>
10:58 pm - Sunday May 22, 2022

በካድሬ እና መንጋ ስነ-ልቦና የምትማቅቅ ሀገር! (ያሬድ ሃይለማርያም)

በካድሬ እና መንጋ ስነ-ልቦና የምትማቅቅ ሀገር!

 

ያሬድ ሃይለማርያም

 

 

የካድሬና መንጋ ስነ-ልቦና ምንጩ አንድ ነው። በምሪት መኖር። በራስ አለማሰብ። የሌሎች መሳሪያ መሆን። መንጋ እና ካድሬ ሃሳባቸውን በሚገልጹበት ስልት እንጂ የሚለያዩት በስነ ልቦና ሁለቱም አንድ ናቸው። መንጋውም ሆነ ካድሬው እራሳቸውን ችለው አይቆሙም። በራሳቸው ጭንቅላትም አያስቡም። ሁለቱም ልክ በኔትወርክ እንደተያያዙ የኮምፒውተር ቀፎዎች ናቸው። ለሁሉም ኮምፒውተሮች እንደ አዕምሮ ሆኖ የሚያገለግለው አንድ የመረጃ ቋት ነው። የተቀሩት ኮምፒውተሮች ከመረጃ ቋቱ የሚመጣላቸውን ነገር ለሚጠቀምባቸው ሰው መስጠት እና መቀበል ብቻ ነው። መንጋ እና ካድሬም እንዲህ አድርጉ፣ እንዲህ በሉ፣ እንዲህ ሥሩ፣ ተነሱ፣ ተቀመጡ የሚላቸው አንድ ሰው ነው። የሚናገሩትም ሆነ የሚሰሩት በዚያ ሰውዮ አዕምሮ ውስጥ ተብላልቶ የሚመጣላቸውን ትዕዛዝ ብቻ ነው።

የመንጋ እና የካድሬ ልዩነት የስልት ብቻ ነው። አንዱ የታዘዘውን ነገር ሁሉ ምንም ማሰላሰል እና ማሰብ ሳያስፈልገው በዱላ፣ በሜንጫ፣ በድንጋይ ወይም በጠመንጃ ያስፈጽማል። ሌላኛው ደግሞ የተነገረውን ነገር ቃላት እንኳ ሳይጨምር እና ሳይቀንስ ያንኑ እየደጋገመ የአለቃውን ትዕዛዝ ይፈጽማል። መንጋ ውሎው ሜዳ ላይ ነው። አንዳንዴ ተከፋይ ነው፤ ሌላም ጊዜ የተስፋ ተሸንጋይ ነው። ነገ ይህን እናደርግልሃለን የሚለው የትስፋ ጉም ደሞዙ ነው። ካድሬ ደግሞ ቋሚ ተቀጣሪ ሰራተኛ ነው። ከግብር ከፋዩ በሚሰበሰብ ገንዘብ ያለችሎታው፣ ያለ እውቀቱ እና ብቃቱ ደሞዝ የሚከፈለው፣ ከረባት አንጠልጥሎና ባማረ ቢሮ ተኮፍሶ ሕዝብን ጠርንፎ የሚይዝ የጋላቢዎቹ መጫኛ ገመድ ነው።

ሁለቱም፤ መንጋውም ሆነ ካድሬው በማሕበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ዋጋም ሆነ የሚያደርሱት ኪሳራ ተመጣጣኝ ነው። አንዱ የሕዝብ እና የአገር ንብረት በእሳት ያጋያል፣ ይዘርፋል፣ ያወድማል፣ ከዛም አልፎ ይገድላል። ሌላኛው ደግሞ በሙስና ሰልጥኖ ሕዝብ ይዘርፋል፣ ያደኸያል፣ አገርን ያቆረቁዛል፣ አንዳንዴም ያጠፋሃል። አንድ ፋብሪካን በእሳት አንድደው ባወደሙ እና ሜቴክን በቁሙ ገንዘው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት በዘረፉት ካድሬዎች መካከል ያለው ልዩነት የአፈጻጸም ስልት እንጂ የሃሳብ አይደለም። በስነ ልቦና ሁለቱም አንድ ናቸው። መንጋው ቢሮ የመቀመጥ እድል ቢያገኝ ከረባት ያሰረ ሙሰኛ ይሆናል። ካድሬው ሜዳ ላይ ቢጣል የአገር ሃብት በእሳት የሚያነድ መንጋ ይሆናል።

