>

ከሰው ተራ ስንርቅ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ!?! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከሰው ተራ ስንርቅ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ!?!

ያሬድ ሀይለማርያም
የአንድ አገር ፖለቲካ ምህልቁን የብሔር ወይም የኃይማኖት ወይም የቀለም ወይም ሌላ የማህበረሰብ መለያ ላይ ሲጥል እያደር መዘዙ ብዙ ነው። እነዚህ የልዩነት መስፈርቶች ዜጎችን ከሰውነት ተራ እየገፉ ያወጡና ብሔር ወይም ኃይማኖት ወይም ሌላ የወል ካምፕ ውስጥ ገብተው እንዲዋጡ ያደርጋል። የሰውነትን ቦታ ብሔር እና ኃይማኖት ይቆጣጠሩታል። ለሰዎችም የሚቀርበው ጥያቄ ማነህ ሳይሆን ከየትኛው ጎራ ነህ ይሆናል። ውድቀታችንም ሆነ ስኬታችን፣ ሹመታችንም ሆነ ሽረታችን፣ ኪሳራችንም ሆነ ትርፋችን የሚለካው በሰውነታችን ሳይሆን በከተምንበት ካምፕ ይሆናል። ስንጠቃም ሆነ ስናጠቃ እንዲሁ በቡድን መለያችን ይሆናል።
እራስህን ከሰው ተራ ስታርቅ ወይም ሌሎች ከሰው ተራ እንዲያወጡህ ስትፈቅድላቸው ያኔ አንተነትህ ይደበዝዛል። ብቻህ መቆም የምትፈራ ደካማ ፍጥረት ትሆናለህ። እንደ ሰው አስበኽ፣ ያሰብከውን እንደ ሰው መተንፈስ ትፈራለህ። የገዘፍክ መስሎህ የምትጠለልበት የወል ማንነት ተፈጥሯዊ አንተነትህን እያደር ያራቁትሃል። ያኔ ስታስብም፣ ስትናገርም፣ ስትራመድም፣ ስትዋዋልም፣ ስትጣላም፣ ስትፋቀርም እኛ በሚል ጥላ ስር ሆነህ ነው። ጽድቅ እና ኩነኔ የግል መሆኑን ሁሉ ትረሳዋለህ።
በደልን፣ ግፍን እና ስቃይንም የምትለካው እንዲሁ እንደ ሰው ቆመህ ሳይሆን በተጠለልክበት የወል መለያ ካምፕ ውስጥ ስለሆነ በደቦ የተጠቂነት ስሜት ይሰኃሃል፤ በደቦም ለአጥቂነት ትዘምታለህ። በደቦ በደልን ታጠነጥናለህ፤ በደቦ በደል ትፈጽማለህ። በደቦ ታለቅሳለህ፤ በደቦ ታስለቅሳለህ። በደቦ ትቆጫለህ፤ በደቦ ሌሎችን ቁጭት ውስጥ ትከታለህ። በደቦ ታቄማለህ፤ በደቦ ሌሎች ውስጥ ቂምን ትዘራለህ። ከሰውነት ተራ ስትወጣ ነገርህ ሁሉ የመንጋ ስሌት ይሆናል። ከሰውነት ተራ ስትርቅ ነገርህ ሁሉ የምቧይ ካብ ይሆናል። በደቦ የካብከውን በደቦ ትንዳለህ።
በቅርቡ ጦቢያ ጃዝ ግጥም ምሽት መቶ አንደኛ ዝግጅታቸው ላይ ለመገኘት እድል ገጥሞኝ ነበር። እጅግ የማደንቀው እና ሁሌም ታዳሚ ለመሆን በምጓጓለት መድረክ ላይ ይባስ ብለው ተናጋሪ እንድሆን ጋብዘውኝ ስለነበር አንድ አጭር ንግግር ለማቅረብ ሞክሬ ነበር። የንግግሬ ማጠንጠኛም ለምን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ያለንበት ቅርቃር ውስጥ ገባን የሚል ነበር። በጊዜ እጥረት የተዘጋጀሁበትን ጽሁፍ ሙሉውን ለማቅረብ ስላልቻልኩ እዚህ ላካፍላችሁ ወደድኩ። የጽሑፌ መነሻ ለምን ከሰው ተራ እርቀን እርስ በርሳችን የምንገዳደል፣ የምንጨካከን፣ የምንሳደድ፣ አንዳችን ሌላችንን የምናዋርድ፣ የምንፈራራ፣ የምንጠላለፍ፣ የምንፈራረጅ ሆንን የሚል ነበር።
ዛሬ እንደ ማህበረሰብ ለገባንበት ቅርቃር ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶችን እንደጠቀሱኩ ነበር ከመድረኩ ላይ የወረድኩት። እንደ እኔ ዛሬ ላለንበት ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ዋናው ምክንያት በማህበረሰባችን ላይ ለበርካታ አመታት ተደጋግመው የተፈጸሙ ሦስት ነገሮች ውጤት ማፍራታቸው  ይመስለኛል
