>
5:13 pm - Sunday April 19, 6201

"...አካላችን እንጂ መንፈሳችን አልታሰረም! በልልን" አንድ አፍታ ከኤልያስ ገብሩና ከበሪሁን አዳነ ጋር!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

አንድ አፍታ ከኤልያስ ገብሩና ከበሪሁን አዳነ ጋር!!!
ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
“…አካላችን እንጂ መንፈሳችን አልታሰረም! በልልን”
 
ዛሬ ጠዋት
ረፋድ 5 ሰዓት ገደማ፡፡ እኔ እና የሙያ አጋሬ ግሩም ተ/ኃይማናት 40 ደረጃ አካባቢ የሚገኘው ቢሮው ውስጥ ተገናኘን፡፡ የዱሮ የነፃው ፕሬስ ሕይወታ ችንን እያስታወስን ፣ ትዝታችንን እያመነዠክን፤ ደሞ የባጥ የቆጡን እያወጋን እያወን ቆየን፡፡ በመሃሉ “ባክህ እዚህ ቁጭ ብለን ከምንቀባጥር፣ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እነዛን ልጆች እንጠይቅ” አልኩት፡፡
“አሪፍ ሃሳብ አመጣህ እንሂድ” አለ ግሩም፡፡
ተያይዘን ሄድን፡፡
አዲስ አበባ ፖሊስ ስንደርስ 60 ሰባ የሚሆኑ ሰዎች በሰልፍ ቆመዋል፡፡ ጠያቂዎች ናቸው፡፡
እንደደረስን ገባ ብለን የምንመለስ ነበር የመሰለን፡፡
“ኡ …. ይሄን ሁሉ ሰው እስኪገባ ልንጠብቅ ነው” አልኩኝ፡፡ ከሰልፈኞች መሃል አንዷ  ሰምቶኝ “እንደውም ዛሬ ሰው የለም” አለችኝ፡፡ “ውስጥ አዳራሽ ውስጥ ስትገባ ደግሞ የሰውን መአት አይተህ ትደነግጣለህ” ስትል አከለች፡፡ ተመላላሽ ጠያቂ ሆና ኖሮ ስንገባ ሞባይል ምናምን እንደምናስረክብ፣ ቀበቶ አውልቀን እንደምንፈተሽ ወ.ዘ.ተ ነገረችኝ፡፡
15 ደቂቃ ያህል እንደጠበቅን ተራችን ደርሶ ወደውስጥ ዘለቅን፡፡ ተፈትሸን ወደ አንድ መለስተኛ አዳራሽ ገባን፡፡  አዳራሹ ውስጥ ያለው ጠያቂ ብዛት ለስብሰባ  የተጠራ ይመስል ችምችም ብሎ ተቀምጧል፡፡ ገሚሱ ቆሟል፡፡ ከፊሉ ወዲያ ወዲህ ይንቆራጠጣል፡፡ የሰው ብዛት የጋዜጠኛ ግርማ ተስፋውን ሁለት መስመር ግጥም አስታወሰኝ፡
“አገሩ ታሰረ፤
እስር ቤት መቀለስ እንደ ዱሮው ቀረ”