ኢትዮጵያ መንጋ እና ካድሬ እየተፈራረቁ፤ አንዳንዴም አብረው እንደፈለገ የሚፈነጩባት አገር ነች። የትላንት ካድሬዎች የዛሬ አለቆች ግራ ተጋብተው አገሪቱንም ግራ እያጋቡ መሆኑ ሳይ ወይ ካድሬና መንጋ ብዩ ማሰብ ጀመርኩ። ሲያማችው ታመን፣ ሲያቃዣችው ቃዥተን፣ ሲያብዱም አብደን፣ ሲደመሩ ተደምረን፣ ሲቀናነሱ ተቀንሰን፣ ሲደንሱ ደንሰን፣ ሲዋሹ አብረን ዋሽተን፣ ሲደናቆሩ ተደናቁረን፣ ሲምታታባቸው ተምታቶብን፣ ሲስቁ እያለቀስን፣ ሲያለቅሱ እየሳቅን እንዴት እንዘልቀዋለን።

የኢትዮጲያ ፖለቲካ መቼ ይሆን ከካድሬ እና ከመንጋ እጅ የሚወጣው። ካድሬ ከአገሩ በፊት ፓርቲውን እና አለቃውን ያስቀድማል። የካድሬው አለቃ ደግሞ እንዲሁ ከአገር እና ከሕዝብ በፊት ለራሱ የቅዠት ፖለቲካ እሳቤ ሙቶ አዳሪ ይሆናል። የእሱ አስተሳሰብ እና የፖለቲካ ምሪት አገር ቢያጠፋ ባያጠፋ ግድ የለውም። ከሕዝብ እና ከአገር ይልቅ ላመነበት የፖለቲካ እሳቤ እና ለጥቅሙ ሲል የገዛ ወንድሙን ይገድላል። ሲገድልም አይተናል። ካለፉት ስልሳ አመታት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ የአብይ እና የለማ ፖለቲካ የሚታየው ይሄው ነው። መንጋም እንዲሁ አገር፣ ሕዝብ፣ ሕግ፣ ሞራል የሚባሉ ነገሮች አያውቅም። ለሱ የህሊና ሚዛኑም፣ ሕጉም፣ አገሩም ሆነ ወዳጁ የሚያዘው የመንጋው መሪ ነው። አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ መንጋ እና የመንጋ መሪዎች አሉ።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ መንጋ እና ካድሬ ተፋጠዋል። ሌላው ጨዋ ሕዝብ ከዳር ቁጭ ብሎ እዝጊዮ እዝጊዮ እያለ ድራማውን በመከታተል ላይ ይገኛል። ለኢትዮጵያ ግን ከሁለቱ ማንም ቢያሸንፍ ወይም ሁለቱም ቢያሸንፉ የሚበጃት ነገር የለም። የአገሪቷ ፖለቲካ ከመንጋ እና ከካድሬ ምሪት ሊወጣ ይገባዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ለአገር ተቆርቋሪ ዜጋ መረባረብ ይኖርበታል። በመንግስት ውስጥ ያሉ አቅም እና ችሎታ ያላቸው በርካታ ድንቅ ሰዎች፣ በተቃዋሚው ጎራ ያሉ እና ጥሩ እውቀት ያላቸው ሰዎች፣ ምሁራን እና ለህሊናቸው ያደሩ ልሂቃን ሊረባረቡ ይገባል። ያኔ ሥልጡን ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ ማበብ ይጀምር ይሆናል።

ቸር ያሰማን!

Filed in: Amharic