>
4:53 pm - Monday May 25, 2331

የታህሳስ 4/1953 ግርግር አጠቃላይ ሁነት!!! (አወድ ሞሀመድ)

የታህሳስ 4/1953 ግርግር አጠቃላይ ሁነት!!!

 

አወድ ሞሀመድ
*  “ቴዎድሮስ እጅ መስጠት አላስተማረንም! ይልቁንም የምላችሁን ስሙ፤ እኛ የተነሳነው እኛ ተበድለን ሳይሆን፤ የሀገራችንን ችግር ለማስወገድ ነበር እኛ ጀምረነዋል እናንተ ጨርሱት!”
ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ 
ወርሃ #ታኅሳስ_1953 ዓ. ም በኢትዮጲያ ታሪክ ለየት ያለ ክስተት አስተናግዶ የለፈ ወር ነው። ሁኔታዉ እንዲህ ነዉ፣ ቀዳማዊ አጽ ኃ/ስላሴ ከብራዚል ፕሬዚዳንት በቀረበላቸዉ የጉብኝት ጥያቄ መሰረት ህዳር መጨራሻ ላይ አዲስ አበባን ለቀዉ ሄዱ። የእርሳቸዉን ከሀገር መራቅ ሲጠባበቁ የነበሩ የስርዓቱ ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ማለትም ብርጋዴር ጀኔራል መንግስቱ ነዋይ የክቡር ዘበኛ ዋና አዛዥ፣ ግርማሜ ነዋይ የጅጅጋ አዉራጃ ገዥ፣ ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ የቀዳማዊ አጽ ኃ/ ስላሴ ካቢኔ ምክትል ኤታማጆር ሹም እና ህዝብ ጸጥታ ጉዳይ (ደህንነት) ሃላፊ ለወራት ቢሮቻቸዉን ዘግተዉ ሲወያዩበት የነበረዉን ንጉሰ ንግስቱን ከስልጣን የማስወገድ እቅድ ወደተግባር ለመቀየር ተንቀሳቀሱ።
.
ታኅሳስ 4 1953 ዓ.ም-ለመፈንቀለ መንግስቱ መሳካት እንቅፋት ይሆናሉ ብለዉ ያሰቧቸዉን የስርዓቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር አዋሉ::
.
ታኅሳስ 5- ልዑል አልጋ ወራሸ አስፋወሰን በማስገደድ በኢትዮጵያ ሬድዮ ጣቢያ የመንግስት እዋጅ አስነገሩ። አልጋ ወራሽም እንዲህ ሲሉ አዋጁን አነበቡ “ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ3000 አመታት በላይ የሚታወቅ ታሪክ አለው:: ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ገበሬዉ ከሞፈር ከደግርና ከቀንበር የእርሻ መሳሪያ፣ ነጋዴዉ ከችርቻሮ ሌላዉ በልዩ ልዩ የሚተዳደር አባቶች ካቆዩት ያአሰራር ዘዴ ያልወጣ ነዉ። በጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድንቁር የኑሮ ደረጃ እስከ ዛሬ ሊወጣ አልቻለም፡፡
የአስተዳደር አመራር ዓላማም ሕግንና ሥርዓትን መሰረት አድርጎ ህዝብን መበደያና መጨቆኛ አይነተኝ መሳሪያ ሆኖ ቀረ…………” እያሉ የስርዓቱን አስከፊነት እና የለውጥ አስፈላጊነትን አስረግጠዉ ተናገሩ፡፡ አያይዘውም እንዲ ሲሉ ሰለ ራሳቸዉ አዲስ በተቋቋመዉ መንግስት ውስጥ እንዴት ህዝቡን ሊያገለግሉ እንደተዘጋጁ ተናዘዙ “….ከዛሬ ጀምሮ በሃብት በኩል እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሆኜ በሚቆረጥልኝ ደሞዝ ብቻ በስልጣኔ እዉነተኛዉን ህገ መንግስት መመሪያ በማድረግ ሀገሬና የኢትዮጵያ ህዝብ ፍጹም በሆነ ቅን ልቦና ለመስራት ወስኛለሁ።”
.
አክለዉም ህዝቡ አዲስ ከተቋቋመዉ መንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪያቸዉን እንዲህ ሲሉ አስተላለፉ“ አዲስ የተቋቋመዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስት በኔው በራሴ፣ በጦር ክፍሎቸ፣ በፖሊስ ሰራዊት፣ በተማሩ ወጣቶችና እንዲሁም በኢትዮጵያ ህዝብ የተደገፈ ሰለሆነ ሰለዚህ የሚደረገዉ ሹም ሽርም ሆነ ስራዉ ማንኛውም ዓይነት ውሳኔ የጸና ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በዓለም ህዝብ ፊት ተገቢ የሆነውን ግርማ ሞገስ የተጎናጸፈ ክብር የሚያስገኝልህ ታሪክ መሆኑን አውቀህ ኅብረትህ ከብረት የጠነከረ ይሁን።” ሲሉ “የሞትንም እኛ ያለንም እኛ” አይነት ንግግራቸዉን አሳረጉ።
.
