>
10:53 am - Wednesday December 7, 2022

ከፕሬዝዳንቱ፣ ከጄነራሉና ከኢንሳው ቁልፍ ሰው ጋር የቃሊቲ ውሏችን!!! (ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን)

ከፕሬዝዳንቱ፣ ከጄነራሉና ከኢንሳው ቁልፍ ሰው ጋር የቃሊቲ ውሏችን!!!

ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን
እንዲህም ሆነ፡-
ትናንትና የ“ሐበሻ ወግ” መፅሔት ባለቤት ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ ስልክ ደወለልኝ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት “ነገ ቃሊቲ ሄደን ከለውጡ በኋላ የታሰሩ ሰዎችን የእስር ቤት አያያዝ በተመለከተ አንድ ዘገባ ብንሰራ ምን ይመስልሃል?” አለኝ፡፡
“አሪፍ ሃሳብ ነው”
ተስማማን ተቀጣጠርን፡፡
በጠዋት በቀጠሮአችን መሰረት ተገናኘን፡፡ ወደ ቃሊቲ መረሽን፡፡ 3፡ 30 ደረስን፡፡ ወደ በሩ ስናመራ አንዲት ወጣት አገኘን፡፡ ከቴዲ ጋ ይተዋወቃሉ፡፡ ሰላምታ ተሰጣጡና ማውራት ጀመሩ፡፡
“ቆይ፤ ጥሩ አጋጣሚ ሳናገኝ አንቀር፡፡ የሚመጡ ሰዎች አሉ እያለችኝ ነው፡- አብረን እንገባለን” አለኝ ቴዲ፡፡
ዐይኔን ጠያቂዎች ወደሚገቡበት በር ወረወርኩ፡፡ ዱሮ በማውቀው በዋናው በር አይደለም ጠያቂዎች የሚገቡበት፡፡ የደርግ እስረኛን የሚጠይቁ ሰዎች በሚገቡበት በር ነው ጠያቂዎች የተሰለፉት፡፡
ከአፍታ በኋላ “ይመጣሉ” የተባሉ ሰዎች ሲመጡ አየሁ፡፡ ከቴዲ ጋር የቆመችው ልጅ ናት ሰዎቹን በሩቁ የጠቆመችን፡፡ አምስት ናቸው፡፡ ከአምስቱ ሰዎች አንዱ ረዥም ናቸው፡፡ እየቀረቡን ሲመጡ ረዥሙን ሰውዬ ለየኋቸው፡፡ ገረመኝ፡፡ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ናቸው፡- የትዴት ሊቀመንበር፡፡
እኛ ጋ እንደደረሱ ሰላምታ ተለዋውጠን ወደ መዝጋቢው ፖሊስ አመራን፡፡ “የት ናችሁ?” አለ ፖሊሱ፡፡
“ዋይታ” አለች ልጅቷ ፈጠን ብላ፡፡
“ዋይታ የሚባል የእስር ክልል አለ እንዴ?” አልኩኝ፡፡
“ቤትህ አይደል እንዴ? እንዴት አታውቀውም?“ አለኝ በሹፈት መልክ፡፡
ፖሊሱ መዝግቦን አንገት ላይ የሚንጠለጠል የጠያቂ መታወቂያ ሰጠን፡፡ ወደ ግቢው ገባን፡፡ ከዋናው በር ፊት ለፊት ያለች የቆርቆሮ ቤት እየጠቆመን ታወቂያ፣ ወረቀት፣ እስኪሪፕቶ … ወዘተ አስረክቡ ተባልን፡፡ አስረከብን፡፡ ጫማችሁን አውልቁና አራግፉ ተባልን፡፡ አራገፍን፡፡ ሌላ ፖሊስ ከፊት ያለውን ክፍል እየጠቆመን ቀበቶ አውልቁ፣ ብረት ነክ ነገር እና ሳንቲም… ከያዛችሁ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣችሁ በመፈተሻው መሣሪያ ውስጥ እለፉ አለን፡፡ (እኔ ቃሊቲ እስር ቤት በነበርኩ ጊዜ መፈተሻ ማሽን አልነበረም) እናም “ዋይታ” ወደተባለው እስር ክልል ደረስን፡፡
ዶ/ር አረጋዊ እና አብረዋቸው ያሉት ሰዎች ከፊት ናቸው፡፡ እኔ የቃሊቲን የእስር ጊዜ ትዝታ እያስታወስኩ “እዚህ ጋ እንዲህ ነበር፤ እዚያ ጋ እንዲህ “ እያልኩ ለጓደኛዬ እየነገርኩት ከኋላቸው እየተከተልን ነው፡፡
