>

በብአዴን ሚዛን አስጠባቂነት የተመሰረተው የኦሕዴድ/ኦነግ የበላይነት (አቻምየለህ ታምሩ)

በብአዴን ሚዛን አስጠባቂነት የተመሰረተው የኦሕዴድ/ኦነግ የበላይነት
አቻምየለህ ታምሩ
የኦሮሞ ብሔርተኞች ባገራችን ላይ እያደረሱ ያለውን መከራ ለማድረስ የቻሉት የማዕከላዊውን መንግሥት ሥልጣን በሞኖፖል ስለተቆጣጠሩ ነው። ይህ ደግሞ የሆነው ብአዴኖች ስለፈቀዱላቸው ነው። እስከመጨረሻው ድረስ ከለጠጥነው የኦሮሞ ብሔርተኞች የተረጋገጠ ድጋፍ ከ30% አይበልጥም። የብአዴንን ድጋፍ ቢያጡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ኃይል ያጣሉ። የብአዴንን ድጋፍ ሲያጡ ኃይል ስለሚያጥራቸው ከውጭ የሚደግፋቸው ማንም ኃይል አይኖራቸውም።
የፖለቲካ ነገር ልክ እንደ ውኃ ነው። ውኃ የሚፈሰው ሚዛኑ ወዳጋለበት ነው። ሕዝብ ለፖለቲካ የሚሰጠው ድጋፍም  እደዚያ ነው። ወያኔ የሰጠንን የሕዝብና የቤት ቆጠራ እንኳ ብንወስድ ከኦሕዴድ መሰረት ጋር ተገዳዳሪ የሕዝብ ቁጥር ያለው ብአዴን መሰረቴ ነው የሚለው የአማራ ሕዝብ ነው። ውኃ የሚፈሰው ወዳጋደለበት ስለሆነ ብአዴን ለኦሕዴድ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ቢያቆም የኦሕዴድ የኃይል ሚዛን በኃይለኛው ይቀላል።
ኦሕዴዶች የብአዴንን ድጋፍ ሲያጡ ኃይል ስለሚያጡና ድጋፋቸው ስለሚቀንስ የኦሕዴድ/ኦነግ የበላይነት ተዳክሞ የማዕከላዊ መንግሥቱ ሚዛን ከቁጥጥራቸው ውጪ ይሆናል። የማዕከላዊ መንግሥቱ ሥልጣን ከኦሕዴድ/ኦነግ ቡድን ቁጥጥር ውጪ ሆነ ማለት የማዕከላዊ መንግሥቱን ስልጣን ካልተቆጣጠሩ በስተቀር የበላይነታቸውን ማስቀጠል የማይችሉት የኦሮሞ ብሄረተኞች ድጋፍ በሁሉም አካባቢ ይደረሰማል ወይም collapse ያደርጋል። ምሳሌ ያደረግነው  ውኃ የሚፈስበት አቅጣጫ የሚነግረን ይህንን ነው።  እውነተኛ ምርጫ ከተካሄደ ደግሞ እስካሁን ያገኙት ሁሉ ያጣሉ።
ብአዴን ቢያውቅበት እወክለዋለሁ የሚለው ሕዝብ ኃይል ከባድ ነበር።  ብአዴን ይህ ኃይል ቢያውቅበት አይደለም የኦሕዴድ/ኦነግን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ  ለፖለቲካቸው ሲሉ የአማራን ሕዝብ ሲያጠለሹ የኖሩ የአፍሪካ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ኮንግረሶችና ሰኔቶችም  ሳይለምናቸው ይሰሙት ነበር። የአለም ፖለቲካ  የሚመራው በኃይል ሚዛን ነው። ሀገራት ለራሳቸው ሲሉ አሉ ከተባሉ ሚዛን አስጠባቂ ኃይሎችና ወኪሎቻቸው ጋር ይነጋገራሉ። ዋናው  ሚዛን አስጠባቂ ሆኖ መገኘት ነው።
