>

በፍቅር ደብዳቤ  የተገረሰሰው ዙፋን ¡  ¡ ¡  (አሌክስ አብርሃም) 

በፍቅር ደብዳቤ  የተገረሰሰው ዙፋን ¡  ¡ ¡ 

አሌክስ አብርሃም
‹‹ ….  ጓዶች  ይሄን የበሰበሰ ዙፋን አናታችን ላይ ተሸክመን ነገ ዛሬ ማለት የለብንም !!  ›› አሉ ጓድ መንግስቱ ሃይለማሪያም አይናቸው በብስጭት እየተንቀለቀለ . . . በዚህ ጉዳይ የደርጉ አባላት ፈራ ተባ ስላሉ ጓድ መንግስቱ ደማቸው ፈልቶ ነበር
‹‹ ጓድ መንግስቱ ! መረጋጋት አለብህ  አሮጌ ቤት ስታፈርስ ተደርምሶ ሊጫንህም እንደሚችል ማሰብ ደግ  ነው  …ደርሶ ምሰሶውን መጎተት ምንድን ነው ›› አሉ  በእድሜ  በሰል ያሉ የደርግ አባል …  የኮሮኔል መአረግ ስላላቸው  ወታደራዊ  ግልፍታ ምን እንደሚያስከትል ያውቁታል ….!
‹‹ ይጫነና !  አፍርሰነው እንፍረስ …. ቀሪው ትውልድ በእኛ ሬሳ ላይ ተረማምዶ ነፃ እና የሰለጠነች ኢትዮጲያን ይፍጠር ›› አሉ ጓድ መንግስቱ ከበፊቱ የበለጠ ተቆጥተው ጠረንቤዛውን በቡጢ እየወገሩ  . . .
 የተሰበሰቡባት ክፍል በጭንቀት ልትፈነዳ ሆነ ፡፡ የደርጉ አባላት ይሄን ጥቁር ወጣት ቀልባቸው ፈርቶታል ፡፡ ተው ብለው አይናገሩ ነገር በዚህ አካሄዱ ነገ ጧት ወደስብሰባው አዳራሽ ታንክ ይዞ ከመምጣት የማይመለስ ጉድ ነው  ፡፡ ዝም አይሉ ነገር ያሳደጓቸውን ያስተማሯቸውን ህዝቡ ሁሉ ከማክበር አልፎ የሚያመልካቸውን  ንጉስ ነገውኑ ከዙፋናቸው ላይ ጎትተን እናውርዳቸው እያለ ነው . . . አጣብቂኝ !
‹‹ ምንም ውጣ ውረድ የለውም ሽማግሌው  አብቅቶለታል ቀጥ ብለን ገብተን በቃህ ማለት ነው ››  አሉ ጓድ መንግስቱ
‹‹ ማ…ንን ..ጃንሆይን ?›› አለ አንዱ በድንጋጤ አማትቦ
‹‹ አዎ ! ››
‹‹  አባባ ጃንሆይን ?››
‹‹ ምን ነካህ ጓድ አዎ አልኩህኮ ! ››
‹‹  እኮ…..ቀ…ቀ…..ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉስሰ ነገስ……..? ››
‹‹ እችን ይወዳል መንጌ  …  ዝጋ ! የምን ስም ማንዘላዘል ነው ….›› አሉና ጠያቂው ላይ አፈጠጡበት . . . እንደገና አማትቦ አቀረቀረ
በፍርሃትና ጭንቀት በታፈነው አዳራሽ ውይይቱ ቀጠለ …አንዳንዶቹ  ‹‹የንጉሱ መውረጃ ጊዜ አሁን አይደለም ትንሽ እንረጋጋ ›› ሲሉ ሌሎቹ ‹‹ እንደው ንጉሱ ባይወርዱስ አድባር ናቸው ፣ ዋርካ ናቸው  ውረዱ ብንላቸው እርግማናቸውም መንፈቅ አያከርመን ….ዝም ብለው ለወጉ  ይቀመጡና  ደርጉ ስልጣኑን ይዞ አገር ይምራ ››
‹‹ ጓዶች የግማሽ ክፍለዘመን ዙፋን  ከነስንክሳሩ    አናታችን  ላይ  ተሸክመን እንኳን  ለአመታት የዛገ ስልጣን ላይ  ቀርቶ መርከብ ላይ ብንቆም ስንዝር አንርቅም !  እኛንም አገራችንንም ተጭኖ ነው የሚያሰምጠን ›› ሲሉ ጓድ መንግስቱ ተናገሩ !