፩ኛ/ ፍርሃት፤ በማህበረሰባችን ውስጥ በተለይም ከደርግ ሥልጣን መያዝ ማግስት ጀምሮ ፍርሃት እንዲሰርጽ እና ሥር እንዲሰድ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ዛሬ ፍርሃት በደም ሥራችን ውስጥ ገብቶ ሁለመናችንን ተብትቦ ይዞናል። ማህበረሰባችን ላለፉት አርባ አመታት በጥልቅ ፍርሃት ውስጥ እንዲቆይ በመደረጉ ዛሬ መንግስትን ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱም እንዲፈራራ ተደርጓል። አዎ እርስ በርሳችንም እንፈራራለን። የፍርሃት ቆፈን አካላችንን ብቻ ሳይሆን አዕምሮዋችንንም ተብትቦ ስለያዘው እንደ ሰው የማሰብ ችሎታንንም አቀንጭሮታል። በነጻነት ማሰብ የማይችል ሰው የፈጠራ ባለቤት ወይም የአዲስ አስተሳሰብ አፍላቂ ሊሆን አይችልም።
፪ኛ/ ጨለምተኝነት ወይም በጽልመት መዋጥ፤ ሰዎች በአገራቸው፣ በመንግስታቸው፣ እንዲሁም በሚኖሩበት ማህበረሰብ እና በራሳቸው ጭምር ተስፋ እንዲቆርጡ ብዙ ተሰርቷል። በመቶ ሺዎች አገር ጥለው እንዲሸሹ ተደርጓል፣ ሌሎች ብዙ ሺዎች በእስር ለዘመናት እንዲማቅቁ ተደርጓል፣ ሌሎች ሺዎች በአደባባይ በጠራራ ጸኃይ እየተረሸኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ፍርሃትን ብቻ ሳይሆን ጨለምተኝነት እንዲሰርጽ ተደርጓል። በርካቶች ለፍተው ያፈሩትን ሃብት ተነጥቀው ለከፋ ድህነት ተዳርገዋል።
፫ኛ/ ማዋከብ እና ማዋረድ፤ ሕዝብ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን፣ የሚያከብራቸውን እና የሚሳሳላቸውን ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ታሪካዊ እና ኃይማኖታዊ እሴቶች ማዋረጅ፣ ማንኳሰስ፣ ማሸማቀቅ፣ ማዳከም እና ማጥፋት። የአገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችን፣ ምሁራንን፣ ጠንካራ የሆኑ የማህበረሰብ ተቋማትን የማጥፋቱ ሥራ በደንብ ጊዜና ገንዘብ ተመድቦለት ለአመታት ተሰርቶበታል። ቀሳውስት እና ሼኾች በአደባባይ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተዋክበዋል። ምሁራን በካድሬዎች ተገፍተዋል፣ ታስረዋል፣ ተገድለዋል፣ ተዋክበዋል። ታሪክ ተዛብቶ እንዲቀርብ ተደርጓል። የታሪክ ባለውለተኞችም ተንቋሸው ለአገር ከሰሩት ዘጠኝ መልካም ነገር ይልቅ የገደፉት አንድ ጎልቶ እንዲነገር ተደርጓል።
እንግዲህ ፍርሃት የተበተበው፣ የጨለምተኝነት ጽልመት የወረረው እና እራሱን እንዲያዋርድ የተደረገ ማህበረሰብ ሊገጥሙት የሚችሉት ፈተናዎች አብዛኛዎቹ ዛሬ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን እየተፈታተኑን ይመስለኛል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹን በአጭሩ ልግለጽ፤
