>
5:13 pm - Thursday April 20, 9939

ሞጣን ባሰብኳት ጊዜ ...  " (ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ) 

ሞጣን ባሰብኳት ጊዜ …  ” 

* የነገሩ ምንጭ መፍትሄውን ይጠቁማል !!!

> በጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ 
  የሆነው ሁሉ ነውርና መደገም የማይገባው ነው። ሳወግዝ አድሬያለሁ። ሳወግዝ እኖራለሁ።  ግን የሆነው ለምን ሆነ? መፍትሄው ያለው የችግሩን ምንጭ ጠንቅቆ ከማወቅ ነው።
ልጅነትና ጉርምስናዬ እንደዚህ ነው ሞጣ ላይ ያለፈው።
   ሞጣ ላይ ካሉት መስጊዶች ሶስቱ ሲሰሩ ወይም ሲታደሱ ተሳትፌያለሁ። የአዳሻው መስጊድ ሲታደስ እኔ የጊዮርጊስ ሰፈር ነዋሪ ነበርኩና ከጓደኞቼ ከነጡሃርና ሙሀመድ ይብሬ ጋር የልስን ጭቃ አቡክተናል። የውሃ ልክ ድንጋይ አቀብለናል።
የግራር ውሃው ትልቁ የከተማው መስጊድ ሲታደስ ሲሚንቶ ከነ ዘይኑ መሀመድ ፡ ከነ አህመድ እንዳለው ጋር ሆነን ከመኪና አውርደናል ፡ ውሃ ከጉድጓድ ቀድተን በበርሜል ሞልተናል።
ላይማሪያም ሰፈር ቀይሬ ስኖርም አዲስ ሰፈር ነበረና አዲስ መስጊድ ተቋቋመ። ያኔ ደግሞ ከነ አህመድ ሃሰን ከነ አሊ ጋር ሆነን አጥር አጥረናል። ከአባ ሀሰን ጋር ሆነን የመስጊዱን ግድግዳ መትከያ ጉድጓድ ቆፍረናል። ሁላችንም ታላላቅ ሰዎችን አባ እከሌ ነበር የምንለው። ጋሼ እንደማለት።
ጥንታዊውና በአፄ ፋሲል የልጅልጅ ልዕልት ወለተ እስራኤል በ 1747 ዓም የታነፀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሲታደስ እነ አባ ቃሲም ፡ እነ አባ ሃሚድ ፡ እነ አባ እንዳለው ሀሚድና እልፍ ሙስሊሞች ቆርቆሮ ገዝተዋል። በመኪኖቻቸው አሸዋ አመላልሰዋል። ሌሎችም እንደዛው።
ግራር ውሃ የገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲገነባ የከተማው ሙስሊም ብዙ ረድቷል። የምረቃው ዕለት ሰንጋቸው አርደው በደስታ እየተንጎማለሉ አስመርቀዋል።
ይህ የአብሮነት ጥቂት ማሳያ ነው። በየቤቱና በየጎረቤቱ ብሎም በየጓደኝነታችን ያሳለፍነውን ፅፌ አልጨርሰውም።
ታዲያ ይህ ለኛ ለሞጣ ልጆች የተለመደ ነው። መስጊዶች ሲሰሩ አብሬ የነበርኩት የእናቴን ቤት እንደመስራት እንጅ ለውለታ አልነበረም። እነ አባ ሃሚድ በየ ጊዜው ስለት ሲያስገቡ ወይ ደግሞ እጣን ከሱቃቸው ሲለግሱ ለክርስቲያኑ ውለታ ብለው አልነበረም። የራሳቸው ስለሆነ እንጅ።
እንዲህ ነው ሞጣ ያደግነው ፡ እንዲህ ነው ሞጣ የኖርነው። ሞጣ ቀራኒዮ ጒልጅነትና ጉርምስናዬ እንዲህ ነበር ያለፈው።
የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬን አጠናቅቄ ፡ ስራ አዲስ አበባና ባህር ዳር ጀምሬ ከርሜ ወደ ከተማዬ ስመለስ የተወሰኑ ለውጦች ጠበቁኝ።
የማላውቃቸው ሰዎች ውርውር ይላሉ። የሆነ ጊዜ ብጥብጥ ተነስቶ በውድ አባቶቻችን ሽምግልና መርገቡን ሰምቻለሁ።
ወዘ ልውጦቹ ፅንፈኝነትን በከተማዋ ሊያሰርጉብን ነው የሚል የነዋሪው ስጋት ከፍተኛ መሆኑን ከራሳቸው ከሙስሊም ጓደኞችምና ከጓደኞቼ ወላጆችም አረጋግጫለሁ።
ይህ ስጋት የተጋባበት የከተማው እስልምና ምክር ቤት የግጭት መነሻ ሊሆን እንደሚችል ስጋቱን ለከተማው አስተዳደርና በግልባጭም ለከፍተኛ አካላት በደብዳቤ አሳውቆ ነበር።