‹‹ የለም የለም ጓድ ይሄ  ፈጥነን እንድንደርስ ብሎ የጫነንን መኪና ሹፌር ከመግደል አይተናነስም …ሹፌሩ ነው ጉድጓዱን የሚያየው ገደሉን የሚመለከተው ….ረጋ ብሎ ይንዳው ግዴለህም ›› አሉ አንድ አባል ፡፡
ደርጉ በዚህ ጉዳይ አንድ ቀን ከግማሽ ሲከራከር ዋለና   ንጉሱ መውረዳቸው ላይ እያቅማማም ቢሆን  ተስማማ ፡፡
ቃለ ጉባኤ ፀሃፊው
እያቅማማን
ተስማማን ! ብሎ ፃፈ ፡፡ (አብዮት ከፈነዳ በኋላ ይህ ሰው በወሳኝ ሰብሰባ ላይ ግጥም በመፃፍ ተከሶ ተረሽኗል )
‹‹ ጓዶች እኔም ቆራጥ የኢትዮጲያ ወንድሞቸ ጋር እንደተሰበሰብኩ  ከጅማሬው  ቀልቤ ነግሮኛል ›› አሉና ጓድ መንግስቱ ሸንጎውን አሞካሹት ፡፡  የተሞካሸው ሸንጎ ደረቱን ነፋ ትከሻውን ሰፋ አድርጎ ለዋናው ውሳኔ ተዘጋጀ
‹‹ ጃንሆይ እንዴት ይውረዱ ? ›› ዋናው ጥያቄ ፈነዳ ፡፡ ዝምምምምም!
‹‹ ህዝቡ ጠልቶሃል አገር ምድሩን በኋላ ቀርነት ፣ በእርሃብ  ፣ በባርነትና በፍትህ እጦት አጎሳቅለኸዋል  በቃህ ቦታህን ለተረኛው ልቀቅ ››  ብሎ መንገር ነዋ !! ›› አሉ ጓድ መንግስቱ
‹‹ ኧረ ጓድ ቀስ … የቤት ሰራተኛ እንኳን ስትባረር ስርአት አለው እንኳን ይሄን ያህል ዘመን የመራ ንጉስ ››
‹‹ እና እነዴት እናውርደው ? ሃሳብ አምጡ ›› አሉ  ጓድ መንግስቱ ወንበራቸው ላይ እየተቁነጠነጡ  ይሄ ደረቅ ወንበር አልተመቻቸውም  ‹‹ መደገፊያ ያለው ባለስፖንጅ ወንበር  ቢገኝ . . . አለ አይደል እንደዙፋን ያለ ነገር ›› ብለው አሰቡና በውስጣቸው ፈገግ አሉ !
‹‹ ባይሆን በደብዳቤ ፅፈን እንላክላቸውና መልስ ብንጠብቅ ›› አለ ያማተበው ወታደር
‹‹ የባሰው መ……ጣ !›› አሉ ጓድ መንግስቱ ….. አሁን የእውነትም የግርምት ሳቅ ፊታቸው ላይ ላጭር ጊዜ ፍንትው ብሎ ነበር …‹‹ ንጉስ ሆይ ዙፋንወትን እንዲለቁና  ‹ለቅቄላችኋለሁ ኑ › ብለው እንዲጠሩን አራተኛ ተሰብስበን እየጠበቅነዎት ነው ›› ብለን ደብዳቤ እንላክና መልስ እንጠብቅ …? ጓዶች ወይ የስብሰባው መርዘም እንቅልፍ ለቆብን እየቃዠን ከሆነ እስቲ ወጥተን ንፋስ እንቀበልና እንመለስ  ›› አሉ
‹‹ ኧረ ምን ንፋስ አለ ጓድ ? ድፍን አገሩ ታፍኖ እንኳን በኮሚቴ በግለሰብም የሚተነፈስ አየር የለም ›› አለ ሌላኛው  … አዳራሹን ሳቅ ሞላው …በእርግጥም ከተማው በተማሪ አመፅ በወታደሮች የደመወዝ ጥያቄ በደርጉ ሹክሹክታ ታፍኖ ነበር ፡፡
በመጨረሻም ደርጉ ኮሚቴ እንዲመረጥና ለንጉሱ ውሳኔውን በፅሁፍ እንዲያሰማ ወስኖ ፅሁፉ  …ሲዘረዝና ሲደለዝ አምሽቶ   ግሩም የሆነና ለንጉሱ የሚመጥን ታሪካዊ ንግግር ተዘጋጀ ፡፡ ለንጉሱ መልእክቱን የሚያደርስ  ኮሚቴ ተቋቋመ ፡፡  ቀጥሎ  ደብዳቤውን ንጉሱ ፊት  የሚያነብ   ድምፁ የሚያምር የኮሚቴ አባል ለመምረጥ ደብዳቤው እየዞረ ተራ በተራ ሁሉም እንዲያነቡ ተወሰነ ፡፡ የመጀመሪያው ሰውየ ደብዳቤው ሲሰጠው
‹‹ ምን ላርገው ›› ሲል ጠየቀ
‹‹ አንብበዋ ››
