>
10:57 am - Wednesday November 30, 2022

ለመስከረም 4 ቀን ታቅዶ የነበረው ሰልፍ ዛሬ ላይ በድርድር ማራዘም ተቻለ፤ ነገስ?!? (ብርሀኑ አድማስ አንለይ)

ለመስከረም 4 ቀን ታቅዶ የነበረው ሰልፍ ዛሬ ላይ በድርድር ማራዘም ተቻለ፤ ነገስ?!?
ብርሀኑ አድማስ አንለይ
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ላትመለስ ተንሥታለች!!!
 
ሰልፉ ቢራዘምም ብዙ ነገሮች ላይ መሠረት እንደጣለ እምነቴ የጸና ነው፡፡ የመጀመሪያው እና ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጎ ማየት የምመኘው የሕዝበ ክርስቲያኑ መናበብና መግባባት ነው!!!
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
 በብሔራዊ ደረጃ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ በእኛ ቤት ገና በተግባር ያልተሞከረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁሉን ሥርዓት የሚያስይዝበትና ደካሞችንም ሳይቀር ለተሻለ ዐላማ የሚጠቅምበትን መንገድ የሚያዘጋጀው ከእኛ ፍላጎትና ዕቅድ ውጭ እንደሆነ እኔ በግሌ የተማርኩበት ይህ የመስከረም አራት ሰልፍ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ትላንትም የጻፍኩበት ለዚሁ ዐላማ ብቻ ነው፡፡ መነሻዬም ብዙጊዜ እንደማደርገው መርካቶ ደብረ ኃይል ራጉኤል ለአዲስ ዐመት ቅዳሴና ንግሥ በተገኘሁበት ከአካባቢው ልጆች የሰማኋቸው እውነተኛ መረጃዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ለጊዜው ይቆዩ፡፡
ኮሚቴው እጅግ በብዙ የሚያስመሰግን ጠንካራ ሥራ ሠርቶ ሁኔታውንም ለዚህ ቢያበቃውም የራሱ የሆኑ ድክመቶች መኖራቸውንም መካድ አይቻልም፡፡ ሆኖም ድክመቶቹ ቀረብ ብሎ ሀሳብ በመስጠት በመደገፍና ይጠቅማል ያሉትን በማሳየት ለውጤት የምናበቃበት እንጂ በውጭ ሆነን ተጠያቂ ስላልሆንና ኖረን ስላላየን ብቻ ግምታችን ይዘን የምንተችበትን መብት ሊሰጠን  አይችልም ብዬ አምናለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር በግሌ የተሰማኝን ተናግሬያለሁ፡፡ ውሳኔያቸውን ግን መቼም አከብራለሁ፡፡ እንዳላከበር የሚያስገድድ ሁኔታ ሲገጥመኝ ደግሞ አማራጭ የምለውን አደረጃጀት እጠቀማለሁ እንጂ ለስድድብ የምባገበዝበት ምክንያት ሊኖረኝ አይችልም፡፡
እውነቱን ለመናገር አብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ ሰው በበደሎቹ ሲያዝን ከመቆየቱና ለሃይማኖቱ ካለው እንደ ፍም የሚፋጅ ቅንዓቱ የተነሣ በውስጡ የታመቀውን ስሜት ለመገላገል በፍጹም ጥብዓትና ናፍቆት ቢዘጋጅም የኮሚቴውን ውሳኔ ለመስማት የነበረውን ዝግጅት መግለጫው በሚሰጥበት ቦታ እንደእኔ ተገኝቶ ላዬ ደግሞ በእውነት ልብ ያሞላል፤ ትልቅ ተስፋም ያሳድራል፡፡ እንደሌሎቹ ስውር ሥልጠና ሳይሰጠው፤ ኔት ወርክ ወይም ሴል ሳይዘረጋለት፣ ተሰብስቦ እንኳ በአካሔዶቹ ላይ የመመካከር እድል ሳያገኝ በዚህ ደረጃ መግባባት በርግጥም መንፈስ ቅዱስ ከአዲስ አበባ ወጣት ጋር መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶች ተንኮለኞች በጥበብ፤ ከእኛ ወገን ያሉ ገራገሮችም በቅንነት ተቆጥተውም ተቆጭተውም በሚያደርጓቸው ግፊቶች የመከፋፈል ሁኔታ ለመፍጠር ቢጣርም አልተሳካም፡፡ በዚህ እግዚአብሔርን በእጅጉ አመሰግነዋለሁ፡፡ ፈሪና ደፋር፣ ሞኝና ብልህ፣ ተሞዳሟጅና ተቆርቋሪ አድርገው ሊያቧድኑ የጣሩ ሁሉ አልተሳካላቸውም፡፡ ውሳኔያችሁ ይጠቅመም ይጉዳ፣ ትክክልም ይሁን ስሕተት አንድ ሀሳብ ስለሆናችሁ ብቻ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ትላንት ማታ በጹሑፍ ዛሬ በአካል ተገኝቼ ያሳሰብት አንድ ነገር ብትኖር አትከፋፈሉ የሚለው ብቻ ነበር፡፡ ይህን አድርጋችሁት ሳይ ደስታዬ ወሰን የለውም፤  በድጋሜ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ኅብረታችን ከብረት እየጠነከረ፤ ድምጻችን ከአድማስ አድማስ እንደ ሌሊት ጥሪ ኩልል ብሎ እየተሰማ መሔድ መጀመሩን የዛሬው ሁኔታ አስመስክሯል፤ ተመስገን ጌታየ፡፡
ኦርቶዶክስን አንቋሾ ኦርቶዶክሳዊያንን አሸማቅቆ ለመሔድ በብዙ የተተለመለት መንገድ ዛሬ መፍረስ ጀምሯል፤ በዚህ መንገድ ከቀጠልን ዝክሩ ጠፍቶ ቅዱስ ዳዊት “ኀሰስኩ ወኢረከብኩ መካኖ” – ‘ፈለግሁት የነበረበትም ቦታ ጠፋኝ’ እንዳለው ባድማው እስከማይገኝ ድረስ እንደሚጠፋ እምነቴ የጸና ነው፡፡ ኦርቶዶክስን የሚጠሉ ፖለቲከኞች፣ በማንቋሸሽና በማሸማቀቅ እንጓዛለን ብለው የሚያስቡ ሕልመኞች፣ ጨቋኝ፣ የነፍጠኞች ሃይማኖት፣ ወዘተርፈ የሚሉ ዘላባጆች ሁሉ ከዚህ በኋላ እንደ ፈለጉ በየሚዲያው እየደሰኮሩ የሚሔዱበት የጭቃ መንገድ ዛሬ ገደል አፋፍ ላይ አድርሶ የሚጠብቃቸውን መንገድ ያሳያቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያዋጣው መከባበር፣ መደማመጥና መግባባት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እስካሁን ተበታትነን በያለንበት አንዳንዶቻችን እያለቀስን፣ አንዳንዶቻችንም ከንፈር እየመጠጥን፣ በተናጥል እየተሰደብን የመጣንበት መንገድ  ከዚህ በኋላ ላይመለስ የተዘጋ እንደሆነ ተስምቶኛል፡፡ የሚያዋጣው መደራጃት፣ አዎ በብዙ መልኩ መደራጀት፣ መናበብ፣ መደማመጥና በአንድነት መጓዝ ነበረ፤ እነሆ በተግባር አንድ ተብሎ ተጀምሯል፡፡
አንዳንድ የዋሖች ይህን ኮሚቴ የመደራደር መብት ማን ሰጠው ይላሉ? የቅንነትና የፍርሃት ስለሆነ  አልነቅፍም፡፡ ግን የሚደራደረው እኮ በክርስቲያኖች መብት ላይ እንጂ በሃይማኖታቸው እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አይደለም ፡፡ በዚህም ላይ እንኳ እኔን ኤወክሉም የሚል በግድ ወክለንሃል ያለውም የለም፡፡ በዚያው መጠንም ደግሞ ሌላውን ተቀመጡ የማለት መብትም እንደሌለው ወይም ደግሞ አትውክሉም ብሎ ለመናገር እርሱንም የወከለው እንደሌለ መረዳትም አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው የክርስቲያኖችን መብት ሲጥስና ተደራጅቶ እንደፈለገ ሲቦርቅ ዝም ብሎ ለተገፉት ተደራድሮ መብት የሚያስከበር ውጥን ሲታይ የጎደለውን እየሞሉ መሔድ እንጂ አንዱ በጀመረው ገብቶ መተቼት ከዚህ በኋላ መታየት የለበትም፡፡ ኮሚቴውን ከማጠናከርና በሌሎች ታላላቅ ሰዎች ጭምር ደግፎ ከመሔድ በቀር አሁን ሌላ አማራጭ ለእኔ በግሌ አይተየኝም፡፡ የተሻለ ነገር ያለውና በሌላ መንገድም ተደራጅተን ብንሞክር የሚል ካለ ይምጣ እርሱንም ድጋፍ እንሰጠዋለን፤ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም፡፡ በራሳቸው የግል ቁጭት ተነሥተው መረጃ አሰባስበው በብዙ ድካም ከዚህ የደረሱትን ሰዎች ተነሥቶ መርገም ግን ራስን ከመርገም የተለየ ውጤት አይኖረውም፤ ትልቅ ስንፍናም ይመስለኛል፡፡
