>

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአ.ብ.ን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ!!!

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአ.ብ.ን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ!!!
*****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰኔ 2 እና ሐምሌ 1፣ 2011 ዓ/ም በደሴ ከተማ ባካሄደው ስብሰባ በወቅታዊ የሕዝባችን የፖለቲካና የፀጥታ ጉዳዮች የሁኔታ ግምገማ በማድረግ ጥልቅ ውይይት አካሂዷል። በዚህ መሰረትም የሚከተሉትን የአቋም ነጥቦችን በመውሰድ ስብሰባውን አጠናቋል።
1) ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ/ም በአማራ ሕዝብ ከፍተኛ አመራሮች ላይ በተፈፀመው መላ ሕዝባችንን ያሳዘነ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ  አብን ከፍተኛ የሆነ ልባዊ ኃዘን ተሰምቶታል። የተፈፀመውን ግድያም በከፍተኛ ሁኔታ እያወገዘ ይኸን ወንጀል ያቀዱ፣ ያቀነባበሩ፣ ያስፈፀሙና የፈፀሙ አካላትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲወጣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይጠይቃል። በዚህ አጋጣሚ በዚህ ክስተት ላጣናቸው ወንድሞቻችን ቤተሰቦችና ለመላው ሕዝባችን እንዲሁም ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች መጽናናትን እንመኛለን።
2) የአማራ «ክልላዊ» መንግሥትና ገዥው የአማራ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ በተፈጠረው ግድያ የተነሳ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመሸፈን ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ በፀዳ ሁኔታ መሪዎችን እንዲሰይም፤ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ ውዥንብሮችንም እንዲያጠራ እንጠይቃለን።
3) የተፈጠረውን ግድያ ተክትሎ በ«ክልሉ» የፀጥታ መዋቅር ላይ ለአማራ ሕዝብ ቀና አመለካከት የሌላቸው ኃይሎች በቃልም በተግባርም የማዳከም ሴራና ሥራ ውስጥ በግልፅ እየታዩ ነው። ጉዳዩ ከሕዝባችን ኅልውና ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ ሕዝባችንን በከፍተኛ ሁኔታ ለቁጣ ያነሳሳ ሆኗል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄንም በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቦታል። ስለሆነም አጋጣሚውን በመጠቀም የአማራን ሕዝብ ለማንበርከክ የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰብን፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለአግባብ የተያዙ የፀጥታ አመራሮችና አባላት ካሉ በአስቸኳይ ተለቀው ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ እንጠይቃለን። የ«ክልሉ» ልዩ ልዩ የፀጥታ ዘርፍ አመራሮችና አባላትም ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የሕዝባችንን አንድነትና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሰሩ እየጠየቅን በየደረጃው ያሉ የንቅናቄያችን አመራሮችና አባላትም በሚፈለገው ትብብር ሁሉ ከጎናችሁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
4) የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ወጣቶች፣ ባለኃብቶችና የፖለቲካ ኃይሎች በዚህ ፈታኝ ወቅት የሕዝባችንን አንድነትና ሰላም በመጠበቅ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማመንጨት እንዲሁም ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በመከባበርና በመደማመጥ ሕዝባችን ወደፊት ለማራመድ እንድንሰራ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጥሪውን ያስተላልፋል። በዚህ አጋጣሚ የሕዝባችንን አንድነትና የአብሮነት እሴት በሚሸረሽሩ ድርጊቶች ላይ የምትሳተፉ አካላት ከዚህ እኩይ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡ እናሳስባለን። መሰል እኩይ ተግባራትን የሚፈፅሙ አካላትን ከላይ በስም የጠቀስናችሁ ወሳኝ የኅብረተሰብ ክፍሎችና መላው ሕዝባችን እንዲታገላቸውም ጥሪ እናቀርባለን።
5)  የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የ«ክልሉ» መንግሥትና ገዥው ፓርቲ አዴፓ የሚያደርጉትን ጥረት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚያግዝና አብሮ የሚሰራ መሆኑን እናስታውቃለን። በዚሁ አጋጣሚ የሕዝባችንን ሰላምና መረጋጋት የሚረብሹ  ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ሕዝባችን እንዳይተባበርና የአማራ ጠል ኃይሎችን ፍላጎት ሊያሳኩ ከሚችሉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ራሳችንን እንድንጠብቅ አደራ እንላለን።
6) የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በኦሮሚያ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላት፣ የአስራት ሚድያ ጋዜጠኞች፣ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት አመራሮች፣ በመንግሥት አሰራሮች የሰላ ትቺትና ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችና የነቁ አማሮች  ላይ የተካሄደውን ጅምላ አፈሳና እስር እንዲሁም በእስር ላይ እየተፈፀመ ያለውን ኢሰብአዊ አያያዝ እንዲቆም በጥብቅ እያወገዝን በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ እናቀርባለን። በሰብአዊ መብት መከበር ላይ የምትሰሩ አገርበቀልና ዓለምአቀፍ ተቋማትም ተገቢውን ግፊት እንድታደርጉ እንጠይቃለን።
7) በየደረጃው ያላችሁ የንቅናቄያችን አመራሮች፣ መላው አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ሕዝባችንን ወደፊት ለማራመድ  በንቅናቄያችን ላይ የተጣለው ታሪካዊ ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ለሕዝባችን በሚጠብቅብን ልክ ሆነን መገኘትና የሚመጥን አመራር መስጠት ይጠበቅብናል። በመሆኑም በየደረጃው ካለው የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ መዋቅር ጋር በመቀናጀትና በመተባበር ሕዝባችንን የማረጋጋት እንዲሁም ሰላምና ደኅንነቱን የማስጠበቅ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
ሐምሌ 2፣ 2011 ዓ/ም
ደሴ፣ አማራ
Filed in: Amharic