ታኅሳስ 6- የኢትዮጲያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዑ አቡነ ባስሊዮስ (እኝህ ፓትሪያርክ የመጀመሪያዉ የኢ.ተ.ኦ.ቤ ኢትዮጲያዊ ፓትሪያርክ ናቸዉ) መፈንቅለ መንግስቱን በመቃወም ለህዝቡ እንዲህ ሲሉ መልክታቸዉን አስተላለፉ “…….የኢትዮጲያ ህዝብ ሆይ በሃይማኖታችሁ በቃልኪዳናችሁ ፀንታችሁ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴን ብቻ እንድታገለግሉ። ከሐዲ የሆኑትን ወንበዴዎች እንዳትከተሏቸዉ፡፡ በተሰጠኝ የሃይማኖት አባትነትና ስልጣን መሰረት አውግዣችኋለሁ፡፡” ሲሉ ህዝቡ የንጉስን ዘውድ እንዲጠብቅና ከንጉሱ ጎን እንዲቆም የሚጠይቅ ወረቀት በአዎሮፕላን አዲስ አበባ ላይ ተበተነ።
 .
ታኅሳስ 7ና 8- በልውጥ ፈላጊ የክቡር ዘበኛ ጦር አባላት እና በቀዳማዊ አጼ ኃ/ስላሴ ዙፍን ደጋፊ የምድር ጦር አባላት ከፍተኛ ውጊያ በአዲስ አበባ ተደረገ። አዲስ አበባ ቀዉጢ ሆነች በሴችንቶ ፈንታ ታንኮች፣ የጦር መኪናዎች ከተማዉን ወረሯት፤ የከተማዎ ማድመቂያ ወይዛዝርት ከከታማዉ ተሰወሩ፣ በምትኩ መለዮ ለባሽ ወታደርች ከነሙሉ ትጥቃቸዉ ከተማዋ ሞሏት።
እንብዛም በህዝቡ የማይታወቀዉ የጦር አዉሮፕላኖች ከተማዉን ፋታ ነሷት፤ አዲስ አበባ ተጨነቀች፣ ከ1929 የፋሲስት ጭፍጨፋ ብኃላ በድጋሚ በጭንቀት ተወጠረች አዲስ አበባ፡፡ በመጨረሻም ዉጊያዉ በንጉሱ ዙፋን ደጋፊዎች ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዉም ሙሉ በሙሉ ከሸፈ። የመፈንቅለ መንግስት ዋና ተዋንያንም ዓላማቸዉ እንደተጨናገፈ ሲረዱ ከአዲስ አበባ ለመሰወር ሙከራ አደረጉ።
.
ታህሳስ 9- ነጉሰ ነገስቱ የብራዚል ጉብኛታቸዉን አቌርጠው በአስመራ በኩል አዲስ አበባ ገቡ። በስልጣን ዘመናቸዉ ለሁለተኛ ጊዜ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በድጋሜ ወደዙፋናቸው ተመለሱ። ከቤተ መንግስታቸዉ በመሆን በኢትዮጲያ ራዲዮ ጣቢያ በኩል “አለን…..ወደ ዙፋናችን በሰላም ተመልሰናል” አሉ፣ ታማኛ ሆነዉ ዘዉዱን ለጠበቁት ሁሉ የምስጋና መልክታቸዉንም አስተላለፉ፡፡
.
ታህሳስ 10- የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ለትንሽ ቀናት በአዲስ አበባ ቀጨኔ መድሃኒያለም አካባቢ መደበቅ ቢችሉም በመጨረሻ ለጦር ሰራዊቱ በደረሰዉ መረጃ በከበባ ስር ዋለ። እጃቸዉን እንዲሰጡ በተጠየቀም ጊዜ “ቴወድሮስ እጅ መስጠት አላስተማረንም። ይልቁንም የምላችሁን ስሙ፤ እኛ የተነሳነው እኛ ተበድለን ሳይሆን፤ የሀገራችንን ችግር ለማስወገድ ነበር እኛ ጀምረነዋል እናንተ ጨርሱት”። በማለት በያዙት መሳሪያ እራሳቸውን አጠፉ፤ የዳግማዊ ቴዎድሮስ ልጅ ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ።
.
ታኅሳስ 15 – የተቀሩት ሁለቱ የመፈንቅለ መንግስተ መሪዎች ከከተማዉ ቢሰወሩም ብዙም ሳይርቁ ደብረ ዘይት ዝቋላ አካባቢ በአካባቢዎ ነዋሪዋች ከበባ ዉስጥ ወደቁ። እጅ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸዉ በተደረገ የተኩስ ልዉውጥ የመፈንቅለ መንግሰት ዋና መሪ የነበሩት ቡርጋዴን ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ በከባድ ቆስለዉ ሲያዙ ታናሽ ወንድማቸዉ ግርማሜ ነዋይ ተገደሉ። ሬሳቸውም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አራዳ ጎርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘዉ አደባባይ ላይ ቀደም ብሎ ከተሰቀለዉ … ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ሬሳ ጎን ተሰቀለ።
.
