>

ታኅሣሥ 7 በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተገደሉት የንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት ሹማምንት ( ብርሃኑ አስረስ)

ታኅሣሥ 7 በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ (በታህሳስ ግርግር) የተገደሉት የንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት ሹማምንት 

ብርሃኑ አስረስ
በታኅሣሥ ወር 1953 ዓ.ም በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይና ገርማሜ ነዋይ እንዲሁም በሌሎች ተባባሪዎቻቸው የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ታኅሣሥ 4 ተጀምሮ፣ ታኅሣሥ 5 ዓላማውን ለሕዝብ ይፋ አድርጎና ታኅሣሥ 6 ደግሞ ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተቃዋሚ ኃይል ጋር በአየርና በታንክ ጭምር የተፋፋመ ውጊያ ማድረግ ጀምሮ ታኅሣሥ 7 ላይ ደረሰ፡፡
 – – –
ታኅሣሥ 7 ቀን 1953 ዓ.ም (ከ59 ዓመታት በፊት) መፈንቅለ መንግሥት ሞካሪው ቡድን እየተዳከመ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተቃዋሚ ኃይል ደግሞ እየተጠናከረ ሄደ፡፡ ይህን የተገነዘቡት የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪው ቡድን አባላት  በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን የንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት ሹማምንትን (ሃያ የሚሆኑ መሳፍንትን፣ መኳንንትን፣ ሚኒስትሮችንና መኮንኖችን) ወደ አረንጓዴ ሳሎን አዛውሩና አልጋወራሹንና አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለብቻቸው እንዲጠበቁ ማድረግ ጀመሩ።
የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪው ቡድን አባልና በወቅቱ የፖሊስ ሰራዊት አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ወዲያው ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተቃዋሚ ኃይል በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ዋና ጠንሳሶች እነ ብ/ጀ መንግሥቱ ንዋይ ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር የነበሩ ሹማምንትን ረሽነው ለማምለጥ ወሰኑ፡፡
በዚህም መሰረት ስመ ጥሩ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ፣ ራስ ሥዩም መንገሻ፣ ሜ/ጀ ሙሉጌታ ቡሊ፣ አባ ሐና ጅማ፣ ብላታ ዳዊት ዕቁበ እግዚ፣ ብላታ አየለ ገብሬ፣ አቶ መኮንን ሐብተወልድ፣ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ፣ አቶ ገብረ ወልድ እንግዳወርቅ፣ አቶ ታደሰ ነጋሽ … በጠቅላላው አሥራ አምስት ሰዎች ተገደሉ፡፡
የክብር ዘበኛ መኮንን የነበሩት ሻምበል ደረጀ ኃይለ ማርያም (የስመ ጥሩው አርበኛ የደጃዝማች ኃይለ ማርያም ማሞ ልጅ እና የንጉሠ ነገሥቱ የልጅ ልጅ የልዕልት ሶፊያ ደስታ ባል) የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪውን ቡድን በመቃወም የቤተ መንግሥቱን አጥር በታንክ ደምስሰው ሲገቡ ከመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪው ወገን በተተኮሰ ጥይት ተገደሉ።
ሦስት ግለሰቦች ደግሞ ቆስለው ተረፉ፡፡ በወቅቱ የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አንዳርጋቸው መሳይ እና አንድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው ተርፈዋል፡፡ ቆስለው ከተረፉት ሰዎች መካከል አንዱ በ12 ጥይቶች ተመትተው የተረፉት ብርጋዴር ጀኔራል መኮንን ደነቀ ነበሩ።
የመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪው ቡድን አባልና በወቅቱ የፀጥታ/ደህንነት ክፍል ኃላፊው ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተቃዋሚ ኃይል ሲከበቡ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብለው ራሳቸውን አጠፉ። ብ/ጀ መንግሥቱና ወንድማቸው ግርማሜ ከቤተ መንግሥቱ አካባቢ ሸሹ፡፡
ንጉሰ ነገስቱ አሥመራ በደረሱ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በራዲዮ ያስተላለፉት መልዕክት!!!
 
