, 2022

የወያኔን ‹መንግሥት› የምናምንበት ምን ምክንያት አለ? (ከይኄይስ እውነቱ)

የወያኔን ‹መንግሥት› የምናምንበት ምን ምክንያት አለ?

ከይኄይስ እውነቱ

ከዚህ በታች የተመለከተው አስተያየት የተጻፈው ሰሞኑን በተፈጠረው ‹‹ድንገት›› ምክንያት የወያኔ አገዛዝ እንደ ልማዱ በኢንተርኔትና በኤሌክትሪክ አፈና ባደረገ ማግስት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ወያኔ ለመሆኑ አብዛኛውን የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ የቀድሞው በሕወሓት የአሁኑ ደግሞ በኦነጋውያን ኦሕዴድ የሚመራው፡፡ ስልቻ ቀልቀሎ እንደማለት፡፡ የምናወራው ስለ ድርጅትና ሥርዓት በመሆኑ ጥያቄው የግለሰብ አመራር ለውጥን ወይም ምን እየሠራ ነው የሚለው አይደለም፡፡ በውስብስብ ችግሮች የተተበተበው የኢትዮጵያ ፖለቲካና ማኅበረ ኢኮኖሚ የአንድ የዐቢይ ጉዳይ እንዳልሆነና በሱም እንደማይፈታ አሁን ላይ አብዛኛው ሕዝብ የተገነዘበ ይመስለኛል፡፡ እሱም ‹የመኪናውን› መሪ የጨበጠ ቢመስልም ወዴት እንደሚሄድ ግራ ተጋብቶ ግራ እያጋባን፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር አቅቶት አገራችን የወንበዶች ዋሻ መሆኗ፣ በጊዜያዊውና በዘለቄታው÷በጭፍጫፊና አንኳር ጉዳዮች መካከል ቅደም ተከተሉ ተምታቶበት ወይም ሆን ብሎ በመባከን፣ ምክርም አሻፈረኝ ብሎ ወይም ሁነኛ መካሪ አጥቶ በመንደሩ ሰዎችና በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ዥዋዥዌ መጫወት ከጀመረ ከራርሟል፡፡ በሁለት ልብ የሚያነክስ አንዳች የሚያገኝ አይምሰለው እንዳለ ርእሰ መጻሕፍቱ፡፡

በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ ለሦስት ዐሥርት በጉልበት የዘለቀው ወያኔ አቋሙም፣ መዋቅሩም፣ አስተሳሰቡም ወዘተ እንዳለ ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታም የሕዝብ ሳይሆን የድርጅቱ ፈቃድ ሲፈጸም፣ ‹ክልል› በተባለው ጎጥም የወያኔ ጐሣ መሣፍንቶች እስከ ወንጀላቸው ያለማንም ጠያቂ ሲንቧቹበት ነው፡፡ ዐቢይ የሚንደፋደፈው ይህንን በወንጀል የተጨማለቀ፣ አገርና ሕዝብን ይቅር ለማይባል ጥፋት የዳረገ የድኩማኖች ስብስብ እስከ ‹ሕገ አራዊቱ›፣ የይስሙላ ጐሣ ፌዴራሊዝሙ (በጐሣውም መስፈርት እንኳን ትክክል ባለመሆኑ)፣ እንደ ከብት ጋጣ ከሠራው የ‹ክልል› መዋቅር ጋር ለመጠጋገን እንጂ ለሥርዓት ለውጥ መሆኑን የሚያሳይ አንዳችም ምልክት የለም፡፡ ይህ ጠንቀኛ ድርጅት እስካለና በመንደርተኞች ተከቦ እንዲህ ዓይነቱን መሠረታዊ ለውጥ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ በዚህ ሁናቴ ምርጫ ለማድረግ ማሰብ ውጤቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

