>
5:16 pm - Saturday May 23, 5333

ከፍጥረት ሁሉ አደገኛውና አስመሳዩ ፍጥረት - ሰው!!! (ስብሃት ገብረእግዚአብሔር)

ከፍጥረት ሁሉ አደገኛውና አስመሳዩ ፍጥረት – ሰው!!!

ስብሃት ገብረእግዚአብሔር
ሰው ልዩ ፍጡር ነው ልዩ ከሚያደርጉት ጠባዮቹ አንዱ በስርዓትና በስነ ስርዓት ማመንና መኖሩ ነው። ውትድርና ስርዓትና ስነ ስርዓት ነው። ከተራ ወታደር እስከ ሻምበል እስከ ጄኔራል መለዮውና ማዕረጉ ባይኖር ኖሮ እኮ ማን ከማን ያንሳል። ሁሉስ ለመግደል ወይ ለመሞትስ አይደለም? ተጠንቀቅ አሳርፍ ቀኝ ኋላ ዙር ባለህበት ሂድ በብረት ሰላም በል ስነ ስርዓት።
ቅስና ስርዓት ነው ከዲያቆን እስከ ቄሰ ገበዝ ከጳጳስ እስከ ኤጲስ ቆጶስ እስከ ቆሞስ ቅዳሴውም አቋቋም ማሸብሸቡም ከበሮውም ፅናፅሉም መቋሚያውም ሁሉም የሚንቀሳቀሰው ስርዓቱን እየጠበቀ ነው።
ስንወለድ በስነ ስርዓት ነው አዋላጇ ትጠራለች ወንዶች ይወጣሉ ይሄ የሴቶች ጉዳይ ነው ሴት ስትወለድ ሦስት እልልታ ወንድ ሲወለድ ሰባት እልልታ ግርዛት ክርስትና ፍጥምጥም ሠርግ ለቅሶ መቀመጥ አርባ ሙት ዓመት ከማህፀን እስከ መቃብር ከስነ ስርዓት ወደ ስነ ስርዓት እየተሻገርን ነው የምንጓዘው። ሴቶች የማርያምን ጽዋ ሲጠጡ በስርዓት ነው ማነሽ ባለ ሳምንት? ወንዶች ሲፋለሙ በስነ ስርዓት ነው በልጅነታቸው ሲጫወቱም በስነ ስርዓት ነው የቡድን እና የቡድን አባቶች ከወርቅ እንክብል እስከ ሸማ ጥቅል።
ፍርድ ቤት ያው ጭብጡ ፍትህና ስርዓት ነው የዳኞቹ ግርማዊ አለባበስም እየተስታወሰ የከሳሽ ክስ ይነበባል ቀጥሎ የተከሳሽ መልስ ቀጥሎ የመልስ መልስ የተፈረደበት ወደ እስር ቤት ወይም ወደ ሞት ሲላክ እንኳን በስነ ስርዓት ነው። ስነ ስርዓት በየሁኔታው እየገባ ኑሯችንን በሰልፍ ያስኬዳል።
 ሰውን ልዩ ፍጡር የሚያደርገው ሌላው ጠባይ ከስነ ስርዓቱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው መምሰልና ማስመሰል የሚበዛበት አኗኗር ነው። መስሎ ማደር…
ጠቢቡ ሰለሞን በማስመሰል ነበር ሳባን የተገናኛት እንቅልፍ ሲወስደው ዓይኑን ከፈተ ዓይኑን ሲጨፍን ግን ነቅቶ ነቄ ሆኖ እያያት ነበር።
ለመምሰልም ጊዜ አለው ለማስመሰልም ጊዜ አለው።
ከልጅነት ጀምሮ ማስመሰል አብሮን ይጓዛል እንዲያውም የልጅነት ኑሮ አብዛኛው ማስመሰልና መዋሸት ነው የሚዋሸው ግን ለክፋት ሳይሆን በምናቡና በእውነታው መካከል ያለውን ልዩነት ባለ መገንዘቡ ነው። ክፉና ደጉን በደንብ አይለይም።
ዝንብ ይይዝና ክንፏን ነጭቶ ይጥለዋል ጠጠር ወርውሮ የውሻውን እግር ይሰብረዋል አነጣጥሮ መምታት ይችል እንደሆነ ለማየት እናም የውሻውን ጩኸት ለመስማት የውሻውን ስቃይ ልብ ብሎ አያስተውለውም የዚህ አይነቱ ማስተዋል ገና ነዋ።
ሠርግ እንሂድ እስቲ አናስገባም ሠርገኛ እደጅ ይተኛ።
ያ ሁሉ ስነ ስርዓት ሽማግሌዎች መላኩ የጥሎሽ ልብስ ያ ሁሉ ጌሾ ወቀጣ ሠንጋ መጣል ያ ሁሉ ወጥ መሥራት ሠርገኛ ለመቀበል ነበር። ቢሆንም አናስገባም ሠርገኛ እደጅ ይተኛ ይባላል።
ጦርነት ውስጥ ብዙ ማስመስል አለ። ከጥንታዊ የሮማ ታሪክ የማይጠፋ ምዕራፍ አለ የአንድ አይናው ሃኒባል ሠራዊት ድል ሆኖ ሸሸ የሮማ ሠራዊት አሳደደው አሳደደው አሳደደውና ሮማዊው ጄኔራል ዞር ብሎ ቢያይ ተከበዋል ወሬ ለመንገር እንኳን አንድ ሰው ሳይቀር የሮማው ሠራዊት አለቀ።
ጉግስ ጨዋታ ጦር ሜዳ ገብተን የምንዋጋ ማስመስል ነው።
አንዱ ሌላውን ሲያባርር በጦር ሊወጋው ይወረውራል ያ  የሚሸሸው እየጋለበ ዞሮ በጋሻው ይመክታል ካልቻለ ይወጋል የማስመሰል ውርወራ እንጨት ነው የተወረወረው እንጂ ጫፉ ላይ የብረት ጦር የለበትም።
መድረክ ላይ እነ ሼክስፒር የሚያቀርቡት ተውኔት ማስመሰል ነው። ዛሬ ሐምሌትን ሆኖ ይሞትና ሳምንት ደግሞ ማክቤዝን ሆኖ ይሞታል ተመልካች ሐምሌት መሞቱን ያምናል ሼክስፒር እያስመሰለ መሆኑንም ያምናል።
ተዋናዩ ተመልካቹን እኔ ውሸቴን ነው እናንተ ግን እመኑኝ ይላቸዋል የምትታመን ውሸታም መሆንህን ወደን ተቀብለናል ይሉታል።
የተዋጣለት ሲኒማ ስናይ እዚያ ጨለማ ውስጥ ብዙ ብንሆንም እያንዳንዳችን ግን ብቻችንን ሆነን ነው የተቀመጥነው አንሶላው ላይ እየተተወነ ያለው ድራማ ውስጥ እኔም አለሁበት ተዋናዩም ተመልካቹም እኔው ነኝ ሁለት ነገር በአንድ ላይ መሆን የምችል ፍጡር ነኝ። ለምን? “ሰው ነኝ።”
Filed in: Amharic