>

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገብጋቢ የአንድነት ጥያቄና የኢሕአዴግ የተጭበረበረ መልስ!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው )

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገብጋቢ የአንድነት ጥያቄና የኢሕአዴግ የተጭበረበረ መልስ!!!
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
እናንተየ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ “ኢሕአዴግ አንድ ይሁንልን!” የሚል ነበረ እንዴ??? 
 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄ ጥያቄ እንዲያው ለአንድ ቅጽበት እንኳ ጥያቄው ሆኖ ያውቃል እንዴ??? 
 
“ኢሕአዴግ አንድ ካልሆነ!” ብለን ነው እንዴ ይሄንን ያህል ዘመን ስንታገልና ዋጋ ስንከፍል የኖርነው??? 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ለኢሕአዴግ በዐፅመ ርሥትነት ተሰጥታለች እንዴ ስንት አማራጭ እያለን “ኢሕአዴግ አንድ ካልሆነልን!” ብለን የምንታገለው???
እኛ (የኢትዮጵያ ሕዝብ) ወይ የኢሕአዴግ አባል አይደለን ነገር እንደ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነታችን በርካታ አማራጮች እያሉትና መወሰንም እየቻልን ለምን ብለንና ምንስ አግብቶን ነው “የዘለዓለም የኢሕአዴግ ባሪያ ናቹህ!” ተብሎ የተፈረደብን ይመስል “ኢሕአዴግ ካልተዋሐደ በስተቀር ሞተን እንገኛለን!” ብለን ልንታገል የምንችለው፣ በኢሕአዴግ ጉዳይ ላይ የምንጨነቀውና እጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን ከኢሕአዴግ ጋር ብቻ አቆራኝተን ልናይ የምንችለው??? አያቹህ አይየል እነዚህ ነውረኞች የሕዝብን ጥያቄ ጠምዝዘው እንዴት እንደሚያወናብዱና እንደሚያጭበረብሩ???
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ “ኢሕአዴግ ሆይ አንድ ሁንልኝ?” ሳይሆን “አንድ የነበረች ሀገራችንን በዘር መሸንሸንህ እርስበርስ ለመባላት ለመፋጀት ምክንያት ሆኖናልና፣ ጭራሽም ሊያጠፋፋን ነውና፣ በፈለግነው ቦታ ተንቀሳቅሰን ሠርተን እንዳንበላና ባለሀብት በፈለገው ቦታ ሀብት እንዳያፈስ አድርጓልና፣ ለዕድገትና ለልማት ታላቅ እንቅፋትና መሰናክል ሆኗልና… በዘር የሸነሸንካትን ሀገራችንን እንደሰነጣጠካት አድርገህ መልሰህ አንድ አድርግልን ካልሆነ ግን ፈጽሞ ልናይህ አንፈልግም ወግድልን???” ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ!!!
የችግሩ መንሥኤ የሆነ አካል ከቶውንም የመፍትሔ አካል ሊሆን አይችልምና ኢሕአዴግ ሆይሻ ይሄንን የሕዝብ ጥያቄ ጠምዝዛ ያልተባለችውንና ያልተጠየቀችውን   እራሷን አዋሕዳ በዘር በጎሳ ወይም በብሔረሰብ የሸነሸነችውን የክልል መዋቅር ግን “ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እራሳቸውን በራሳቸው የማሥተዳደር፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሕገመንግሥታዊ መብት ባለበት ይቀጥላል!” በማለት “የሕዝብን ጥያቄ መለስኩ!” ብላ እርፍ!!! አይገርምም??? አያሳዝንም??? ስለሆነም በጎሳ ፖለቲካ መንሥኤነት የተቀሰቀሰው የሀገሪቱ ቀውስ ይቀጥላል ማለት ነው!!!
ለዚህ ለዚህማ የኢሕአዴግና የአጋር ድርጅቶች መዋሐድስ ለምን አስፈለገ ታዲያ??? እስከዛሬም እንዳይዋሐዱ ያደረጋቸው እኮ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችና አጋር ድርጅቶች ለተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች የታገሉና የሚታገሉ እንዲሁም የተለያዩ ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን የሚወክሉ በመሆናቸው እኮነው፡፡ “የተለያዩ ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን መወከላችን ቀርቶ አንድ እንሁንና ሁሉንም እንወክል፣ ሀገር እንወክል!” ካሉ ዘንዳ ደግሞ መሬት ላይ ያለው የዘር ልዩነትና የዘር ክልል ምን ይሠራል ታዲያ???
“አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ግቤ ነው!” እያለ ሲደሰኩርብን የኖረው ምኑን ነው ታዲያ??? በዘር ተከፍሎ የታጠረ ክልልና በድንበር የሚናቆር የሚባላ ሕዝብ ተይዞ ነው እንዴ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚችለው??? ሲጀመር እሱ እራሱ አይደለም ወይ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የነበረውን ሕዝብ እንዲህ መቸም እንዳይግባባና ሰላም እንዳይሆን አድርጎ የሰነጣጠቀው??? አንዳች ነገር ይሰነጣጥቀውና!!!
በዚህች ሀገር ልክ እንደ አሜሪካ እና ሌሎቹ የምዕራባውያን ሀገራት ሁሉ የጎሳ ፖለቲካ ማለትም በዘር ወይም በጎሳ ተደራጅቶ ፖለቲካ መሥራት ወይም የብሔረሰብ ማንነትንና ልዩነትን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል በሕግ ካልተከለከለ በስተቀር የፈለገ ነገር ቢደረግ በዘር ፖለቲካ ምክንያት የተፈጠረውን ይሄንን ቀውስ ከዚህች ሀገር ማጥፋት ወይም ማስወገድ ፈጽሞ አይቻልም!!!
አገዛዙ እያደረገ ያለው ከባድ ችግርና አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻው የልብ ሕመሙ የሆነበትን ሰው እግሩ ላይ ያለችውን ቁስል ያውም ያለ ትክክለኛ ሕክምና በማከም መፍትሔ ለመስጠት ነው እየሞከረ ያለው፡፡ አገዛዙ በዘር ፖለቲካ ምክንያት የተፈጠረውን ቀውስ ለማስወገድ ከልቡ ቢፈልግ ኖሮ በቀጥታ በችግሩ መንሥኤ ላይ ያተኩር ነበረ!!! ኢሕአዴግ የሀገሪቱን ችግር ይበልጥ ማወሳሰብ እንጅ መፍታት አይፈልግም!!!
ኢሕአዴግ “የሀገሪቱን ቀውስ መፍታት ከልቤ እፈልጋለሁ!” ካለና የትም ሀገር በሌለ በዘር ፖለቲካ ምክንያት በሀገሪቱ ባመጣው ቀውስ ከተጸጸተ ማድረግ ያለበት ነገር እንደ የሠለጠኑት ፌዴራላዊ ሀገራት በድንጋይ ዘመን የቀረውንና ኋላቀሩን የዘር ወይም የጎሳ ፖለቲካ በሕግ ማገድ ወይም የዘር ልዩነት ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀምን በሕግ ማገድ የግድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ነገር ሁሉ ውሸትና ማጭበርበር ብቻ ነው ወገኖቸ!!! ፈጽሞ አትመኑ አትጃጃሉም!!!
ወገኖቸ ሌሎች ሀገራት ብዝኀነት የሌላቸው ሆኖ ይመስላቹሃል እንዴ የዘር ልዩነትን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀምን ወይም የጎሳ ፖለቲካን የከለከሉት??? እንዳይመስላቹህ!!! በእነሱም ብዝኃነት አለ፡፡ ቻይና ብዝኀነት የሌለባት ሀገር ሆና ነው ወይ አሐዳዊ መንግሥት የያዘችው??? ሐሰት!!! ቻይና ውስጥ 56 ብሔረሰቦች አሉ፡፡ በሌሎችም ሀገራት እንዲሁ ብዝኀነት አለ፡፡ የትም ሀገር ብትሔዱ ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ ብዝኀነት የሌለበት ሀገር የለም፡፡ የጎሳ ፖለቲካን የማይከተሉት የዘር ፖለቲካ ኋላቀር፣ አደገኛ፣ የሰላምና መረጋጋት ጠንቅና ሀገር በታኝ ስለሆነ ብቻ ነው!!!
እኛም ሰላምና መረጋጋት እንዲኖረን ከፈለግን፣ ባለን ላይ መጨመር እንጅ ያለንን ማጣት ካልፈለግን፣ ለዕድገት ብልጽግና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ከፈለግን፣ ሀገር አልባ እንዳንሆን ከፈለግን ወዘተረፈ. ማድረግ ያለብን ልክ እንደ እነሱ ሁሉ የጎሳ ፖለቲካን ማለትም በዘር ወይም በጎሳ ተደራጅቶ ፓርቲ በመመሥረት ፖለቲካ መሥራትን ወይም የብሔረሰብ ማንነትንና ልዩነትን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋልን በሕግ መከልከል ነው ሌላ ነገር የለም!!!
