>
6:24 pm - Friday August 19, 2022

ጠ/ሚሩ ለምን የመስከረም ፬ ሰልፍ አስተባባሪዎችን ማግኘት ፈለጉ? (አባይነህ ዋሴ)

ጠ/ሚሩ ለምን የመስከረም ፬ ሰልፍ አስተባባሪዎችን ማግኘት ፈለጉ?
አባይነህ ዋሴ
የመስከረም ፬ ሰልፍ አስተባባሪዎች ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የነበራቸውን ውሎ አጠናቅቀው ወጥተዋል፡፡ ስለ ውሏቸው ውጤትም ምንም ዓይነት ነገር ትንፍሽ አላሉም፡፡ ቀድሞ እንደተነገረው ያው መስከረም ፪ትን ጠብቁ እያሉን ነው፡፡ ለዘንድሮ ወሬ የከርሞ ቀጠሮ ኾኗል፡፡
እስከዛሬ ድረስ የትኛውም የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ቤተ መንግሥት ድረስ ተጠርቶ አያውቅም፡፡ ካለም ወይ ፈልጎ ጠይቆ ነው ወይም የራሱ የመንግሥትን ጉዳይ የሚያስፈጽም ከኾነ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በእናታቸው ላይ የሚወርደው ግፍ አንገሽግሾአቸው በሰላማዊ ሰልፍ ጥቃት ይቁም ለማለት እርማቸውን ቢነሡ በየቦታው ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየተዥጎደጎደ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያ ጅማ እና ሻሸመኔ ላይ ይኸው ተፈጽሟል፡፡ ፖሊስ እና የከንቲባ ጽ/ቤቶች እየተናበቡ ጉዳዩን ለማጠማዘዝ እየሠሩ ናቸው፡፡ መንግሥት በቀጥታ እጁን አስግብቶ ሰልፉን ለማስቆም እየሠራ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ከምክትል ከንቲባው ጋር የጀመረው ነገር እስከ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ተራዝሟል፡፡ አዎ ስንነሣ እንዲህ እናንቀጠቅጣለን፡፡ ግን የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተባባሪዎቹን የመጥራት ነገር ሕጋዊ ነውን? ሊሸልሟቸው እንዳልጠሯቸው እርግጠኛ አይደለሁም የሚል መቸም አይኖርም፡፡ የዛሬው ውሎ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የእርሳቸው ጠርቶ ማነጋገር ግን ጣልቃ ገብነት ከመኾን አይሸራረፍም፡፡
አዎ አስተባባሪዎቹን ለማስደንገጥ፣ ወይም ይሉኝታ ለማስያዝ የተደረገ ሙከራ መኾኑ አይጠረጠርም፡፡ ድባቡን ላልለመዱት ወንድሞቻችን ከባድ ፈተና እንደሚኾንባቸው ይገመታል፡፡ በዚያ ላይ እንዴት ሰልፉ ላይ አደጋ ሊያጋጥም እና ብዙ መተላላቅ ሊደርስ እንደሚችል የተጠና እና የሚያስደነብር ዝግጅት ቀርቦላቸውም ይኾናል፡፡ ሽጉጥ መታጠቁን በኾነ መንገድ አፉ ግን ሳይናገር የሚያሳይህ ሰው መልእክት ካልገባህ ችግሩ አንተ ጋ ይኾናል፡፡ እንደዚህ ያሉ በቃል የማይነገሩ ድባባቸው ግን ከቃል በላይ የሚናገሩ ሁኔታዎችን ማሳየት ይቻላል፡፡ ለዚህ ዝግጁ የኾነ ሥነ ልቡና ሳይገነባ አስተባባሪዎቹ ላይ መውረድ አይገባንም፡፡
ነገር ግን መንግሥት ለምን ይህን ያኽል ሕገ ወጥ ይኾናል? ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሔድ ይህን ያህል ዝም ያለ ግን ውስጠ ወይራ መንገድ ለምን ተከተለ? በየትኛው የኢትዮጵያ ሕግ ነው አሠራሩ የተፈቀደው፡፡ የሀገሪቱ ሕግ የፈቀደውን መብት ለማስጣል ከይሴአዊ ጥበብ መጠቀም ከጠላትነት ያድናልን? የእባብን ጠላትነት ያወቅነው በውጤቱ እንጅ በንግግሩ አልነበረም፡፡ ተለሳልሶ ቀርቦ የያዙትን ማስለቀቅ ከገነት ጀምሮ የሚፈታተነን ከይሴአዊ መንገድ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ደጋግመው እየበደሏት ነው፡፡ ጅማ ላይ አሁንም የንጹሐን ደም በሃይማኖት የተነሣ እየፈሰሰ፤ ዛሬም ዝም በሉ ስንባል አንገት ደፍተን የምንቀመጥ ይመስልዎታልን? ለታሪካዊ ጥያቄ ታሪካዊ ስሕተት እየሠሩ እንደኾነ ሊያውቁት ይገባል፡፡ ጣልቃ የመግባቱ ነገር መቼ ነው የሚቆመው? ለምን ከመንገዳችን ዘወር አትሉልንም? በማስፈራራት፣ በማግባባት ከዓላማችን ለምን ታሰናክሉናላችሁ? እኛን ለማስቆም የማይደረግ ተንኮል የለምና የአይ ኤስ ሰዎች ተያዙ ብሎ መግለጫ በመስጠት መንገዳችንን ማወክ ሰኮናን መቀጥቀጥ ነው፡፡ ተይዘውም ከኾነ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሰልፍ ሲጠሩ መነገሩ በራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ እነ እገሌ አደጋ ሊጥሉ ስለሚችሉ የሚል ማስፈራሪያ ብቻ ሳይኾን ጣልቃ ገብነት ነው፡፡
Filed in: Amharic