>

በመቱ [ ሞቱ ] ዩኒቨርስቲ የተመደቡ የዐማራ ተማሪዎች ሰቆቃ !! (ዘመድኩን በቀለ)

በመቱ [ ሞቱ ] ዩኒቨርስቲ የተመደቡ  የዐማራ ተማሪዎች ሰቆቃ !!
ዘመድኩን በቀለ
ተማሪዎቹ ከተቻለ ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት ንገሩልንና ለዐቢይ አሕመድ ነግሮ ይራራልን ብለዋል። የምትችሉ ዳንኤልም ጋር ሆነ የምታውቋቸው የፌደራሉ ባለሥልጣናት ጋር ደውሉላቸው።
 
• ለአዴፓ ለእነ ንጉሡ ጥላሁን፣ ለእነ ላቀ አያሌው፣ ለእነ ዮሐንስ ቧያለው አትደውሉላቸው እነሱ አቅምም ፍላጎትም የላቸውም ብለዋል። መልካም የሰቆቃ ንባብ።
#ETHIOPIA | ~ በቶሎ ካልተደረሰላቸው በቀር ከ3600 እስከ 4000 ተማሪዎች ላይ ጠባሳ የታሪክ አሻራ የሚጥል ዘግናኝ ታሪክ መመዘገቡ አይቀሬ ነው።
•••
ከመቱ ዩኒቨርስቲ የሚሉ መልእክቶች በተደጋጋሚ ሲደርሱኝ የተለመደው የተማሪዎች ሰቆቃ ነው ብዬ ችላ ብዬ በእኔ ዕይታ ይብሳል ብዬ በማስበው አጀንዳ ላይ ብቻ ሳተኩር ቆይቻለሁ። አሁን ግን ሰሞኑን በተለይ ከትናንት ወዲያ የደረሰኝን መረጃ በቸልታ ማለፍ ስላልወደድኩ በቀጥታ መልእክቶቹን ሳይሰለች በተደጋጋሚ ይልክልኝ ወደነበረ አንድ ተማሪ ዘንድ ደወልኩ። እናም በሰማሁት ነገር ከምር አመመኝ። ፎቶ፣ ቪድዮ በሙሉ ላከልኝ። እናም ለእናንተ ላቀርብላችሁ ወደድኩ። አሁን አሁን ሞትና ሰቆቃ ስለተለመደ የሚያዝንና ለመፍትሄ የሚሯሯጥ ሰው ያለም አይመስለኝም። ቢሆንም ባይሆንም ግን አንብቡት።
•••
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሁለቱ የኦሮሚያ ተማሪዎች ሞት በተሰማ ማግስት ነው በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የዐማራ ተማሪዎች ላይ መዓት መውረድ የጀመረው። ተማሪዎቹ በወልድያ ስለሆነው ነገር እንኳ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ብቻ የ OMN ን ዘገባ የሰሙት የኦሮሞ ተማሪዎች ፌሮብረት፣ ፍልጥና ድንጋይ ይዘው ዐማራ ነው ብለው የሚያስቡትን ተማሪ በሙሉ መውገር ጀመሩ። መውገሩ አልበቃቸው ሲል የተማሪዎቹ ዶርም ላይ ቤንዚን አርከፍክፈው እሳት ለቀቁበት። ተማሪ መግቢያ አጣ።
•••
ነገሩ እየባሰ ሲሄድ መሞት ካልቀረ ብለው የዐማራ ተማሪዎች ራሳቸውን ወደ መከላከል ይገባሉ። ቄሮ ሸሸ። እፎይታም ተገኘ። ነገር ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። የቄሮን መሸሽ ተከትሎ ወዲያውኑ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ነን የሚሉ የኦነግ ፖሊሶች ዩኒቨርሲቲውን ወረሩት። ከዚያ የሆነውን ለመናገር ይከብዳል ነው የሚለው ተማሪው። ቄሮ በፌሮ፣ ኦነግ በጥይት በሰደፍ ዐማራ የሚባሉትን በሙሉ አፈር ከድሜ ያበሉ ጀመር። ብዙ ተማሪዎች ተረፈረፉ። እንዲያም ሆኖ የዐማራ ተማሪዎቹ አሁንም ከመሞት በቀር አማራጭ ስለሌላቸው። መተናነቅ ጀመሩ። ኦነጉም ቄሮውም አፈገፈጉ። ተማሪዎችም ከዶርማቸው ወጥተው በሜዳ ላይ ተሰብስበው በጅምላ ለመሞት ወሰኑ። ሴቶችን ከመሃል አድርገው ወንዶቹ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው የሚመጣውን መጠበቅ ያዙ።