የከተማው ወጣቶች ትናንት ያደረጉት ትክክል ያልሆነ ጥፋት መነሻው ከፅንፈኛ አካላት ጋር ግንኙነት ያላቸውና በከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየኖሩ ያሉ ሰዎች ቤተ ክርስትያኑን ለማቀጠል ሲመካከሩና ሲዝቱ ታይተዋል የሚል ወሬ በመነዛቱ ነው።
ሰሞኑን የክርስትያን አማኙ በፀሎትና ምህላ ነው የሰነበተው። ትላንትም አመሻሹን ፀሎት ላይ ነበር ህዝቡ። በመሃል የቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ሲነድ ታዬ። ከቅጥረ ግቢ ውጭ የነበሩና ሲቃጠል ያዩ የድረሱልን ጥይት እየተኮሱ ገቡ።
በከፍተኛ ርብርብ ማትረፍ ተቻለ። የቃጠሎው መነሻ ከውስጥ ምናልባትም ጧፍ እንደሆነ ቢገመትም እርግጠኛው ነገር ግን ገና አልታወቀም።
ይህ የቤተ ክርስትያኑ ተቃጠለ መረጃ ከተማውን አዳረሰ። ቤተክርስትያኑን ያቃጠሉት ተልዕኮ ተጥቷቸው የሚሰሩ ሙስሊሞች ናቸው የሚለው ወሬ ውስጥ ውስጡን ሲታመስ የነበረው ወጣት ወደ መስጊዶችና “በጥርጣሬ” እናየዋለን ወደሚሉት ማርዘነብ ህንፃ ሄደው እንዲቃጠል አደረጉ። አንዳንዶቹም አራት በአራት በማባለው የገበያ ማዕከል የዘረፋ ሙከራ አደረጉ።
ከተለያዩ ሙስሊም ጓደኞቼ ፡ ከከተማው አስተዳደር ባልደረቦችና ከቤተሰቦቼ ደውዬ እንዳጣራሁት በትልቁ ግራር ውሃ መስጊድና በሌሎች ሁለት መስጊዶች ላይ ጉዳት ደርሷል። በህዝብ ርብርብም ቃጠሎውን መረባረብ በመቻሉ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር ተችሏል።
የሆነው ያሳዝናል። በፍቅር ለኖርነው እኛ ፡ ድንጋይ አቀብለን የሰራነውን መስጊድና አሸዋና ጠጠር አመላልሰን ላሳደስነው ቤተክርስትያን ይህ ድርጊት እኛን አይመጥነንም። ያሳፍረናል። አንገታችንን አስደፍቶናል። መስጊዶቹም የኛ ፡ ቤተ ክርስቲኖቹም የኛ ብለን ላደግን ፡ ሙስሊምና ክርስቲያንነታችን ከእምነትነት በዘለለ ትስስራችንንና ጋብቻችንን ላልከለከለን እኛ ዛሬ መሃላችን የገቡ ጥቂት በጥባጮች ስር ሊሰድ የተቃረበ ጥርጣሬን በከተማዋ ዘርተዋል። ስሜታዊና ግብታዊነት የሚነዳውን ወጣት ፈጥረውብናል።
ይህ ሊቆም ይገባል። ለክርስትያኑና ለሙስሊሙ እኩል የሚከበሩ አገር አስታራቂ ከተማዋ ሞልቷታል። ከተማ አስተዳደሩ ችግሩ ስር እስኪሰድና የከተማው መጅሊስ የሰጠውን ማሳሰቢያ ቸል በማለቱና ይህ ጉዳት በመከሰቱ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል። የክልሉም ሆነ የዞኑ መስተዳድር የፀጥታ መዋቅሮች በሞጣ ሊፈነዳ የሚችል የታፈነ ችግር እንዳለ ያውቃሉ። ችግሩ ለመፈጠሩ ሁሉም ተጠያቂ ነው።
እናንት ውድ የከተማዋ ነዋሪ ክርስትያንና ሙስሊም ዘመዶቼ አሁንም ነገሩን ከምንጩ አጣሩት። የከተማዋ ሽማግሌዎችና የሀይማኖት መሪዎች ቁጭ ብላችሁ ምከሩ ፡ የቀድሞውን የጋራ ዕድርና የጋራ ህይወት አፅኑ። አጥፊዎችም ለህግ ይቅረቡ። ይህ እንዲሆን ተረባረቡ።
ከዚያ ውጭ ሌሎች አጋጣሚውን ለክፉ ህልማችሁ ማሳኪያ ተገን እያደረጋችሁ ያላችሁ፡ የከተማውን እውነተኛ ኑባሬና ስዕል የማታውቁ አፋችሁን ዝጉልን። የከተማዋን ችግር ራሱ ነዋሪው የመፍታት ባህል አለው። የምንንናገረው በምናውቀው ልክ ይሁን።
Filed in: Amharic