>

በሀዲያ አካባቢ ቤተ ክርስቲያን መብቷ እየተገፈፈ ነው!! (አብርሀም አንዳርጌ)

በሀዲያ አካባቢ ቤተ ክርስቲያን መብቷ እየተገፈፈ ነው!!
አብርሀም አንዳርጌ
 
 * “መልካም ወጣት” በሚል ሰበብ መንግስት ሆነ ብሎ ባደራጃቸው ሰዎች አማካኝነት የሃይማኖት ወረራ እያደረገ ይገኛል!
 
በጣም አስገራሚው ነገር አርባ ዓመት ስትለምን የኖረችው ቤተ ክርስቲያን እያለች ትላንት ለመጣው ዮናታን አክሊሉ ለ”መልካም ወጣት” ማዕከል ግንባታ የሚሆን መቶ ሺህ ካሬ ሜትር እንዲሰጠው የዞኑ ከተማ አሰተዳደር ፈቅዶለቷል።
—–
በ”መልካም ወጣት” ስም እየተሰራ ያለውን የሃይማኖት እና የመሬት ወረራ በሚገባ ልብ ላለው ሰው እጅግ አሳዛኝ ነው። በተለይም በደቡባዊ ኢትዮጵያ ፤ ቤተ ክርስቲያን ቀደምት ይዞታዎቿን በልማትና በከተማ ውበት ሰበብ እየተነጠቀች ከፍተኛ በደል እየደረሰባት ይገኛል። ይሄ ሳያንሳት ሰሞኑን “መልካም ወጣት” በሚል ሰበብ መንግስት ሆነ ብሎ ባደራጃቸው ሰዎች አማካኝነት የሃይማኖት ወሪራ እያደረገ ይገኛል።
ባሳለፍነው ሳምንት በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ የታየውን ህገወጥ አሰራር እንኳን ብንመለከት እውነት መንግስት አለ ወይ የሚያስብል ነው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአርባ ዓመታት የጥምቀተ ባህር ማክበሪያ ቦታ አጥታ በየጊዜው የሀገረ ስብከቱ ሰራተኞች እንዲሁም ምእመናኖቿ ሳይሰለቹ በየዘመናቱ ለነበሩት የመንግስት ባለስልጣናት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም ሰሚ አጥተው እስከዛሬ ደርሰዋል። በጣም አስገራሚው ነገር አርባ ዓመት ስትለምን የኖረችው ቤተ ክርስቲያን እያለች ትላንት ለመጣው ዮናታን አክሊሉ የ”መልካም ወጣት” ማዕከል ግንባታ የሚሆን መቶ ሺህ ካሬ ሜትር እንዲሰጠው የዞኑ ከተማ አሰተዳደር ፈቅዶለቷል።
ቤተ ክርስቲያን ከግራኝ አህመድ ቦሃላ የተቃጣባት ትልቁ ወረራ በዚህ ዘመን ይመስለኛል ፤ ቤተ ክርስትያን ካህናቶቿ ሲታረዱ፤ ልጆቿ ሲበተኑ ፤ ቅጥሮቿ ሲደፈሩ በዚህ በኩል መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም እየተባለ ራሱ መንግስት መልኩን ቀይሮ አንዱን ሃይማኖት ሲጠቅም አንዱን ሲጎዳ በገሃድ ይታያል ፤ ልክ መንግስታዊ ሃይማኖት ያለ እስኪ መስል ድረስ ፤ እንደ ምሳሌ የሆሳዕናን አነሳን እንጂ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እየተሰራ ያለው አሻጥር የአደባባይ ምስጢር ነው ።
በጣም የሚገርመው ነገር ቢኖር ዓምና የ2011 ዓ.ም የጥምቀት በዓል በሚከበርበት እለት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ  የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሕርያቆስ “ትንሽ ቦታ ቆርሳችሁ ስጡን” በማለት በተማጽኖዎና በምሬት ለዞኑ አስተዳዳሪ እንዲሁም ለከተማው ከንቲባ እዚያው በተገኙበት አቅርበው ፤ አመራሮቹም በአጭር ጊዜ መልስ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ቢሄዱም ከክልሉም ይሰጣቸው የሚል ደብዳቤ ቢመጣም የዞኑ ባለ ሥልጣናት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም።
በሆሳዕና ከተማ ለብዙ ዓመታት የጥምቀት በዐልን እያከበረችበት ስትገለገልበት የነበረችበትን ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ይሰጠኝ ፤ ቦታውን ላልማ ፤ ሥርዓተ አምልኮዬን ልፈጽም ፤ መብቴ ይከበርልኝ እያለች ስትጮህ አለመስማት መልስ አለመስጠት ምን ያህል ሥርዓቱ መበላሸቱን የሚያሳይ ነው። አሁንም በዞኑ ያላችሁ ባለሥልጣናት የሕዝቡን መብት አክብሩ እያደረጋችሁት ያለውን የሃይማኖት ወረራ አቁሙ እንላለን።
ከቤተ ክርስቲያን ላይ እጃችሁን አንሱ
Filed in: Amharic