፩/ በማህበረሰብ መካከል መራራቅ ተፈጥሯል። ዛሬ በመካከላችን ትላልቅ ገደሎች ተፈጥረዋl። ማህበረሰባችንን ለዘመናት ያያዙት ሰንሰለቶች ተበጣጥሰው ሳስተዋል። በሃሳብ ተለያይተናል፣ በመንፈስ ተለያይተናል፣ በራዕይ ተለያይተናል፣ በብሔር እና በኃይማኖት ግንቦች ታጥረን በአካል ጭምር ተራርቀናል። በማህበረሰቦች መካከል የሚፈጠር መራራቅ እየሰፋ በመጣ ቁጥር በስሜት መራራቅ እና መተዛዘንም እየጠፋ ይመጣል። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ Distance between people is desensitize people.
፪/  ጥላቻ እየነገሰ መምጣት፤ የተራራቀ ማህበረሰብ መአከል ጥላቻን ማንገስ ቀላል እንደሆነ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ ትሆናለች። በዘር እና በኃይማኖት ከፋፍለው ያራራቁትን ሕዝብ መካከል የቆዩ እና አንዳንዴም ያልተፈጠሩ ትርክቶችን እየፈበረኩ ሰዎችን ማጋደል እንደሚቻል የቁም ምስክሮች ሆነናል። ዛሬ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር እና አብሮነት ከሚሰብኩት ሰዎች ይልቅ የዘር ጥላቻን የሚያራቡት ሰዎች ብዙ ድጋፍ እንዳላቸውም አይተናል። Hate generates more support than love.
፫/ በመካለል ውስጥ የሚፈጠር መገለል። በብሔር፣ በቋንቋ እና በኃይማኖት በተካለልል ቁጥር የምናገለው የህብረተሰብ ክፍል እና የሰው ዘር አለ። መካለል እኛ እና እነሱ የሚል አቃፊና አግላይ ክቦችን ይፈጥራል። እኛ በሚለው መካለል ውስጥ እርካታ እንዳለ ሁሉ እነሱ በሚለው ማግለል ውስጥ ደግሞ የተገፊነት ስሜት አለ። ተገፊነት ብሶትን ያመነጫል። እኛነት አግላይ እና የበዳይነት ስብዕናን ያላብሳል። በዳይና ተበዳይ፣ አግላይ እና ተገላይ ባሉበት ሰላም አይኖርም። ጤናማ የፖለቲካ ሥርዓትም አይገነባም። ጉልበት ያለው ሁሉ ተረኛ በዳይ ይሆናል። ጉልበት የራቀው ደግሞ ተረኛ ተገፊ ይሆናል። መገለል የመተውን ስሜት ይፈጥራል። ለዛም ነው ፈረንጆቹ Any attention can feel better than no attention. የሚሉት። የእኛ ባልነው ክብ ውስጥ ያገለልናቸው እና እነሱ ብለን የፈረጅናቸው ሰዎች እንደ ሰው አትኩሮትን እንደሚሹ ሁሉ እንረሳዋለን።
፬/ የቁጣ ድምጾች ይበረክታሉ። ያገለልናቸው ሰዎች ወይም የተገለሉ የመሰላቸው ወይም አትኩሮት የተነፈጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደመጥ ጩኸትን አማራጭ ያደርጋሉ። በተለይም እንደኛ እጅግ የተሰባጠረ እና ብሶተኛው በበዛበት አገር ጯኺውም እንደዛው ይበዛል። የጩኸት አገር ይሆናል። ያኔ መደማመጥ ከባድ ይሆናል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጯኺው ብዙ ነው። አንድ ቦታ በዳይ የሆነው ሰው ሌላ ቦታ በብሶት ተውጦ ዋና ጯኺ ነው። ኃይማኖተኛው ይጮኻል፣ ፖለቲከኛው ይጮኻል፣ ተማሪው ይጮኻል፣ መምህሩ ይጮኻል፣ ምሁሩ ይጮኻል፣ ገዢዎቻችንም አብረውን ይጮኻሉ፣ እናቶች ይጮኻሉ፣ ነጋዴው ይጮኻል፣ ሸማቹም እንዲያው። እስኪ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ሆድ ያልባሰው እና የማይጮኽ ማን አለ? ጩኸት መገለጫችን ሆኗል። የቁጣ ድምጾች ከሁሉም አቅጣጫ ይሰማሉ። ሰሚ ግን የለም። ለምን?