በታኅሣሥ ወር 1953 ዓ.ም በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይና ገርማሜ ነዋይ እንዲሁም በሌሎች ተባባሪዎቻቸው የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከሽፎ የውጭ አገር ጉብኝት ላይ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከብራዚል ተመልሰው በአስመራ በኩል አዲስ አበባ የገቡት/የደረሱት ከዛሬ 59 ዓመታት በፊት (ታኅሣሥ 8 ቀን 1953 ዓ.ም) ነበር፡፡
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አሥመራ በደረሱ ጊዜ ለኢትዮጲያ ሕዝብ በራዲዮ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ ከዛሬ 59 ዓመታት በፊት (ታኅሣሥ 8 ቀን 1953 ዓ.ም) አሥመራ በደረሱ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በራዲዮ ያስተላለፉት መልዕክት ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ነው …
‹‹ … የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን ታላቅ ያሰኘው የሕዝቡ ታማኝነትና ቆራጥነት ነው። ይልቁንም ሕዝቡ ሕዝቡ አገሩን መልካም ስም ስጥቶት በዓለም እንዲታወቅ ያደረገው በቆራጥነት የአምስት አመት አርበኝነትና ስደተኝነት የተፈጸሙት ቆራጥ ሥራዎች ሲሆን ይህንን ጀብዱ በመላው ዓለም የማያደንቅ የለም።
አሁን አገራችን ወደ ሥልጣኔ እርምጃ አደረገች በሚባልበት ጊዜ በአዲስ አበባ ብቻ የተነሳው ሁከት አገራችን ወደ ኃላ ለመመለስ ከሚያስቡ የተጋጠመ ይመስላል። አንድ ጠብታ ደም ማፍሰስ ወይም ሁከት ማንሳት መላዋን ኢትዮጲያ ከታላቅ ፈተና ላይ መጣል አይደለምን? በየጊዜው የሚደርሰው የራዲዮ ወሬ የክብር ዘበኛና ፓሊሶች ናቸው ይባላል ።ይህንንም ማንኛውም ፍጡር የሆነ ሰው ሊያምነው አስቸጋሪ ነው። ከህዝባችንም ውስጥ የተመረጡበት ሥራ እጅግ ከባድ ኃላፊነት ያለው ነው።
መላው የኢትዮጵያ በጸጥታ ላይ ሆኖ በአዲስ አበባ ሁከት ስለፈጠሩ በጣም አሳዝኖናል ። በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የአፍሪካ ክፍለ አለም ሀገሮች የደቡብ አሜሪካ ህዝቦችና መሪዎች ጋር መተዋወቅና መዛመድ እንደዚሁም ቃል በቃል መነጋገር ለሀገራችን ታላቅነትና እድገት ይረዳል ብለን በማሰብ ጀምረን የነበረውን ጉዞና ቀጠሮ ሰርዘን ወደ አዲስ አበባ ተመልሰን በመምጣት አሁን አስመራ ደረስን።
ከክብር ዘበኛ ከፓሊስም ወይንም ከሁከት አንሺዎችም ቢሆን ወደ እኛ መጥቶ ሊያስረዳን የሚፈልግ ሰው ቢኖር ተቀብለን እናነጋግረዋለን። ሁከት አንሺዎችን በመቃወም መንግሥታችንና ህዝባችንም እንደዚሁ የሀገሩን ጽጥታ ለማስከበርና ለመጠበቅ የጦር ሠራዊታችንና የአየር ኃይላችን ሕዝባችንም የሚያደርገውን ትግል ሰምተናልና መልካም አደራረግ ነው። እስክንደርስ ድረስ ሁከቱን ለመደምሰስ ትግላችሁን ቀጥሉ።
መላውስ ኢትዮጵያ በሰላም ረግቶ አዲስ አበባ ለምን የሁከት ምንጭ ይሆናል? ሁከት አንሺዎቹም ወገናቸው በማስመሰል የተወደደ ልጃችን የአልጋ ወራሻችንንና እንደዚሁም ከመኳንንቶቹ በጣም የምናምናቸውን ሰዎች ስም እያገቡ የሚያወሩትና የሚያስወሩት ወሬ በፍጽም ሀሰት መሆኑንና ይህውም ሁከቱን ለማጋነን የተደረገ ሥራ መሆኑን ተገንዝበናል።
በጠቅላላው በአጭሩ ለሁከት አንሺዎቹ የምንነግራቸው ለታላቋ ኢትዮጵያና ሕዝቧ እንደዚሁም ለታሪኳ እኛና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የደከመበትን በማስታወስ በዚህ ሁከት ምክንያት የውጭ እጅ ገብቶ የኢትዮጵያን እንደገና ከአደጋ ላይ እንዳያደርሳት በማሰብ አሁኑኑ ደም መፋሰሱ እንዲቀር ይሁን። እንደምታውቁትም ያባትነት ርኃራሄና ፍርድ ልማዳችን ነው። በተረፈ ዝርዝሩን ሁሉ እዚያው አዲስ አበባ በደረስን ጊዜ እናካፍላችሁዋለን።››
– – –
ምንጭ፡ ‹‹ማን ይናገር የነበረ … የታህሳስ ግርግርና መዘዙ›› (በአቶ ብርሃኑ አስረስ)
Filed in: Amharic