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አላማችን ሌሎችን ማስደንገጥ፣ ማስፈራራት፣ ኃይላችን ማሳየትም አይደለም፡፡ በኃይላችን ለመመካት ማሰብ የመጀመሪያውና ትልቁ ጉዳት እግዚአብሔርን ከእኛ የሚያርቅ መሆኑ ነው፡፡ ኮሚቴው በመግለጫው እንደጠቀሰውም በሚችለው መጠን ከገዳም አባቶች ጀምሮ ብዙ አካላትን ለማማከር ያደረገውን ጥረት እያደነቅሁ ከዚህ የተሻለ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ነቅቶና ተግቶ በመሥራት የጀመረውን ጉዞ አጠናክሮ እንደሚሔድ እምነቴ የጸና ነው፡፡ ይህን ካደረገ የእግዚአብሔር ኃይል ገና ይገለጻል፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ እንዳየነውም ብዙ ሥራ ይሠራል፤ እግዚአብሔር ትሑታንን ይወድዳልና፡፡ በዚህ መሐል አንዳንድ ምክሮችን ከብዙ አካላት በተገቢው መንገድ ማግኘትም ይጠቅማል፡፡ ለጊዜው አንዳንድ ነገሮች እኔም እንደተሰማኝ ልጠቁም፡፡ ካለው ያካፈለ ንፉግ አይባልም ይባላልና፡፡
ወከባዎች፣ ማስፈራራቶች (የደኅንነትም የፖሊስም) ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ማራገብና ማውራት በጣም የደካማ ሰዎች ጠባይ መሆኑን አውቆ ማቆም ተገቢ ነው፡፡ እንኳን አሁን ኦርቶዶክስን ለማጥፋት የተደራጁ አካላት በብዛት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ይቅርና መንግሥት ለፖለቲካው ሥጋት ናቸው ብሎ ባሰበ ጊዜ ብቻ በአንዳንዶቻችን ላይ ያደርገው የነበረው ወከባ ማስፈራራት በጣም ብዙ ነው፡፡ እኔ በግሌ ከዚህ በፊት ከታዘብኳቸው ለማስፈራራት ሲባል በአንድ በሚያስጠላና በሰገራ በተሞላ ቤት ብቻን አድርጎ እዛው እንደሚቀሩ ከማስፈራራት አንስቶ ከዚህም የተለዩ ሁኔታዎች የለመድናቸው መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ እኔ በተግባር ባየሁት አብዛኛዎቹ እንደ ቴርሞሜትር ሙቀት መለኪያዎች ናቸው፡፡ ከዚህም አልፎ በአንዳንድ ወንድሞቻችን ላይ እንዳየነው ከእሥር እስከ ግርፋት ቢያጋጥም ለዐላማ የሚያደርጉት ነገር አይመጻደቁበትምና ከቁብ የሚገባ አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ማውራት ጥቅም አለው ብዬ አላምንም፡፡ ሁሉም የሚጻፈበት የሚነገርበትም ጊዜ አለው፡፡ አሁን ግን ትግል ላይ ሆኖ ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡ ማተኮር የሚገባው ዓላማ ላይ ብቻ ነው፡፡ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ እንደማይቀረው እነዚህን ነገሮች ፈርቶ ስራ መሥራት አይቻልም፡፡ ለዐላማ የሚከፈልም ለወሬ አይናኝም፡፡
ሁለተኛ ከተለያዩ አካላት በብልሐት ለሚፈጠሩ ወሬዎች ጆሮ መስጠት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን በማንኛውም ትግል ውስጥ የመጀመሪያው ጠንካራ የውጊያ ስልት ወሬ ነው፡፡ ይህን መቋቋም ያልቻለ ለውጤት ሊበቃ አይችልም፡፡ ለተወራ ወሬ ሁሉ መልስ ለመስጠት መዳከርም ሞኝነት ነው፡፡ ወሬ ዛሬ የራሱ ሳይንስ አለው፡፡ ፕሮፖጋንዳ ማለት እኮ ሳይንስን ወይም የአድማጭና የተቀባይ ሥነ ልቡናን በማጥናት የተዘጋጀ ወሬ ማለት ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ እንኳን ለጦር ለወሬም አልፈራም ያሉትም ለዚህ ነው፡፡ ጀግና ወሬ አይፈራም፡፡  ወሬን ማሸነፍ የቻለ ሁሉንም ማሸነፍ ይችላል፡፡ ባደግንበት ማኅበረሰብ ወሬ ለመስማት የጓጓን ሰው “እስኪ ለወሬ ሞትኩ በል” እያሉ የወሬ ስሜቱን እየገቱ ያሳድጉ የነበረው ወላጆቻችን ምን ዐይነት ረቂቅ እንደነበሩ የገባኝ አሁን ከተማ ገብቼ የወሬን ጉልበት በተግባርም በትምህርትም ስመለከተው ነው፡፡ ስለዚህ ለወሬ የሞተውን እንደ አሳዳጊዎቻችን ስቃችሁ ተውት፡፡
