>

ስልጣንና ወንጀል በኢትዮጵያ !! (አሥራደው - ከፈረንሳይ )

ስልጣንና ወንጀል በኢትዮጵያ !!

 

 አሥራደው –  ከፈረንሳይ 

                                

   

ኢትዮጵያ እድለኛ ናት ፤ የሬሳ ዘር የሚቆጥር መሪ አላት (አግኝታለች) !!

 

” ቁርጪን ፈርዳራ ኩፍቴ ” !!  ጀናኒ

አኒ ሞ፤ ፉንድሩማቱ  ቁርጪን አካም ፤ ፈርዳራ ባቴ ?!  ጀዴ ኢንጋፈዳ !

ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን፤ ብሂል የተወሰደ ::

ትርጉም

” ቆማጣ ከፈረስ ላይ ወደቀች ” !!  ቢሉኝ

እኔ ደግም፤ መጀመሪያውኑ : ቆማጣ እንዴት ፈረስ ላይ ወጣች ?!  ብዬ እጠይቃለሁ

 

ማስታወሻ :

በአገራችን ኢትዮጵያ፤ በስልጣን ዙሪያ  ቀደም ብለው የተፈጸሙትን ወንጀሎች፤ እንዳመቺነቱ በቀጣይ፤ እመለስበታለሁ ::

አሁን በአገራችን አስገዳጅ ሁኔታዎች በመኖራቸው፤ ዛሬ እየተፈጸሙ ባሉት የስልጣን ወንጀሎች መጀመሩን መርጫለሁ ::

የሰው ልጅ ያለፈውን በታሪክ መዝገብ መዝግቦ በመያዝ፤ ዳግም ላለመሳሳት ትምህርት እንዲሆነው፤ እራሱ የሠራቸውን ስህተቶች ብቻ ሳይሆን፤ የሌሎችንም ስህተቶች በማከል፤ ዛሬን በብልሃትና በጥረት እየኖረ ነገን በተስፋ ያለመልማል::

ሰው የወደፊቱን እንጂ፤ የኋላውን ስለማይኖር፤ እኔም ባለፉ ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ለጊዜው በማቆየት፤ ትናንትናና ዛሬ፤ በህዝባችን ላይ የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ያሉትን፤ የስልጣን ወንጀሎችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ ::

ምልከታዬ ፍጹማዊ ላይሆን ይችላል፤ እናም፤ የአገር ጉዳይ ግድ ይለናል የምትሉ ወገኖቼ፤ በጉዳዩ በመሳተፍ፤ የበኩላችሁን እንድታክሉበትና ወደተሻለ መፍትሄ እንድንደርስ እጋብዛለሁ ::

ከዳር ሆነን በመመልከት፤ ነገ በሚፈጠረው፤ የአገር መፍረስና፤ የወገኖቻችን መከራና ስቃይ ተጠያቂዎች ላለመሆን፤ ከፈለግን ጊዜው አሁን ነው :: 

ነገ የኛ ለመሆኑ እርግጠኞች ባለመሆናችን፤ ነገ የሚለውን ትተን፤ ዛሬን ከወገኖቻችን ጋር አብረናቸው እንቁም :: ይህን ስናደርግ ብቻ ነው በጥቂቱም ቢሆን፤ ሰብዕናችን ሰው ሰው የሚሸተው:: ያ ካልሆነ ከሰውነት ተራ ወጥተናልና፤ ኤላስ አከተመ ! አገርም ወገንም አይኖረንም !!

ማሳሰቢያ :

ጠ/ም አብይ አህመድ የሠራቸው ስህተቶች እንዳሉ ሆኖ፤ ችግሮቻችን አብይን በመወንጀል፤ ወይም የአብይን ሃጢያት በማብዛት ብቻ፤ ይወገዳሉ ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው ::  

ይልቁንም በማወቅም ሆነ፤ ባለ ማወቅ የህወሓት ወጥመድ ውስጥ ዘለን በመግባት፤ እነሱ የቆፈሩት የዘረኝነትና የጎሠኝነት ቆሻሽ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስት ገብተን ስንቦጫረቅ እንዳንገኝ፤ አጥብቀን መጠንቀቅ ይኖርብናል :: 

