>

የተሸጠው ሰልፍ!!!  ዘመድኩን በቀለ

የተሸጠው ሰልፍ!!! 
ዘመድኩን በቀለ
ይሄ አጭቤ ኮሚቴ በእለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ያቀደው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ   የጠራውን ስብሰባና ውጤቱን ካየ በኋላ  ሰልፉ በፖለቲከኞች ስለተጠለፈ አስቀርተነዋል ( አራዝመነዋል) ብለው እስክንድርን የጦስ ዶሮ ሊያደርጉት ፈልገው ነበር። አልተሳካም!!!
★ ማሳሰቢያ፤ ማስታወሻም፥ የአደባባይ ሰልፉ ቢቀርም ለሰልፉ የተዘጋጃችሁ ሁሉ ግን የዚያን ዕለት ነጭ ልብሳችሁን ለብሳቸሁ ቅዳሴ አስቀድሱ። በመጨረሻም ዘምራችሁ ወደየቤታችሁ ሂዱ። ቅድሚያ ግን ንስሐ እንግባ።።
 ቃሌንና ተማጽኖዬን ምስጋናዬንም መዝግቡልኝ። የምለምናችሁም፣ የማመሰግናችሁም ሰዎች ልመናዬንም ምስጋናዬንም ተቀበሉኝ።
•••
ሲጀመር ከቀድሞ ጀምሮ በዘመነ ኢህአዴግ ከሰልፍ የሚገኝ ምንም ዓይነት ውጤት እንደሌለ ተናግሬአለሁ። አሁን ይሄ እንደ ይሁዳ  ሽጦ ቅርጥፍ አድርጎ የበላንና ያስበላን ኮሚቴ ቀደም ሲል በቀጥታ መስመርም፣ በውስጥ መስመርም እየደወለ ስለሰልፉ አስፈላጊነት እንድጽፍ በብዙ ሲወተውተኝም ነበር። እኔ ግን  አልተቀበልኩትም ነበረ። ያልተቀበልኩትም ከአዘጋጆቹ ውስጥ እንኳን ለቤተ ክርስቲያን ለራሳቸውም የማይታመኑ ሰዎች ስለነበሩበት ነበር። ነገርግን በመጨረሻም የዛሬ ሳምንት አከባቢ በሰልፉ ውስጥ የማኅበረ ቅዱሳንን ያለወትሮው ጀግኖ በኮሚቴው የፊት መስመር ላይ መኖርን ሳይ፣ ነገሩም እየገፋ መጥቶ እዚህ ከደረሰ በኋላ መስመር እንዳይስትና ከመስመር እንዳይወጣ ለምን የራሴን አስተዋጽኦ አላደርግም ብዬ ሰተት ብዬ የገባሁት። እናም እኔ አልፀፀትም።
•••
አሁን ያለፈው አልፏል። ሁለተኛም አይለምደኝም። በአቋሜ ብቀጥል ጥሩ ነበር። ግን አልሆነም። አልጸጸትም። አልቆጭምም። ሆኖም ግን ምስጋና የማቀርብላቸው አካላት አሉኝ። እናም ምስጋናዬን እንደሚከተለው አቀርብላችኋለሁ።
•••
ይሄ አጭቤ ኮሚቴ የዛሬውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ያሰበው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የጠራውን ቀጠሮ ካየ በኋላ እስክንድርን የጦስ ዶሮ አድርገው ሰልፉ በፖለቲከኞች ስለተጠለፈ አስቀርተነዋል። አራዝመነዋል ብለው እስክንድርን ሊያስወግሩት ፈልገው ነበር። እኔም ይህቺ ዘዴያቸው ስለገባችኝ እስክንድር ነጋ የሚያከበርቸውን አንድ ታላቅ የሃይማኖት አባት ፈልጌ እስክንድር ጋ ሽምግልና ልኬ እስክንደር ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዳይሰጥ አስደርገነዋል። እስኬው ታላቅ ሰው። እኔን ሳትንቅ ስለሰማኸኝ እግዚአብሔር ያክብርህ። አንተ ያን ባታደርግ ኖሮ እነ “ዋቄ” ዛሬ አስበልተውህ ነበር። ክብርና ምስጋና ለመድኃኔዓለም ይግባው። ትከሻዬን ቀላል ሸከከኝ መሰለህ እስኬው። አመለጥካቸው። አከተመ።