ጥቂት መቶ ሜትሮችን ተጠማዝዘን “ዋይታ” የተባለው ስፍራ ደረስን፡፡ ዶ/ር አረጋዊ የሚጠይቋቸውን ሰዎች አስጠሩ፡፡ ከሁሉም ቀድመው የሜቴኩ ሜ/ጄ/ል ክንፈ መጡ፡፡ ጨበጧቸው፡፡ ጨበጡን፡፡ ብ/ጄ/ል ፅጋቡ ተከተሉ፡፡ ኮ/ል ቢንያም፣ ቴዲ ማንጁስ …. ወዘተ፡፡ መጥተው ከሽቦው አጥር ወዲያ የቆሙትን ሰዎች ቆጠርኳቸው፡፡ አስር የሜቴክ፣ የኢንሳ እና የደህንነት መ/ቤት ሰዎች ከፊት ለፊታችን ቆመዋል፡፡ የሁሉም ገፅታ ላይ የመገረም ስሜት ይነበባል፡፡ ይህ ግራሞት በዶ/ር አረጋዊ እዚያ መገኘት የመነጨ ይመስላል፡፡ (የኋላ ኋላ ከእስረኞቹ ንግግር ያረጋገጥኩም ይሄንኑ ነው)
.
ዶ/ር አረጋዊ ስለእስራቸውና ስላሉበት ሁኔታ ጠየቋቸው፡፡ ሜ/ጄ/ል ክንፈ በትግርኛ መልስ መስጠት እንደጀመሩ ከእኛ ጋር ከገቡት ጠያቂዎች መሃል አንዱ “በአማርኛ” አላቸው፡፡
“እሺ” አሉ ክንፈ፡፡ በአማርኛ ስለክሳቸው አይረቤነት፣ ስለፍ/ቤት ፍትህ አልቦነት፣ ስለ ቤተሰብ ወዘተ መናገር ቀጠሉ፡፡ ከእሳቸው በኋላ ሜ/ጄ/ል ፅጋቡ ቀጠሉ፡፡ የኢንሳው ኮ/ል ቢንያም ቀጠለ፡፡ እኔ እነሱን እያዳመጥኩ፣ አሁንም አሁንም መጠየቂያው በር ላይ ወደቆሙትና ወደተቀመጡት ፖሊሶች እየተገላመጥኩ ከመመልከት አልቦዘንኩም፡፡
ምክንያቱም እኔ ከቅንጅት መሪዎች ጋር በታሰርኩ ጊዜ እንደዚህ በፈለጉት ርዕስ ላይ የመናገር ነፃነት አልነበረም፡፡ ያኔ ከአንድ ጠያቂያችን ጋር አስር እና ከአስራ አምስት ደቂቃ በላይ መነጋገር አይቻልም ነበር፡፡ ይህም በዛ ተብሎ ጠያቂዎቻችን ጋር የቆመው ፖሊስ ከደበረው ቤተሰቦቻችንን አመነጫጭቆ ከግቢው ያስወጣቸው ነበር፡፡ እናም ከአሁን ከአሁን ፖሊሶቹ እንደዚያ ያደርጋሉ፤ “በቃችሁ” ይላሉ ብዬ ነበር አስሬ እየተገላመጥኩ የማያቸው፡፡ እስረኞቹ ብሶታቸውን እየነገሩን ከአንድ ሰዓት በላይ ሆኗል፡- ፖሊሶቹ ምንም አላሉም፡፡
.
በዚህ መሃል
“….. እኔ የምናገረው ነገር አለ፤ እንዴት ሰው ስራህን ሰራህ ተብሎ ይታሰራል” አለ አንድ እስረኛ፡፡ የእስረኛውን ማንነት ለመለየት ትኩር ብዬ አየሁት፡፡ አላውቅትም፡፡
“ይቅርታ፤….ያሬድ ዘሪሁን እባላለሁ፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ሃላፊና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ነበርኩ፡፡ በሰዎች ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመሃል ተብዬ ነው የታሰርኩት፡፡ ማንም ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት አልፈፀምኩም፡፡ … በምስክርነት የተቆጠሩብኝ ከእስር የተፈቱ የኦነግ አባላቶች ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ቶርች አድርጎናል አላሉም፡፡ እንድንያዝ አድርጓል ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ኦነግ በአሸባሪነት የተፈረጀ ድርጅት ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ደህንነት ነኝ፡፡ በአሸባሪነት የተጠረጠሩ ሰዎችን መያዝ ሥራዬ ነው፡፡ ለምን ሥራህን ሰራህ ብሎ ክስ ….”