ህወሓትና ዘረኞቹ የኦነግ/ኦህዴድ ጥምር አሽከሮቿ፤ በጠ/ም አብይ አህመድ ላይ ጦር ንድንመዝላቸው፤ ስልታዊ በሆነ መልኩ፤ አጥብቀው ይሻሉ፤ ለዚህ ምኞታቸው መሳካትም ሌት ተቀን ተግተው ይሠራሉ :: 

የህወሓት ጥምር አሽከሮች፤ ኦነግና/ኦህዴድ ፤ አብይን የአንድ ዘርና ጎሣ ጥቅም አላስከበረም እያሉ ሲያብጠለጥሉት፤ እኛ ደግሞ ሌሎች አገራዊ ጉዳዮችን በተሻለ መልኩ በሥራ ላይ ባለማዋሉ፤ የምንደቁሰው ከሆነ፤ በድርብ ቅራኔ ከ’ነሱ ጎን አብረን እንዳንሰለፍ አጥብቀን መጠንቀቁ ተገቢ ነው ::

ይህ ማለት አብይ ሲሳሳት፤ የአገርና የዜጎችን መብት ሲደፈጥጥ፤ የአገር ሉአላዊነት ሲያስደፍር፤ የህግ የበላይነት ጠፍቶ ዜጎች የመኖር ዋስትና ሲያጡ፤ የአገር ሃብት ሲመዘበር፤ እያየን ዝም እንበል ማለት እንዳልሆነ እንድትረዱኝ እሻለሁ ::

ለ27 አመታት በትጋት ወያኔን የታገለች ብዕሬ፤ ዛሬ ታንቀላፋለች ማለት ዘበት ነው:: የአገሬን ልዕልና፤ የፍትህ የበላይነትን፤ የህዝቤን ነፃነትና ሠላም ሳታይ ላለማሸለብ ቃል ገብታለችና !! 

ሳይማር ያስተማረኝ ወገኔ እዳ ስላለብኝ፤ እዳውን ቆጥሬ ባልከፈለውም፤ በመከራውና በችግሩ ወቅት አብሬው ዘብ መቆም፤ የሰብዕናዬ ምሰሶ ነው ::

በአንፃሩ የአብይን ሰብዕና ጧትና ማታ የብርና የወርቅ ቀለም እየቀቡ፤ ሰማየ ሰማያት በማውጣት እየካቡ፤ አብይን አትንኩብን ! ለምን ይተቻል? ለምን ይጠየቃል? ለተፈጠሩ ችግሮች ለምን ሃላፊነት ይወስዳል? ለሚሉን ያስተሳሰብ ድኩማን፤ ትላንት በመለስ አምልኮነት እንደተዘፈቃችሁ፤ ዛሬ ደግም በአብይ አምልኮ ላለመዘፈቅ፤ ከትላንቱ ስህተታችሁ ተማሩ እንላቸዋለን ::

ሰዎችን ስናቀብጥ፤ የሌላቸውን ሰብዕና፤ በማጎናጸፍና በመካብ፤ ወደ አምባ ገነንነት በማሳደግ እናገዝፋቸዋለን :: እነሱም መሞገስ፤ መደነቅና መሞካሸትን ከለመዱ፤ አልፈው ተርፈው ወደ አምልኩኝ ደረጃ ያሻቅባሉ :: ከዛም ከህግ በላይ በመሆን፤ በሚሠሩት በደልና ጥፋት፤ መጠየቅ፤ መተቸትና መወቀስ ይቀርና፤ ከተሰቀሉበት የሚወርዱት፤ ወይ በግድ በህዝብ አመጽ ሲናዱ፤ ወይ ሲሞቱ፤ ብቻ ይሆናል:: 

ከዚህ አይነቱ አደጋ የምንድነው፤ ዛሬ አብረን እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ በጋራ ለአገራችንና ለህዝባችን ደህንነት ዘብ ስንቆም ብቻ ነው :: ከአሁን በኋላ፤ ወደ ላይ እያንጋጠጡ፤ ከዚህ ሰውረን ማለቱ፤ አይሠራም ! በጣም ረፍዷል !! 

እግዚአብሔርም ሰልችቶታል፤ እኛን በአምሳሉ በመፍጠሩ፤ ከማዘኑም በላይ፤ በስንፍናችን በእጅጉ ተጠይፎናል ::

የበቀለ ገርባና የጃዋር መሃመድ የህወሓት ሎሌነት ማሳያዎች !

” ጃንደረባ ሎሌ በጌታው ሙርጥ ይኩራራል ”  እንዲሉ 

* በቀለ ገርባና: ጃዋር መሃመድ፤ ስለ የህወሓት አሽከርነታቸው፤ በራሳቸው አንደበት ከተናገሯቸው ጥቂቶቹን ልጥቀስ፤

– በቀለ ገርባ መቀሌ ድረስ ሄዶ ህወሓት ለእኛ ባለውለታችን ነው ሲል፤ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ለዳግም ባርነት በእጩነት አቅርቧል:: (ለነገሩ ከራሱ በቀር ማንንም እንደማይወክል አገር ያውቃል)

– በለየለት ዘረኝነቱ፤ ሌላ ቋንቋ ከሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ጋር አብራችሁ አትገበያዩ ብሎ አውጇል::

– እንደ እኔ፤ ከሁለት ኢትዮጵያዊያን ቤተሰብ አብራክ፤ የተወለድን ልጆችን አስጠቂዎች ሲል ወንጅሎናል::

– የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱ በመረጣቸው ተወካዮቹ መተዳደር አይችልም ሲል፤ የአዲስ አበቤዎችን መብት ሊደፈጥጥ ይፎክራል ……….ወዘተ.

* የጃዋር መሃመድ የለየለት የህወሓት አሽከርነት፤ ከራሱ አንደበት በግላጭ ሲታይ:

“በደቡብም በምስራቅም ሄጃለሁ፡፡ብዙ ሰዎች ፈርተው አይናሩትም እንጅ አቋማቸው ከህወሃት የተለየ አይደለም፡፡ ፖለቲካ ያስተማሩኝም የብዙ ፓርቲዎች አመራር፣ ምሁራን፣ ወጣቶችም ጭምር በተለያየ ዘዴ አዋርቻቸዋለሁኝ፡፡ በይዘት ህወሃት የሚያራምደውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋሉ፡፡ እኛም አሁን ከህወሃት ጋር የሚያጣላን የታክቲክም ሆነ የእስትራቴጅ ልዩነት የለም፡፡ ህወሃቶች ፌደራሊስቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባርም በአቋምም አሳይተዋል፡፡ ድሮ ብዙ ተባብለናል፡፡ ያለፈው አልፏል፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግን በአብይ ዙሪያ ካሉት ሰዎች መካከል አብይን ከልብ የሚደግፉ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በስም ሁሉ ልጠራቸው እችልላለሁ፡፡ አሁን ኦሮሞ ማድረግ ያለበት ለእስትራቴጅክ  አጋሮቹ አጋርነቱን ማሳየት ነው፡፡ ሽማግሌም ቢሆን ልከን  ዋናውን እስትራቴጅያዊ ወዳጅ አብሮን እንዲሰራ እንሞክር፡አብይ ብቻውን ነው እየሄደ ያለው፡፡ እንደተናገርኩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው አጠገቡ ያሉት፡፡” 

ጃዋር መሃመድ በተለያየ ጊዜ የሚቀባጥረውን በሙሉ ትተን፤ ይህን አባባሉን ብቻ ብንወስድ፤ ምን ያህል በህወሓት እግር ስር ተነጥፎ፤ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን፤ ዳግም የህወሓት ባሪያዎች ለማድረግ፤ ደጅ የሚጠና መሆኑን በደንብ እንረዳለን :: 

እንግዲህ ጃዋርና አጋሮቹ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን፤ ለህወሓት እንደ ይሁዳ በስንት ብር ለመሸጥ እንደተዋዋሉ ባናውቅም፤ ለመሸጥ መወሰናቸውን ግን በደንብ ነግርውናል ::

 ጠ/ም አብይ አህመድ ” ከወንድማችን ጃዋር መሃመድ ጋር አብረን እንሠራለን፤ አስፈላጊው ጥበቃም ይደረግለታል” ብሎ በይፋ የብዙ ወገኖቻችንን ህይወት ካስቀጠፈ፤ ብዙ ንብረት እንዲወድም ካስደረገና ለብዙ ቤተክርስትያናት መቃጠል ምክንያት ከሆነ ወንጀለኛ ጋር አብሮ የሚሠራ መሆኑን ነው፤ ሐረር ድረስ ሄዶ ያለ ሃፍረት የተናገረው:: 

