>
7:51 am - Wednesday December 7, 2022

የአዲስ አበባ ባለደራው ምክር ቤት አመራሮችና አባላት ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል!!! (የባልደራሱ ምክትል ሰብሳቢው ኤርሚያስ ለገሰ)

የአዲስ አበባ ባለደራው ምክር ቤት አመራሮችና አባላት ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል!!!
 
ባልደራሱ ምክትል ሰብሳቢው ኤርሚያስ ለገሰ
 (ኢትዮ 360 – ሐምሌ 1/2011)
የአዲስ አበባ ባለደራው ምክር ቤት ባልደራስ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መብት ለማስከበር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ የአመራሮቹም ሆነ የአባላቱ ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ምክትል ሰብሳቢው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ አስታወቀ።
 አቶ ኤርሚያስ እንደሚለው ከሆነ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢውን በውጭ ሃገር ለመሾም የተገደደውም የሃገር ውስጥ እንቅስቃሴው ፈተናዎች ስለገጠሙት ነው።
 የምክር ቤቱ ህዝብ ግንኙንት ሃላፊ ስንታየሁ ቸኮልና ጸሃፊውን ኤሊያስ ገብሩን ጨምሮ በርካታ አባላቱ በጸረ ሽብር ህግ ተከሰው ወደ እስር ቤት ተግዘዋል።
 ቀደም ብለው ወደ እስር ቤት እንዲወሰዱና በጸረ ሽብር ህጉ ክስ ተመስርቶባቸው የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በፍርድ ቤት እንዲተላለፍባቸው የተደረገው እነ ስንታየሁ ቸኮል ጭለማ ቤት ተዘግቶባቸዋል ብሏል ኤርሚያስ ለገሰ።
 ቅዳሜ ምሽት በባልደራሱ ስብሰባ ተገኝቶ ወደ ቤቱ እያመራ የነበረው ኤልያስ ገብሩ አራት ኪሎ አካባቢ በደህንነት ሰዎች ተይዟል ነው ያለው።
 ከሌሎች 14 ሰዎች ጋር ፍርድ ቤት እንደቀረበ የተገለጸው ኤልያስ ገብሩ እሱና ሌሎቹ እስረኞች የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል፣ህገወጥ ሰነድ አዘጋጅተዋል፣የጦር መሳሪያ በድብቅ ይዘዋል ሲል ፖሊስ ክስ አቅርቧል።ፍርድ ቤቱም የ28 ቀን የጊዜ ቀጥሮ ሰቷል ይላል ኤርሚያስ ለገሰ።
 በባለ አደራው አመራርና አባላት ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ዜጎች አላግባብና የሰሩት ወንጀል በማይታወቅበት ሁኔታ በጅምላ እየታፈሱ በመታሰር ላይ ናቸው። ይሄን ደግሞ አለም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያቀው ይገባል ባይ ነው።
 የባላደራው ምክር ቤት ባልደራስ ምክትል ሰብሳቢውን በውጭ ሃገር እንዲሆን ሲያደርግም ሁኔታዎች አቅጣጫቸውን እየቀየሩ በመምጣታቸው ምክንያት ነው ብሏል።
 በቀጣይም በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚደረጉ ገልጿል።
 ለዚህ የሚሆኑ በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ነው ምክትል ሰብሳቢው ኤርሚያስ ለገሰ ከኢትዮ 360 ጋዜጠኛ ኢየሩሳሌም ተክለጻድቅ ጋር በነበረው ቆይታ የገለጸው።
 አሁን ስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር ከእንደዚህ አይነት ድርጊቱ እንዲቆጠብና ወንጀላቸውን ሳያጣራ ያሰራቸውን ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ብሎም እየሄደበት ያለውን አሰራር እንዲያስተካከል የሚጠይቅ ደብዳቤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለሆኑት ለአምባሳደር ፍጹም አረጋ ያስገባል፣ፍቃደኛ ከሆኑም በቢሯቸው ተገኝቶ በጉዳዩ ዙሪያ ይመክራል ብሏል።
 ከዚህም ሌላ በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ሁሉንም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባሳተፈ መልኩ የሚካሄዱት ሰልፎች በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ግፊት የሚያደርጉ ናቸው።
 አቶ ኤርሚያስ እንደሚለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዩን እንዲያውቁና ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪ ይቀርባል፣ጉዳዩን የሚመለከት ደብዳቤም እንዲደርሳቸው ይደረጋል፣በየቢሯቸው ደጃፍ የተቃውሞ ሰልፎቹ ይደረጋሉ።
 አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው አካል ለጥያቄዎቹ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት ካልቻለና ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ከቀጠሉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ሌሎች ተከታታይ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ይደረጋል ብሏል ምክትል ሰብሳቢው ኤርሚያስ ለገሰ ለኢትዮ 360።
Filed in: Amharic