>
6:10 am - Wednesday December 7, 2022

እንግዲያውስ ሕዝብ ይወቅ! (ጌታቸው ሽፈራው)

እንግዲያውስ ሕዝብ ይወቅ!
ጌታቸው ሽፈራው
አዴፓ  በ2011 ዓ/ም መጀመርያ ወራት ባደረገው ስብሰባ አንድ ድክመቱን አመነ። ከሌሎች በባሰ ብአዴን/አዴፓ ስለ ክልሉ ሕዝብ የረባ መረጃ አይደርሰውም። ትህነግ/ሕወሓት በጎንደር፣ ኦነግ በወሎና በሸዋ የአማራን ሕዝብ ሲያምስ አዴፓ/ብአዴን መረጃ አልነበረውም። ቀድሞ መተንበይ፣ መተንተን፣ መከላከል የሚችልበት መረጃና የመረጃ ስርዓት አልነበረውም። ሌሎቹ  አልፈው ሲያጠቁ አዴፓ ግን የአማራ ሕዝብ ላይ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ በሚዲያ ነበር የሚሰማው። ያም ሆኖ  የሚረባ እዝ ስላልነበር መፍትሔ ለማምጣትም ሲከብድ  ታይቷል። አዴፓ ይህን ድክመቱን አምኖ፣ ከሌሎች ክልሎች እጅግ ያነሰም ቢሆን መረጃ የሚሰበስቡለት ሰዎች መኖር እንዳለባቸው አመነ። ይህን ለመስራት ዋነኛው ሰው ኮ/ል አለበል አማረ እንደሚሆን አምኖ የቤት ስራ ሰጠው።
ኮ/ል አለበል ይህን ስራ ከውኗል። ሰራተኞቹን አሰልጥኗል።  ተመርቀው ወደ ስራ ሊገቡ አንድ ወር ሲቀራቸው የሰኔ 15ቱ ክስተት አደናቀፈ። እነ ኮ/ል አለበል ይሰሩት የነበረው ስራ ከዚህና ከዚህ ጋር የተያያዘ ብቻ ነበር። ይህኛውን ስራ እየከወኑም ቢሆን ግን ላይ ታች ይሉ ነበር። በዚህ ወቅትም ወደ ከሚሴና ሸዋ እየሄዱ  ጥቃት ሲከላከሉ ቆይተዋል። ሰኔ 15/2011 ዓ/ም ችግር ሲፈጠርም እነ ኮ/ል አለበል ከዚሁ አካባቢ እንዲመለሱ ተደርገው፣ መግለጫ እንዲሰጡ ተደርገው ነው የታሰሩት።
እነ ኮ/ል አለበል ስራ የአማራን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል  ነበር የሰሩት። ሆኖም ከሰኔ 16 ጀምሮ ለእስር ተዳርገዋል። እነ ኮ/ል አለበል የክልሉን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ያሰለጠኗቸው የመረጃ ሰራተኞች (በርካታ ሚሊዮን ብር ፈስሶ)  እንዲበተኑ ተደርጓል። በእስር ላይ የሚገኙም አሉ።  እነዚህ ሰራተኞች ስልጠና ወስደው ገና ስራ እንኳን ባልገቡበት “አሳምነው ያሰለጠናቸው ናቸው” ተብለው ለእስር ተዳርገዋል። በመረሰቱ እነዚህ ሰልጣኞች ስራ አልጀመሩም።   እነዚህን ልጆች ያሰጠኗቸው ሰዎች  ከሰኔ 15  በኋላም የሌሎች ክልሎችን መረጃ ሰራተኞች አሰልጥነዋል።