የጠያቂው ብዛት “አገሩ የታሰረ” ይመስላል፡፡ ለማንኛውም እዛ የምንጠይቀውን ሰው ስም ማስመዘገብ አለብን፡፡ ግሩም፤ ኤልያስ ገብሩን እኔ በሪሁን አዳነን እንደምንጠይቅ ተናገርን፡፡ ከጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ ጋር በአካል የተገናኘው አንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ የጋሽ ያሬድ ጥበቡ መፅሐፍ ምረቃ እለት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ነበር፡፡ የምረቃ ፕሮግራሙን በአጭር ንግግር የከፈተው እሱ ነበር፡፡ ለካ የጋሽ ያሬድን ፅሁፍ አሰባስቦ ለትውልድ ይጠቅማል ብሎ ሕትመት ያዘጋጀው እሱ ነበር፡፡
 በሪሁን አዳነ የአስራት ቴሌቪዥን እንዲመሰረት ግንባር ቀደም ሚና እንደነበር ያወቅኩት በዚህ በማህበራዊ ድረ ገፅ ፅሁፎች ነው፡፡ እና ፖሊስ ጣቢያ ከሄድን አይቀር ሁሉንም መጠየቅ ባንችል ቢያንስ በሙያ አጋርነታችን በሪሁንን መጠየቅ አለብን ብለን ነው ያስጠራነው፡፡
የሆነ ሆኖ ስማቸውን ካስመዘገብን በኋላ ተቀምጣችሁ ጠብቁ ተባልን፡፡ የአዳራሹ አንዱ ጥጋት ጋ ቆመን ስለጠያቂዎች ጋር ተደባልቀን ስለጠያቂዎች ብዛት ማውራት ቀጠልን፡፡ (ለነገሩ በተለያየ ወንጀል በስርቆትም፣ በመኪና ግጭት  ሰው በመግደልም በሌላ ሌላ ወንጀልም የታሰሩ ሰዎች ጠያቂዎች ጭምር ናቸው) ይህንን ወሬአችንን የሰማችው አንድ ቀላ ያለች ወጣት “እንደውም ዛሬ ሰው የለም” አለችን እንደዘበትን፡፡ አዳራሹ ውስጥ ያለው ሰው በግምት ከ200 በላይ ይሆናል፡፡
“ከዚህም በላይ …..?”
“ብዙ ቀን እዚህ አዳራሽ ውስጥ ጠጠር መጣያ ቦታ አይገኝም” አለችን፡፡ ትኩር ብዬ አየኋት፡፡ ዕድሜዋ በአስራዎቹ የሚገመት ወጣት ናት፡፡ ፊቷ ላይ የድካም ስሜት ይነበባል፡፡ ከአጠገቧ ስንቅ የያዘ ዘንቢል ተቀምጧል፡፡
“አንቺ ብዙ ጊዜ ትመላለሽ ማለት ነው?”
“በየቀኑ!”
“በየቀኑ? ማለት ከመቼ ጀምሮ? ለምን ያህል ጊዜ ተመላለሽ?” ጥያቄ አከታተልኩባት፡፡
“ከሰኔ 16 ጀምሮ!”
“በባህርዳሩ ጉዳይ ሰው የታሰረብሽ? ማነው የታሰረብሽ?”
“አዎ! አባቴ ነው የታሰረው! ሽማግሌ አባቴ!”
“ከባህር ዳር ነው የተያዙት? ምን ነበር ሥራቸው?”
“ኧረ ከዚሁ ከአዲስአበባ ነው፡፡  ካራቆሬ መብራት ኃይል  ዘበኝነት (ጥበቃ) ነበር የሚሰራው፡፡ ሽማግሌ ነው፡፡ የ73 ዓመት ሽማግሌ፡፡ በዚያ ላይ በሽተኛ ነው፡፡ የኤች አይ ቪ ተጠቂ ነው፤ በጣም ታሟል፡፡ ፍ/ቤት የሚቀርበው ራሱ በሰው ሸክም ነው” አለችን፡፡
ደነገጥኩ፡፡
“አባትሽ ማነው ስማቸው?”