•••
መሸ ነጋ፣ መሸ፣ ነጋ መሸ ነጋ ወይ ፍንክች የሚነቃነቅ ጠፋ። ከ 3600 – 4000 የሚገመት ተማሪ ሜዳ ላይ ተሰጥቶ ይውላል ያድራል። ታዲያ በቀ10/03/2012 ዓም እንዲህ ሆነ። ይናገራል ተማሪው የመረጃ ምንጬ “ ይኸውልህ ዘመዴ የኛን ሀሳብ ለማስቀየስ ከፌሮና ከገጀራ፣ ከድንጋይና ከጩቤ የተረፍነውን ለማስጨረስ በትናንትናው ዕለት በ0 ማለቱ ነው ያልመጣ የመንግሥት አካልና የሃይማኖት አባት የለም። እኛም ተሰቃይተናልና በሞቱት ወገኖቻችን አጥንትና ደም ስም ይዘናችኋል እባካችሁ ሀገራችን ስደዱን ብለን አልቅሰን እነሱም አልቅሰው ተመለሱ።
•••
ነገር ግን በ10/03/2012  ዓም ከጠዋቱ 5:20 አካባቢ ቁጥሩ ይሄ ነው የማይባል መከላከያ፣ የፌደራል እና ልዩኃይል መጥቶ በግቢው ፈሰሰ። እናም እንዲህ አሉን። አሁን የመጀመሪያው ማረፊያችሁ እንደተቃጠለባችሁ አይተናል። አሁን ግን ሌላ ቦታ ስላዘጋጀንላችሁ በግዴታ ወደተዘጋጀላችሁ ዶርም ተሰለፉና ትሄዳላችሁ ብለው መሳሪያ አቀባብለው ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኛም ሞተን ነው ቆመን እዚሁ በያዛችሁት መሣሪያ ጨርሱን እንጂ አንነቃነቃትም ብለን ቁርጥ ያለ ውሳኔ ወሰነን ነገርናቸው።
•••
መከላከያው ከዳር ቆሞ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና የፌደራል ፖሊሶቹ ከነሙሉ ትጥቃቸው ተጠጉን። እኛም ንቅንቅ አልል አልን። ከዚያማ ምን ይነገራል። የጭስ ቦንቡን ያዘንቡብን ጀመር። ከቄሮ ፌሮ አይበልጥም እያልን እየተቃጠልን ወደ ፖሊሱ መልሰን መወርወር ጀመርን። ወንድ የለ፣ ሴት የለ። እስላም ክርስቲያን የለ ሁላችንም በጀግንነት ተዋደቅን። እንዲሁ ስንዋደቅ መሸ። ምግብ ስላልቀመስን መቋቋም አቃተን። ብዙ ተማሪ የጭስ ቦንቦ አስክሮት ወደቀ። ተማሪው  እወደቀበት ላይ ነፍሰ በላው ኦነግ እኛን ለማጥቃት ቦታ ሲፈልግ የነበረው ልዩኃይል ደበደበን፣ ቀጠቀጠን። ደሙና ጭሱ አስክሮት በላያቸው ላይ እየዘለለ ከዩኒቨርሲቲ የእውር ድንብሩን የወጣውን ተማሪ ደግሞ ገጀራውን ይዞ ከውጭ የሚጠብቀው ቄሮ መከራቸውን አበላቸው። ጭስ ቦንቡም አለቀ። ወደ ዶርም ግቡ ሲሉን በፌሮና ጩቤ ድንጋይ ከምንሞት እዚሁ እንደጀመራችሁ በመሳሪያ ግደሉን እንጅ አንነቃነቅም ብለን በጥይት ብዙ ተማሪ ተጨፈጨፈ። የተጎዳውን ተማሪ የሚያመላልሰውን አንቡላንስም መንገድ ላይ በቄሮ ታገተ። መከላከያም ደርሶ የተጎዱትማ ይታከሙ ብሎ ቄሮን ለምኖና አሳምኖ ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ። በጫካው የጠፉትን መድኃኔዓለም ይወቃቸው። ያ አፍኖ ሊወስደን የመጣውን ኃይል ግን በፅናት መክተን ወደ ኋላ መለሰነው።
•••
