ክስ ሳይመሰረትባቸው የታሰሩት የአዲስ አበባ ወጣቶች አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ለሚያደርጉላቸው ማናቸውም ድጋፍ እና አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል
ይድነቃቸው ከበደ
” የአዲስ አበባ ወጣቶች ክስ ሳይመሰረትባቸው 1 ዓመት …!!!”
ዛሬም እንደ-ወትሮው በእስር ቤት የሚገኙት ወንድሞቻችን እንዴት ናችሁ ?! ለማለት እኔ፣ ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ፣ ናትናኤል የአለምዘውድ እና ጌታነህ ባልቻ አንድ ላይ ሆነን፤ ጠዋት አረፋፈዱ ላይ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (3ኛ ፖሊስ ጣቢያ) ተገኝተን ነበር ።
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ፣ መርከቡ ሀይሌ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ሲሳይ አልታሰብ ፣ ክርስትያን ታደለ፣ ምስጋናው ጌታቸው፣ አዳም ውጅራ እና ሌሎች አብሯቸው የታሰሩ ወንድሞቻችን አግኝተናቸዋል። ሁሉም ለጤናቸው ደህና ናቸው፤ በሁሉም ፊት ላይ የሚንጸባረቀው “መንግስት” ከወነጀላቸው ድርጊት ከቶውንም እንደሌሉበት እና በራስህ የመተማመን መንፈሳቸው በእጅጉ ኃይሎ ይታይባቸዋል።
በእኛ በኩል ለሁሉም ያቀረብንላቸው ጥያቄ ፤ ከሰሞኑ ምን የተለይ አዲስ ነገር በእስር ቤት ውስጥ አለ ?! በማለት ነበር፤ በእነሱ በኩል ከበፊቱ ብዙም የተለየ ነገር እንደሌለ ከገለፁልን በኋላ፤ እኛን መልሰው የጠየቁን “ውጪ ምን አዲስ ነገር ?! ” አለ በማለት ነበር፤ ከነገርናቸው መካከል ” ዶ/ር ዐብይ ከሱዳን ከ100 በላይ እስረኛ አስፈትተው ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ” ለሁሉም አግራሞት’ን የፈጠረ ነበር ።
ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ እንዲህ በማለት ሃሳብን አጋርቶናል፦ ” በሰው ሃገር ያሉ ወገኖቻችን መፈታታቸው ደስ ይላል፤ ነገር ግን በማናውቀው ወንጀል ተፈርጀን በሃገር ቤት እየታሰርን አሁን ደግሞ የምንሰማው ነገር ግራ የሚያጋባ ነው። የዛሬ 1ዓመት መስከረም ላይ አዲስ አበባ ተክስቶ ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘ በጅምላ የታሰሩ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ ክስ ሳይመሰረትባቸው እስካሁ ድረስ እዚሁ እስር ቤት ታጉረው ይገኛሉ፤ እነሱም ፍትህ ይሻሉ” በማለት ” ዶ/ር ዐብይ ሱዳን ድረስ ሄደው እስረኞች ካስፈቱ እዚህስ ?! ” በማለት፤ አግራሞት የተሞላበት ጥያቄ ጠይቋል ።
ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ፦ ” ይህ ቀልድ ነው፤ እኛ በማናውቀው ነገር እዚህ አስሮ እንዲህ አይነት ነገር ማድረግ የሚገርም ነው። በፊት ወያኔ አስሮ አካላዊ ቶርቸር ያደርስብን ነበር፤ አሁን ደግሞ የተፈለገው አይምሮዊ ቶርቸር ለማድረግ ነው። እዚህ አብዛኛው የታሰረው ከዚህ ቀደም በአገራችን ለውጥ እንዲመጣ ዋጋ የከፈለ ነው። አሁንም ዋጋ እየከፈልን ነው፤ ሱዳን እስረኛ እያስፈቱ እኛ በማናውቀው ወንጀል ማሰረ አይምሮዊ ቶርቸር ለማድረግ ነው። ” በማለት ሃሳቡን ገልጿል ።
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፤ የተለመደውን ፈገግታውን አጨፍግጎ፤ ኮስተር በማለት ” ይህ የለየለት የፖለቲካ ንግድ ነው ! እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ንግድ ትርፍ የለውም፤ ለሰውም ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኝ አይደለም። ዜጎቻችን በመፈታታቸው ደስተኛ ነኝ፤ አብዛኞቻችን በማናውቀው ወንጀል እዚህ አስሮ፤ ከሃገር ቤት ውጪ እስረኛ አስፈታው ማለት፤ ንግድ ነው ” በማለት ቁጣውን ገልጿል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁሉም እስረኞች፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ለሚያደርጉላቸው ማናቸውም ድጋፍ እና አጋርነት፣ እንዲሁም ተገቢውን ፍትህ እንድናገኝ ከጎናችን ለሆናችሁ ሁሉ፤ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ብለዋል ። እናም ምስጋናቸውን እንካችሁ ተቀበሉ ።