“አምባዬ ገላዬ ይባላል፡፡ በያዙት በማግስቱ “መርማሪዎች መጥተው ቤታችንን አብጠርጥረው ፈትሸዋል፤ ምንም ያገኙት ነገር የለም፡፡ ይኸው እዚህ አምጥተው ወርውረውታል፤ በዚያ ላይ ሕክምና እንኳን እንዲያገኝ አላደረጉም፡፡ ፍ/ቤትም ሕክምና ለማግኘት አመልክቶ ነበር፡፡ ሰሚ አላገኘም፡፡ ….. ይኸው በበሽታ እየተሰቃየ ነው ታስሮ ያለው፡፡ እኛም ተሰቃየን፤ ከካራቆሬ እዚህ ለመድረስ ብቻ ከአንድ ሰዓት በላይ ይፈጃል፤ ወጪውን ተወውና ለመመለስ ደግሞ ከአንድ ሰዓት በላይ ይባክናል፡፡ ቀለብ ለማዘጋጀት ብቻ አንድ ሰዓት ከዚያም በላይ ይቃጠላል፡፡ በየቀኑ 6 ሰዓት ግማሽ ቀን እሱን ለመጠየቅ ነው የሚጠፋው፡፡ በየዕለቱ መባከን በለው …. ” ወዘተ አለችኝ በምሬት ስሜት፡፡
.
አውቀዋለሁ፡፡ እንዲህ አይነቱን የቤተሰብ ስቃይ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ አልፌበታለሁ፡፡ አንዳንዴ ያንን የቤተሰብ ሕይወት ሳስበው “አንድ ፊቱን መታሰር ይሻላል” እላለሁ፡፡ ከታሳሪው በላይ፣ የታሳሪው ቤተሰቦች ሕይወት መባከን ያበሳጨኛል፡፡ ይህቺም ለጋ ወጣት ከዚችው እድሜዋ ላይ ቀንሳ ለአባቷ እያባከነች ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ ከማዘን ውጪ ምን ይደረጋል!? በቃ ዝም ብሎ ማዘን ብቻ!
በዚህ መሃል የኤልያስ፣ የበሪሁን ጠያቂዎች የሚል የጥሪ ድምፅ መጣ፡፡ የተጠራነው 15 ያህል ሰዎች በፖሊስ እየተመራን ወደመጠየቂያው ስፍራ ተወሰድን፡፡ ከሽቦ አጥሩ ወዲያ እስረኞች ቆመው ከጠያቂዎች ጋር ይጯጯሃሉ፡፡ ኤልያስ ገብሩ  ከእስረኞች መሃል ቆሞ በምልክት ጠራን፡፡ መጨባበጥ የለም፡፡ አጥሩ ጣት እንኳን አያሾልክም፡፡ በሩቁ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡
“አምሮብሃል ጃል” አልኩት፡፡
“የታሸገ ነገር እኮ ያምራል” አለ እየሳቀ፡፡
“ማለት?”
“ አምጥተው የሆነ ከፍል ውስጥ አሽገውናላ! ጥያቄ የለ፤ ምን የለ”
“የፖሊስ ምርመራስ?”
“ ….. ወይ ምርመራ …. የገባው ቀን ማግስት ብቻ ለምርመራ ተጠርቼ ነበር፡፡ ያን ቀንም ምንም የረባ ነገር አልጠየቁኝም……. ስልክ ስትደዋወል የዶ/ር አቢይን ስም ጠርተህ ነቀፋ ሰንዝረሃል (በሱ አባባል “ተሳድበሃል” ) ምናምን ነው ያሉኝ፡፡
“አ……!”
“እይገርምህም፤ በቃ በስልክ ተሳድበሃል ነው ያሉኝ” እየሳቀ፡፡ ሳልወድ በግድ ሳቅኩ፡፡ እያረሩ መሳቅ፡፡
“በሪሁን የለም እንዴ?” አልኩት ከምሬት ሳቄ በኋላ፡፡ “አለ ይመጣል፡፡ ይልቅ ማዘር (ወ/ሮ የሺ) እንዴት ናት?” የተገላቢጦሽ፤ ጠያቂ ተጠያቂ ሆነ፡፡ ወዲያው ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ መጣ፡፡ ኤልያስ እኛን በምልክት ጠራውና ወደ አኛ ጠቆመው፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ስናበቃ “አውቀኸኛል?” አልኩት፡፡
“በደንብ ነዋ፤ ወሰንን ማን የማያውቅ አለ!? (ለካ ታዋቂ ነኝ 🙂 ሞቀኝ) እሱን ግን አላውቀውም፡፡”
“ጋዜጠኛ ግሩም ይባላል፡፡ ከቀደምቶቹ የፕሬስ ጋዜጠኛች”
“ኦ…… ስሙን አውቀዋለሁ፡፡ ስለመጣችሁ በጣም አመሰግናለሁ”
ገፅታውም ሆነ ንግግሩ የመንፈስ ብርታት ፅናት ይነበብበታል፡፡ ኤልያስም እንዲሁ፡፡
“እንዴት ነው ምርመራ ምናምን?”