ብአዴን የአማራ ባለጉዳይ ሆኖ ሚዛን አስጠባቂ ኃይል ቢሆን አማራን መታደግ ብቻ ሳይሆን ራሱም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይችል ነበር። ሚዛን አስጠባቂ ድርጅትና ከጀርባው ኀምሳ ሚሊዮን ሕዝብ ያለውን ኃይል የማያናግር ያገር መሪና ዲፕሎማት የለም። ይህ የአሜሪካ መሪዎችና አማራን ሲያጠለሹ የሚውሉ  ዲፕሎማቶቻቸውን ይጨምራል። አያቶቻችን ሲተርቱ «ወርቅ የጫነች አህያ የማትገባበት የለም»  ይላሉ። ይህን ተረት ግን ከወሬ ማጣፈጫ ባለፈ  ኮስተር ብሎ የአማራ ሕዝብ ያለውን ኃይል በተግባር የተጠቀመበት የብአዴን ሰው እስካሁን ድረስ አላጋጠመኝም።
ባጭሩ የኦሮሞ ብሔርተኞች ማዕከላዊ መንግሥቱን ተቆጣጥረው የሚፈልጉትን ሁሉ ያለ ሀይ ባይ  እያደረጉ ያሉት በብአዴን መቅለል ምክንያት ነው። ብአዴን ደግሞ የቀለለው በሁለት ምክንያቶች ይመስሉኛል።
አንዱ ምክንያት ብአዴን ፖለቲካን ወይም ዲፕሎማሲን ከመለማመጥ መለየት ያልቻለ በመሆኑና ዲፕሎማሲንና ፖለቲካን በማምታታቱ ነው። ብአዴን እስካሁን ድረስ ኦሕዴድን ሲለማመጥ ወይም appease ሲያደርግ እንጂ እንደ የራሱ ፍላጎት እንዳለው የፖለቲካ ድርጅት እወክለዋለሁ የሚለውን ማኅበረሰብ ፍላጎት አንግቦ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ፖለቲካ ሲሰራ ወይም በሰጥቶ መቀበል መርኅ ሲደራደር አላየነውም። በሌላ አነጋገር ሰማዩንም ምድሩንም ኬኛ እያሉ ሁሉን እየሰለቀጡ ያሉት የኦሮሞ ብሔርተኞች አልጠግብ ባይነት ፖለቲካ የብአዴን መለማመጥ የወለደው እብሪት ነው።
ብአዴን መለማመጥ እንደማይሰራ ዊስተን ቸርችል የተናገረውን የሰማ አይመስልም። ዊስተን ቸርቺል መለማመጥ እንደማያዋጣ ሲገልጽ «An appeaser is one who feeds a crocodile, hoping it will eat him last» ብሎ ነበር። ይህ ቀለል ባለ አማርኛ ሲተረጎም «መለማመጥ ሊበላ የተዘጋጀን አዞ ለማባበልና እንዳይቆጣብን ብለን እስኪበላን ድረስ ጊዜ ለመግዛት ስጋ እንደመቀለብ ነው» እንደማለት ነው። ሊበላን የተዘጋጀን አዞ ማባበል ከመበላት አያድንም። የኦሮሞ ብሔርተኞችን ማበበል ትርፉ ሁሉን ነገር ጨርሰው እስኪውጡት ድረስ ጊዜ እንዲያገኙ ማገዝ ብቻ ነው። የማይጠረቃ ፍላጎት ያላቸውንና ስንዝር ሲሰጣቸው ክንድ የሚጠይቁትን የኦሮሞ ብሔርተኞች ማባበል እንደማያዋጣ  በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ኦሕዴድ  የጠቅላይነት ክብረ ወሰንን መስበሩ መለማመጥ እንደማይሰራ ብአዴንን ያስተማረው አይመስልም።