ትኩር ብዬ አየሁት፡፡
ሌላ እስረኛ ብሶቱን መናገር ቀጠለ፡፡ እኔ የሁሉንም እስረኞች ብሶት በጥንቃቄ በህሊናዬ እየመዘገብኩ ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ አስሩም ተናገሩ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከ10 በላይ የሚሆኑ የእሰረኞቹ ጠያቂዎች በጥሞና ይከታተላሉ፡፡ በመጨረሻም ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ምክር ቢጤ ነገር ለገሷቸው፡፡ የምንሰናባበትበት ጊዜ የደረሰ መሰለ፡፡
ይኼኔ ነበር እኔ ድንገተኛ ጥያቄ የሰነዘርኩት፡፡
“ይቅርታ የተናገራችሁትን ሁሉ ሰምተናል፡፡ ግን ሁለት ጥያቄ አለኝ፡፡ አንደኛው ጥያቄ ለአንተ ለያሬድ (ለደህንነቱ) ነው፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ ለጄኔራል ክንፈ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ራሴን ላስተዋውቅ ወሰንሰገድ እባላላሁ፡፡ የግል ጋዜጠኛ ነኝ”
በዚህች ቅፅበት “አ…..” የሚል የድንጋጤ ቃል ሰማሁ፡፡ ከቤተቦቻቸው፡፡ የግል ጋዜጠኛ እዚያ ይገኛል ብለው ስላልጠበቁ ይሆናል መደነቅ ወይም ድንጋጤ የተሰማቸው፡፡ ለማንኛውም ለያሬድ ጥያቄዬን ሰነዘርኩ፡፡ ቀጠልኩ፡፡ ወደ ሜ/ጄ/ል ክንፈ ፊቴን አዞርኩ፡፡
“እርስዎ ምንም ዓይነት ችግር ከሌለብዎት ለምንድነው ከሃገር ለመሸሽ የፈለጉት፡፡ በዜና እንደሰማነው ሲሸሹ እንደተያዙ ነው፡፡ እውነት ነው? እውነት ካልሆነ ለምን ወደዚያ ቦታ ሄዱ? ሊነግሩኝ ይችላሉ?
“እችላለሁ” አሉኝ ዐይኖቻቸውን ጠበብ አድርገው ግን ትኩር ብለው እያዩኝ፡፡
“እነግርሃለሁ! ግን አንተ ትፅፈዋለህ?”
“አዎ!”
“ትፅፈዋለህ?” እንደገና ጠየቁኝ፡፡
“አዎ!”
እናም በሚገርም ሁኔታ በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ዕለትና ሁኔታ ነገሩኝ፡፡
መልሳቸውን እንደጨረሱ ፊቴን አዞርኩ፡፡ ወደ ውጪ በር አንድ ሁለት እርምጃ እንደተራመድኩ ጓደኛዬ ቴዲ “አብዲ ኢሌ! አብዲ ኢሌ!” አለኝ ጣቱን እየቀሰረ፡፡ ዞር አልኩ፡፡
“ጋዜጠኛ ላንተ አይደለም የምነግርህ ለእሳቸው ነው” አለ፡- አብዲ ወደ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እየጠቆመ፡፡
“እሺ”
ሁለት እርምጃ ያህል ውደኋላ አፈገፈግኩ፡፡
አብዲ ለዶ/ር አረጋዊ መናገር ቀጠለ፡፡ የሚናገረው ጮክ ብሎ ስለሆነ ይሰማኛል፡፡
“ግን እኮ የተናገርከውን ሁሉ ሰማሁህ” አልኩት፡፡
ከት ብሎ ሳቀ አብዲ ኢሌ፡፡
በስተመጨረሻ በእጅ ምልክት ጠራኝና አንዳች ነገር ነገረኝ፡፡
ምን ነገረኝ?
አሁን አልነግራችሁም፡፡
ሜ/ጄ/ል ክንፈ ምን ምላሽ ሰጡኝ? ሌሎቹስ ምን አሉ? አሁን አልነግራችሁ!!
የሁሉንም የምነግራችሁ በክፍል ሁለት መጣጥፌ ይሆናል የዛ ሰው ይበለን።
.
አበቃሁ!!
Filed in: Amharic