>
5:13 pm - Sunday April 19, 6212

በቃጠሎው የተቃጠለው ማነው? (ደረጄ ደስታ)

በቃጠሎው የተቃጠለው ማነው?

ደረጄ ደስታ
ዛሬ ያወራነው ነገር መች ሄዶ እሳት እንደሚሆን አናውቅም። ክብሪቱ ከተለኮሰ ቆይቷል እሳቱ ገና ዛሬ መንደዱ ይሆናል። ዛሬ ጠላቶቻችን ናቸው ብለን እነሱን እያሰብን ያወጣነው ህግና ውግዘት ነገ ለወገኖቻችን ሊሆን ይችላል።
ነገሩን እንደ ተራ ነገር አሳንሶም ሆነ አለቅጥ አግንኖ ማራገብ አይጠቀምም። ጨርሶ ያጠፋናል ከሚል ስጋት ግን አይደለም። እስልምናም ሆኑ ክርስትና በዚህ አይጠፉም። እስልምና መስጊድ ወይም ክርስትና ቤተክርስቲያን አይደሉም። እነሱ የእምነቱ መገለጫዎች ናቸው። በነዚህ መገለጫዎች እሚፈጸመው ጥቃት የአጥቂውን አስተሳሰብና አደገኝነት የሚያሳይ ነው። አደገኝነቱ እሚያሳስበው ዛሬ መገለጫውን ያቃጠለ ነገ የ እምነቱን ተከታይ ከማቃጠልና ከመግደል አይመለስም ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ድርጊቱ የጥላቻ ፍሬ ስለሆነ ነው። ጥላቻ ደግሞ በጥላቻ ብቻ አይደመሰስም። ምክንያቱም መንስኤው ብዙ ነው።
ከአለማውቅ ድንቁርና እስከ ተወሳሰበው የፖለቲካ ውንብድና ድረስ ሊሄድ ይችላል። እንዲሁ ዝም ተብሎ በዘራፍና በሰይፍ ብቻ እሚጠፋ ውግዘት እሚያቆመው የአንዲት ቀን ውሳኔ ቀጥ እሚያደርገው ነገር አይደለም። ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያንም መስጊድም ተቃጥሎ እሚያውቅ ከሆነ ለወደፊቱም እማይቃጠልበት ምንም ዋስትና አይኖርም። ፕሮግራም ይዘንለት ተራ በተራ እንቀጣጠል እንደማለት ባይሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ ለመጨረሻም ጊዜ መሆን እሚገባው አናስመስለው። ከኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። መስጊድና ቤተክርስቲያን እንዳይቃጠል ማድረግ አንችል ይሆናል ሁኔታዎችን በሂደት እምናሻሽልበት አደጋና ግጭቶችን እምንቀንስበትን መንገድ ግን ያላማቋረጥ ማፈላለግ እንችላለን።
 ይህን ወገን ለማስደስት ወይም ያኛውን ወገን ለማሳዛን ተብሎ እሚደረግ ነገር ነገ ወደራስ ወገን ተመልሶ ይመጣል። በፈረጅነው ጅምላ መሠፈር ባቀናነው ውግዘት መወገዝ አለ። ምክንያቱም ጥቃትን ብቻ ሳይሆን ቅሌትንም ሲጋሩ ያቃጥላል። ባንተ ወገን ላይ የተደረገውን ብቻ አይተህ ያኛውን ወገን አብዝተህ አትኮንነው። የኔ ወገን ነው ያልከው ወንድምህ ነገ ምን እንደሚያደርግ አታውቅም። በዚህች ዓለም በብሔርተኝነቱም ሆነ የእምነት ጥላቻና ፖለቲካው ዓለም ለይቶ የከበረም ሆነ የከሰረ ወገን የለም። ወረሩን መጡብን ተስፋፉብን መባባል ከተጀመረ ዘመን የለውም። የሚሆነውን ሁሉ ከመሆን አቁሞ የታየ ግን ምንም ነገር የለም። በዚች አንድፍሬ ህይወታችን እንኳ እየተለወጡ የመጡ ነገሮችን ማስተዋል ካልቻልን መጭውን ማየቱ እንዴት ይሆንልናል? ለመቀበል የፈራነውን እንኳ ትተን ሳናውቅ የተቀበልናቸውን ነገሮች ፈትሸን ብናውቅ ምንኛ በተገረምን!
ከሁሉ ከሁሉ በላይ ግን አገር ካልገለብጥኩ ከማለት ሀሳብን ገልባብጦ መጫወቱ አንዳች ነገር ሳይገልጽ አይቀርም። እስኪ በዚህ በኩል ደግሞ ዞር አድርገን እንየው። ምናልባት ችግራችን አንድ አለመሆናችን ሳይሆን በጣም አንድ ከመሆናችን የተነሳ መለያየት አለመቻላችን እንደሆነስ? ከአንድነት ይልቅ ልዩነት እሚጠማን ምናልባት ልዩነትን አጥተነው ከሆነስ? ማንኛችን ሙስሊም ማንኛችን ክርስቲያን እንድሆን እንኳ እማናውቅ ድብልቆች እንደሆንስ? እምነታችንን ብቻውን ተነጥሎ አስተዳደጋችን ሠፈራችን ትምህርታችን ሥራ ገበታችን ትዳራችን ሳይቀር አንድ ይመስላል። የክርስቲያን ወይም የእስላም ሉካንዳ ቤት ሐራም ሆኖብን የጎረቤታችን እትዬ ከድጃ ወይም የጋሽ ሐሰን ምግብ ቤት ቅቅል ግን ነፍሳችን ነው። ለማንኛውም ያ ሁሉ ቅስቀሳ ያ ሁሉ ቃጠሎ ያ ሁሉ የታሪክ መጽሐፍ ዘንብቦን እኛ ግን እቴ….ሥራም አልጠፋብን። እሚጮኹት እየጮኹ ይኸው ስንት ዘመናችን ቀጥለናል። ከጯኺዎቹ አንዳቸው ነገ ራሳቸው ፈጥነው ሊዘነጉት – ይሄማ ማዘናጋት ነው ሊሏችሁ ይችላሉ። ማረጋጋትስ ሊሆን እማይችለው ለምንድነው በሏቸው?
Filed in: Amharic