>

የጥላሁን ግዛው 50ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የጥላሁን ግዛው 50ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ (ትግል) ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ የነበረው ጥላሁን ግዛው የተገደለው ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት (ታኅሣስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም) ነበር፡፡
ጥላሁን ግዛው የተወለደው በ1933 ዓ.ም ነው፡፡ ቤተሰቦቹ በዘመኑ ‹‹ባላባት›› ተብሎ ከሚጠቀሰው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ የሚመደቡ ነበሩ፡፡ አባቱ ንቡረእድ አበራ ግዛው፣ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ደሴ አደዬ ረታ ይባላሉ፡፡ ጥላሁን የእድሜውን የመጀመሪያዎቹን ዓመታት ከአያቱ ከወ/ሮ ጥሩ ለገሠ ጋር አሳልፏል፡፡ ከእናቱ ጋር ወደ ላስታ አውራጃ በመሄድም በአካባቢው ኖሯል፡፡ ወልድያ በሚገኘው ጣይቱ ብጡል ት/ቤትም ተምሯል፡፡
ከዚያም ከአባቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንጦጦ ሚሽን አዳሪ ት/ቤት ገብቶ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። በመቀጠልም ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገብቶ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ በ1959 ዓ.ም. የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ቀ.ኃ.ሥ) ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ “አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ”) መግባት ቻለ፡፡
ጥላሁን ግዛው የቀዳማዊ አፄ ሃይለሥላሴ ልጅ፣ የልዑል መኮንን ባለቤት የሆኑት የልዕልት ሣራ ግዛው ወንድም ነው፡፡ ከባላባት ቤተሰብ ቢወለድም ዕድገቱ ግን ከአርሶ አደር ልጆች ጋር እንዲሁም በገጠር ኑሮው በአለባበሱም ሆነ በባህሪው ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ለመመሳሰል ይጥር እንደነበር ይነገራል። በተማሪነት ዘመኑም ጊዜውን የሚያሳልፈው ከመሰል ተማሪ ጓደኞቹ ጋር እንጂ ከባለስልጣናትና ከከበርቴዎች ጋር አልነበረም ይባላል።
ጥላሁን ልዩ የአንባቢነት ተሰጥኦ እንደነበረውም ይነገርለታል፡፡ በቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ በመሆን ባገኘው ከፍተኛ ነጥብ መሠረት የመጀመሪያው ምርጫው ወደ ሆነው የፖለቲካ ሳይንስ የትምህርት ክፍል በመግባት ይበልጥ የሀገሩንና የዓለምን ፖለቲካ በሚገባ በመረዳት ግንዛቤ እንዲያገኝ ረድቶታል።
በዩኒቨርሲቲውም በየደረጃው ባሉ ክበባትና አደረጃጀቶች በመሳተፍ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ (ትግል) ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ መያዝ ቻለ፡፡
በኅዳር 1962 ዓ.ም. በወቅቱ ዝነኛ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር (University Students Union of Addis Ababa – USUAA) ፕሬዝደንት ሆኖ ተመረጠ፡፡ ጥላሁን በማኅበሩ ፕሬዝዳንትነቱ ቀዳሚው ሥራው የተማሪውን የመናገር፣ የመጻፍና የመደራጀት ነጻነት ይበልጥ ማጠናከርና የተለያዩ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ መታገል ሆነ፡፡
ታህሳስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም. ከታናሽ ወንድሙ መኮንን ሲሳይ ጋር በመሆን ከስድስት ኪሎ በስተጀርባ አፍንጮ በር በሚባለው አካባቢ ፍቅረኛውን ዮዲት ታዬን ለመሸኘት (ታክሲ ሊያሳፍሯት) ወደ መኪና መንገድ ወጡ። ሰዓቱ በግምት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከሩብ ይሆናል። ታርጋ የሌላት አንድ መኪና ወደነጥላሁን ቀረብ በማለት የሞት ጥይቷን በጥላሁን ላይ አርከፈከፈችበት። ሕይወቱን ለማትረፍ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀረና ጥላሁን ሞተ፡፡
ታኅሣስ 22 ቀን 1962 ዓ.ም የቀርብ ስርዓቱ በትውልድ አካባቢው ተፈፀመ፡፡ የጥላሁን ሞት በርካታ ጥላሁኖችን ወለደ፡፡ በትውልድ አካባቢውም ት/ቤቶች በስሙ ተሰይመውለታል፡፡
(የመረጃው ምንጭ ፡ ያ ትውልድ ተቋም)
Filed in: Amharic