>

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጨዋነት የተሞላው ድፍረት!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጨዋነት የተሞላው ድፍረት!!!

 

ያሬድ ሀይለማርያም
የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ለመብቱ በጋራ ያለ ምንም ፍርሃት የመቆም ልምምዱን እና መንፈሳዊ ጥንካሬውን ከአመታት በፊት ነው ያሳየው። በዛ በጨለማ ዘመን ከአገዛዝ ሥርዓቱ ጋር ለሦስት ተከታታይ አመታት ያደረገው ፍጹም ሥልጡን እና ድፍረት የተሞላበት ትንቅንቅ ለሰላማዊ የመብት ትግል ጥሩ ማሳያ ነው። ደጋግሜም አድናቆቴል ገልጫለሁ። ዛሬም በሞጣ የተከሰተውን አስነዋሪ ተግባር ከጀርባው ማንም ይኑን ማን ድርጊቱን ለማውገጽ ከጫፍ ጫፍ ተንቀሳቅሰው ቁጣቸውን አሳይተዋል። ሰልፍ በተከለከለባት አዲስ አበባ ሳይቀር ድምጻቸውን አሰምተዋል። ለመብት ያለ አንዳች ፍርሃት በጽናት መቆም ይሉሃል እንዲህ ነው። መሪዎቻቸው ሲታሰሩ ይጮሃሉ፣ የእምነት ቦታቸው ሲደፈር ይጮኻሉ፣ መንግስት ጣልቃ ልግባባችው ሲል ይጮኻሉ።
በተቃራኒው ያየን እንደው ላለፉት አሥርት አመታት ያሁሉ መከራና ውርጅብኝ ሲወርድባት የቆየችው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ድምጿን በአዲስ አበባ በሰልፍ ለማሰማት የመንግስትን ፈቃድ ደጅ ስትጠና ተመልክቻለው። ስልፍ ለናካሂድ ነው እያሉ ከወራት በፊት ጋዜጠኛ እየሰበሰቡ የማስጠንቀቂያ ጋጋታ ሲሰጡ እና ሲፎክሩ የነበሩ አስተባባሪዎች አገዛዙ አትችሉም ሲላቸው ሙሽሽ ብለው ነው የቀሩት። ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት በአንዳንድ አካባቢዎች ለሰልፍ ልውጣ ቢል እኛ የለንበትም ሲሉም ተሰምተዋል። በአዲስ አበባ ልደታ ቤተክርስቲያን ብቻ ትመስለኛለች ተቃውሞዋን ያሰማችው። ልደታ አካባቢ ያልው ሕዝብ እምቢተኛ እንደሆነም እንዲሁ በጨለማው ጊዜ ከአገዛዝ ሥርዓቱ ጋር ተፋጦ ለቤተክርስቲያኗ ዘብ ቆሞ የሥርዓቱን ትዕግስት በጨዋነት እና በሰላማዊ መንገድ ተፈታትኗል።
ለነገሩ በኦርቶዶክስ እምነት በኩል የሚታየው የተለማማጭነት እና ለመንግስት የማጎብደድ ነገር ቤተክርስቲያኗን ክፉኛ ጎድቷታል። ላለፉት አሥርት አመታት ለቁጥር የሚታክቱ ቤተክርስቲያናት በአክራሪዎች ጋይተዋል፣ ታሪካዊ ቅርሶቿም ተዘርፈዋል፣ ጥንታዊ ገዳማትም በመንግስት ኃይሎች ጭምር ለጥቃት ተዳርገዋል። ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ሲወርድባት የቤተክርስቲያኗ አመራሮች እና አብዛኛው ምዕመን ጎመን በጤና ብሎ፣ ገሚሱም እንዳላየ እና እንዳልሰማ መስሎ ቤተክርስቲያኗ ክፉኛ እንድትጠቃ ምክንያት ሆኗል። በዋልድባ ገዳም ላይ የተፈጸመው ግፍ፣ የቤተክርስቲያኗ ዝምታ እና ተባባሪነት፣ የምዕመናኑም ምላሽ ጥሩ ማሳያ ነው። የዋልድባ ነገር ሲነሳ እንደውም አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ ይህን ሳላካፍላችው ብቀር ትዝብቴን ጎዶሎ ያደርገዋል።
ዋልባ ገዳም ጥቃት ተሰንዝሮበት እና መነኮሳቱ ለእስር በተዳረጉበት ወቅት ጉዳዩ ያበሳጨን ሰዎች የመንግስትን ድርጊት ለመቃወም አውሮፓ ፓርላማ ደጃፍ ሰላማዊ ሰልፍ አደረግን። ይህ አይነት ተመሳሳይ ሰልፎች የሙስሊሙ ማህበረሰብ አመራሮች በታሰሩበትም ጊዜ ደጋግመን አድርገናል። ሰልፉን ካዘጋጀን በኋላ በቤልጂየም ለሚገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራሮች እና ምዕመናን አስቀድመን የሰልፉን አላማ በመግለጽ ጥሪ አደረግን። ይሁን እና