በሌላ በኩል ብ/ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ህክምና ተደርጎላቸዉ ፍርድ ቤት ቀረቡ፣ ሆኖም ፍርድ ቤቱ በስቀላት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላለፈባቸዉ፡፡ ይግባኝ እንዲሉ በተጠየቁበት ወቅት ለችሎቱ ታሪካዊ ንግግር አደረጉ
«እናንት ዳኞች የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለ ይግባኝ ተቀብያለሁ፡፡ ይግባኝ ብየ ጉዳየን የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለሁና በይግባኝ የአፄ ኃ/ስላሴን ፊት ማየት አልፈቅድም፡፡ በእግዚያብሄር ስም ተሰይማችሁ ከተቀመጣችሁበት የፍርድ ወንበር ላይ ከመቀመጣችሁ በፊት በእኔ ላይ የምትሰጡትን የዛሬውን ፍርድ ታውቁት እንደነበር ሳስብና ፍርድ እስከዚህ ደረጃ ወርዶ መርከሱን ስታዘብ ሀዘኔ ይበዛል፡፡
.
ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ ነፃነትና እርምጃ የተነሳሁ ወዳጅ ነኝ እንጅ ለማፋጀት የተነሳሁ ወንበዴ አይደለሁም፡፡ ይህንን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሰራዊትና መሳሪያ ሳላጣ ዛሬ እዚህ ከእናንተ ፊት ለመቆም ባልበቃሁ ነበር፡፡
.
እኔ ከአፄ ኃ/ስላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደመወዝ የሚያገኙ ሁለት የተራቡ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና አገር ለማፍረስ አለመምጣቴን የሚያረጋግጥልኝ እናንተ በትዕዛዝ ፍረዱ የተባላችሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው፡፡
.
ከእኔ በፊት በግፍ የፈሰሰው ንፁህ የኢትዮጵያዊያን ደም ብዙ ነው፡፡ በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ግፍ ሽልማት በመሆኑ እኔ ለመሞት የመጀመሪያው ሰው አልሆንም፡፡ ስልጣን አላፊ ነው፤ እናንተ ዛሬ ከጨበጣችሁት የበለጠ ስልጣን ነበረኝ፤ ሀብትም አላጣሁም፡፡ ነገር ግን ህዝብ የሚበደልበት ስልጣንና ድሃ የማይካፈለው ሀብት ስላልፈለግሁ ሁሉንም ንቄ ተነሳሁ፡፡
.
አሁንም እሞታለሁ፤ ሰው ሞትን ይሸሻል፤ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትንና አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄያለሁ፡፡
.
የጀመርኩት ስራ ቀላል አይደለም፤ አልተሸነፍኩም፡፡ ወገኔ የሆነው ድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመርኩለትን ስራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈፅሞ ራሱን በራሱ እንደሚጠቅም አልጠራጠርም፡፡ ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ልሰራለት ካሰብኳቸው ስራዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን፤ ይህ ሃሳቤና ፍላጎቴ ህይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡
.
ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ አሜን ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ፤ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡ እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አስርና አስራ አምሰት ዓመት በቀጠሮ የምታጉላሉትን ህዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትመለከቱለትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገም ነበር።
.
ከእናንተ ከዳኞቹ እና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ፤ እኔ ፍርድ ተቀባይ የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ። የኔ ከጓደኞቸ መካከል ለጊዜው በህይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የዘመኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡
.
ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተ እና ለገዢአችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡
.
በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባለ አደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድ እና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡»
.
በተለምዶ የታኅሳስ ግርግር ተብሎ የሚታወቀዉ የ1953 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ቢዚሁ ተቋጨ። “ንጉስ አይከሰስም፣ ሰማይ አይታረስም” የሚባለዉ አባባል ተረት ሆኖ ቀረ። ንጉስም ይከሰሳል፣ ሰማይም በመብረቅ ይታረሳል የሚሉ መፈክሮች ማስተጋባት ጀመሩ፣ ልክ ይህ ከሆነ 13 አመታት በኃላ ንጉሰ ነገስቱ ከስልጣናቸዉ ተወገዱ፡፡
ሆኖም ከታኅሳስ ግርግር በኋላ ከአንዴም ሁለቴ የስርዓት ለዉጥ ቢደረግም የታሰበውን የህዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ ተስኖት በተቃራኒዉ በጥቂት የስልጣን ጥመኞች ተጠልፎ ለጥቂት ግለሰቦች የሁብትና የስልጣን ጥም ማርኪያ ውሏል። የታኅሳስ የለዉጥ ኳስ ግን ከታህሳስ ነጥራ የካቲት ላይ ከዛም ግንቦት ላይ ብታርፍም ምቹ ማረፊያ ሜዳ አላገኘችም ነበር።
(ምንጭ፡- የታህሳስ ግርግር እና መዘዙ በብርሃኑ አስረስ ፤ ገድለ መፈንቅለ መንግሰት በታደሰ ቴሎ)via ነጋሪት_negarite
Filed in: Amharic