ጠ/ም አብይ አህመድ የሚጠየቅባቸው የራሱ የሆኑ የጎሉ ስህተቶች እንዳሉ ሆኖ፤ አብይን ከለላ በማድረግ፤ አብረውት ያሉ በማስመሰል፤ የህወሓትን፤ የዘርና የጎሣ ጥላቻ በማቀንቀን፤ አብይን ዋጋ በማስከፈል፤ በህዝብ ዘንድ ካስጠሉት በኋላ፤ ባገኙት ቀዳዳ ሾልከው ስልጣን ላይ ፊጢጥ ለማለት፤ የሚሯሯጡ የኦነግና የኦህዴድ አንጃዎች፤ ብብቱ ውስጥ ተሰግስገው፤ አምኖ ተቀብሎት ከነበረው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ሊያስፍቁት ጥቂት ቀናት ቀርቷቸዋል ::

የጠ/ም አብይ አህመድ ስህተቶች :

1) በግራ እጁ የህወሓትን ማኒፌስቶ አንግቦ፤ በቀኝ እጁ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ፤ አገር ልምራ ማለቱ፤ 

በግራ እጁ ያነገባት የህወሓት ማኒፌስቶ፤ ለጥላቻ አብዮት ታማኝነት ዘብ መቆም አለብህ እያለች ስታስፈራራው፤ በቀኝ እጁ የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ደግም፤ ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችልም ይለዋል:: እናም አብይ በምርጫው ወይ ይድናል፤ ወይ ይጠፋል:: 

እኛም በትግላችን አብረን በጋራ ጸንተን በመቆም፤ አገራችንና እራሳችንን ከጥፋት እናድናለን፤ ወይም በዘርና በጎሣ ተነጣጥለን በመባላት አብረን እንጠፋለን ::

ምርጫው ለእሱም፤ ለእኛም በጋራ ቀርቧል ::  

2) የህግ የበላይነትን ለማስከበር ባለመቻሉ፤ በመላ አገሪቱ የተንሰራፋው ሥርአተ አልበኝነት::

3) በህዝብ ድምጽ ባይመረጥም፤ ለጊዜው የመላ አገሪቱ ዜጎች መሪ መሆኑን እያወቀ፤ ከዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች ጋር ትከሻ ለትከሻ  በመተሻሸት፤ አገሪቱን ወደ ብጥብጥ መክተቱ ::

4) የኦነግ/ኦህዴድ ጥምር ዘረኞች በአዲስ አበባ ከተማ በኢሬቻ በዓል ዕለት የዘር ጥላቻ ፉከራ ሲያቅርሩ አደብ ግዙ በማለት ፋንታ፤ በዝምታ ይሁንታውን መስጠቱ ::

5) ያን ያህል ሰው በዘርና የጎሳ ብጥብጥ ሲሞት፤ ጠ/ም አብይ አህመድ ከሩሲያ ጉብኝቱን አቋርጦ ባለመመለሱ፤ ለአገሩ ክብር ከመንፈጉም በላይ፤ በሕዝባችን ልብ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ እንዲፈጠር አድርጓል ::

የብዙ አገራት መሪዎች፤ በአገራቸው ውስጥ ችግር ሲፈጠር፤ እንኳን ይኸን ያህል ሰው ሞቶ፤ ወዲያውኑ  ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው በመመለስ፤ ከህዝባቸው ጋር ሃዘኑን ይካፈላሉ :: 

እሱ ግን፤ ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ፤ ጉብኝቱን ቀጥሏል:: ለመሆኑ የሄደበት ጉዳይ ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ደህንነት ፍለጋ፤ ወይስ እንደለመደው የራሱን ክብር (ሌጋሲ) የብርና የወርቅ ቀለም ለመቀባት ?! 

