>

ኢትዮጵያን አድናለሁ ተብሎም ተወላግድ ቆሞም አይሆንም! በሰባራ ሚዛን የሚቀና ሃገር የለም!!! (መስከረም አበራ)

ኢትዮጵያን አድናለሁ ተብሎም ተወላግድ ቆሞም አይሆንም! በሰባራ ሚዛን የሚቀና ሃገር የለም!!!
መስከረም አበራ
* የማይነካው በመነካቱ ህዝብ አዝኗል፣አዝኖም ጎዳና ወጥቷል-የጨዋ አወጣጥ። ይህን ጥያቄ ችላ ማለት ዋጋ ያስከፍላል!
 መንግስት ዶሮ ሲታመም በሬ ማረዱን ማቆም አለበት። ባለፈው ሰሞን አንድ የሲኖዶስ እንኳን አባል ያልሆነ ከክድርናውም ከንግዱም፣ከሊጡም ከወጡም የሚንከወከው ሰውዬ የሆነ ስርቻ ውስጥ ቁጭ ብሎ የሰጠውን መግለጫ በቀጥታ ስርጭት ሳይቀር ያስተላለፉ የመንግስት ሚዲያዎች የሲኖዶሱን መግለጫ ሳይዘግቡ የቀሩት ነገር ለዶሮ ህመም በሬ የማረድ ቂልነት ነው።የዛሬ ሳምንት የተደረገውን ሰፊ ህዝባዊ ሰልፍም እንዲሁ አልዘገቡም።
 በበኩሌ ለዚህ ድርጊት የምሰጠው ስም አጥቼ ተደናግሬ ቀርቻለሁ።አንድ የገባኝ ነገር መንግስት ከፍተኛ የሚዛናዊነት እና የፖለቲካ ብልህነት ችግር እንዳለበት ነው።  ይህ የሚመጣው ከመንግስት ወልጋዳ አቋም ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያን አድናለሁ ተብሎም ተወላግድ ቆሞም አይሆንም።በሰባራ ሚዛን የሚቀና ሃገር የለም።
 ዛሬ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተደረገውን ሰልፍ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ አይቻለሁ። አዎ!እንዲህ መስተካከል ብቻ የምንሳሳላትን ኢትዮጵያን በቸር ውሎ ያሳድራል!ይህን የመንግስትን መስተካከል የሚያመጣው ደግሞ የህዝብ ትግል ነው።ህዝብ ሲታገል ሃገሩን እንዳይጨፈልቅ ብቻ ተጠንቅቆ፣ከሃይል እና ሁከት ተቆጥቦ እንዲህ በሰላም ቅሬታን ማሰማት የነገስታትን ልብ ወደልቦናው መመለሱ አይቀርም!
በስተመጨረሻም በእነዚህ ፎቶዎች ላይ ያየሁትን የሃገሬን ሰው የሁልጊዜ አዋቂነት አይቼ መገረሜ አልቀረም!
Filed in: Amharic