የቄሮው ኦነግ ፖሊስ የቻለውን ያህል ቀጥቅጦን ሊጨርሰን ስላልቻለ ጥይትና ቦንቦንም ስለጨረሰ ተመለሰ። ታዲያ ይሄን የሰማው የመቱ ከተማ ቄሮ ነኝ ባዩ ግሩፕ፣ ገጀራና ፌሮውን ይዞ ወደ ዩኒቨርሲቲው እየተመመ መጣ። የመጣው ይምጣ ብለን ተዘጋጅተን ጠበቅነው። ጾም ስለነበረ ምግብ የሚባል አልቀመስንም። 50 ከሚሆኑ ሙስሊም ወንድም እህቶቻችን በቀር በሙሉ ማለት ይቻላል ኦርቶዶክሳውያን ነን። እናም ረሃቡን በጾም ስለለመድነው ተቋቁመነዋል። እናም ቄሮ ሲመጣም ተዘጋጅተን ጠበቅነው። በመጨረሻ ግን ሁኔታው ያላማረው የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ጣልቃ ገብቶ ቄሮን ከነገጀራው መልሶ ከእልቂት ታደገን።
•••
እኔም ጠየቅኩ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና የከተማው ማኅበረሰብስ ምን ይላሉ ብዬ ጠየቅኩ። የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ራሱ ፀረ ዐማራ መርፌ የተወጋ ነው። የሞተ፣ የተደበደበ ዐማራ ሲያዩ ገና ምን አይታችሁ ባዮች ናቸው። ምኒልክ እንዲህ አድርጎን፣ አጼ ዮሐንስ 30 ሺ አርዶብን ነው የሚሉት። በሚኒልክም በአፄ ዮሐንስም ነው የምንወገረው። አፄ ዮሐንስ የትግራይ ሰው ቢሆኑም የትግሬ ተማሪዎች በሃይማኖታቸው ካልሆነ በቀር በትግሬነታቸው የሚነካቸው የለም። በትግሬው ዮሐንስ መከራውን የሚበላው ግን ዐማራው ነው። አስተዳደሩ ነውረኛ ነው። የተማሩም አይመስሉም። የቀበሌ ሊቀመንበር ነው የሚመስሉት።
•••
የከተማው ህዝብ ግን ኦሮሞዎቹ አባቶችና እናቶች እየሆነ ባለው ነገር ያለቅሳሉ። በቤታቸው ተማሪዎችን ይደብቃሉ። እርጎ ወተት አቅርበው ይመግባሉ። ቅያሬ ልብስና ቁስላችንን ያክማሉ። የኦሮሞ እናቶችና አባቶች ያሳዝናሉ። አሁን ከሌላ ቦታ የመጡ መንግሥት ራሱ ያሰማራቸው ቄሮዎች ናቸው ያስቸገሩት። ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር እጅና ጓንት ናቸው። ፖሊስም፣ መከላከያም ቄሮ የሚባሉትን ጫፋቸውን እንዳትነኩ ተብለናል ነው የሚሉት። ከወታደሮቹ መሃል ሰብአዊነት ተሰምቶት ሊረዳን የሚፈልግ እንኳን ካዩ ልዩ ኃይሉም ሆነ ቄሮው ሊገሉት ነው የሚደርሱት። የጨነቀ ነገር ነው።
•••
የከተማው ህዝብ ዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጩ ነው። ዩኒቨርሲቲው ደግሞ ከመንግሥት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል። ባለፉት ዓመታት በፈፀመው በደል ምክንያት መንግሥት ሊዘጋው እንደሚችል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል። እናም የከተማው ህዝብ ለእኛ የሚያግዘው ለራሱም ጥቅም ሲል ነው። ተማሪው ከሌለ የገቢ ምንጩ ይደርቃል። ነገር ግን ማን ሰምቷቸው። ዩኒቨርሲቲው አጥር እኮ የለውም ዘመዴ። ጫካ ነው። የኦነግ ጦር ተግተልትሎ የሚሄድበት አስፈሪ ቦታ እኮ ነው። ጨነቀን። ጠበበን።
•••
ቄሮው የሚለው በዐማራ ክልል ያሉ የኦሮሞ ተማሪዎች ይውጡልንና እናንተ ወደ ክልላችሁ ሂዱ ነው የሚሉት። በዐማራ ክልል ያሉት የኦሮሞ ተማሪዎች ደግሞ በሰላም እየተማሩ ነው። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች መስጊድና ቤተ ክርስቲያን ጭምር እየጸለዩ ነው። ባህርዳር የተመደቡ የኦሮሞ ተማሪዎች ጣና ሀይቅ ዳር ዓለማቸውን እየቀጩ ነው። እኛ ነን እንጂ በረሃ ተጥለንም እንዳንማር ፍዳችንን የምንቆጥረው።