ወሬና መረጃም የተለያየ ነው፡፡ መረጃን መረጃ የሚያሰኙትና ብቻ ሳይሆን የሚየደረጉትም ተጠቃሚዎቹ ናቸው፡፡ ካልሆነ እርሱም ቢሆን ጠቀሜታው ለጠላት ይሆናል፡፡ አንድ ወታደር ቦንብና ፈንጅን የራሱ ክልል ውስጥ እንዳልባሌ ቢጥለው ራሱን እንደሚጎዳው ሁሉ መረጃም እንዳልባሌ ከጣሉት የራስ ክልል ውስጥ ያፈነዱት ቦንብ ማለት ነው፡፡
ልክ እንደወሬው ሌላም አደገኛ ወጥመድ መኖሩን ማስታወስ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ በስሜታዊ ምስጋና መኮፈስና በስሜታዊ ስድብና ትችት መኮሰስ፡፡ መጀመሪያውኑ ምስጋና ፈላጊ፣ እና ትችት ፈሪ እንደመሆን ያለ ደካማ ጠባይ የለምና በእነዚህ በሽታ የተለከፈ ሰው ካለ በጊዜ ከኮሚቴነት ቢሰናበት ይሻለዋል፡፡ ዐላማ ያለው ሰው ለሁለቱም የሚከፈት ልብ ሊኖረው አይገባም፡፡ እነዚህ ማለት ሁለት ትልልቅ የሌባ በሮች ማለት ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ስሕተትን ላለማየት በግትርነት መቆም ማለትም ደግሞ አይደለም፡፡ ነገሮችን በአግባቡ መርምሮ ከጠላት ብቻ ሳይሆን ከሞኝ ወዳጅ የሚመጣ ሁለቱንም ፈተና ተጋፍጦ የማለፍ ልበሙሉነትን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡
ከዚህም ሁሉ ጋር ሁሉን ነገር ሥርዓት ባለው መንገድ እየተወያዩ ለወሰኑት ውሳኔ እስከመጨረሻው መታመን ያስፈልጋል፡፡ ውሳኔን አስፈላጊ ከሆነ በሌላ ውሳኔ መሻር እንጂ የወሰኑትን ትቶ ሌላ ከማድረግ መጀመሪያ አለመወሰን ይሻላል፡፡ ከወሰኑ በኋላ ውሳኔው ስሕተት እንኳ ቢኖረው በአግባቡ እስኪታረም ድረስ ምሥጢር ጠብቆ ለሌላ ውይይት ማብቃት እንጂ እነ እገሌ ናቸው እንዲህ ያደረጉ እያሉ በየሜዳው መለፍለፍ ራስን ከማስገመትና ዐላማን ሜዳ ላይ ከመጣል ያለፈ ጥቅም የለውምና ሐዋርያው እንዳለው ሁሉን በአግባቡና በሥርዓት ብቻ ለመፈጸም መጣር ጊዜ የማይሰጠው ግዴታ መሆኑን ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚነግሩን ሰዎች ቀናዎችና ተቆርቋሪዎች በመሆናቸው ብቻ ሀሳባቸው ሁልጊዜም ትክክል ሊሆን አይችልምና አክብሮ ሰምቶ እንደየሁኔታው መተግበር ተገቢ ነው፡፡ የሚጠቅመውን መውሰድ የማይጠቅመውን ደግሞ አቆይቶ ማየት፡፡ እኔ ያልኩት ካልሆነ ለሚለው ግን ምንም ዐይነት ጭንቀት አያስፈልግም፤ ራሱ ያድርግና ያሳይ፡፡ እነዚህን የምጠቁመው አይታወቁም ብዬ ሳይሆን በዚህ መንገድ የምትተቹ መሆኑን ቀድሞ ለመናገር ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ኮሚቴያችን እያጠነከርን ከሔድን እጅግ ብዙ የተከበሩ ባለሞያዎች ድምጻቸውን ሳያሰሙ መጥተው እንደሚያግዙ እምነቴ የጸና ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር እንዲሆን እየተመኘሁ በብዙ ሐሳብ እየጎተትናችሁ ላሳያችሁት ትዕግሥት ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የሚያዋጣን አንድነትና መሰማማት ብቻ ነውና  እኔ በግሌ ኮሚቴው የሚለውን አከብራለሁ፡፡ በዚሁ ከቀጠልን የማንደረምሰው የጠላት ምሽግ አይኖርም፡፡ በርግጥም ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ላትመለስ ተነሥታለች፤ ልጆቿም አብረው በልዕልና ይጓዛሉ፡፡ ከተጓዦቹ ያድረገን፤ አሜን፡፡
Filed in: Amharic