‹‹ ማንበብና መጣፍ አልችልም ጓዶች !  እኔ የገበሬ ልጅ … ኋላም ለእናት አገሬ በዱር በጫካ ስንከራተት የኖርኩ ወታደር ነኝ ›› ሲል አስተዛዝኖ ተናገረ (በእርግጥ ይህ ሰው የኋላ ኋላ ጋዜጣ ሲያነብ ተገኝቶ አቢዮቱን በመዋሸት በሚል እንደተረሸነ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ )
ቀጣዩ ሰው ሰው ፅኑ የእይታ ችግር እንዳለበትና መነፅሩን ረስቶ መምጣቱን በመናገሩ ታለፈ …. በመጨረሻም አንድ ቆፍጣና ወጣት ‹‹ ፅሁፉን ወዲህ በሉት››  ብሎ ሲያንበለብለው ሁሉም ደስ አላቸው  ‹‹ በቃ አንተ አንብበው ›› ተባለ ፡፡ ሲያጠናው እንዲያድር ስለተነገረው  ደብዳቤውን ይዞ ወደ ማደሪያው ሄደ፡፡
በቀጣዩ ቀን ኮሚቴው ወደቤት –  መንግስት መንገድ እንደጀመረ  አንባቢው ወጣት እነዲህ ሲል ኮሚቴውን ጠየቀ ‹‹ ጓዶች ለድፍረት እዚች ማንአህሎሽ ግሮሰሪ ገባ ብለን አንድ ሁለት ብለን ብንሄድስ ?››
‹‹ የተቀደሰ ሃሳብ››  አለ የተጨነቀው ኮሚቴ … ኮሚቴው ወደግሮሰሪው ገባ አለና ለሰላሳ ደይቃ ያህል በቁሙ  ጠንከር ያለ መጠጥ ቀማምሶ  ድፍረት በድፍረት ሁኖ ወደቤተመንግስት ገሰገሰ . . . ንጉሱ ፊትም ሳተና ሁኖ በመቆም የተመረጠው ወጣት ደብዳቤውን መዝረጥ አድርጎ ከኪሱ በማውጣት ማንበብ ጀመረ
‹‹ ሰላም ከፀሃይ ለደመቁ አይኖችሽ … ሰላም የሃር ጉንጉን ለመሰለ ፀጉርሽ … ሰላም እንደወፍ ለሚስረቀረቅ ድምፅሽ … ሰላም  እንደሚሳኤል ለተቀሰሩ ጡቶችሽ . . . አንች  የውቦች ውብ  የአለም  ልእልት …›› እያለ ማንበብ ጀመረ ፡፡  ጃንሆይ ግራ በመጋባት
‹‹  እኛን ነው ? ›› ሲሉ ጠየቁ ፡፡
ኋላም ፊታቸው ቁሞ  እንደዳዊት ደብዳቤውን የሚደግመውን ወጣት በጥሞና አደመጡና
 ‹‹  ምድረ ወታደር ሊገለብጠን ነው ስንል ለካስ ልጃችንን ውቧን  ልእልት  ለጋብቻ ሊጠይቅ ነው ተንጋግቶ  የመጣው ›› ሲሉ ዙፋናቸው ላይ ተመቻችተው ፈገግ አሉ . . . አንባቢው ወታደር  ግን ከጎኑ በቆመ ሌላ ወታደር ክንድ ሲጎሸም  ደንግጦ  ወረቀቱን ወደአይኑ ጠጋ አድርጎ ተመለከተው … ላፈቀራት ቆንጆ የፃፈውን ደብዳቤ  ነበር አላውጦ ከኪሱ በማውጣት  በሞቅታ ያንበለበለው  ! ንጉሱ በአክብሮት ነበረ ከዙፋናቸው የተነሱት . . . .መልሰው ዙፋናቸው ላይ አልተቀመጡም …. !
የንጉሱ ፀጉር አስተካካይ  የነበሩት  ጋሽ አፍለኛው እንደሚሉት ከሆነ ግን ንጉሱ ወደሰማይ እያዩ ተራግመዋል ‹‹ በፍቅር እንዳታለላችሁን ፍቅር ይንሳችሁ … ያባላችሁ ያናጫችሁ ››ብለው
አንዳንድ የራስ ተፈሪያን እምነት አራማጆች ታዲያ እስከዛሬ  ድረስ  ‹‹ የኛ ንጉስ በፍቅር ደብዳቤ እንጅ በደርግ ማስፈራሪያ አይደለም ከዙፋናቸው የወረዱት ›› እያሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ ፡፡ስለፍቅር ደግሞ እንኳን እሳቸው ክርስቶስም ከሰማይ ወርዷል እንደማለት  የጀማይካ ህፃናት መዝሙር ሁሉ አላቸው
‹‹ጃ ፍቅር እንጅ አይፈሩም ጠመንጃ !››
Filed in: Amharic