>
5:18 pm - Sunday June 15, 6183

ኢሬቻ - የኦሮሙማ ካስማ!!! (በፈቃዱ ዘ ሃይሉ)

ኢሬቻ – የኦሮሙማ ካስማ!!!
በፈቃዱ ዘ ሃይሉ
“ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በአማራ አንብሮ እና በኦሮሞ ተፃርሮ መሐል በተፈጠረ መስተፃምሮ (synthesis) ነው!”
 ዶናልድ ሌቪን 
ይህ ሰው የነገረንን አምነን የተቀበልን፣ ተቀብለንም በሰላም እየኖርን ያለን ሰዎች አለን። በዚህ ጽሑፍ እንደምንረዳው የአማራ አንብሮ (Amhara Thesis) ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል በክርስቲያናዊ ትውፊት እና ሲወርድ ሰወራረድ በመጣ የንግሥና ስርዓት የተገነባበት ግዛተ ዐፄን ይወክላል፤ የኦሮሞ ተፃርሮ (Oromo Anti-thesis) ደግሞ ከሰሜኑ ጋር በፍልሰትም፣ በጦርነትም፣ በመገበርም፣ በመጋባትም፣ በመዋሐድም የተቀላቀለውን አገር በቀል እምነት እና እስልምና ተከታይ ማኅበረሰቦች የሚያቅፈውን የደቡብ እና ምሥራቁን ክፍል ይወክላል። “ይወክላል” የሚለውን የተጠቀምኩበት ሆነ ብዬ ነው፤ ኢትዮጵያ የሁለቱ ዘውግ ሕዝቦች ብቻ ሥሪት ሳትሆን፥ በሁለቱ ትርክቶች ማዕቀፍ ያለች አገር መሆኗን ለማመልከት ነው።
የአንብሮው እና የተፃርሮው ድርድር ክፍለ ዘመናትን አቋርጦ ዛሬም ደርሷል። ከ1950ዎቹ ጀምሮ ያንሰራራው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ግን ሕዝቦች እና ባሕሎቻቸው ሲቀላቀሉ፣ ተሸናፊው ያሸናፊውን ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት ተቀብሎ እና ተመሳስሎ መኖሩ ቀረ [ማለት ይቻላል]። ከዚያ በኋላ የኦሮሞ ብሔርተኞች የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን (ወይም በተለምዶ “ኢትዮጵያዊ” ማንነት የሚባለውን) በተፃርሮ ትርክታቸው ይሞግቱት ጀመሩ። የዚህ የተፃርሮ ሙግት ዋና አካሔድ ኦሮሙማን ማሳደግ ነበር። ኦሮሙማ – ኦሮሞነት ማለት ነው።
ኦሮሙማ በአሮሞ ቋንቋ፣ ባሕል እና እምነት የመኩራት ንቅናቄ ነው። የኦሮሞ እምነት የሚባለው በኢትዮጵያ ብዙ ተከታይ ካሏቸው እና ከመካከለኛው ምሥራቅ መጤ ከሆኑት አብርሃማዊ ሃይማኖቶች (ክርስትናና እስልምና) ቀድሞ እዚሁ እንደነበር የሚታመነው የዋቄፈና እምነት ነው። የዋቄፈና እምነት በጣም ሥር የሰደደ ጥንታዊ በዓል መሆኑን ለማወቅ ከክርስትና ጋር እንዴት እንደተዋሐደ መመለከት በቂ ነው። በተለይም የሴቶች ድርሻ የሆነው የዋቄፈና እምነት አካል – አቴቴ – በመንዝ አካባቢዎች እስከዛሬም ድረስ እንዴት እንደሚከበር መመልከት እና “አድባር” የሚባለው “የግንቦት ልደታ” በዓል ከአቴቴ ጋር ያለው ተመሣሥሎሽ መመልከት በቂ ነው። በኦሮቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች እና በዋቄፈና አማኞች ዘንድ ያለው የቄጤማ ፍቅርም ያለነገር የተመሣሠለ አይመሥለኝም። ሆኖም ዋቄፈና የእምነት ክብር ያልተሰጠው እምነት ሆኖ እስካሁን ዘልቋል።
የሆነ ሆኖ የኦሮሙማ ንቅናቄ ከዋቄፈና ክብረ በዓላት ሁሉ ኢሬቻን አንጥሮ አውጥቶታል። አሁን አሁን፣ ኢሬቻ የሃይማኖት መገለጫ ሳይሆን የኦሮሞነት መገለጫ ሆኗል ማለት ይቻላል። ለመጨረሻ ጊዜ የኢሬቻን አከባበር ልመለከት ወደ ቢሾፍቱ ሐይቅ የሔድኩት በ2009 ነው። ያኔ የፖለቲካው ተቃውሞ ጣሪያ የነካበት፣ የለውጥ ተስፋ ያንዣበበበት እንዲሁም አሳዛኙ እልቂት የደረሰበት አንደኛ ዓመት ስለነበር ታዳሚው በእልህና በተስፋ ጎርፎ የወጣበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ታዲያ በዓሉን ሊያከብሩ በአገር ባሕል ልብሶች ተሽቆጥቁጠው የመጡት ሰዎች የተለያየ እምነት ተከታዮች ነበሩ። አንገታቸው ላይ መስቀል ያሰሩ እና ራሳቸውን በሒጃብ የሸፈኑትም ብዙዎች ነበሩ። ኢሬቻን የሚያከብሩት የኦሮሞነታቸው ትውፊት እንደሆነ በመቁጠር ብቻ ነው።
ከዋቄፈና እምነት ድንቅ ጠባያት አንዱ አምላክ ጥቁር መሆኑ ነው፤ ዋቃ ጉራቻ – ጥቁር አምላክ፣ ጥቁር ሰማይ። ከነጭ የበላይነት ትርክት ጋር ተጋምዶ የመጣው አምላክን በነጭ የመሳል አባዜ በጥቁሮች ትውፊታዊ እዝነ ሕሊና ግን እንዳልነበረ ለማሳየት ከዚህ በላይ ነባራዊ እማኝ ያለ አይመስለኝም። እናም በኢሬቻ ቀን የእምነቱ ተከታዮች ጥቁር አምላካቸውን ስላዘነበው ዝናብ፣ ስላለመለመው መሬት ያመሰግኑታል። የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ በሰበቡ ኦሮሙማን ያንፀባርቁበታል።
ኢሬቻ ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ ሲከበር መግፍኤው ሃይማኖታዊም፣ ባሕላዊም ላይሆን ይችላል። ፖለቲካዊነቱ ከፍ ያለ ነው። የአከባበሩ ምክንያት ምንም ሆነ ምን ግን ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች አንዱ ስለሆነ ደስ ይላል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እምነቶች እና ባሕሎች ሁሉ በአዲስ አበባችን ቢከበሩ ደስታዬ ወደር የለውም።
ኢትዮጵያ ዥንጉርነቷን ይዛ ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic