>
12:18 am - Thursday December 1, 2022

የለውጡ እራስ ምታቶች ወይስ ለውጡ እራስ ምታት የሆነባቸው ፖለቲከኞች? (ያሬድ ሀይለማርያም)

የለውጡ እራስ ምታቶች ወይስ ለውጡ እራስ ምታት የሆነባቸው ፖለቲከኞች?
ያሬድ ሀይለማርያም
ከኦቦ በቀለ ገርባ ልጀምርና በዛ ክፉ ጊዜ ለፍትሕ እና ለነጻነት ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ሰው ናቸው። በጽናት እና በሙሉ ልብ ህውሃት መራሽ የሆነው ሥርዓት የተጋፈጡ እና በእስር የማቀቁ ጎምቱ ፖለቲከኛ ናቸው። በዚህ ጥንካሬያቸው የሚታወቁት ኦቦ በቀለ በዛው ልክ ደግሞ አወዛጋቢ እና እርስ በርሱ የሚጋጭ የፖለቲካ መልዕክቶችን በማስተላለፍም ከሚታወቁት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ናቸው። በተለይም ይህ ለውጥ ከመጣ ወዲህ ግለሰቡ በተለያዩ መድረኮች በሚያንጸባርቋቸው አወዛጋቢ እሳቤዎቻቸው የተነሳ ከፍተኛ ውግዘትን እና ድጋፍንም ከግራ ቀኝ ሲያስተናግዱ ቆይተዋል። አንዳንድ ንግግሮቻቸውንም ተመልሰው በአደባባይ ሲያስተባብሉ እና ማስተባበያ ሊሰጡ ሲጥሩ ታዝበናል።
ከጎናቸው የተቀመጡት ሌላው አወዛጋቢ ፖለቲከኛ ደግሞ የህውሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና ቀኝ እጅ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው። አቶ ጌታቸው በየጊዜው ወደ ሚዲያ ብቅ እያሉ የሚያንጸባርቁት የፓርቲያቸው አቋም እንዲሁ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ቅዋሜዎችን ሲያስተናግዱ ኖረዋል። ግለሰቡ አፈ ጮሌ በመሆናቸው እንደ ኦቦ በቀለ ገርባ ብዙ ስህተተችን በመግደፍ ባይታወቁም የተንኮል ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን ግን በየንግግሮቻቸው ውስጥ በቀላሉ መታዘብ ይቻላል።
እነኚህ ሁለት ፖለቲከኞች በሃሳብ መስመር ደረጃ ብዙም የማይለያዩ እና ሁለቱም የብሔር ፖለቲካ አራማጆች ቢሆኑም አንዱ ከግፉአን ሌላኛው ደግሞ ግፍ ከሚፈጸመውቱ ወገን ሆነው በሁለት የተቃርኖ ጎራ ውስጥ የተሰለፉ ሰዎች ነበሩ። በዳይ እና ተበዳይ። ምስጋና ለዚህ ለውጥ አሳሪ እና ታሳሪ በአንድ መድረክ ጎን ለጎን ቁጭ ብለው በአገር ጉዳይ ሲመክሩ ማየት ችለናል።
በዚህ ጽሁፍ ላነሳ የፈለኩት ፍሬ ጉዳይ ግን እነኚህ በበዳይ እና ተበዳይ ግንኙነት ውስጥ የቆዩ ፖለቲከኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳዩት ያለው መሳሳብ እና አንዴ መቀሌ፤ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ እየተገናኙ ለውይይት መቀመጣቸው አትኩሮቴን ስለሳበው ነው። ይህ አዲስ መሳሳብ እና ወዳጅነት በይቅርታ እና በፍቅር የተመሰረተ አብሮነት ወይስ ለአጋራ አላማ በተቀየሰ የአካሄድ ስልት አሳስቧቸው መስመር ላይ የተገናኞ ፖለቲከኞች?
እነዚህ ኃይሎች፤
+ በተመሳሳይ ቋንቋ እና አገላለጽ የለውጡን ሂደት ክፉኛ እየነቀፉ እና የአብይን አስተዳደር ሲነቁሩ ደጋግመን አይተናል፤
+ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ ካልተካሄደ አገሪቱ ትበታተናለች ወይም ወደ ከፋ ሁኔታ እናመራለን የሚል ዛቻ አዘል ማስጠንቀቂያ በተመሳሳይ ቋንቋ ሲያንጸባርቁ ሰምተናል፤
+ ሕገ መንግስቱም ሆነ ብሔር ተኮር ፌደራልዝሙ እንዳይነካብን የምል ማስጠንቀቂያቸውም ተደጋግሞ ተሰምቷል፤
+ እፍረት የማታውቀው ህውሃት ስትደፈጥጠው የኖረችውን ሕገ መንግስት እና ፌደራላዊ አስተዳደር ዛሬ አደጋ ላይ ስለወደቀ ኑ ሕገ መንግስቱን እና የብሔረ ፌደራሊዝሙን እንታደጋቸው ብላ አደባባይ ስትወጣ ከጎኗ የቆሙት በቀለ ገርባ እና አጋሮቻቸው መሆናቸውን ታዝበናል፤
እነዚህን እና ሌሎች ተመሳሳይ ምልክቶችን በቅርብ ለተከታተለ ሰው እነዚህ ሰዎች አንድም ለውጡ እየሄደበት ያለው መንገድ እራስ ምታት ሆኖባቸዋል፤ አለያም እነሱ የለውጡ እራስ ምታት ሊሆኑ ቆርጠው በጋራ ተነስተዋል የሚል ግምት ሊያድርበት ይችላል።
በተለይም ትላንት እና ዛሬ በመቀሌ  “ሕገ መንግስቱን እና የፌደራል ሥርዓቱን ከአደጋ እንታደግ” በሚል እየተካሄደ ያለው ውይይት ከለውጡ ጀርባ ምን እየተዶለተ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል። ወደ ኋላ ስታፈገፍግ የነበረችው ህውሃት ዛሬ ምን ተገኝቶ ይሆን በሌላ ጫፍ ካሉ ብሔረተኞች ጋር እየተሳሳበች ለውጡን ልትገዳደር ማሟሟቅ የጀመረችው?
በሂደት ላይ ያለውን ለውጥ፤ ሌላ የለውጥ ጥንስስ ሊያደናቅፈው ይሆን? በህውሃት እና በአክራሪ ብሔረተኞች መካከል የሚታየው አዲስ ቅርርብ እና መሳሳብ ለዚች መከረኛ አገር ምን ተዶልቶላት ይሆን ያስብላል።
Filed in: Amharic