>

"በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ግድያ የመፈጸም ዕቅድ ነበር!!"...መንግሥት

“በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ግድያ የመፈጸም ዕቅድ ነበር!!”…መንግሥት
ፋና ብሮድካስቲንግ
* መንግሥት የጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ገዳይ ነው ያለውን ተጠርጣሪ ማንነት እና ፎቶ ግራፍ ዛሬ ይፋ አድርጓል
የኢትዮጵያ መንግሥት በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ተከታታይ ግድያ የመፈጸም ዕቅድ እንደነበር አስታወቀ። መንግሥት የጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ገዳይ ነው ያለውን ተጠርጣሪ ማንነት እና ፎቶ ግራፍ ዛሬ ይፋ አድርጓል። በባሕር ዳር ከተማ ተሞክሮ ከሽፏል የተባለው መፈንቅለ-መንግሥት በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እና በግብረ አበሮቻቸው ለመቀነባበሩ በተጨባጭ መረጃዎች ማረጋገጡንም አስታውቋል።
ስለ ባለሥልጣናቱ ግድያ እና ተሞከረ ስለተባለው መፈንቅለ መንግሥት የጸጥታ እና ፍትኅ የጋራ ግብረ-ኃይል ዛሬ ምሽት በብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ መግለጫ ሰጥቷል። ይኸ ግብረ ኃይል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፅህፈት ቤት፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እና የፌድራል ፖሊስን ያካተተ መሆኑ ተጠቅሷል።
በመግለጫው «ይኸ ሴራ፤ ተከታታይ ግድያ በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጭምር እርምጃዎችን ለመውሰድ የታቀደ» እንደነበር ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።
መግለጫው የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሰዓረ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር የነበሩት ዶክተር አምባቸው መኮንንን ጨምሮ የአምስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ አዛዦችን ገዳዮች «በሐሳብ ልዕልና የማያምኑ ጸረ- ዴሞክራሲ ኃይሎች»  ብሏቸዋል።
ግብረ-ኃይሉ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጄኔራል ሰዓረ እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ የተገደሉት አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መኮንን በተባለ ወታደር መሆኑን በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ይፋ ባደረገው መግለጫ አስታውቋል። አስር አለቃ መሳፍንት የጄኔራል ሰዓረ የቅርብ ጠባቂ መሆኑንም ጠቅሷል።  «ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ በፌድራል የጸጥታ ኃይሎች ቆስሎ በቁጥጥር ሥር ውሏል» ሲል መግለጫው አክሏል።
የግብረ-ኃይሉ መግለጫ እንደሚለው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው እና ግብረ አበሮቻቸው «ሥልጣንን በኃይል እና በመሳሪያ አፈ-ሙዝ ለመያዝ የተደረገ» የተባለውን ሙከራ አቀነባብረዋል። መግለጫው «የጥፋት ኃይሎች የመንግሥትን ይቅር ባይነት እና ሆደ ሰፊነት ወደ ጎን በመተው፤ ክህደት በመፈጸም እና ከዚህ አልፎ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በማጋጨት፣ ሥልጣን በኃይል እና በአቋራጭ ለመያዝ፣ ሐገራችንን እና ሕዝቦቿን ለመበታተን ተንቀሳቅሰዋል» ብሏል። «ማናቸውም የሽብር እንቅስቃሴዎችን አንታገስም» ሲል አስጠንቅቋል።
በአማራ ክልል ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸው የተባሉ 212 ተጠርጣሪዎች ከነ ሙሉ ትጥቃቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሔደ መሆኑን አስታውቋል።
በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ 43 ተጠርጣሪዎች፤ ሁለት መትረየስ፤ 27 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች እና በርካታ ሽጉጦች ከነ መሰል ጥይቶቻቸው ተይዘዋል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ጥቃት ማስፈጸሚያ ዕቅዶች እና ሰነዶች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ መጀመሩንም የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።
በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጀርባ እጃቸው አለበት ተብለው የተከሰሱት ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው መፈንቅለ መንግሥት በማሴር ሲወነጀሉ የመጀመሪያቸው አይደለም። በ2001 ዓ.ም. የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ አድርገዋል በሚል ተፈርዶባቸው ዘጠኝ አመታትን በእስር አሳልፈዋል።  ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም.  ከዝዋይ እስር ቤት በምኅረት ተፈተዋል።
አሳምነው ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተገፈፉት ወታደራዊ ማዕረግ በጠቅላይ ምኒስትሩ ውሳኔ የተመለሰላቸው ሲሆን መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም. የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ተመርጠዋል። ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የክልሉን የሰላም ግንባታ እና ደሕንነት ቢሮ በኃላፊነት እንዲመሩ ተሾመዋል።  ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው እስከ ዕለተ-ሞታቸው ድረስ ይኸንንው መስሪያ ቤት ሲመሩ ቆይተዋል።
Filed in: Amharic