>
5:46 pm - Tuesday May 17, 2022

የኮ/ል መንግስቱ ቀኝ የነበሩት ፕ/ት ሮበርት ሙጋቤ አረፉ (ታምሩ ገዳ)

ዙምባብዌን ለሶስት አስርት አመታት የመሯት፣ በብዙዎች ዘንድ ጸረ ምእራባዊያን አቋም የተላበሱ፣ የነጻነት ታጋይ እና አምባገነን መሪ ተደርገው የሚገመቱት ፕ/ት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ ከዚህ አለም በሞት ተለዪ።

በዙምባብዌ የጸረ ቀኝ ገዢዎች ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት፣ የአገሪቱ የመጀመሪያ ድህረ ቀኝ ግዛት ፕ/ት በመሆን በአገሪቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እና ብልጽግና ለማምጣት ቃል ገብተው ነገር ግን ቃላቸውን ያላሳኩት የዘጠና አምስት አመቱ ሮበርት ሙጋቤ ካለፈው ሚያዚያ 2019 እኤአ ጀምሮ በህክምና ላይ በነበሩበት ሲንጋፖር ውስጥ ዜና እረፍታቸውን የሰሙ ወገኖች የተለያዩ አስተያየት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የፕ/ት ሙጋቤን ዜና እረፍት የሰሙት የወቅቱ የአገሪቱ ፕ/ት ኤመርሰን ማጋጋዋ በወዳጆች አምድ ትዊተር ገጻቸው ላይ” የጓድ ሙጋቤን መሞትን ይፋ ሳደርግ በ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ሆኜ ነው። ጓድ ሙጋቤ የዙምባብዊ መስራች አባት ናቸው፣ ለህዝባችን እና ለፓን አፍሪካኒዝም ሲሉ ህይወታችንን ለመስዋትነት የሰጡ፣ ታላቅ ባለውለታችን ነበሩ፣ ፈጣሪም ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ያሳርፍልን “በማለት ፕ/ት ሮበርት ሙጋቤን አውስተዋቸዋል።

በእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ለአንድ መቶ አመታት በነበረችበት ወቅት ሮዴሺያ የሚል መጠሪያ ስም የነበራት በሁዋላ ወደ ዙምባብዌነት (በሾና ቋንቋ የተከበረ ቤት ማለት ነው) የተቀየረችው አገርን በአምባገነናዊ አስተዳደር እስከ 2017 እኤአ ድረስ የመሯት ሙጋቤ ያለመከሰስ መብታቸው ተከብሮ ከስልጣን ሲወርዱ ዙምባብዌን ነጻ በማድረጉ ትግል ውስጥ አስተዳደራቸው እና እራሳቸውም በግል ልዩ እገዛ ያደረጉት፣ የሙጋቤ የቀኝ እጅ የነበሩት፣ካላለፉት ሀያ ሰባት አመታት ጀምሮ በመዲናይቱ ሐራሬ ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በልዩ ጥበቃ የሚኖሩት የቀድሞው የኢትዬጵያ ፕ/ት፣ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም በቀረበባቸው የቀይ ሽብር ክስ እና በሌሉበት በተበየነባቸው ውሳኔ ሳቢያ ወደ ኢትዬጵያ ለፍርድ ይመጣሉ ተብሎ በስፋት ተገምቶ ነበር።

ኮ/ል መንግስቱን አሳልፎ እንዲሰጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች በአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግፊት የተደረገበት አዲሱ የዙምባብዌ መንግስት በበኩሉ የፕ/ቱ አፈቀላጤ የሆኑት ጆርጅ ቻሬምባ ለዜና ሰዎች ቀደም ሲል በሰጡት ምላሽ ” የኢትዬጵያ ገዢ ፓርቲ (ኢሕአዲግ) ምንም ሳይለን እነዚህ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ወገኖች ዝም ብለው ባይዘባርቁ ይሻላል በአሁኑ ወቅት በብዙ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተጠምደናል፣ ተቃዋሚዎቻችን በቅድሚያ ኮ/ል መንግስቱ ወደዚህ አገር የመጡበትን አለማቀፋዊ የህግ አግባብነትን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። ለመሆኑ እኛ አገር ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ጥገኛ ኮ/መንግስቱ ብቻ ናቸው እንዴ?፣ የሩዋንዳ፣ የኮንጎ፣ እና የሞዛምቢክ ተገን ጠያቂ ፖለቲከኛች የሉንም?ለምን በኮ/ል መንግስቱ ላይ ብቻ ጣት መቀሰር ተፈለገ?” በማለት ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም ለዙምባቤ መንግስት ሁሌም ልዩ እንግዳቸው እንደሆኑ በመግለጽ ፣ለማንም አካል አሳልፈው እንደማይሰጧቸው ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም። አንዳንድ የዙምባብዌ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ኮ/መንግስቱ ለፕ/ት ሮበርት ሙጋቤ አስተዳደር ወታደራዊ የምክር አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው በማለት ሲወነጅሏቸው ነበር ።

በ ኮ/ል መንግስቱ የስልጣን ዘመን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ኢትዬጵያኖች በቀይ ሽብር ስም መሞታቸው ባያጠያይቅም፣ በህግ ባለሙያዎች ምልክታ ኮ/ሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንኳን ባይሆኑ በመሪነታቸው ሊጠየቁ እንደሚገባ ይገምታሉ። እኤአ በሌሉበት የሞት ብይን የተፈረደባቸው ኮ/ል መንግስቱ የችሎት ውሳኔን በተመለከተ የህዩማን ራይት ዎች ልዩ አማካሪ የሆኑት እና የተለያዩ አምባገነን መሪዎችን የተፋረዱት ሬድ ብሮድሌይ ” ወንጀል ለሰሩ መሪዎች አለም የቱንም ያህል እየጠበበች ብትመጣም አንዳንድ አምባገነኖች ግን መደበቂያ አላጡም፣ እድሜ ለፕ/ት ሙጋቤ ይበሉ እና ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያምም ዛሬ ልዩ ጥበቃ ባልተለየው የቅንጦት አለማቸውን እየቀጩ ይገኛሉ” በማለት የፕ/ት ሙጋቤ እና የኮ/ል መንግስቱ የጠበቀ ወዳጅነትን ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ ኮ/ል መንግስቱ የቅርብ አጋራቸው የነበሩት ጉምቱ ፕ/ት ሮበርት ሙጋቤን በሞት ሲለዩዋቸው “አወይ ጓዴን!!!” በማለት ያሳለፏቸው ወርቃማ ጊዜያትን ማስታወሳቸው አይቀሬ ነው።

ኮ/ል መንግስቱ ለፍርድ የመቅረባቸውን ጉዳይን በተመለከተ የቅርብ ወዳጃቸው እና በእየ ጊዜው በስልክ የሚያገኟቸው የነበሩት ብ/ጄን ታመነ ድልነሳው ቀደም ሲል ለህብር ራዲዬ በሰጡት አስተያየት”ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም በኢትዬጵያ ውስጥ ነጻ ፍርድ ቤት ከተቋቋመ እና ነጻ ዳኞች ከተሾሙ በገዛ ፍላጎት ከችሎት ቀርቤ ንጹህነቴን አረጋግጣለሁ ብለውኛል” ማለታቸው ይታወሳል።

Filed in: Amharic