እንደ ሰሞኑ ዓይነት ‹ድንገት› በድርጅታቸው ውስጥ ሲከሠት ጉዳዩን የሕዝብ ለማድረግ ሲደክሙ መታየትም የተለመደ የድርጅቱ አሠራር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ድርጅት ጋር ምንም ኅብረት የለውም፡፡ ኢንተርኔት፣ መብራት ዘግተው ለራሳቸው ጥቅም ከተቆጣጠሩትና በሕዝብ ገንዘብ ከሚንቀሳቀሰው ‹መንግሥታዊ› ብዙኀን መገናኛ ብቻ የአንድ ወገን ወሬ ስሙ ይሉናል፡፡ የ‹‹ለውጡ›› ግንባር ቀደም መሪ ከተባለ ባለሥልጣን አይደለም እንዴ የመከላከያ ሠራዊቱ ከዘር ከጐሣ አመለካከት የፀዳና ኢትዮጵያዊ አቋም እንዳለው በሚያስተዛዝብ መልኩ የተነገረው? ከምልመላው እስከ ተግባር ስምሪቱ መከላከያው፣ የፖሊስ ኃይሉና የፀጥታው መ/ቤት መሠረቱ ጐሣ አይደለም እንዴ? በሁሉም የመንግሥት መዋቅርና ተቋማት የጐሣ ተዋጽኦ ማመጣን የሚለው አንድምታው ምንድን ነው? እነዚህ ተቋማት በወያኔ አገዛዝ ከወገንተኝነት ነፃ የሆኑት መቼ ነው? ለአገር አንድነትና ለግዛት ሉዐላዊነት ሕዝብ በአለኝታነት የሚመካባቸውና የሚኮራባቸው ሳይሆኑ ለሕይወቱ፣ ለነፃነቱና ለንብረቱ እንደ ሥጋት የሚያያቸው አይደሉም እንዴ? ይህማ ባይሆን መንግሥት የሌለ እስኪመስል አገር በሥርዓተ አልበኝነት መረን ባልወጣች ነበር፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛው ኀላፊነት የማይሰማቸው፣ ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው፣ በሞራልም በሥነምግባርም የዘቀጡ፣ የሐሰትና የተዛባ መረጃ የሚያሠራጩ፣ አንዳንዶቹም አፍራሽ ወሬ መንዛቱን በተደራጀ መልኩ ዓላማዬ ብለው የሚሠሩ እንዳሉ ዛሬ አብዛኛው ተጠቃሚ ያውቀዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ቅጥፈት የጀመሩትም ሆነ ያስፋፉት በሚሠፈርላቸው ድርጎ የሚተዳደሩ ወያኔዎችና ተረፈ-ወያኔዎች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ (ዛሬም በመንግሥትነት የተሰየመው አካል ለሽብርተኞች ኦነጋውያን ድርጎ እየሠፈረ አይደለም? በሆቴል አስቀምጦና ጠባቂ መድቦ)

ይህ የኢንተርኔት አገልግሎት የመዝጋቱ ጉዳይ ለጊዜው ካልሆነ መፍትሄ እንደማይሆን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ዓላማውስ እውነት ለሕዝብና ላገር ደኅንነት ነው? እውነትን ፍለጋ ነው? የመንግሥት ብዙኃን መገናኛውስ እውነተኛ መረጃ በመስጠትም ሆነ ኃላፊነት የተሞላበት መረጃ በማቀበል ረገድ ከማኅበራዊ ሜዲያው ልዩነት አለው? መልሱን ለአንባብያን እተወዋለሁ፡፡ ለመሆኑ የኢንተርኔት በዚህም በኩል የማኅበራዊው ሜዲያ ተደራሽነት ለምን ያህሉ ኢትዮጵያዊ ነው? መሠረታዊ አገልግሎቶችን መዝጋት ልማድ ያደረገ አገዛዝ አፋኝነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች በተለይም የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎቶችን ማቋረጡ ላለፉት 20 ዓመታት የወያኔ አገዛዝ መለያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡ አነስተኛ ሽፋን ያለውም ኢንተርኔት እንዲሁ፡፡ በሰበብ አስባቡ ሲዘጋ ተስተውሏል፡፡ ባጭሩ አገዛዙ እነዚህንና መሰል አገልግሎቶችን ለራሱ ተልካሻ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሲያደርጋቸው ከርሟል፡፡ በመሆኑም ወያኔን ማመን በዐቢይ መጠጋገን (እሱም የተሳካለት አይመስለኝም) ሳይሆን ቀብሮ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ደግሜ እላለሁ ይህ ጠንቀኛ ድርጅት (ወያኔ) ለኢትዮጵያ ጥፋቷ እንጂ በጭራሽ መድኅኗ አይሆንም፡፡

Filed in: Amharic