፭/ የጅምላ ፍራጃ እና መወነጃጀል፤ Ultimate attribution error፤ ለሁሉም ውድቀቶቻችን ወይም ክሽፈታችን ሁሉ ጠአት የምንጠነቁልበት አንድ አካል አለ። ካስፈለገም በመቶዎች አመታት ሽምጥ ጋልበን ከታሪክ ተዋናዮች አንዱን ጎትተን አምጥተን ለዛሬ ውድቀታችን ተጠያቂ እናደርጋለን። ለውድቀታችን ሁሉ እራሳችንን ሳይሆን ሌላ አካልን ወይም ከእኛነት አጥራችን ውጭ ያስቀመጥነው አካል ዋነኛ ተጠያቂ ማድረግ። ሌላውን ዘር፣ ኃይማኖት፣ ወይም እነሱ ብለን ከእኛ ውጭ ያደረግናቸውን አካላት ሁሉ የክፋት ምንጭ አድርጎ ማሰብ እና ለውድቀታችን ተጠያቂዎች ማድረግ። ስለራስ እና ከእኛ ውጭ ስላደረግናቸው ሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝ። hold positive illusion about our ingroup and negative illusion about others.
፮/ እነሱ ብለን በፈረጅናቸው ወይም ባገለልናቸው ማዕቀፎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሁሉ አንድ አይነት አድርጎ ማሰብ። እነዚህን ሰዎች በአስተሳሰብ ወይም በሚጋሩን ብሔር ወይም ኃይማኖት ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ በመልክ ሁሉ አንድ አድርገን መሳል። ሁሉም ትግሬ፣ ሁሉም ኦሮሞ፣ ሁሉም አማራ፣ ሁሉም ጉራጌ፣ ሁሉም ወላይታ፣ ሁሉም ሃረሪ፣ ሁሉም ክርስቲያን፣ ሁሉም ሙስሊም፣ ሁሉም ኢ አማኝ እያሉ ጥቅል ፍረጃ። ይህ አይነቱ ፍረጃ በማህበረሰቡ መካከል ያለው ቅራኔ እየሰፋ እና እየከረረ ሲመጣ ወደ ጅምላ ጥቃይ ያመራል። ይህንንም በተግባር እያየን ነው።
፯/ ከሳይንሳዊ ምርምር ይልቅ የተሳሳተን ትርክት የእውቀት እና የእምነት መሰረት ማድረግ። ሆን ተብሎም ይሁን በስህተት የተነገሩ የሃሰት ትርክቶችን በታዳጊው ወጣት አዕምሮ ውስጥ ታትሞ እንዲቀር ማድረግ። በዝህ መልኩ ወጣቶች እንደ እውነት ተደርጎ በሚያምኑት ሰው የተነገራቸውን የተሳሳተ ትርክ ምንም አይነት ማስረጅ ቢቀርብ እንኳ መቀበል ይቸገራሉ። የስነ አዕምሮ አጥኚዎች ይህን ችግር፤ Belief perseverance and illusory correlation በማለት ይገልጹታል። ስለ አንድ ማህበረሰብ የተሳሳተና የፈረጃ ምልከታ እየሰማ ያደገ ሰው ያንን ማህበረሰብ ቀርቦ ትክክለኛ ገጽታውን ለማየት ቢችልም እንኳ ቀድሞ አዕምሮው ውስጥ የተቀረጸውን ምልከታ ለመቀየር ሲቸገር ልታዩት ትችላላችሁ። ይህ ችግር በኛ ማህበረሰብ ውስጥ በተለያየ መልኩ ይስተዋላል።