(ይህን ጉዳይ የምፅፈው የፌደራል መንግስቱም፣ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሌሎችም የሚያውቁት በመሆኑ ነው። እንዲያውም ተለጥጦ እነዚህ ሕዝብ ላይ የሚፈፀምን ጥቃት የሚከላከሉ ሰልጣኞች ለሌላ አላማ  እንደሚሰለጥኑ ተደርጎ ሪፖርት ሲፃፍ ከርሟል። በአንፃሩ ሕዝብ መረጃ ላይኖረው ይችላል በሚል ነው።)
እነ ኮ/ል አለበል ለዚህ ስራ ወደ ክልል ከመጡ ጀምሮ ደስተኛ ያልሆኑ አመራሮች እንደነበሩ ይታወቃል። ሰኔ 15ን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው እነ ኮ/ል አለበል አማረንና የተወሰኑ ሰልጣኞችን አስረው ሌሎቹን በትነዋቸዋል።  ሰልጣኞቹ ከፖለቲካ ነፃ ሆነው ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ የነበሩ ሲሆኑ  አንዳንድ የአዴፓ ሰዎች ይህን ለሕዝብና ለሕዝብ ብቻ ይሰራል ተብሎ የተገመተ ኃይል የፈለጉት አይመስሉም።  በሰኔ 15  ሰበብ የታሰሩት አንዳንድ ሰልጣኞች ሲፈቱ ሌሎቹ በእስር ላይ ናቸው። የአማራ ሕዝብ  ጥቃት ላይ ሆኖም ቀሪዎቹ እንዲበተኑ ሆኗል።
እነ ኮ/ል አለበል ከታሰሩ ጀምሮ ማስረጃ አልመጣባቸውም። እንዲያውም  ከሰኔ 15 ግድያ በተአምር የተረፉ ሰዎች ናቸው። “ከተፈቱ ይለይልናል” የሚል የአማራውን ብርታት የማይፈልግም እንዳለ  እየሰማን ነው።
እነ ኮ/ል አለበል ላይ የምትቀርበው አንድ ነገር “ችግር እንደሚከሰት እያወቁ ሪፖርት አላደረጉም” የሚል ነው። ይህ  እነሱን ሆን ብሎ በእስር ላይ ለማቆየት የመጣች ምክንያት እንጅ ችግር እንደነበር ይታወቅ ነበር። አይደለም የአዴፓ ከፍተኛ አመራር ይቅርና ከተማው ውስጥ ብዙ ሰው የሚያውቀው ችግር ነበር። አዴፓ ከሁለት ጊዜ በላይ ስብሰባ ተቀምጦ ጉዳዩን ለማርገብ ሞክሯል። “ፋኖ ይውደም” ተብሎበታል የተባለው ስብሰባ አንደኛው ነበር።  ሰኔ ወር መጀመርያ አቶ ምግባሩ ከበደ  መወያያ ፅሁፍ አቅርቦ የተወያዩበት ሌላኛው ነበር። እነ አለበል “ሪፖርት አያደርጉም” የተባለውም ከእውነት  የራቀ ነው።  የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ችግር መኖሩን አውቀው ምክክር እንዲደረግበት ጥረት ያደረጉበትን ሁሉ ማስታወስ ተገቢ ነው። በዚህ ጉዳይ እነ ዮሃንስ ቧ ያለው፣ መላኩ አለበል፣ ላቀ አያሌው ጉዳዩን የማያውቁት ሆነው አይደለም። ለአዴፓ አንድነት ሲባል ለአማራ ሕዝብ ዘብ የቆሙና መቆም የሚችሉት በእስር እንዲማቅቁ ሊፈረድባቸው አይገባም!