ሁለተኛው ብአዴን የቀለለበት ምክንያት ለአማራ የሚቆረቆሩ ልጆች ብቅ ባሉ ቁጥር በነንጉሡ ጥላሁን፣ ዳግማዊት ሞገስና ብናልፍ አንዷለም አይነት ነባር ይዞታቸው አድርባይነት የሆነና አሽከርነት በለመዱ የኦሕዴድ ግብረ በላዎች እንዲመቱና እንዲንሳፈፉ በመደረጉ ብአዴን ውስጥ ሁኔታዎች ተለውጠው፣ በቃ ብሎ ሕዝቡን ከጎኑ የሚያቆም ኃይል ባለመምጣቱ ነው። ብአዴን ውስጥ ሁኔታዎች ተለውጠው፣ በቃ ብሎ ሕዝቡን ከጎኑ የሚያቆም ኃይል ከመጣ ቅጥ ያጣው የኦሮሞ ብሔርተኞች ጥጋብ ያልቅለታል።
ብአዴን እንደ ድርጅት ዛሬም ቢሆን በቃ ብሎ ሕዝቡን ከጎኑ የሚያቆም ኃይል ከውስጡ እንዳይመጣ እያደረገ ያለ ድርጅት ነው። ብአዴን እንደ ሕወሓት በኦሕዴድ እንደ አቻ ድርጅት ለመከበር ለድርድር የማይቀርቡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን አንግቦ ባለጊዜው ኦሕዴድ እንደ ሕወሓት ሁሉ ብአዴንም ሕዝብ ከጎኑ ቆሟል ብሎ ቆም ብሎ እንዲያስብና ሚዛኑን እንዲጠብቅ ማድረግ አልቻለም።
ስለነዚህ ሁለት ምክንያቶች ብአዴን ቀሏል። የኃይል ሚዛኑ ወደ ለኦሕዴድ/ኦነግ ያጋደለው የሕዝብ ድጋፍ  እንደ ውኃ መሆኑን ያልተገነዘበው የብአዴን ይትበሀልና ፖለቲካን/ ዲፕሎምሲና ማባባበል የሚያምታቱ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በዝተው እንጂ  በብአዴን መቅለል ላይ ብቻ የጸናውና መሰረት የሌለው የኦሕዴድ/ ኦነግ  የኃይል ሚዛን መቼም ቢሆን መናዱ ሊናድ ይቻላል። ብአዴን ቢያውቅበት የሕዝብ ድጋፍ እንደ  ውኃ  በሚፈስበት ፖለቲካ ውስጥ  የኦሕዴድ/ ኦነግን የኃይል ሚዛን ብቻውን መናድ ይቻለዋል።
የብአዴን ፖለቲካ መለማመጥ ባይሆን ኖሮ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣኑን ኦሕዴድ  ከወሰደ  ቢያንስ ሌላው ቁልፍ የስልጣን  ቦታ አዲስ አበባ እንደመሆኑ መጠን አዲስ አበባን ብአዴን መያዝ አለብኝ ብሎ ይደራደር ነበር። ፖለቲካው መለማመጥ በመሆኑ  ጠቅላዩንም፣ አዲስ አበባንም፣ ፓሊሱንም፣ አቃቢ ሕጉንም ለኦሕዴድ ከስረከበ ኋላ የኦሕዴድን ሚዛን አስጠብቆ እንደ ተሸናፊው ሕወሓት ከማዕዱ በጣም ርቆ ባሕር ዳር ገብቶ  ተቀመጠ።
ባጭሩ የኦሮሞ ብሔርተኞችን ጽንፍ ያደረሳቸው፣ የአማራ ሕዝብ ነፍሱን ገብሮ ያመጣውን ድል ብአዴን አማራውን ከድቶ ወደ ኦሕዴድ አሽከርነት መመመለሱ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ  ያለ ብአዴን ድጋፍ ኦሕዴድ እንዲህ ምድሩም ሰማዩንም ጠቅልሎ መቆም ባልቻለ ነበር።
Filed in: Amharic