•••
የኦሮሞ ልዩ ኃይሉ በቦንብ አስለቃሽ ጭሱ የተረፈረፈውን ተማሪ የሴቶቹን ሻንጣ ቤንዚን አርከፍክፎ ነው ያቃጠለብን። ምክንያቱ ደግሞ በሴቶቹ ሻንጣ ውስጥ በሶ ስላለ እሱን አንዳንድ ጭብጥ እህቶቻችን እየጨበጡ ስለሚሰጡን ስንቃችንን ማውደማቸው ነው። የኦሮሞ ፖሊስ ሲበዛ ጨካኝ ነው። አብዛኛው ፖሊስ እስላምና ጴንጤ ስለሆነ እኛን መግደል መደብደብ እንደ ጽድቅ ይቆጥሩታል። አረመኔዎች ናቸው።
•••
የተመዘገበ 70 ተማሪ ሆስፒታል ደርሶ ተመዝግቧል። ፖሊሶቹንም እኛንም ያረጋጋ የነበረ አንድ የአዲስ አበባን ልጅ ፖሊሶቹና ቄሮዎቹ እንዳይሞት እንዳይተርፍ አድርገው ቀጥቅጠውት አሁን ሪፈር ወደ አዲስ አበባ ተልኳል። እናም ዘመዴ እባካህ ለዳንኤል ክብረት ንገርልንና፣ ቪድዮውንም ላክለትና ቢያንስ ሴቶቹን ከዚህ ሲኦል ያውጧቸው። ለመያዣነት እኛ ወንዶቹን የፈለጉትን ያድርጉን። አዴፓን እርሳው። አዴፓ ኦነግ ነው። አይናችን እያየ አለቅን። እኛስ ለነገሩ መፈጠራችንን ወቅሰናል ። እባካችሁ ባለ ወንበሮች የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ በልልን። ዘመዴ እስኪርቢቶአችን ሳይቀር እኮ ነው ያቃጠሉብን። ዶክመንታችን፣ ልብሳችንን እኮ ነው ያነደዱብን። እናም ዘመዴ ጩኹልን። የሆነ የመንግሥት ኃይል መጥቶ ከዚህ ሲኦል ያውጣን።
•••
መከላከያዎቹ አልታዘዝንም ምን እናድርግ ነው የሚሉን። ከእኛው እኩል መሃረባቸውን አውጥተው ነው የሚያለቅሱት። አሁን እንዲያውም የፈለገው ይምጣ ብለው ልዩኃይሉን አስወጥተውታል። የሀገር ሽማግሌዎቹ ጨንቋቸዋል። የሆነ መንግሥት ራሱ የቋጠረው ነገር እንዳለ ያስታውቃል። እንጂ ቀላል ነበር እኮ ከቄሮ ላይ ገጀራ፣ ፌሮ፣ ዱላ ቀምቶ በሕግ ልክ ማስገባት እኮ ነው። ግን አልፈለጉም። አልታዘዝንም ነው የሚሉት። እስላም ቄሮዎችማ ሲያዩን ቢበሉን ደስታቸው ነው።
•••
መታወቂያ ሲያዩ እስላም ሆኖ ዐማራ ቢሆን እንኳ አይፋቱትም። በዐማራነቱ ብቻ ይወግሩታል። ቤተሰቡ ኦሮሞ ይሆንና እሱ ደግሞ ከተማ አድጎ ኦሮምኛ አይችልም። ኦሮምኛ ካልተናገረ እሱም ቢሆን አለቀለት። መከራ እኮ ነው። በኪሳችን ይዘን የምንዞረው መታወቂያ ማለት መገደያችን የሆነ ካራ ማለት ነው። እስቲ አንድ ጊዜ መታወቂያችሁን አውጥታችሁ እዩት። ዐማራ የሚል ከሆነ ቀናችሁን ብቻ ነው የምትጠብቁት። አከተመ።
•••
አሁንም እደውልላቸዋለሁ። ስንቅ ጨርሰዋል። በግሩፕ፣ በግሩፕ እየሆኑ በተራ ምግብ ከካፌው እንዲበሉ መከላከያ ፈቅዶላቸዋል። ህፃናት ተማሪዎች ሳያስቡት የጦር ምርኮኛ መስለዋል። በማንኛውም ሰዓት ሊረሸኑ እንደሚችሉ ነው የሚናገሩት። እናም የምትችሉ ሰዎች የፌደራል መንግሥቱን ባለ ሥልጣናት በሥልክም ቢሆን ወትውቱላቸው።
•••
ሻሎም !   ሰላም !  
ህዳር 12/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ
Filed in: Amharic