  እነ ኮ/ል አለበል አማረ “ሪፖርት አላደረጉም የሚባለውን ማሞኛ ለሟች ቤተሰቦች ጭምር ለማስያዝ የተሞከረበት አካሄድ የሚያሳዝን ነው። አንድ ሰሞን የአዴፓ አመራሮች ራሱን ኮ/ል አለበልን ሽምግልና ልከው እንደነበር ሊያስታውሱት  ይገባል።
ዋናው ነገር እነ አለበል አማረ የታሰሩት ከሰኔ 15 ጋር ግንኙነት ኖሯቸው አይደለም። ሰኔ 15 እንደሚከሰት የአዴፓ አመራር ጠፍቶት አይደለም።    ከአዴፓ ጋር ግንኙነት የሌላቸው አካላትም ሽምግልና ለመላክ  ጥረት ማድረጋቸው ሁሉ እናውቃለን።  የአዴፓ አመራር ልዩነት እንደነበር ያውቅ ነበር። እነ  ኮ/ል አለበልና ጄ/ል ተፈራ ማሞን በእስር ለማቆየት የሚፈልገው አመራር አማራ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዳይሄድ የሚፈልግ ካልሆነ ሌላ ሊባል አይችልም።
አንዳንድ መረጃዎችን ይዘን ዝም የምንለው በክልሉ ላይ ያለው ችግር ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆንና ከዕለት ዕለት ይሻሻላል በሚል እንጅ ንፁሃንን ሲታፈኑ ዝም ልንል አይደለም።
የአዴፓም ሆነ የአማራው ሕዝብ ችግር የሚፈታው ሰኔ 15 የተፈጠረው ክስተት በገለለልተኛ አካል ተመርምሮ ሕዝብ እውነታውን ሲያውቅ ነው። ሆኖም የዚህን ክስተት ጉዳይ ምርምራ ይዞታል። ይህ ምርመራ እውነታውን ያወጣል ይሆናል የሚል ግምት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። በንፁሃን ላይ የሚደረው አፈና ግን በምርመራው ላይ ሌላ ጥላ የሚያጠላ እየሆነ ነው።
እነ ኮ/ል አለበል ለአማራ ሕዝብ መከታ  የሚሆን ተቋም እንዳይመሰርቱ እንቅፋት ሲሆን የነበረና አጋጣሚውን ያገኘ አካል “ምርመራቸው በፌደራል መንግስቱ መታየት አለበት” እስከማለት ደርሷል። በፍርድ ቤት ጣልቃ እየገባ፣ ዳኞችንና ሌሎችንም እያዋከበ ይህን አላማውን ለማስፈፀም ጥረት እያደረገ ነው። እነዚህ አካላት ከዚህ ፀረ አማራ ተግባራቸው ካልተቆጠቡ የአማራው ፖለቲካ ሳንካ ሊገጥመው እንደሚችል መገመት አይከብድም!
ሕዝብ ግን ማወቅ አለበት። እነ ኮ/ል አለበል አማረ ወንጀል ሰርተዋል ከተባለ ያ ወንጀላቸው አማራን ከጥቃት ለመከላከል መጣራቸው ብቻ ነው! ይህን ደግሞ የሰሩት አዴፓ አምኖበት፣ በጀትም በጅቶላቸው ነው።
እነ ኮ/ል አለበል ከእስር መፈታት ብቻ አይደለም የሚገባቸው። ወደ ቦታቸው ተመልሰው የጀመሩትን ስራቸውን መከወን አማራውን ከጥቃት መከላከል ይገባቸዋል።  ከየትም ስራቸውን ጥለውና ቤተሰብ በትነው  ለአማራ ሕዝብ ደሕንነት ሲባል ስልጠና የወሰዱ አካላትም ከመሳደድና ከእስር ወጥተው ሕዝባቸው ሊያገለግሉ ይገባል። በስልጠናው ወቅት አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩ ይታወቃል። ይህ ችግር ደግሞ የእነ አለበል አይደለም። የአዴፓ አመራር ነው። ይህን አስፈላጊ ከሆነ ሌላ ቀን የምንመለስበት ይሆናል። ሆኖም በስልጠናው ወቅት ችግር ነበር ከተባለም የሚስተካከለው ነገር ተስተካክሎ እነ አለበል ስራቸውን መቀጠል እንጅ ሰበብ እየተፈለገ በእስር ሊማቅቁ አይገባም!
Filed in: Amharic