•••
ስለዚህ የእስክንድር ሰበብ ሲታጣ፣ የጦስ ዶሮ ፍለጋ ተባዘነ። በኦነግና በአይሲስም ተሳበበ። በመጨረሻም የጸጥታና የደኅንነት ስጋት ስላለብኝ ሰልፉን አራዝሙልኝ ብሎ አረፈው። ያ ባይሆን ኖሮ የዛሬው መግለጫ እስክንድር ነጋ ስለገባበት ትተነዋል። ደንቃራ የሆነብን ራሱ እስክንድር ነጋ ነው ብለው እስክንድርን የጦስ ዶሮ ያደርጉት ነበር። የእስክንድር አምላክ ግን ታላቅ ነው።
•••
ሰልፉ የቀረው ሰልፉን ካዘጋጁት 9 ማኅበራት መካከል 7ቱ ማኅበራት ሰልፉ እንዲደረግ ተሟግተው፣ ልዩነታቸውንም አስመዝግበው ሲሆን 2ቱ ማኅበራት ደግሞ አይሆንም፤ አይደረግምም ለሌላ ጊዜም ይተላለፍ ብለው አቋማቸውን ገልጸው ነው። ዋና ዋናዎቹን በተለይ ጀግናውን ቀሲስ ምትኩን አስቀድመው ሸራተን ወስደው አስረውት ነው። ይሄን የወሰኑት።
•••
በመጨረሻም 2ቱ የአንድ እናት ልጆች የሆኑት መንትያ ማኅበራት 7ቱን ማኅበራት ተጭነው፣ ደፍጥጠው አሸንፈዋል። የሆነውና የደረሰኝ የድምጽ መረጃም ማስረጃም የሚያረጋግጠው ይሄንኑ ነው።
•••
አሁን ያለፈው አልፏል። ምድረ ቀዌ ሁላ። መጀመሪያም አቅምና አቋም ሳይኖርህ ወደዚህ ከባድ ኃላፊነት ወደ ሚጠይቅ ተግባር ባልገባህ ነበር። ከሃይማኖቱ ይልቅ ማኅበሩን የሚያመልክ ጨካኝና ራስ ወዳድ ስግብግብ ሁላ ጉዳዩን ሲይዘው ነው ነገሩ ሁሉ የተበላሸው።
•••
የእኔ የዘመዴ ተማጽኖዬን እንደሚከተለው አቀርባለሁ። ስሞት ስቀበርላችሁ። በእመ አምላክ በወላዲተ አምላክ ይሁንባችሁ። በተለይ በተለይ በዐማራ ክልል ያላችሁ የእምዬ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እንዲች ብላችሁ መስከረም 4 ሰልፍ እንዳትወጡ።
•••
ሙሉ ጎንደር፣ ሙሉ ጎጃም፣ ሙሉ ወሎ፣ ሙሉ ሸዋ፣ ሐረር፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ፣ ድሬደዋ፣ ናዝሬት፣ አሰላ፣ ደብረ ዘይት በተሰቀለው መድኃኔዓለም። በእማምላክ በወላዲተ አምላክ ብላችሁ፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል፣ በተክለ ሃይማኖት፣ በቅዱስ ላሊበላ፣ በቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ሰልፍ ብላችሁ እንዳትወጡ። ድንጋይ ተሸክሜ እማጸናችኋለሁ።
•••
አውቃለሁ እናንተ ሃይማኖተኞች ናችሁ። አውቃለሁ እናንተ ባለ ማዕተቦች ናችሁ። ከማኅበር ይልቅ ሀገር፣ ሃይማኖት የምታስቀድሙ ናችሁ። አውቃለሁ፣ እመሰክራለሁም ወንድ ሱሪ የታጠቃችሁ የቅዱሳን ልጆች ናችሁ። ሞትን የማትፈሩ፣ የሱስኒዮስን ሰይፍ በዝማሬ የተቀበላችሁ፣ የደርቡሽ፣ የእንግሊዝ የጣልያን ቦንብ ያላፈራረሳችሁ። የደርጉ መላኩ ተፈራ በሊማሊሞ ገደል ከትቶ ያልጨረሳችሁ፣ የህወሓት ገዳይ የአግአዚ ጦር ጨፍጭፎ ያላጠፋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ፣ እናንተም ልጆቹ የሆናችሁ አማኝ ባለ ማዕተቦች እንደሆናችሁ ዓለም ሁሉ የመሰከረው እውነት ነው።