ከቤተክርስቲያኗ አመራሮች ያገኘነው ምላሽ አስደማሚ ነበር። ከበርካታ ውትወታ በኋላ ዘግይተው በሰጡን ምላሽ በሰልፉ ላይ መሳተፋቸው ከቤተክህነት ጋር ሊያጋጫቸው ስለሚችል (በወቅቱ ቤተክርስቲያኗ ከራስ ቅሏ እስከ እግር ጥፍሯ በካድሬዎች የተተበተበችበት ወቅት ስለነበር) ቅሬታችንን ውስጥ ለውስጥ እናሳውቃለን እንጂ አደባባይ አንወጣም ነበር ያሉን። እናም ሰልፉ ላይ ሃምሳ የማንሞላ ሰዎች ስንገኝ ከዛ ውስጥ የሚገርመው ትልቁን ቁጥር የሚይዙት በቤልጂየም የሚገኙ የሉቅማን የሙስሊሞች ማህበር አመራሮች እና አባላት ነበሩ። ለዋልድባ ገዳም ተቆርቁረው እና ለእኛም አጋርነታቸውን ለመግለጽ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት አደባባይ ወጥተው ሲጮኹ አብዛኛው የኦርቶዶክስ አማኝ እና አመራሮቹ እዛው ቤተክርስቲያኗ ውስጥ እዝጊዮ እያሉ በመነኮሳቱ ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍ በርቀት ያዩ ነበር።
እንዲህ ያለውን መብትን በልምምጥ የመጠየቅ፣ ለግፍ አገዛዝ መልመጥመጥ እና እሚኝ የሚባልን ነገር እምቢ ብሎ አደባባይ በድፍረት የመቆም ጽናት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙም አይሰዋልም። ይህ አይነቱ ልምምድ ቢኖር ኖሮ ሰልፍ ልናካሂድ ነው እያሉ የጋዜጣዊ መግለጫ ግርግር ባላየን ነበር። ፍርሃት ሥር የሰደደበት ተቋም ሁሌም የጥቃት ሰለባ ነው። የተቆጣ ሕዝብ ቅሬታውን ለመግለጽ የመንግስትን ፈቃድ አይጠብቅም። ፈቃድ ጠይቆም ሲከለከል ኩምሽሽ ብሎ አርፎ አይቀመጥም። ትልቁ ቁምነገር ፍጹም ሥልጡን እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብትን መጠየቁ ላይ ነው። መብት በፈቃድ የሚገኝ፣ በልምምጥ የሚጠየቅ ሳይሆን በግድ እና በሰላማዊ መንገድ የሚገኝ ነገር ነው። ያንን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ደጋግሞ እያሳየ ነው።
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጨዋነቱንና ሰላማዊነቱን በሚያሳይ መልኩ ቅሬታውን አደባባይ ወጥቶ ሲገልጽ መንፈሱን ሊያደፈርሱ የሚፈልጉ አክራሪዎች እዚም እዛም አጓጉል እና ጸብ ቀስቃሽ መልዕክት ይዘው በመውጣት ለላውን ማህበረሰብ ለማስቆጣት ሲጥሩ አይቻለው። እነሱን ለይቶ መውቀስ፣ ማውገዝ እና ካስፈለገም የሕግ ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል። የሙስሊሙን ማህበረሰብ ግን ስለማይወክሉ ጅምላ ፍረጃው አግባብ አይደለም። ይህን ክስተትም ለድብቅ የአክራሪነት ተልዕኳቸው የሚጠቀሙበት እኩይ ሰዎች ይኖራሉ። እነሱንም በጋራ መዋጋት ይቻላል። ለነገሩ ከሞጣውም ክስተት ጀርባ እነዚሁ አክራሪዎች እንዳሉ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ነው።
በብሔር ሊያፋጩት አስበው የፈለጉትን ያህል እና በፈለጉት ፍጥነት ውጤት አላመጣ ያላቸው ቡድኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ በኃይማኖት ሊያጫርሱት የጀመሩት እኩይ ተግባር እንደሆነ ግልጽ ነው። ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በለመደው የመተሳሰብ እና መከራን የመጋፈጥ ጽናቱ ይህንንም ፈተና ይሻገረዋል ብዮ ተስፋ አደርጋለው።
ለመብታችሁ በአደባባይ ያለፍርሃት ለምትቆሙ ሁሉ ክብር ይሁን! መብት በችሮታ ከመንግስት የሚሰጥ ሳይሆን በተፈጥሮ የታደልነው እና በግድ የምናስጠብቀው ነገር መሆኑን ገብቷችኋልእና።
መልካም ሰንበት!
Filed in: Amharic