>

ዝም በሉ! አስከሬናችሁን ቅበሩ! ቀስታችሁን አስለቅሙ! ነገር ግን ዝም በሉ! እንዲሆንን፣ እንዲያ ተደረግን አትበሉ!!! (ዘመድኩን በቀለ)

በጥይት የተረሸነው፤ በቀስት የተወጋው ዐማራ ስለሆነ ሀገር እንዳትረብሹ ዝም፣ ጭጭ በሉ!!
 ዘመድኩን በቀለ
 ዝም በሉ! አስከሬናችሁን ቅበሩ! ቀስታችሁን አስለቅሙ! ነገር ግን ዝም በሉ! እንዲሆንን፣ እንዲያ ተደረግን አትበሉ!!! 
•••
በገዛ መሬቱ፣ በእራሻ በማሳው ላይ ከመረሸን፣ ከመሞት፣ ከመገደል፣ ከመወጋት፣ ከመሰደድና ከመፈናቀል በቀር ሌላ ዕድል እንዳይኖረው የተፈረደበት ምስኪን የምድራችን ፍጡር ነው ዐማራ። አሁን አሳምነው ጽጌ የለም። የጉምዝ ቀስተኞችም ወደ ቀደመው የመግደል ስራቸው ተመልሰዋል። በቀስትም በጥይትም ዐማራ በገዛ መሬቱ ላይ ይረሸን ጀምሯል። ሚዲያ ግን አይዘግበውም፣ መንግሥት አይተነፍስም። ምክንያቱም የሞተው ዐማራ ነዋ።
•••
ይሄንን አረመኔያዊ ድርጊት መቃወም ደግሞ በዚህ ዘመን ፖለቲከኛ ነው የሚያስብለው። የዐማራን በደል መናገር የሀገር ገጽታ ያበላሻል፣ ቁጣ ይቀሰቅሳል፣ ሀገር ይረበሻል፣ ትርምስ ይፈጠራል፣ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ እናም ዝም በል፣ ቻል፣ ዋጥ አድርገው ትባላለህ።
•••
ከሌላው ብሔር አንድ ሰው የሞተ ጊዜ ግን መንግሥት መግለጫ ያወጣል። መከላከያ ይሰፍራል። ሚዲያዎች ሙሾ ያወጣሉ። ክልሎች የሀዘን መግለጫ ያወጣሉ። የውጭ መገናኛ ብዙሃን ይጋበዛሉ። የሃይማኖት መሪዎች ምህላ ያዛሉ። የተቃዋሚ ፓርቲዎች በየተራ ሚዲያ ጠርተው መግለጫ ያወጣሉ። አዴፓ ለሟቹ ክልል ካሳ ይከፍላል።
•••
ዐማራ በጅምላ ሲገደል ግን ሁሉም ባላየ ባልሰማ ላሽ ብሎ ይሄዳል። አሁን የዐማራ ሞት የተለመደ፣ የማያስደነግጥ፣ የማያሳስብ እንደሆነ ተደርጎ እንዲቆጠር ተሥርቶበታል። የዐማራ ነፍስ ከዶሮ ነፍስ እኩል እንዲታይ ተደርጓል። ማነው የተገደለው?  ይልህና ዐማራ ስትለው ነው እንዴ ነው የሚልህ? ሌላ ብሔር ከሆነ ግን እዚያው ከፊትህ ነው ነጠላ መዘቅዘቅ የሚጀምረው።
•••
የዐማራ መሪ ተብዬዎቹም እነ ላቀ አያሌው ጉዳያቸው አይደለም። ደመቀ መኮንን ከቤተ መንግሥት አይውጣ፣ ምክትልነቱን አይንጠቁት እንጂ የዐማራ ሞት ደንታውም አይደለም። በአጠቃላይ የዐማራ ሞት ለአሁኒቷ ኢትዮጵያ ምኗም አይደለም።
•••
እየቆየ ሲሄድ ዐማራ የኩርድ ህዝብ ዕጣ ይደርሰዋል። ሀገር ዐልባ ሆኖ ያርፈዋል። በል ደግሞ ለዐማራ ታደላለህ በለኝ። እኔ ሰው ነኝ። የሰው በደል፣ ህመም የሚሰማኝ ሰው ነኝ። እኔ ዐማራም ምንም አይደለሁም። እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። የኢትዮጵያውያን ሁሉ ህመም የሚሰማኝ። የተረሸኑት ዜጎች ያስረሸናቸው ዐማራ መሆናቸው ብቻ ነው። ስለ ፖለቲካ የሚያውቁትም፣ የሰሙትም ነገር የሌላቸው ምስኪን ዜጎች።
•••
ነፍስ ይማር ወገኖቼ  !!
•••
ሻሎም  !  ሰላም  !  
ታህሳስ 6/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic