>

ብልጽግና ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ተሰጠው (ኦ.ዴ.ፓ - አማርኛ)

ብልጽግና ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ተሰጠው!

ኦ.ዴ.ፓ – አማርኛ
 
‹እናት ፓርቲ› በሚል በመቋቋም ሂደት ላይ ለሚገኝ ፓርቲ ደግሞ ጊዜያዊ የምሥክር ወረቀት እንዲሰጠው ተወስኗል!!!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ጥያቄ እና የፓርቲ መለያ ሰንደቅ ዓላማ የማጸደቅ ጥያቄን ያቀረቡ ፓርቲዎችን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔዎችን መስጠቱን በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
በውሳኔው መሠረትም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል የነበሩ ሦስት ፓርቲዎች እና ሌሎች አምስት ፓርቲዎች ራሳቸውን በማክሰም በጋራ ‹ብልጽግና ፓርቲ›› የሚል አዲስ ፓርቲ መመሥረታቸውን በማሳወቅ የዕውቅና የምሥክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በጽሑፍ ለቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሷል፡፡
ቦርዱም ጥያቄያቸውን በፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ 1162/2011 መሠረት መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቦርዱ የዕውቅና ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ በተጨማሪ መሟላት ያለባቸውን ሰነዶች በታኅሣሥ 01 ቀን 2012 ዓ.ም በመጠየቅ በጥያቄውም መሠረት ታኅሣሥ 06 ቀን 2012 ዓ.ም የጥያቄዎቹ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሟልተው መቅረባቸውን በማረጋገጡ ብልጽግና ፓርቲን ዕውቅና መስጠቱን አስታውቋል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ አማራ ዴሞክራያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋሕአዴን) እና የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) በተናጠል በጠቅላላ ጉባኤያቸው ውሳኔ መሠረት አድርገው ውሕደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም መወሰናቸውና ውሕደቱን ለመመሥረት ያደረጉት ስምምነት በሙሉ ሕጉን ተከትሎ የተፈጸመ በመሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የዕውቅና የምሥክር ወረቀት እንዲሰጠው መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ውሕዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሠረት በተመዘገበ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ውሕደቱ ያስገኘውን ሀብትና ንብረት እና ዕዳ የሚያሳይ የሒሳብ ሪፖርት ለቦርዱ እንዲያቀርብ መወሰኑንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
‹‹እናት ፓርቲ›› በሚል አገር አቀፍ ፓርቲ ለማቋቋም በአዋጅ 1162/ 2011 መሠረት ጊዜያዊ የዕውቅና የምሥክር ወረቀት እንዲሰጠው ጥያቄ የቀረበለት ቦርዱ በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን ጊዜያዊ የምሥክር ወረቀት መውሰጃ መስፈርት በማሟላቱ እንዲሰጠውም ቦርዱ ወስኗል፡፡
Filed in: Amharic