– እንደተመለሰ ለሞቱት ወገኖቻችን ክብር ሳይሰጥና፤ ሃዘኑን ሳይገልጽ፤ ሐረር ድረስ ሄዶ “ከወንድማችን ከጃዋር ጋር አብረን እንሠራለን፤ ጥበቃም ይደረግለታል” በማለት፤ የገዳዮችን ልብ ሲያደነድን፤ የኛን ልብ ክፉኛ ሰብሯል::

– ቀደም ብሎ በፓርላማ የተናገረውን ቃል ክዶ፤ “የሁለትአገር ዜግነት ያላችሁ” የሚለውን አባባል፤ በመኪና ጎማ መለወጫና፤ በጥበቃ አስመስሎ በመናገር አጉል አራዳ ለመሆን በመመኮር፤ ሕዝብን ለማታለል ሞክሮ፤ አልገባንም ቢሉት፤ የሆነና ያልሆነውን ቀባጥሮ፤ ህዝቡን ሳይሆን፤ እራሱን ብቻ አታሎ መመለሱ ትልቅ ትዝብት ውስጥ ከቶታል:: 

– በእጅጉ ልብ ሰባሪ የሆነው የአብይ ድርጊት፤ ” በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” እንዲሉ የሞቱት ወገኖቻችን በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ሆነው ሳለ፤ የሬሳ ዘር ቆጠራ ውስጥ ገብቶ፤ የሰጠው አሳፋሪ መግለጫ ሲሆን፤ ህሊና ካለው ጸጸቱ ህይወቱን ሙሉ እየተከተለ እንደሚያሳድደው አልጠራጠርም :: 

ሌላዋ የሂሳብ ስሌት ደግሞ፤ ለዘርና የጎሣ ፖለቲከኞቹ፤ ከሌላው ዘርና ጎሣ፤ በይበልጥ የሞቱት፤ የኛ ዘሮች ወይም ጎሣዎች ናቸው ብሎ፤ ርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ለመቃረሚያ፤ የወረወራት የአፍ ልፋጭ መሆኗ ነው ::  ይህን ደግሞ ጊዜው ወደ ፊት ያሳየናል ::  

– ለመሆኑ አብይ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ስንት ወገኖቻችን አለቁ ?

– ስንቶቹ ተወልደውና አድገው ከኖሩበት ቦታ ተፈናቀሉ   ?

– ገና ስንቶች ይሙቱ ?

– ስንቶች ይፈናቀሉ ?

– አንገፍግፎን በቃ!! ለማለት፤ ስንትና ምን ዓይነት የሥልጣን ወንጀል በአገራችንና በዜጎቻችን ላይ ይፈጸም ?! 

መቋጫ

አንዱ ባላ ሲገነጠል : በሌላው ላይ ተንጠልጠል ፤ እንዲሉ፤

እነዛው የትላንቶቹ ፤ ህወሓት ጠፍጥፎ የፈጠራቸው፤ ኢህዴግ ተብዬ አባላት፤ የህዝባችን አሳሪዎች፤ ገራፊዎች፤ ገዳዮችና የአገር ሃብት ዘራፊ ሌቦች፤ ” የቀን ጅቦች ” ዛሬም ከያሉበት ተጠራርተው፤ ኮታቸውን በመገልበጥ፤ እንደለመዱት፤ የቀረችውን የአገር ሃብት ሊዘርፉና፤ የዜጎችን መብት ሊደፈጥጡ፤ በድህነት ያደቀቋቸው ወገኖቻችንን መልሰው ሊግጡና፤ በብድር እስከ አንገቷ ያሰጠሟት አገራችንን፤ ከነ አካቴው ደፍቀው ለማስመጥ፤ በዕዳ ባቆራመዷት አገራችን ላይ ዳግም በልጻጊዎች ለመሆን፤ ” የብልጽግና ፓርቲ” እየተባባሉ ይሞዳሞዳሉ :: 

ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖቻችን በቅርብ ጊዜ ለረሃብና ለበሽታ እንደሚጋለጡ፤ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት ሰጪ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ፤ እነሱ በአገር ሃብት ስርቆትና ዘረፋ: ስለበለጸጉ ብቻ፤ ብልጽግና ሳይኖር ስለ ብልጽግና፤ ሠላም ሳይኖር: ስለ ሠላም፤ ዜጎች በሚከፍሉት ግብር ወጪ፤ በሚተዳደሩ የዜና ማሰራጫዎች፤ በድሃ ወገኖቻችንን ላይ ጠዋትና ማታ፤ ያናፋሉ::  

ድንቄም ሠላም !! ድንቄም ብልጽግና !!     

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!

እግዚአብሔር፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!

 

Filed in: Amharic