በቅጡ ካጠናነው እነዚህን እና መሰል ችግሮችን በማህበረሰባችን ውስጥ ጎልተው እየወጡ እያየን ነው።
እነዚህ ችግሮች በዘር እና በኃይማኖት በታጠሩ ምናባዊ ግንቦች ለtእከፋፈለ ሕዝብ ተደማምረው የሚፈጥሩትን አደጋ በግላጭ እያየን ነው። በተለይም በስሜት የሚነዳውን ወጣት ትውልድ ከሰውነት ተራ የማራቅ (dehumanized) አቅማቸው ከፍተኛ ነው።
በዝር ወይም በኃይማኖት ጥላቻ ውስጥ ሆኖ የጠላውን የህብረተሰብ ክፍል አባል የሆነን ሰው የሚገድል ሰው፤ ልክ እንደሱ ያሌ ሌላ የሰው ዘር እየገደለ ወይም እያጠቃ እንደሆነ አድርጎ አይደልeም የሚያስበው። በገዳዩ አዕምሮ ውስጥ ድርጊቱን ሲፈጽም የሚታሰበው ያ የጠላው ዘር ወይም ኃይማኖት እንጂ። ጭካኔውም የሚበረታው እና አድራጊው ወደ አውሬነት የተጠጋ ድርጊት የሚፈጽመው የሚያጠቃውን ሰው እያሰበ ሳይሆን ሰውየው የሚገለጽበትን ዘር ወይም ኃይማኖት እያሰበ ድርጊቱን ስለሚፈጽም ነው።
ከሰውነት ተራ የመራቅ ክፋቱም ይሔው ነው። ዛሬ አብሮት የትምህርት ገበታ ላይ የተቀመጠ ወገኑን በጩቤ ወግቶ የሚገድል ወይም ከፎቅ ላይ ወርውሮ የሚፈጠፍጥ ወጣት ጸቡ ከዛ አጠገቡ ካለው የጥቃት ሰለባ ጋር እንዳይመስላችው። ጸቡ ያ ወጣት ከመጣበት ማህበራዊ መሰረት ጋር ነው። አጠገቡ ያለውን ሰው ሳይሆን የገደለው፣ የደበደበው ወይም ያሳደደው በአዕምሮው ውስጥ በጠላትነት የፈረጀውን ብሔር ወይም ኃይማኖት ነው። የdehumanization ዋና አላማም አንድን ሰው ከሰውነት ተራ አርቆ የአምሳያውን የሰውን ልጅ ስቃይ፣ ህመም እና ስሜት እንዳይጋራ ማበደን ነው። ያኔ አጠገቡ ካለው የሰው ልጅ ይልቅ የማይጨበጡት እና የማይዳሰሱት ብሄር እና ኃይማኖት ይበልጡበታል። ለብሔሩ እና ለኃይማኖቱ ክብር ሲል ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ይገድላል፣ ያርዳል፣ ሰውነቱን ቆርቅርጦ ይጥላል፣ ያፈናቅላል፣ ያዋርዳል፣ ያሳድዳል።
ወደ ሰውነት እንመለስ። ከሰውነት በራቅን ቁጥር እርስ በርስ እንጨካከናለን። ፍቅር እና መተሳሰብም ከኛ ይርቃሉ። ተገፍተን ከገባንበት ቅርቃር ለመውጣት በጋራ እንጣር።
በቸር እንሰንበት!
Filed in: Amharic