የጎሳ ፖለቲካ ደጋፊና አቀንቃኞች ማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ የግዛት አወቃቀር አላቸው በሚሏቸው በካናዳ፣ ቤልጂየም፣ በስዊዘርላንድ፣ በሕንድ፣ በናይጄሪያ፣ በደ. አፍሪካ፣ በሌፓል ሀገራት እንኳ ሳይቀር የዘር ልዩነትን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ወይም የጎሳ ፓርቲ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ አይፈቅዱም!!! ለምን ይመስላቹሃል የማይፈቅዱት??? በዓለማችን በደናቁርቱና የድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ባላቸው ወያኔ/ኢሕአዴግ ተተክሎባት ኢትዮጵያ ብቻ ናት ኋላቀሩን፣ ጠንቀኛውን፣ ሀገር በታኙን የጎሳ ፖለቲካን እየተከተለች ያለችው!!!
አገዛዙ “ለውጥ!” የሚለውን ጊዜ መግዣና ሕዝብን ማጃጃያ ድራማ አምጥቶ ሲተውን ከወሸከታቸው ብዙ ነገሮች አንዱ ሀገሪቱን በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ከገባችበት ቀውስ አውጥቶ አንድነትን እንደሚያመጣ ነበር፡፡ አንድ ቀን እንኳ ለሕዝብና ለቃሉ ታምኖ የማያውቀው ኢሕአዴግ አሁን እንደምትሰሙት “ኢሕአዴግንና አጋር ፓርቲዎችን ማዋሐድ!” ብሎ በመቀለድ ለመሸወድ ሞከረ  እንጅ!!!
አገዛዙ በዚህ የብልጽግና ፓርቲ በሚለው ውሕድ ፓርቲ መመሪያ ወይም ሕገደንብ መሠረት “ሁሉም ዜጋ ‘ክልልህ አይደለም!’ ሳይባል በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መምረጥ መመረጥና የዕኩል ተጠቃሚነት ይረጋገጣል!” ብሏልና ከዚህ አኳያ ምን ለማድረግ አስቧል መሰላቹህ ለምሳሌ አማርኛ የሚችሉ ትግሮችንና ኦሮሞዎችን ሌሎችንም “የአማራ ክልል!” የሚለውን ምክርቤትና ካቢኔ ተቆጣጥረው እንደፈለጉ እንዲዘውሩት ማድረግ ያስችለዋል!!!
የአማራ ክልል በሚለው ብቻ ሳይሆን አማርኛን የሥራ ቋንቋ ባደረጉ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ የጋምቤላ ክልል፣ የደቡብ ክልል፣ የሐረሪ ክልል በሚላቸው የክልል መዋቅሮቹ አማርኛ ቋንቋን የሚችሉ ትግሬዎችንና ኦሮሞዎችን የምክርቤትና የካቢኔ ወንበሮቻቸውን በማስያዝ መቆጣጠር ያስችለዋል!!!
የኔ ጥያቄ ይሄ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ሆኖ ነው “ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እራሳቸውን በራሳቸው የማሥተዳደር፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሕገመንግሥታዊ መብት አላቸው ተጠብቆላቸዋል!” ሊባል የሚችለው??? የሚለው ነው!!!
ለነገሩ በሌሎቹ አገዛዙ ክልሎች በሚላቸው ነው እንጅ የማይቻል የነበረው የአማራ ክልል በሚለው ግን ከዚህ ቀደምም ወይም እስከዛሬም ቢሆን “እራስን በራስ የማሥተዳደር…. ሕገመንግሥታዊ መብትና ድንጋጌን!” የሚለውን በሚጻረር መልኩ ብአዴንንና “የአማራ ክልል መንግሥት!” የሚሉትን ካቢኔ ተቆጣጥረውት የቆዩት ትግሮች፣ ኦሮሞዎችና ደቡቦች መሆናቸውን የምታውቁት ነገር ነው!!! አሁን ደግሞ ጭራሽ በብልጽግና ፓርቲ ሕገደንብ መሠረት ከላይ የጠቀስኩላቹህን ምቹ የሕግ ማዕቀፍ ስላበጁለት ማንንም ከየትም እያመጡ ሥልጣን በማስያዝ አማራን “ክልልህ ነው!” ባሉት መንግሥት ካቢኔ እንኳ ድርሽ እንዳይል ማድረግ ያስችላቸዋል!!!