“…. ባክህ ተወው! ቀልድ ነው የተያዘው፡፡ የሚሉት ነገር ሁሉ ቀልድ ነው! ይልቅ እናንተ እንዴት ናችሁ?”
ጭራሽ ታሳሪዎቹ ጠያቂ ሆነው እርፍ!
“አይዞአችሁ! በርቱ! ሰውም ስለ እናንተ መብት እየጮኸ ነው፡፡ ጋሽ ያሬድም ስለአንተ ፅፏል፡፡ የመፅሐፉን አዘጋጅነትህን ጠቅሶ፡፡ ሌሎችም ፍትህ አየጠየቁ ነው…..”
“አዎ ያሬድ መፃፉን ሰምቻለሁ፡፡ ጋሽ ያሬድን አመስግንልኝ፡፡ በአጠቃላይ ስለእኛ መብት የሚጠይቁልንን ወገኖቻችንን በሙሉ አመስግንልኝ፡፡…. አካላችን እንጂ መንፈሳችን አልታሰረም በልልኝ” አለኝ፡፡ (ይህ መልዕክት የጋዜጠኛ ኤልያስም ነው) ወዲያው ከጀርባችን ሌላ ጠያቂ መጣና በሪሁን ወደሱ ሄደ፡፡ (እነሆ እኔም ለመላው የታሳሪዎቹ መብት ጠያቂዎች  የምስጋና መልዕክታቸውን አድርሻለሁ”
ብቻ እንዲህ እንዲህ ተጨዋውተነ ተሰነባበትን፡፡ ከግቢው ስወጣ “በስልክ ከደዋይህ ጋር ስትነጋር ዶ/ር አቢይን ሰድበሃል” ብሎ የምርመራ ጥያቄ ፌዝነቱ እየታሰበኝ ፈገግ አልኩኝ፡፡ ወዲያው የዶ/ር አቢይ ምስል በዐይነ ህሊናዬ እየታየኝ አንድ የዱሮ ዘፈን ታወሰኝ፡፡ “ቀልዱን ተይ…….” የሚል፡፡
“ቀልዱን ተይ! ቀልዱን ተይ!”
እናም ልክ ከዚያ ግቢ ስወጣ
“ንፁሐንን አስራችሁ አስራችሁ በተደጋጋሚ  28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመጠየቅ ፍትህን የምታዛቡበት ተግባራችሁ፤ በስልጣን ላይ ተወዝፋው ያሳለፋችሁትን የስልጣነ ብልግና ዓመታት ቁጥር እንዳይጠፋችሁ የሰጋችሁ ያስመስላችኋልና ይህንን ቀልዳችሁን ቁሙ!” ብዬ መጮህ አማረኝ፡፡ ሆኖም ጮኬ አልተናገርኩም፡፡ ጮኬ ባልናረውም ይኸው እንዳይጠፋ አድር ከተብኩት፡፡ በአጭሩ፤ ግን ጎላ ባለ ድምፀት የምለው ይህንን ነው፡-
“የሥመ ፍትህ ቀልዳችሁን በአስቸኳይ  አቁሙና አላግባብ ያሰራችኋቸውን ጋዜጠኞች ልቀቁ!!”
ይኸው ነው!!
Filed in: Amharic