•••
ነገር ግን እነ ጃዋር ፖለቲካ እንዳይሠሩበት፣ አጀንዳም አግኝተው እንዳይፎክሩበት እባካችሁ ሰልፍ ብላችሁ እንዳትወጡ። አደራ በሰማይ፣ አደራ በምድር። አባ ገብረእየሱስ የዋልድባው ወንድሜ፣ አባቴም እርስዎን አማላጅ አድርጌ ልኬዎታለሁ። ሰልፉን አዲስ አበባዎች ነገ ጠዋት እንኳ ቢጠሩት ሰርዙት። የድሃ እናት ዛሬም ማልቀስ የለባትም።
•••
የምነግራችሁ ግን ሰማዕትነት የግድ አለ። ዛሬ ተደብቀው ወይን እየጠጡ ከጎናችሁ ያልቆሙት የሲኖዶስ አባላትና ማኅበራት እሪሪሪ ድረሱልን ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣል። ቀኑ ሩቅ አይደለም። በጣም ቅርብ ነው። አፍንጫችን ስር ነው። መደበቂያ ምድር ሁላ ይጠፋል። ተፈትነው ሁላቸውም ወድቀዋል። ያንጊዜ ማኅበራቸው ሲያድናቸው እናያለን። ከባድ የኦርቶዶክሳዊያን ፈተና የሆነ ጊዜ ከፊታችን ይጠብቀናል። ንስሐ ገብቶ ሥጋወደሙ ተቀብሎ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ ብቻ ይሻገራታል። የአባቶች መልእክት ነው። ቢቻልና ቢሆን መከራው እንዲቀንስ ማዕጠንቱ እየታጠነ፣ ዝማሬና ምህላ እየተደረገ፣ በመስቀል እየተባረከ ቢለቀስ ብዬ ጓጉቼ ነበረ። አልሆነም። ኢሬቻ አሸንፏል።
•••
በዚህ ጉዳይ ዐቢይ አህመድ ያለውን ልንገራችሁና ጦማሬን ላብቃ። “ ኮሚቴው ሰልፉን ማድረግ ይችላል። ሕገ መንግሥታዊ መብታችሁም ነው። ውጡ አትውጡ ማለት አልችልም። ወቅቱ ግን ጥሩ አይደለም። እንኳን እናንተ እየዘመራችሁ ለምትሰለፉት እየተቃወሙስ ይወጡ የለም እንዴ? እናም መውጣት ትችላላችሁ። ነገር ግን እኔ ኃላፊነቱን አልወስድም። ለሚደርሰው ጥፋት ራሳችሁ ኃላፊነት ትወስዳላችሁ። አሁንም በኦርቶዶክስ ላይ ለደረሰው ጉዳት ይቅርታ አልጠይቅም። ሆኖም ግን ለደረሰው ውድመት ጥናት ተጠንቶ ይቅረብልኝ። ስማ ዳንኤል ለኮሚሽነሩ ይደወልለት። መሰለፍ ይችላሉ። ይህንን ነው የተናገረው።
•••
ቤተ ክህነቱ ኃላፊነት አልወስድም አለ። የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት በከተማዬ የተቃጠለ ቤተ ክርስቲያን ስለሌላ አይመለከተኝም አለ። አቡነ ቀለሜንጦስ የሰንበት ማደራጃ መምሪያው አያገባኝም ብለው ሸሹ። አቡነ ዮሴፍ ዘመዶቼ ጋር በዓልን ላሳልፍ ብለው ወደ ሀገራቸው ሄዱ። አቡነ ያሬድ በእነ ሰለሞን ቶልቻ ተጠመዘዙ። ቅዱስ ፓትርያርኩ እኔ ውጡም አትውጡም አልልልም ብለው አቋም ያዙ። በመጨረሻም 2 ድምጽ 7 ቱን አሸንፎ ሰልፉ እንዲቀር ሆኗል።
Filed in: Amharic