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ የጋምቤላ ክልል፣ የደቡብ ክልል፣ የሐረሪ ክልል በሚላቸውም በተመሳሳይ መልኩ “ክልላቹህ ነው!” የተባሉትን ዜጎች ድርሽ እንዳይሉ አድርጎ ካቢኔያቸውንና የምክርቤት መቀመጫቸውን በሌሎች ተወላጆች ለማስያዝ ያስችለዋል!!! በአፋር፣ በሱማሌ፣ በኦሮሞም ቢሆን ቋንቋ ቋንቋቸውን በሚችሉ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆች ካቢኔያቸውንና የምክርቤት መቀመጫቸውን ለማስያዝ ያስችለዋል!!!
ስለሆነም ከዚህ በኋላ “የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እራሳቸውን በራሳቸው የማሥተዳደር፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሕገመንግሥታዊ መብት!” የሚለው ነገር ማወናበጃ፣ ማደናገሪያ፣ ማታለያ ነው እንጅ በተጨባጭ ወይም በተግባር ላይ አይሠራም ወይም ተፈጻሚ አይሆንም ማለት ነው!!!
ይህ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ቴክኒካሊ እንዲህ መሻሩ ካልቀረ ምን አለበት እራስን በራስ የማሥተዳደር መብትን በጎሳ ወይም በዘር ማስላቱን ትቶ አንደኛውን እንደ ፖለቲካ የገባቸው የሠለጠኑ ሀገራት አንድን አካባቢ ተጋርተው በጋራ ለሚኖሩ ዜጎች ብሎ በመተርጎምና ሁሉንም የሀገሪቱን ክፍል ለሁሉም ዜጎች በማድረግ ፖለቲካችንን ቢያዘምነው ወይም ቢያሠለጥነው??? ይሄንን ቢያደርግ ብልህነትና ማስተዋል አልነበረም ወይ???
አሁን ግን ከላይ ለማስረዳት እንደሞከርኩት ከሁለቱም ያልሆነ መመሪያ፣ ሕገደንብ ወይም መተዳደሪያ ደንብ ነው ይዘው የመጡት!!! ይሄ ደግሞ ከሁለት ያጣ ያደርገዋል እንጅ ተጠቃሚ አያደርገውም፡፡ እነሱ በርግጥ ያሰቡት የጎሳ ፌዴራላዊ መዋቅር እንዲቀጥል ባደረጉበት ሁኔታ “ተዋሐድን የአንድነት ፓርቲ መሠረትን!” ብለው አንድነት የሚለውን ሕዝብ አታለው ለመማረክ ነበረ ሐሳባቸው፡፡ ሕዝባችን ግን መሬት ላይ የሚያየውን ሐቅ ስለሚረዳ እንዳሰቡት የሚታለልላቸው አይመስለኝም!!!
የሚገርመኝ ነገር ሀገሪቱ “ይሄ ክልል የእነ እከሌ ነው፣ ይሄ ደግሞ የእነ እከሌ ነው!” ተብላ ሳትሸነሸን ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሁሉም ዜጎች ቢደረግ ሁሉንም ባለቤትና በዕኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሆኖ ሳለ “የብቻችን ጎጥ ካልተሰጠን በስተቀር!” የሚሉት ጠባቦች እንዴትና ለምን እንደሚቃወሙት ነው??? ሌላ ዕኩይ የጥፋት ዓላማ ከሌላቸው በስተቀር ሰው እንዴት ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሁሉም መሆኑን ይቃወማል??? የሚገርመው ደግሞ እንዲህ እያሉ የሚበጠብጡት አካላት ሰፍረው ያሉበትን የሀገሪቱን ክፍል የያዙት በስደትና በወረራ የያዙ መሆናቸው ነው!!! አይገርምም??? አያሳዝንም???
እናም ወገኖቸ የኢሕአዴግና የአጋር ድርጅቶች ውሕደት ከተራ ማጭበርበሪያነት የዘለለ አይደለም!!! አትታለሉ፣ አትጭበርበሩ፣ አትጃጃሉ!!! የችግራችን ሁሉ መንሥኤ የሆነው ኢሕአዴግ ፈጽሞ በምንም ተአምር ቢሆን የመፍትሔያችን አካል ሊሆን አይችልምና ያረጋገጠልንም ነገር ይሄንኑ ነውና ወገባችንን አጥብቀን ይሄንን ነቀርሳ ነቅለን መገላገል ብቻ በመሆኑ መፍትሔያችን ለዚህ በርትተን እንታገል!!! በየጊዜው በሚያመጣው አዳዲስ የማጃጃያ አጀንዳ አንታለል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic